ዘውዲቱ ምኒልክ የተወለዱት ከታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አና ከወ/ሮ አብችው በያን ነው፡፡ ገና የስድስት ዓመት ተኩል ልጅ ሳሉ ለንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ልጅ ለራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ተዳሩ፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላም ራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ስለሞቱ ዘውዲቱ ወደሸዋ ተመለሱ፡፡ በ1884 ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድን አግብተው መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ጋብቻም ፈረሰና፣ በ1893 ዓ.ም የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅና የጎንደር ገዢ የሆኑትን ራስ ጉግሳ ወሌን አገቡ፡፡
🔯🔯🔯
መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከስልጣን ሲሻሩ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ታላቁን የሰለሞን ኒሻን ተሸልመው ‹‹ራስ›› ተባሉና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ፡፡ ራስ ጉግሳ ወሌም ከቤተ-መንግሥቱ ገለል እንዲሉ ተደረገ፡፡
🔯🔯🔯
ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ተሽረው ዘውዲቱና ተፈሪ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ዘውዲቱ ሞተው ተፈሪ መኮንን ንጉሰ ነገሥት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ እጅግ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ የታየበት ወቅት ነበር፡፡ ተፈሪ መኮንን ተቀናቃኞቻቸውን በስውርም በግልፅም እያዳከሙ ለከፍተኛው ስልጣን እስከሚበቁበት ጊዜ ድረስ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል አብዛኞቹ የንግሥት ዘውዲቱን ስልጣን እየገዘገዙ የተፈሪን ስልጣን ደግሞ ያጎለበቱ ነበሩ፡፡ በዚህም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለከፍተኛ ስቃይና ብስጨት እንደተዳረጉ በታሪክ ላይ ሰፍሯል፡፡
🔯🔯🔯
ልዑል አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ንጉስ ሚካኤል ዓሊን በሰገሌ ጦርነት፣ እነደጃዝማች አባውቃውንና ሌሎች የዘውዲቱ ደጋፊ መኳንንትን በጉልበትና በድርድር ካሸነፉ በኋላ አንድ ተቀናቃኝ ቀራቸው፤ ይህ ሰው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የቀድሞ ባል ራስ ጉግሳ ወሌ ነበሩ፡፡
🔯🔯🔯
ራስ ጉግሳ ከቤተ-መንግሥት እንዲርቁ በመደረጋቸውና የባለቤታቸው የዘውዲቱ ምኒልክ ስልጣን በራስ ተፈሪና ደጋፊዎቻቸው እተገዘገዘ በመሄዱ በራስ ተፈሪ መኮንን ላይ ቂም ከቋጠሩ ውለው አድረዋል፡፡ የሁለቱ ወገኖች ልዩነትና ፀብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሄደ፡፡
🔯🔯🔯
ራስ ጉግሳ ወረኢሉ መጥተው ከራስ ተፈሪ ጋር እንዲገናኙ ቢጠየቁም ‹‹አልመጣም!›› አሉ፡፡ በመንግሥት ላይ ያመፀውን የራያንና አዘቦን ሕዝብ እንዲያረጋጉና ፀጥ እንዲያሰኙ ቢታዘዙም ያመፀውን ሕዝብ ከጎናቸው አሰልፈው ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር፡፡ ከጦርነቱ በፊት እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ‹‹አሻፈረኝ›› አሉ፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክም ‹‹እባክህ እሺ ብለህ ግባ፤ ከክፉ እንዳትወድቅ›› ብለው ደብዳቤ ቢጽፉላቸውም ‹‹እምቢ›› አሉ፡፡
🔯🔯🔯
ራስ ተፈሪም ለጦርነቱ በቂ ምክንያት አገኙና በጦር ሚኒስትሩ በራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራ ጦር ላኩባቸው፡፡ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም የአንቺም ጦርነት በጌምድር ውስጥ ተካሄደ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ዋሉ፡፡ ራስ ጉግሳም የጨበጣ ውጊያ ላይ ሳሉ ጭንቅላታቸውን ተመትተው ሞቱ፡፡
🔯🔯🔯
ከእርሳቸው ሞት በኋላም ጦራቸው ውጊያውን ቢቀጥልም ሳይሳካለት ቀረ፡፡ በጦር አውሮፕላኖች የታገዘውና ከራስ ጉግሳ ጦር የተሻለ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀው የነራስ ተፈሪ ጦር ባለድል ሆነ፡፡
🔯🔯🔯
ራስ ተፈሪ ተቀናቃኞቻቸውን መንጥረው ጨረሱ፡፡ ዘውዲቱና ዘውዳቸው ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ከጦርነቱ ሁለት ቀናት በኋላ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ (መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ መቼም የመሪዎቿን ትክክለኛ የሞት ምክንያት ለማወቅ ያልታደለችው ኢትዮጵያ፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ትክክለኛ የሞት ምክንያትም ከሐሜት አላመለጠም፡፡
🔯🔯🔯
የሞታቸው ምክንያት ናቸው ተብለው ከተነገሩት መካከል … አንዳንዶች ንግሥቲቱ ከጦርነቱ አንድ ሳምንት በፊት ታመው ስለነበር በሕመሙ ምክንያት እንዳረፉ፤ ሌሎች ደግሞ የባለቤታቸውን የራስ ጉግሳን ሞት ሲሰሙ በድንጋጤ እንደሞቱ ተናግረዋል/ጽፈዋል፡፡ ‹‹ራስ ተፈሪ አሳፍነው አስገድለዋቸዋል›› የሚሉም አሉ፡፡
🔯🔯🔯
ያም ሆነ ይህ በራስ ተፈሪ መኮንንና ደጋፊዎቻቸው ሴራ እየተሰቃዩ 12 ዓመታት ከስድስት ወራት በታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዙፋን ላይ ተቀምጠው አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነፁት፣ ትምህርት እንዲስፋፋ የጣሩት … ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም በ53 ዓመታቸው አርፈው፣ ስርዓተ ቀብራቸው ራሳቸው ባሰሩት በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም በደማቅ ስርዓት ተፈፅሟል፡፡
🔯🔯🔯
ነፍስ ይማር!