>
5:13 pm - Thursday April 19, 7612

ትልቅ አስብ! ትልቅ ታገኛለህ! - (ክፍል ሁለት) - [ኤርሚያስ ለገሰ]        

 1• ግብረ-መልስ
 በሕዝብ እምቢተኝነት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጣው ዶክተር አቢይ አህመድ  በመቶ ቀናት ሊፈፅማቸው ይገባል ያልኳቸውን የአደረጃጀትና የፓለቲካ ጉዳዬችን የያዘ አራት ግቦች በክፍል አንድ መጣጠፌ (ቀጣዮቹ 100 ቀናት!)  ጠቁሜ ነበር። እነዚህ አራት ግቦችና በስራቸው ያሉ የተቆጠሩ ተግባራት ከአረጃጀት፣ በመንግስትና በፓርቲ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስልጣንን እና ሌብነትን እንዲሁም የዲሞክራሲ እሴቶችን ለመገንባት የተዘረዘሩ ነበሩ። በወቅቱ ግቦቹና ዝርዝር ተግባራቱ ያለቀላቸው ሳይሆኑ ለውይይት መነሻ ሆነው የሚያገለግሉ እንደሆነ ተጠቁሞ ነበር።
እንደጠበኩት በተቀረፀው አጀንዳ ላይ ከፍተኛ ውይይት ተደርጐበታል። የውይይቶቹ ግብረ መልሶቹ በጥቅሉ ሲታዩ በሁለት ሊከፈሉ የሚችሉ ናቸው።
                  ***
1•1  የለውጥ ፈላጊዎች ግብረ -መልስ
 በቀረበው ሃሳብ ግራ የተጋቡ፣ ሰውየው በጤናው ሆኖ ነወይ የፃፈው የሚሉ አስተያየቶች መደመጥ ችለዋል። ከቅዠት የዘለለ አይደለም በሚል ተግባራዊነቱን የተጠራጠሩም ቀላል አይደሉም። እንዴት እንደዚህ አይነት ሀሳቦችን ለማንሳት እንደፈለኩ የጠየቁኝም ብዙ ናቸው። ትንሽ ቢሆንም “ እነ እከሌን ለምን አላየሃቸውም?” የሚል ተጨማሪ ሰዎችን የጠቆሙም አልጠፋም።
በፍፁም ንዴት ውስጥ ሆነው “ የኦነግን ፍላጐት ያሟላ!” በማለት ከፍ ዝቅ ያደረጉኝም አሉ። እግዜር ይታያችሁ እኔን የአዲሳአባ ጤባ በኦነግነት መክሰስ የጤነኝነት ነው። ያውም በግልፅ በሚነበብ መፅሐፍ “ የዘር ፓለቲካ የጥፋት መንገድ ነው!” ለማለት የከተብኩ ሰው በኦነግነት መጠርጠር ነውር አይሆንም። ከእኔ በላይ ፋራ መሆን አይመስላችሁም። ከሁሉም በላይ ያስደነገጠኝ አነዚህን የፍረጃ ፓለቲካ ጤባዎች “ እስቲ እናንተ ለሽግግር ሂደቱ የሚሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት እነማን ቢሆኑ ምርጫችሁ ይሆናል?” ተብለው ቢጠየቁ ምን ሊጽፉ እንደሆነ ሳስበው ነው።
 አሁንም ቢሆን ትችት ያቀረቡ ሰዎች “ እስቲ የእናንተን የካቢኔ አባላት ምርጫ ( ፍላጐት) እነማን እንደሆኑ በዝርዝር አቅርቡ” ማለት እፈልጋለሁ። የውጭ ጉዳይ፣ የደህንነት፣ የፋይናንስ፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ፣ የመገናኛ ሚኒስትር እንዲሆን የምትፈልጉትን በግለሰብ ደረጃ እየገለፁ እንዲሞግቱኝ እፈልጋለሁ። ፍላጐታቸውን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ካቀረበው ሰውነት ከሚነዝር ንግግር ጋር ክብደቱን እንዲመዝኑት እመክራለሁ። ምኞታቸውን የሰርቫንት ሊደርሽፕ ደቀ መዝሙር ከሆነው ዶክተር አቢይ ራዕይ ጋር አስተሳስረው ቢመለከቱት ምክሬን አቀርባለው። የሕዝብን ፍላጐት ያወቀ፣ ኢትዬጲያችንን ከሰላሳ ምናምንቴ በላይ በኩራት የጠራ መሪ ፍቃዳችንን ለመፈፀም ዝግጁነት ያንሰዋል ወይ ብለን እንጠይቅ። የሰርቫንት ሊደርሺፕ አባት የሆነው ክርስቶስ የደቀ መዝሙሮቹን እግር ሲያጥብ ሊያስተምረን ከፈለገው አንዱ “ የማይጠበቀውን እንድንጠብቅ” ነበር።
 ( ውድ አንባቢያን! መንፈሳዊ ነገር ያበዛሁት የምፅፈው የስቅለት ዋዜማ ላይ ሆኞ መሆኑን ልብ በሉልኝ። የአገር ቤቱ ጉልባን በአይኔ ላይ እየሄደ።እንደውም ሐይማኖቱን እና የኢትዬጲያን ፓለቲካ ጠንቅቆ የሚያውቅ ወዳጄ ይሄ ሳምንት መጥፎ መንፈስ ያዘሉ ጥያቄና አስተያየቶች የሚቀርቡበት ነው ብሎ እንዳስደነገጠኝ መግለጥ እፈልጋለሁ።)
 ለማንኛውም እኔ በምኖርበት የሰለጠነው አለም ፕሬዝዳንቱ ሊመርጣቸው የሚያስባቸው ሰዎች እየተባለ ለተራዘሙ ሳምንታት ጥንካሬና ድክመታቸው እየተነሳ ከፍ ዝቅ ሲደረጉ ማየት የተለመደ ነው። ይሄን አጭር መጣጥፍ እየከተብኩ እንኳን አማኑኤል መግባት የሚኖርበት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠቅላይ አቃቤ ጄኔራል የሆነውን Sessions አንስቶ Pruitt በሚባል ሰው ሊተካ ነው በማለት CNN ላይ እየተፋጩ ነው። እጅግ የምወደውና ትራምፕ ሲመረጥ በንዴት እምባውን የረጨው የቀድሞ ኦባማ አስተዳደር ያገለገለው Van Jones ( “The messy Truth”) ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ ሲሟገት ነበር።
 ይሄ የአሜሪካኖች የዲሞክራሲና ተጠያቂነት የመፍጠር ባህል በኢትዬጲያችን መለመድ አለበት። ዶክተር አቢይ በፓርላማ ያቀረበው እቅድ ከዚህ ቢልቅ እንጂ የሚያንስ አይደለም።እናም የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ሰዎች ፍላጐታችሁን የሚያሳይ አማራጭ አቅርቡ። ለትግበራው ከተጠራጠራችሁ ቢያንስ ለአምላካችሁ ስጡት። ቀይ ባህርን የከፈለ ፣ ኢትዬጲያን አልተውሽም ያለ አምላክ ለሰናፍጭ የምታክል ጥያቄያችሁ ምላሽ የማይሰጣችሁ ይመስላችኃል።
 የሆነው ሆኖ አማራጭ ሳታቀርቡ ትችት ያቀረባችሁ ወዳጆች መተቸቱ ተገቢ ቢሆንም እስቲ የእናንተንም ፍላጐት በአደባባይ ግለጡ። እስቲ  እኛም በፋንታችን አጥር ላይ ተንጠልጥለን እንድንተቻችሁ እድሉን ስጡን። ከለውጥ ፍላጐታችሁ (ጥገናዊ፣ ትራንስፎርሜሽናል፣ ራዲካል) በመነሳት ምርጫችሁ ያስኬዳል፣ አያስኬድም እንበላችሁ። እስከዛው ግን ቢያንስ ፍላጐታችንን በግላጭ በማቅረባችን “ሃሳብን በመግለፅ” የሞራል ከፍታ ላይ እንደተሰማን ከመግለፅ አንቆጠብም።
                  ***
1•2 የኮካ እና አለቆቻቸው ግብረ-መልስ
 በነገራችን ላይ ከምድረ-ፌስቡክ በዝረራ የወጡት የሕውሓት የኮካ አለቆች ሳይቀሩ ንዴታቸውን ደብቀው ጉዳዩን ለማጣጣል ሲሯሯጡ ተመልክቻለሁ። ውሎና አዳራቸውን ጫት ቤትና ቺቺኒያ ያደረጉ የኮካ አለቆች የእኔን የሺሻ ዶሴ በድሮ የራሳቸው ነውር ሲመዝኑት አይቻለሁ። አዲሱን ወይን ወደ አሮጌው አቅማዳ ሊዘረግፋት ሲንቦጫረቁ ተመልክቻለሁ። በፅሁፋቸው ከይሉኝታ መሰናበታቸውን እና የኃፍረት የመጨረሻ ድንበር መጣሳቸውን ተመልክቻለሁ። ለምን እንዲህ ሊሆኑ ቻሉ? ውስጣዊ ምክንያታቸው ምንድነው?
 ያለምንም ጥርጥር የፌስቡክ የኮካ አለቆች በምክረ ሃሳብ ፍላጐት ላይ የተነሱት በርካታ ቁምነገሮች አስደንግጧቸዋል። በዚህም ምክንያት አንዷን ግብ ለማሳካት የቀረበ አንዲት ተግባር ላይ (የግብ አንድ ተግባር ሁለት) ብቻ በማተኮር አጀንዳ ለማስቀየስ ተረባረቡ። ይህቺን ተግባርም ቢሆን ሐሳቡ ላይ ሕዝበ አዳም እንዳያተኩርና ለሚኒስትርነት የቀረቡ ግለሰቦች ላይ ብቻ አጨንቁሮ እንዲመለከት አደረጉ። ከዚህ አንፃር ከሞላ ጐደል ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል።
 ህዝቡ የካቤኔ እና ደጋፊ አደረጃጀት፣ የፓርቲና መንግስት ግንኙነት፣ የሲቪል ሰርቪስና የፓርቲ ግንኙነት፣ ስልጣንና ሙስና፣ የፓርቲ ኩባንያዎች እና የህግ የበላይነት ላይ የቀረቡትን አራት ግቦችና ግቦቹን ለማስፈፀም የቀረቡ 19 ተግባራት ነቅሶ በማውጣት እንደ “ የግብ አንድ ተግባር ሁለት” ለመከራከር እና ለመወያየት አልቻለም። በእኔ በኩል በአቀራረብ ዙሪያ የነበሩ ችግሮች ነበሩ። የአቀራረቡን ችግሮች ወደ ኃላ እመለስበታለሁ።
ከኮካ አለቆች ጋር የነበረውን ለማጠቃለል ወደ እኔ ገፅ ሳይመጡ በራሳቸው ገፅ ላይ ቢያንስ ሁለት ነገር በመግለጥ እርስ በራስ ማውራት ይችላሉ። የመጀመሪያው ኢትዬጲያዊነትን ባነገሰው በባለ ራዕዩ መሪ ዶክተር አቢይ አህመድ ውስጥ የሚካተቱት ሚኒስትሮች እና ምክትላቸው፣ የተቋማት ዋና ስራ አስፈፃሚዎች፣ ዋና ስራ አስኪያጆች፣ ኢታማዦር ሹም፣ ጠቅላይ አቃቤ፣ የፓሊስ ዴሬክተር ጄኔራል …ወዘተ እነማን ቢሆኑ ፍላጐታቸው እንደሚሆን እርስ በራስ ይወያዩ። የስርአቱ ባለቤቶች እንደ መሆናቸው መጠን ለመረጃው ሩቅ አይደሉም። ሁለተኛው የኮካ አለቆች ለሽግግር ጊዜው በምክረ ሃሳብ የቀረቡትን አራት ግቦች እና 18 ተግባራት ተመርኩዘው እርስ በራስ ይመካከሩ። ከዚህ በላይ ከእነሱ አልጠብቅም።
             ***
2• የእኔ የለውጥ ፍላጐትና የአቀራረብ ችግር
  2•1  “ ምን አይነት ለውጥ?”
የአንድ ግለሰብ ፍላጐት ” ምኞቱ” ነው። ምኞት ደግሞ ግለሰቡ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ይተሳሰራል። ለምሳሌ እኔ መሰረታዊ ለውጥ ( radical change) የምፈልግና የምተጋ ሰው ነኝ። ላየው የምፈልገው ህልም ደግሞ በኢትዬጲያ ፕሬዝዳንታዊ ስርአት ሰፍኖ ህዝቡ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመረጠው ግለሰብ በእኩልነት አገር ሲመራ ማየት ነው። ፍላጐቴ ወደዚህ ህልም የሚያደርሱንን የሽግግር መሪ ፈልጐ ማግኘት ነው። ፍላጐቴ ህልሜን ያሳካልኛል ብዬ የማስበው የሽግግር መሪ ጥሩና ሞጋች ተከታይ መሆን ነው።
         ***
2•2 የአቀራረብ ችግር፣
አስቀድሞ እንደተገለጠው በክፍል አንድ የቀረበው የምኞት ምክረ ሃሳብ የአቀራረብ ችግሮች ነበሩበት። አንዳንዶቹ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው።
• የመጀመሪያው ችግር 4 ግቦች እና 19 ተግባራት ተጃምለው ከሚቀርቡ በተናጠል ቢቀርቡ የተሻለ ይሆን ነበር።
•ሁለተኛው ለሽግግር ጊዜው የካቤኔ እና ደጋፊ አደረጃጀት፣ የፓርቲና መንግስት ግንኙነት፣ የሲቪል ሰርቪስና የፓርቲ ግንኙነት፣ ስልጣንና ሙስና፣ የፓርቲ ኩባንያዎች እና የህግ የበላይነት ላይ የቀረቡትን አራት ግቦችና ግቦቹን ለማስፈፀም የቀረቡ 19 ተግባራት አስፈላጊነት በዝርዝር መቅረብ ነበረበት። ላየው ከምፈልገው ህልምና አላማ ጋር ተቆራኝተው መተንተን ነበረባቸው። ለወደፊት በዛ መልኩ እመለስበታለሁ።
• ለሽግግር ጊዜው የቀረቡት ግቦቹና ተግባራቱ በክብደታቸው ቅደም ተከተል ከላይ ወደ ታች መቅረብ ነበረባቸው። ለምሳሌ ለእኔ ቁልፍ ግብ “ የፓርቲና የመንግስት ስራ መነጣጠል” የሚለው ግብ ሁለት ነው። ትልቁ ተግባር ደግሞ “ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩንቨርስቲ ያሉትን ወጣቶች፣ መምህራን እና የትምህርት አመራሮችን ከፓለቲካ ድርጅት አባልነት ነፃ ማድረግ ነው” የሚለው የግብ ሁለት ተግባር አራት ነው። ቀጥሎም “ የሲቪል ሰርቪሱ አባላት የማንኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል የማይሆኑበት ህግ ማውጣት” የሚለው የግብ ሁለት ተግባር ሁለት ነው።
• ለሽግግር ጊዜው ለእኔ ከካቢኔ አባላቱ ይልቅ ትልቁ ስፍራ “ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ምክር ቤቱ” ነው። የሽግግር ሂደቱን የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የአማካሪ ምክር ቤቱ ነው። ዶክተር አቢይ በኢትዬጲያ ህዝብ የምርጫ ሳጥን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተመረጠ መሪ አይደለም። ሰላማዊ፣ ዶሞክራሲያዊና በነፃ ምርጫ እየተባለ የሚነገረው አደገኛ አስተያየት በአስቸኳይ መቆም አለበት። አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ፕሮፌሰር መረራ አሊያም አንዷለም አራጌ የኢትዬጲያ ህዝብ በሙሉ በተሳተፈበት የፕሬዝዳንት ዲሞክራሲያዊ ነፃ ምርጫ ቢፎካከሩት በዝረራ እንደሚያሸንፋት ሳይታለም የተፈታ ነው። በሞራል እና ተቀባይነት ቢስተካከላቸው እንኳን እሱ ህውሓት/ ኢህአዴግን ወክሎ፣ በአብዬታዊ ዲሞክራሲና ማእከላዊነት ተሸብቦ ህዝብ ፊት የሚቀርብ በመሆኑ ኮስምኖ መታየቱ የሚቀር አይደለም።
 በመሆኑም ዶክተር አቢይም ሆነ ካቢኔዎቹ በሕዝብ ያልተመረጡ የሽግግር ጊዜ “ ባለ አደራ ካቢኔ” ናቸው። ለዲሞክራሲ ሽግግር ባለአደራ ካቢኔ እንደመሆኑ መጠን ለጊዜው ሲደራጁ የአገዛዙን ድርጅቶች ጨምሮ የኢህአዴግን ህገ መንግስት ተቀብለው ከሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ድርጅቶች ቅድሚያ የተሰጠበት ነው።
 የኢህአዴግ ድርጅቶች የትኛውንም መመዘኛ ባያሟሉም ካልተካተቱ የሽግግር ሂደቱን ይበጠብጣሉ በሚል የተካተቱ ናቸው። በተለይ ህውሓት የተሰጠው ቦታ ከችሎታው በላይ ቢሆንም የሽግግሩ ራስ ምታት ከሚሆን በችሎታ ማነስ የሚመጣው ጉዳት ይሻላል በሚል ነው።
 የኢህአዴግን ተቀብለው ለምርጫ ከሚንቀሳቀሱት ድርጅታቸውን በበላይነት የሚወክሉት ሊቀ መናብርቱ በመሆናቸው የተካተቱ ናቸው። ፕሮፌሰር መረራ፣ አብርሃ ደስታ እና የሺዋስ ለዚህ አብነት ይሆናሉ።የደረሰባቸው እስርና መከራ እንደተጠበቀ ሆኖ። ሁለተኛው የአገዛዙ ግፍ የተገለጠባቸው ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ናቸው። ሶስተኛው ከፓርቲ ውጭ ያሉ ሞዴል ተሟጋቾች የተካተተበት ነው። አራተኛው የመንግስታዊ አሰራር፣ ሙያዊ እውቀትና ህዝቡ ሊማርባቸው የሚችሉ ፓለቲካዊ ዶክመንቶችን ያቀረቡ ናቸው።
ለምሳሌ በሽግግር ጊዜው በፍትሕ ሚኒስትርነት ቢመደብ ፍላጐቴ የሆነው አቶ ተማም አባቡልጋ ለፍትሕ መረጋገጥ ህይወቱን የሰጠ የግፍ ምልክት ስለሆነ ነው። ኢፍትሐዊነትን በመታገሉ ምክንያት ፍቃዱን ተነጥቆ ለችግር እንዲጋለጥ የተደረገ ነው። ለማህበራዊና መዝናኛ የተመደበችው አርቲስት አስቴር በዳኔ የህውሓት “ ጠላት/ ወዳጅ” ትርክት ነውረኝነት ምሶሶው በቆመበት ደደቢት የገለጠች እንስት ናት። በሂደትም አንገታቸውን አስደፍታ እየተናነቃቸው “ ተፎካካሪ” እንዲሉ አድርጋለች። ዛሬም በረኸት ስምኦን በተጐለተበት ስብሰባ “ መቼ ነው ስልጣናችሁ የሚያልቀው፣ አንድ ፓርቲ ከሁለት ጊዜ በኃላ ለሌላ ይስጥ!” በማለት በአደባባይ የገለጠች ጀግና ናት። የትነበርሽም ብትሆን ለኢትዬጲያውያን በፅናት ከታገሉ የማይቻል ነገር እንደሌለ ተምሳሌት የሆነች ናት።
ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ በቀለ ገርባ፣ ኮረኔል ደመቀ፣ አንዷለም አራጌ፣ ስዩም ተሾመ ከሙያዊ እውቀታቸው በተጨማሪ ሞዴል ተሟጋቾች በመሆናቸው ነው። ይሄ ማለት እነዚህ ከሁሉም የተሻሉ ናቸው ማለት አይደለም። በካቢኔው ተልእኮና ግቦቹ ላይ መስማማት ከተደረሰ እከሌ ከእንቶኔ ይሻላል በማለት መተካት እጅጉን ቀላል ይሆናል።
           ***
3•  የሚጠበቅና እየሆነ ያለው
    3•1 “ ክላስተሪንግ በጓሮ በር!”
  ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች እየሰማን ያለነው ነገር በጣም አስደንጋጭ ነው። አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከጨዋታ ውጪ የሚያወጣ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች የወሳኝ ስራዎች ባለቤት ሆነዋል። መጀመሪያ በ12 የተደራጁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃላ ወደ 7 የወረዱ ግብረ ሃይሎች ( Task Force) ተደራጅተው የጠቅላዩን ወሳኝ ስራዎች ጠቅልለው ወስደዋል። ከሁሉም በላይ ለውጥ ይመጣል በሚል ተስፋ ላደረጉ ኢትዬጲያውያን የሚያሳዝነው ክላስተሩን የሚመሩት ሰዎች እነማን እንደሆኑ መታወቃቸው ነው። ቡድኑ እስከሚቀጥለው የኢህአዴግ ጉባኤ ይቀጥላል መባሉ ሌላ አስደንጋጭ መርዶ ነው። ቢያንስ አራቱን እንመልከት።
 # የመጀመሪያው ግብረ ሀይል “ ዲሞክራታይዜሽን” የተባለ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የክላስተሩ አስተባባሪ በረኸት ስምኦን እና ህላዌ ዬሴፍ ናቸው። በረኸት በመላው ኢትዬጲያ ያሉ የህዝብ አደረጃጀቶችን፣ ሲቪክ ማህበራትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ወጣቶችና ሴቶችን በሀላፊነት እንዲመራ ተሰጥቶታል። በሌላ አነጋገር የኢህአዴግ ቢሮን፣ የወጣቶች ሚኒስትርን፣ ሴቶች ሚኒስትርን፣ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን በክላስተር የሚመራው በሕዝብ እጅግ የሚጠላው በረኸት ስምኦን ሆኗል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ቦታዎች የሚካሄዱ የህዝብ ስብሰባዎች ሰነድ የሚዘጋጀው፣ መድረክ መሪ የሚመርጠው፣ በየቀኑ የመወያያ ነጥቦች የሚያሰራጨው እና የሚመራው በረኸት ስምኦን ነው። ከዚህ በተጨማሪም “ ምድር አንቀጥቅጥ” የሚል ስያሜዎች የተሰጣቸውን ስብሰባዎች እየገመገመ በድርጅት እና የመንግስት ሚዲያዎች እንዲተላለፋ፣ ተሳታፊዎችን ወደ ፓርቲ ምልመላ መምጣታቸውን የሚያረጋግጠው ህላዌ ዬሴፍ እንደሆነ ተነግሮኛል። በረኸት፣ ህላዌና ሽፈራው ሽጉጤ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እሳትና ጭድ መሆናቸው ለሚያውቅ ደግሞ ዶክተር አቢይ የገባበትን አጣብቂኝ በቀላሉ ይገነዘባል።
# ሁለተኛው ክላስተር “ የኢኮኖሚ ጉዳዬች ግብረ ሀይል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ክላስተሩን የሚመሩት ህውሓቶቹ አርከበ እቁባይ እና ዶክተር አብርሃም ናቸው።
# ሶስተኛው ክላስተር “ ድርጅት የማጠናከር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ፓርላማውን፣ የክልል ምክር ቤቶችን፣ የማእከላዊ ኮሚቴ እና እስከ ቀበሌ ያለውን ምክር ቤት የሚመራ ነው። ለዚህ ክላስተር ሃላፊነት የተሰጠው በዋናነት ለአባዱላ ገመዳ እና ሽፈራው ሽጉጤ ነው። ከዚህ በኃላ ከላይ እስከ ቀበሌ ያሉት የምክር ቤት አባላት ወደ ድሮ አድርባይነታቸው እንዲመለሱ ለአባዱላ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
# ሌላው አስቂኝ ግብረ ሃይል “ ህገ ወጥነት መከላከል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የበላይ አስተባባሪው አባይ ፀሀዬ መሆኑ እየተገለጠ ነው።
# ሌላው ክላስተር “ የውጭ ግንኙነት” የሚባል ሲሆን አስተባባሪው ስዩም መስፍንና ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው። ይሄ ቡድን የውጭ አገሮችን ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያንን እና ትውልድ ኢትዬጲያውያንን የማማለል ስራ ይሰራል። በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ አንዳንድ ግለሰቦች በዲያስፓራው ስም እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ከጀርባ ሆኖ የሚመራው ይሄ ቡድን እንደሆነ ይነገራል።
ማስጠንቀቂያ:-
መልእክቱን ያደረሱን ሰዎች ዶክተር አቢይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይሄንን በግብረ ሃይል ስም በጓሮ በር የገባውን ክላስተር ማፍረስ ካልቻለ በመጀመሪያው ወራት ኃይለማርያም የገባበትን ቅርቃር ሰተት ብሎ ይገባል። እናም ጊዜ ሳያጠፋ በይፋ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ ክላስተሮቹን ማፍረስ ይኖርበታል። አባይ ፀሀዬን፣ በረከትን፣ ስዩም መስፍንን፣ አርከበ እቁባይን በጡረታ መሸኘት አለበት።
               ***
3•2  የካቢኔ ለውጥ ይኖራል ወይ? 
 የካቢኔ ለውጥ ይኑር አይኑር የሚለው አጀንዳ አዲስ መጨቃጨቂያ ሆኖ ብቅ ብሏል። ህውሓቶች ባጠቃላይ፣ ብአዴን ውስጥ የበረከት ኔትወርክና የሽፈራው ሽጉጤ ክሊኮች በአንድ መስመር ተሰልፈዋል። እነዚህ ሀይሎች ክፍተት የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ በመሆኑ አዲስ ካቢኔ መኖር የለበትም የሚል አቋም ወስደዋል። ህውሓት በደብረጺዬን ምትክ ከህውሓት ስራ አስፈፃሚ ይመድባል በሚል ግልፅ አድርገዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ሕውሓቶችና ተላላኪዎቻቸው የያዙት አቋም “ አዲስ ካቢኔ የሚደራጅ ከሆነ እንኳን ስልጣኑ የብሔራዊ እና አጋር ድርጅቶቹ ነው” የሚል ነው።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን የሰጠነውን ተቀብሎ ስምሪት መስጠት ብቻ ነው እስከማለት ደርሰዋል። በተለይ በበረኸት የሚመራው ብአዴን ከህውሓት በላይ ህውሓት የሆኑትን ጌታቸው አምባዬ፣ ከበደ ጫኔ፣ አለምነው መኮንን፣ ዶክተር ጥላዬ ጌቱ፣ አቶ አህመድ አብተውን ለሚኒስትርነት በፊት መስመር አሰልፏል። ሽፈራው ሽጉጤም ራሱን ጨምሮ ከዶክተር አቢይ ጋር አይንና ናጫ የሆኑትን ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ሞፈሪያት ካሚል፣ ተስፋዬ በጅጋ፣አሰፋ አቢዩና ተክለ ወልድን ማሰለፋ እየተነገረ ነው።
 መጨረሻው ምን ይሆናል? ከዶክተር አቢይ አቅም በላይ ነው? በፍፁም! የማያቋርጥ የህዝብ ትግል እስከቀጠለ ድረስ! በተጨማሪም ትልቅ የሚያስብ በመሆኑ።
Filed in: Amharic