>
5:09 pm - Tuesday March 3, 5316

ይህ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም! (በድሉ ዋቅጅራ-ፋክት መጽሄት)

ሚኒስትር ሲያረጅ አምባሳደር ይሆናል፡፡
ሀሳብ ቁፋሮ ነው፤ በ‹ለምን› ዶማ ዙሪያ ገባን በተጠየቅ መቆፈር ነው ሀሳብ! ምን፣ እንዴት፣ ለምን፣ በማን … እያልን የእራሳችንን፣ የቤተሰባችንን፣ የማህበረሰባችንን፣ የሀገራችንን ውሎና አዳር ስንጠይቅ አሰብን ማለት ነው፡፡ እንደ ዶማችን ጥንካሬ የቁፋሯችን ስፋት ይለያያል፡፡ አንዳንዶቻችን የለምን ዶማችን ዶልዱሞ የራሳችንን ማሳ እንኳ በወጉ አንቆፍርም፤ የአንዳንዶቻችን የለምን ዶማ ደግሞ የሾለ ነው፤ ከራስ ጠለል፣ ከቤተሰብና ከሸንጎ ተሻግሮ፣ የዜጎችን ማሳ፣ የሀገርን ርስት በተጠየቅ ይቆፍራል፡፡ ከፋም ለማ፣ ጠበበም ሰፋ ሰው በህይወት ካለ ያስባል፡፡
እኔም ሰው ነኝ፣ በህይወትም አለሁ፤ እና አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ሀሳቦች አሉኝ፤ ሳልወድ የማስባቸው፡፡ በለምን ዶማዬ ብቆፍር ብቆፍር ተጠየቃዊ ሰበብ የማላገኝላቸው፡፡ ተጠየቃዊ ሰበበ-መንስኤ አላገኘሁላቸውምና ሁልጊዜ ለቁፋሮ የለምን ዶማዬ ፊት ይጋረጣሉ፡፡ ደጋግሜ ብቆፍራቸውም ጠብ የሚል ተጠየቃዊ ነጥብ አላገኝላቸውም፡፡ ዘወትር በለምን ዶማዬ ቆፍሬ፣ ልብ የሚያርስ እንኳን ባይሆን ከልብ የሚደርስ ተጠየቃዊ መልስ ካላገኘሁላቸው ነጥቦች አንዱ የኢህአዴግ ሹም – ሽር ነው፡፡
ሁልጊዜ (ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት) ሳስበው የኢህአዴግ ሹም-ሽር ይገርመኛል፡፡ ግን ቆይ በኢህአዴግ ዘመን የተደረገ ሹም-ሽር አለ? በጭራሽ! የለም! ኢህአዴግ ሾሞ አይሽርም፡፡ በኢህአዴግ ሹም-ሽር የለም፡፡ በኢህአዴግ አንድም ሹም-እስር፣ አንድም ሹም-ሹም ነው ያለው፡፡ ሹም-እስር ማለት ከሹመት ወደ እስር ቤት የሚደረግ ሽግግር ነው፡፡ በዚህ ስር አቶ ታምራት ላይኔ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣… ሌሎችም ይመደባሉ፡፡ ሁለተኛው መደብ ደግሞ ሹም-ሹም ነው፡፡ በዚህ ስር ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሀገሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት መኮልኮል አይገድም፡፡ ለአብነት ግን ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ አቶ አያሌው ጎበዜ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ … የአሁኑን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱን ጭምር መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሁልጊዜ ስለዚህ እርስተ-ጉልት ስለተደረገ የሀገሬ ስልጣን አስቤ… ቆፍሬ… ቆፍሬ ጠብ ያለልኝ አንድ እውነት፣ አንድ ተረት ብቻ ነው፡፡ እውነቱን ላስቀድም፤ ‹‹የኢህአዴግ ሹመት ስለተደረገለት ውለታ ክፍያ እንጂ፣ ለሀገርና ወገን ለመስራት መመረጥ አይደለም፡፡›› ተረቱን ላስከትል ‹‹ሚኒስትር ሲያረጅ አምባሳደር ይሆናል›› እዚህ ላይ በሃያ ምናምን አመት የሀሳብ ቁፋሮ አንድ እውነትና አንድ ተረት ቁምነገር ሆኖ ነው? የሚል ዘላፊ ተሟጋች አይጠፋም፡፡ መልሴ ‹‹እውነት ነው! ነጠላ እውነትና ነጠላ ተረት፣ በሃያ ምናምን አመት ቁምነገር አይደለም፡፡ ግን ልብ በል የግንቦት ሀያን ምንዛሪ 8395 ቀናትን ወይም 23 ዓመታትን ለኖረ፣ የአንድን ቀን አዋጅና የአንድን ቀን ዜና ለሃያ ሶስት አመታት ያውም በየሰዓቱ ላዳመጠ፣ የአንድ ቀን እጣ ለሃያ ሶስት አመታት፣ በየአምስት አመቱ ደጋግሞ ላጸደቀ፣ የዚያች ቀን ሹመኞች ሃያ ሶስት አመት ሲሾሙ ላጨበጨበ፣ የአዲስ ነገር ናፍቆቱን ከሃያ ሶስት አመት በፊት ለቀበረ… በቃ የአንድ ዶላር ምንዛሬ 18 ከምናምን ብር ሆነ ተብሎ በሚጮህበት ሀገር፣ ግንቦት ሃያን በ8395 ቀናት ተመንዝሮ ለኖረ ዜጋ፣ ከነዚህ በውሎ ገባ ከሄደባቸው 8395 ተመሳሳይ ቀናት አንድ እውነትና አንድ ተረት፣ ማግኘት ሮቦት የመስራት ያህል ነው፡፡›› የሚል ነው፡፡
ኢህአዴግ ባለብረት ቆቡንና ባለትላልቅ መጫሚያውን አምባገን፣ ግፈኛ መንግስት አሸንፎ ሀገሬን ሲረክብ (ለነገሩ መረከብ በፈቃድ ሲሆን ነው፣ በጉልበት ሲሆን መንጠቅ ነው) እሺ ሲነጥቅ፤ በሚገባ ያስተዳድረን ዘንድ በየደረጃው ባለስልጣናትን መሾም ነበረበት፤ ይህ መቼም ብርቅ አይደለም፡፡ አዲስ መንግስት ከአዲስ ሹመኞች ጋር መምጣቱ የተለመደ ነው፡፡ በእውነቱ እኔ በየሚኒስትሩና ትልልቅ የስልጣ ቁንጮ፣ የዛሬ ሃያ ሶስት አመት (አቤት ጊዜው እንዴት ይንቀራፈፋ፤ ሃያ ሶስት አመት ሳይሆን፣ ሁለት መቶ ሰላሳ አመት የሆነው መሰለኝ፤ ሲሰለች) በተቀመጡት ባለስልጣናት አልተከፋሁም፡፡ እንዲያውም ደስ ነው ያለኝ፡፡ ከጣሉት መንግስት የተሻሉ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ትንሽ ቅር ያለኝ ነገር ቢኖር፣ ከሹመቱ ያካፍሏቸው ይሆን ያልኳቸውን ሰዎች ከስራ አባረው፣ የስልጣን ዘመናቸውን መጀመራቸው ነው፡፡ ቢሆንም ቅር አለኝ እንጂ አልተበሳጨሁም፡፡ በቅንነት ተመለከትኩት፡፡ አስራ ሰባት ዓመት እየተኮሰና እየተተኮሰበት፣ ገድሎ እየጣለና መስዋእት እየሆነ፣ በጦርነት ውስጥ የኖረ ታጋይ ጦርነትን አቁሞ፣ ከስራ ማባረር መጀመሩ በቅንነት ከተመለከትነው ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ በእውነት ነው የምለው፣ በሰላም ይኖር የነበረ ወታደር ንጉሱን አስወግዶ፣ ወደ ጦርነት/መግደል/ መረሸን ገባ፡፡ በጦርነት/በመግደልና በመሞት የኖረ ተጋዳላይ ግን ደርግን አስወግዶ በሰላም ከስራ ወደ ማባረር መግባቱ ትልቅ እርምጃ አይደለምን? ለማንኛውም ግን ይህን ነጥብ ከልቦና ለመጻፍ ቅን መሆን ያሻል፡፡
አንድ ጊዜ ያነበብኩት የስነ-አስተዳደር መጽሐፍ፣ አንድ ሰው በአንድ ስልጣን ላይ ሲሾም ያለውን የማስተዳደርና አዲስ ነገር የመፍጠር ችሎታ ለመጠቀም አምስት አመት ይበቃዋል፤ በአምስት አመት በጎ ነገር ያላመጣ፣ አዲስ ነገር ያልፈጠረ ሹመኛ በጎነቱም አዲስነቱም የለውምና በሌላ ቢተካ ይበጃል፤ ይላል፡፡ ይህን መጽሀፍ ያነበብኩ ሰሞን ትዝ ይለኛል … በ83 የተሾሙት ባለስልጣናት አስራ ሁለት አመታት ግድም ሆኗቸው ነበር፡፡ እድሜ ለዚያ መጽሐፍ ‹የኢህአዴግ ሹመኞች ትልቅ አዲስ ነገር፣ ትልቅ በጎነት አምጥተዋል- ሰላም፡፡ በርግጥ በ1983 ያሰፈኑት ሰላም፣ ከአስራ ሁለት አመታት በኋላ (እኔ ይህን ሳስብ) እያረጀ ነበር፡፡
ዛሬ ሃያ ሶስተኛው አመት ላይ ሆኜ፣ እዚያ መጽሀፍ ውስጥ ያነበብኩትን የአምስት አመት የሹመት ወሰን አስታውሼ፣ ባለስልጣኖቻችንን የምሞግት ባለድርብ ቆሽት አይደለሁም፡፡ ታዛቢ ሆኛለሁ፡፡ ጠያቂ ሰው፣ ለጥያቄው መልስ ሲገደው አንድም ታዛቢ፣ አንድም ተራች ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ መላሽ በሌለበት መጠየቅ ጦስ አለው፡፡ እና መታዘብ መረጥኩ፡፡
ለምን አልታዘብ! መጠየቅ እንጂ መታዘብ አያሳስር፣ አያስገድል… ስንቱን ታዘብኩት! ስንቱን የኢህአዴግ ባለስልጣን ታዘብኩት፡፡… እንደዚያ በታንክ አናት ተቀምጠው፣ ሆሆሆሆ! እያሉ እንዳልተቀላቀሉን፣ ዛሬ ይፈሩናል፡፡ እኛን ከግፈኛ መንግስት ነጻ ያወጡበት ታንክና ጠመንጃ ዛሬ እነሱን ከእኛ ለመጠበቅ በየቤተ መንግስቱና በየሚኖሩበት ቪላ ዙሪያ ቆሟል፡፡ …መጠየቅ ጦስ አለው፤ ‹ለምን ይፈሩናል?› ብዬ አልጠይቅም፡፡ ‹አሁን እውነት እኛ የምንፈራ ሆነን ነው!›› ብዬ እታዘባለሁ፡፡
ብዙ ጊዜ ሳስበው በህይወት መኖርና የኢህአዴግን ፖለቲካዊ አጀንዳ መደገፍ (ፖለቲካዊ እንጂ ልማታዊ አላልኩም) በስልጣን ለመቆየት ዋስትና ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ ልማታዊ አጀንዳውን መደገፍ ለኢህአዴግ ሹመኛነት እንደ ትልቅ መስፈርት አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢሉኝ አብዝቶ ልማታዊ በሆነ መንግስት ትላልቅ የስልጣን ሹመት ላይ አንድ ከተማ የሚያለማ ገንዘብ ያላቸው ሹመኞች ተቀምጠዋል፡፡ ‹ልማታዊ› የሚለው ቃል የባለስልጣናትን የባንክ ደብተር፣ ሀብትና ንብረት ማልማትን ካልጨመረ በስተቀር እንደምን እነዚህ ሰዎች በስልጣን ላይ ይቆያሉ? ብዬ ላስብ አስብና እተወዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥያቄ እንጂ ትዝብት አይደለም፡፡ እናም… ‹‹እስቲ በከፈላችሁት መስዋእትነት፣ ባሳለፋችሁት አስራ ሰባት አስቸጋሪ አመታት ይሁንባችሁ … አሁን ከእኛ ከድሆቹ መዝረፍ በምድር ባያስጠይቅ በሰማይ አያስኮንንም!›› ብዬ እታዘባለሁ፡፡
ሰማንያ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ በሚኖርበት ሀገር፣ ሰማንያ ገደማ የሆኑ ሰዎች ለሃያ ሶስት አመታት ከሹመት ሹመት እየተቀያየሩ ሲኖሩ በእውነት ያሰለቻል፡፡ ለኢህአዴግም ቢሆን፣ አለማየሁ ገላጋይ እንዳለው ህዝቡን ለማብሸቅ ካልሆነ በቀር፣ ለሀገርና ለልማቱም ጭምር ቢሆን የሚያመጣው በጎ ነገር እምብዛም ነው፡፡ ለመበሻሸቅ ግን ይሆናል፡፡ በየካቢኔ ሹም-ሽሩ አዲስ ተሸሚ ቋምጦ ራዲዮና ቲቪ ላይ ያፈጠጠን ህዝብ የክልል ፕሬዚዳንቱን ሚኒስትር፣ ሚኒስትሩን አምባሳደር አድርጎ የፖለቲካ ስርዓቱም፣ ህዝቡም ላይ ከማፌዝ የበለጠ የሚያበሽቅ የለም፡፡ … አንዳንዱ የኢህአዴግ ሹም-ሹም (ልብ በሉ ሹም- ሽር አላልኩም) ይገርማል፡፡ ከአንዱ መስሪያ ቤት ወደሌላው መስሪያ ቤት የሚደረገው ሹም-ሹም የሚፈታ ውል የለውም፤ ዳሩ በውል ያልተቋጠረ እንደምን በውል ይፈታል! የኢህአዴግ ሹመት እንኳን እኛን በላያችን የተሾመብንን፣ የሹመኞቹንም አቅል ይነካል፡፡ በመጀመሪያው አምስት አመት የመሬት ሚኒስትር የነበረ ታጋይ በሚቀጥለው አምስት አመት የጠፈር ሚኒስትር ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ በየአምስቱ አመቱ በዚህ ርቀት መሽቀንጠር አእምሮ አይነካም፤ ጤና አያቃውስም? ለምንድነው ኢህአዴግ፣ በተገቢው ቦታ ተገቢውን ሹም የማያስቀምጠው? ሀገሬ ኢትዮጵያ እንደሁ የተማረ፣ እውቀቱን በልምድ ያበለፀገ ዜጋ አላጣች፣ ብዬ ልጠይቅ አስብና እተወዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥያቄ እንጂ ትዝብት አይደለም፡፡ እናም ምናለ ኢህአዴግ ስንት ውለታ የዋሉልንን ሰዎች ከወንበር ወንበር፣ ከሙያ ሙያ እየወረወረ ባያሰቃይብን፤ አሁን ማን ይሙት ለእነዚህ ሰዎች፤ ያውም በዚህ እድሜ ይህ ይገባቸዋል፤ እያልኩ እታዘባለሁ፡፡
ቆይ እኔ የምለው አምባሳደርነት ኢሉባቡር ነው እንዴ! ድሮ ድሮ በንጉሱ ዘመን፣ የተጠላ ወይም የስራ ሃላፊነቱን መወጣት ያቃተው ነበር ከንጉሱ ፊት ዞር የሚደረገው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ የግዞት ቦታ ኢሉባቡር ነበር፡፡ ሳስበው ዛሬ ዛሬ አምባሳደርነት የኢህአዴግ ኢሉባቡር ይመስለኛል፡፡ በሚኒስትርነት ወይም በሌላ ስልጣን የቆዩ ሰዎችን ዞር ለማድረግ የአምባሳደርነት ሹመት ተመራጭ የሆነ ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያ ምን የምትመስል ሀገር ናት? ዜጎችዋስ ምን ይመስላሉ? ምን ያስባሉ? የሀገሪቱ ፖሊሲ እንዴት ያለ ነው?… እነዚህን ለመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት ቦታ ነው አምባሳደርነት ሌላው አለም ስለኛ ምን ይላል? ምን ያስባል? የሚሉት ጥያቄ መልሶች በአምባሳደሮቻችን እውቀትና ልምድ ይወሰናል፡፡ ኢህአዴግ ግን ለዚህ ግድ የለውም፡፡ አምባሳደርነትን የሹመት ማስተዛዘኛ አድርጎታል፡፡ እነ ሀዲስ አለማየሁና ዘውዴ ረታን የመሳሰሉ ሰዎች ናቸው ለኔ የአምባሳደርነት ልክ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን ያውቋታልና የማን አምባሳደር እንደሆኑ ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን ይወዷታልና ጉዳትዋን ለማከም፣ ለጥቅሟ ለመሟገት ከህሊናቸው በላይ ጎትጓች አይሹም፡፡
ትዝ ይለኛል የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ቢቢሲ በእንግሊዝ የሁለቱን ሀገራት አምባሳደሮች አነጋግሮ ነበር፡፡ አሁንም የአምባሳደራችን ንግግር ትዝ ሲለኝ አፍራለሁ፡፡ ግን ለምንድነው ኢህአዴግ የሀገራችንን ገጽታ አውቀው፣ ለአለም ማሳወቅ፣ አለማቀፋዊውን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተረድተው በዚያው መንገድ መጓዝ የሚችሉትን ሰዎች አምባሳደር የማያደርገው¬? ኢህአዴግን መውደድ ሀገርን መውደድ አለመሆኑን አያውቅምን? ብዬ ልጠይቅ አስቤ ተውኩት፤ ለምን? ቢሉ፣ ያደለው ተረት እውነት ይሆናል፣ ‹‹ሚንስትር ሲያረጅ አምባሳደር ይሆናል፡፡››
Filed in: Amharic