>
5:13 pm - Saturday April 19, 6977

የዶ/ር አቢይ መመረጥ መጻኢ እድላቸውና ፈተናዎቻቸው [ሸንጎ]

“ምርጫችን መለያየት ወይም መበታተን ሳይሆን መደመር/አንድ መሆን ብቻ ነው። አማራና ኦሮሞ በወንፊት እንኳ እንደማይለያዩ ሠርገኛ ጤፍ ማለት ናቸው። ታሪካችን የአንድነትና በአንድነት አብሮ የመሥራት ታሪክ ነው፤ ለዚህም የፋሲል ግምብ ግምባታና አድዋ በቂ ምሣሌዎቻችን ናቸው። ይህ አገር የወረስነው ሳይሆን ከልጆቻችን የተዋስነው አገር ነው።” አቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዶክተር አቢይ አህመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ ከላይ የተጠቀሰውን መሰል፤ በርካታ ቀስቃሽና አገር ወዳድ ንግግሮችን በማሰማታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገዝፈውና ተወዳጅ ሆነው ብቅ ያሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ ስማቸው አሁን ጎልቶ ተሰማ እንጂ፤ እነ አቶ ለማ መገርሳና አዲሱ ኦህዴድ ለጀመሩት ለውጥ እንደ አንድ ዋነኛ አጋር ሆነው፤ ድምጻቸውን አጥፍተው ሲሰሩ እንደቆዩ ይነገራል።

ሸንጎ በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት ችሎታና አገር ወዳድነት በአያሌው የተለገሳቸው ግለሰብ ለአገር መሪነት መመረጣቸው ደስ  የሚል ዜና መሆኑን እየገለጽን፤ በሌላ በኩል አገሪቱ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ አንጻር፤ በርካታ ጠጣርና ጠመዝማዛ ፈተናውች እንደሚገጥሟቸው ከወዲሁ ማሰብ እንችላለን። ከነዚህ ውስጥ ዋነኛው የመከላከያና የጸጥታ ሀይሎች በህወሃት እዝ ስር መሆናችው ነው። ይሁን እንጂ ዶክተር አቢይ ከመመረጣቸው በፊት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ተከትለው ወደፊት ከተራመዱ (ለምሳሌ እኔ የማንም ቱቦ አልሆንም ያሉትን እናስታውሳልን) ህዝቡ ሲጠይቅና ሲዋደቅለት የቆየውን ለውጥ ለመተግበር አንዲት ቀጭን እድል ይኖራቸዋል ብለን እንገምታለን።

ይህም ቀጭን እድል ዶክተር አቢይ የሚያቋቁሙት መንግስት (ካቢኔ) ከህዝብ ጋር በተለይም ከወጣቱ ጋር የሚፈጥረው አጋርንት ነው። እስካሁን ከሰማነው ዶክተሩ በአማራና በኦሮሞ እንዲሁም በከፊል ደቡብ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው። በቅልጥፍና ወጣቶች ተደራጅተውና ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ የለውጡ አስተማማኝ ሃይል እንዲሆኑ መርዳት ይጠበቅባቸዋል ። ህጋዊ መድረኮችን በመጠቀም መንግስታቸው ክሌሎች ህዝቦች ጋር (ቤንሻንጉል፤ ጋምቤላ፤ ሱማሌ) የሚኖረውን ዝምድና ማጥበቅ;። አሁን በኢህአደግ ውስጥ ያለውን ወደ እርሳቸው ያጋደለውን የሃይል ሚዛን በመጠቀምና በኦሮሚያ ውስጥ ያላችውን የህዝብ ድጋፍና የለውጥ ፈለግ መሰረት በማድርግ ደፈር ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በፓርላማ ውስጥ ለውጥ ፈላጊ ግዛቶች ያላቸውን የቁጥር ብልጫ በአግባቡ በመጠቀም ህዝቡ የሚጠይቃቸውን ለውጦች ሊጀምሩና ወደ ቀጣዩ የለውጥ አቅጣጫ አገሪቱን ማድረስ ይችላሉ። ይህ እንግዲህ ቀጭኑ ግን ትልቁ እድላቸው ነው።፡

ጎታችና አፋኝ ሃይሎች የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ በየደረጃው መሰናክል እንደሚፈጥሩ ሊታሰብ ይገባል። ከዚህ ውስጥ በዋናነት ሊጠቅስ የሚገባው ሰሞኑን የተጀመረው የለውጥ አራማጆችን እየለቀሙ ወደ እስር ቤት ማጎር ነው። ዓለምን ጉድ ባሰኘ የአፈና አካሄድ ከእስር ቤት ከወጡ ገና ጥቂት ቀናት ያስቆጠሩ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ መሪዎችን እንደገና መልሰው  ለእስር ሰቆቃ ዳርገዋቸዋል። ሸንጎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እስራትና አፈና አጥብቆ ይኮንናል። የዶክቶር አቢይ ሃቀኛ የለውጥ ፈላጊነት የሚረጋገጠው ይህን በሰላማዊ ህዝብ ላይ የተቃጣ የመከራና የእስራት ጉዞ ማስቆም ሲችሉ ነው።  ህዝቡ እስካሁን የህወሃትን ደባ ተቋቁሞ ከመበተን አንድነትን፤ ከጥላቻ ፍቅርን፤ ከመራራቅ መቅረብን መርጧል። የዶክተር አቢይ መንግስት ስኬት ሊያመጣ የሚችልውና ከአደናቃፊዎቹም የሚመጣብትን ጥቃት ሊመክት የሚችለው  በህዝቡ ላይ እምነት ሲኖረውና ከህዝቡ ጋር ሲወዳጅ ብቻ ነው።

ዶ/ር አቢይ አሕመድ ይህንን አገር የመምራት ከፍተኛ ግዴታና ኃላፊነት ሲቀበሉ ከፊታቸው የተደቀኑ ብዙ ችግሮችና አማራጮች እንደሚጠብቋቸው ቢያውቁም፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ፤ አማራጮቹን ለማየትና ብሎም ችግሮቹን ለማስወገድ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ሊያደርጓቸው በሚችሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሸንጎ ሊያነሳቸው የሚሻቸው ዐበይት የፖለቲካ ኃሳቦች የሚከተለት ናቸው-

1.1         የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዋነኛና ቀዳሚ ዓላማ መሆን የሚገባው፤ አንዳንድ መሠረታዊ ያልሆኑ ለውጦችን አድርጎ ኢሕአዴግን ከነጉድፉ ሥልጣን ላይ ማሰንበት ሳይሆን፤ ለሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት በሩን መክፈት ይሆናል። ለሽግግር ሥርዓቱ በር ከፋች የሚሆኑ ርምጃዎች የሚከተሉትን ሊያጠቃልሉ ይገባል፦

  • ሳይውል ሳያድር በአጭር ጊዜ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስወገድ
  • ለወደፊትም የመከላከያ ሰራዊት በሲቪል አስተዳደ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ በህግ መገደብ
  • ድርጅታዊ የስለላና የግድያ መዋቅሮችን ማስወገድ፤
  • ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ባስቸኳይና ያላንዳች ቅድመ-ሁኔታ መፍታት፤

1.2        ሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት በሮችን መክፈትና የቀዳሚም ሆነ የተባባሪነት ሚና ወስዶ የሰላም ኮንፈረንስ በአገር ውስጥ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ወይም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጥሪ ጋር መተባበር፤

1.3        ተቃዋሚ ድርጅቶች ያላንዳች ተጽዕኖ በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱና የየራሳቸውን ድርጅት ምልመላ እያደረጉ ለምርጫ እንዲዘጋጁ ማበረታታትና ሕጋዊ ድጋፍም እንዲያገኙ ማድረግ፤

1.4        የሕዝቡን የመናገር፣ የመጻፍ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶችን ከአሁን ጀምሮ ማስከበር።

1.5     የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል አሁን ያሉትን ዳኞች በሙሉ በማባረር፤ አዲስ የዳኞች መደባ ስርዓት ማቋቋም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አቢይ አሕመድና በዙሪያቸው የሚያስቀምጧቸው ባለ-ራዕዮችና ዴሞክራሲያዊ አገር ወዳዶች እነዚህን ማድረግ ከቻሉ በርካታ የአገሪቱ ችግሮች ባመዛኙ ይቀረፋሉ የሚል ጽኑ ዕምነት አለን። እስካሁን በሕዝብ ላይ በአንዳንድ ወገኖች የተፈጸሙ ግፎችና ወንጀሎች ቀናቸውን ጠብቀው ፍትህ እንዲያገኙም በሩን ለውይይት መክፈት አግባብ ነው እንላለን።

ያለፍትህ ወደፊት መግፋት አይቻልምና ትውልዱ የሚጠይቀውን የፍትህ ጥያቄ በደፈናው ካሳለፍነው “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” እንዳይሆንብን ሸንጎ ጥብቅ ዕምነቱ ነው። ዶ/ር አቢይ ባሕር ዳር ላይ በተደረገው ስብሰባ ተገኝተው ተናገሩት የተባለውን ታሪካዊ ጥቅስ ሠፋ አድርገንና ለኢትዮጵያዊነትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እንዲሠራ በማድረግ፤ “ኢትዮጵያዊነት በወንፊት እንኳ ተለይቶ የማይወጣ ሠርገኛ ጤፍ ማለት ነው” ብለን በማጠቃለል ነው።

 

አንድነት ኃይል ነው!

ሰላምና ፍትኅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Filed in: Amharic