>

የአፍህን ሰማን፤ እጅህ ከምን?! (መስፍን ነጋሽ)

የጠ/ሚ አብይን ንግግር በጽሞና አደመጥኩት። ታሪካዊ ንግግር ነው። ሲጠቃለል፣ ሰውየው በቃል የመፈወስ ተሰጥኦ አለው። አይተናል። ሰምተናል። ቀጥልበት እንለዋለን።
ከ27 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያችን፣ በኢትዮጵያ ፓርላማ፣ በኢትዮጵያ መሪ በክብር ተዘከረች፣ የመጽናናትን ቃል ሰማች። ኢትዮጵያ “መጪው ጊዜ የፍቅርና የይቅርታ ነው፤” ተዘጋጂ ተባለች። ድንቅ ነው።
ከመሪዎቿ መልካም ተግባርን ብቻ ሳይሆን መልካም ቃላትንም ተነፍጋ የሰነበተች አገር በዚህ ንግግር በሐሴት ብትሞላ የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባም። ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል። በአብይ ንግግሩ ቅር ሊሰኙ የሚችሉት ሰዎች ቢኖሩ በጣም ጥቂት ናቸው። አሰባሳቢ እና ጋባዥ ንግግር ነው።
ለበዓለ ሢመት የተገባ፣ ጊዜውን የሚመጥን ንግግር ነው። (እርግጥ ከ35 ደቂቃ ማጠር ይችል ነበር።) መሰል ንግግሮች የይዘት ዝርዝር ሳይሆን የመንፈስ ጉዳዮች ናቸው። አብይ ንግግሩን የገነባው በለውጥ ተስፋና በአንድነት ዙሪያ ነው። ሁሉንም የንግግሩን ዘለላዎች እያነሣን ብንተነትን ማሰሪያቸው የለውጥ ተስፋ እና አንድነት ሆኖ የምናገኘው ይመስለኛል። ስለእናቱና ሚስቱ ባነሣበት የተዘክሮ ዘለላው ሳይቀር፣ ውለታቸውን በማስታወስ በኩል የሚጠራን ወደ ተስፋና ትብብር ነው። ኢትዮጵያውያን በየዳር ድንበሩ መሰዋታቸውን ያነሣበት አቀራረብም እንደዚያው ነው። ሌሎችም ይኖሩ ይሆናል። ያስቀመጠው የለውጥ ተስፋ የማያረካው ሰው ቢኖር ስለአንደነታችንና ስለጋራ ታሪካችን ያነሣው ያካክስለታል። በተገላቢጦሹም እንደዚያው። እንደቀዳሚዎቹ መሪዎች የኢህአዴግን ስኬቶች በማጋነን አልተጠመደም። እያንዳንዱን ስኬት ጠቅሶ የሚያስከትለው ጎዶሎ እንደነበረና ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው።
የአብይ ንግግር የሚለየው በአቀራረቡ ብቻ ሳይሆን በመንፈሱም ነው። የራሱ የንግግር/አጻጻፍ ስልትም በጉልህ ተለይቶ የሚታይ ነው። እንደጭብጥ ብቻ ካየነው ግን ጥቂት የማይባሉትን ጭብጦቹን በኀማደ እና በመለስ ንግግሮች ውስጥ የምናገኛቸው ናቸው። ጊዜ ስላላገኘሁ ዝርዝሩን ልሔድበት አልችልም። ጊዜው ያላቸው ሰዎች በስፋት ቢተነትኑት እመኛለሁ።
ማሰሪያው ግን ተስፋው ወደተግባር የሚለወጥበትን ፍኖተ ካርታ ማቅረብ ነው። አብይ በቀጣዮቹ ቀናት፣ ቢበዛ ሳምንታት ውስጥ ዋና ዋና የትግበራ አቅጣጫዎቹን ማሳወቅ ይኖርበታል። የአፍህን ሰማን፤ እጅህ ከምን?!

መልካም ዕድል፣ ኢትዮጵያችን!

Filed in: Amharic