>

‘የወንጁካን’ ነገር እስኪ እንነጋገር* (ዘላለም ክብረት)

ዲቫና፣ ጨንገሬ፣ አዋሳ፣ ኦሮሚቲ፣ ፈላው፣ ጋጋ፣ ዴታ፣ መለኛው፣ ያኪኒ፣ ጨሰ፣ ቤባ፣ ዚጊ፣ ጆጅየ … ቅፅል ስም የሌለው እስረኛ ማግኝት ከባድ ነው፡፡ ሁሉም በተለያየ ምክንያት ነው ቅጽል ስም የሚሰጠው፡፡

ለምሳሌ ‹ዴታ› የእውነት ስሙ ‹ታደሰ› ነው፡፡ ታደሰ ሲቆላመጥ ‹ታዴ› ነው፡፡ ‹ታዴ› ሲዘንጥ ፊደላቱ ተገለባብጠው ‹ዴታ› ይባላል፡፡ ታዲያ ዴታ ቀላል ሰው አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ወዳጆቻችን አንዱ ነበር፡፡ ግዙፍ ነው፡፡ እጁ በጣም ትልቅ ስለሆነ፡ ‹‹ይሄ እጅ ለዓለም ሠላም ያሰጋል›› እያለ በራሱ ይቀልዳል፡፡ ‹ጋጋ› ደግሞ ፊቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተቦጫጨረ ስለሆነ ‹ወርቁ› የሚለውን ስም ትቶ ሁሉም እስረኛ ‹ጋጋ› ይለዋል፡፡ ‹‹ጠዋት ጠዋት ፊትህን በቦምብ ነው እንዴ የምታጠበው?›› ብሎ ሲጠይቀው አንድ ወዳጃችን ትዝ ይለኛል … እስር ቤት የራሱ ክፋት ቢኖረውም አብዛኛው እስረኛ በጣም ጨዋ፤ ሰላማዊና ጨዋታ አዋቂ ነው፡፡

ብዙ ጓደኞቻቸን ትዝ አሉኝና ነው ይሄን መፃፌ፡፡ አቡሽ የኛ ከባድ ጀለስ ቤቱን በአንድ እግሩ ያቆመው ነበር፡፡ ‹‹ጀለስካ ምንሼ? ጦማሪ ነኝ አላለሽም አንዴ? እስኪ ቢጫ ወዬ በይኝ?›› እያለ መቀለድ አመሉ ነው፡፡ ትርጉም፡ ‹‹ጦማሪ ነኝ አላልሽም እንዴ ወዳጄ? አስኪ አንድ አምስት ብር ሲጪኝ?›› ማለቱ ነው፡፡ አንድ ቀን ስለኢትዮጵያ ስናወራ አቡሽ እንዲህ አለን፡

‹‹አሁን ኢትዮጵያ ምኗ ይወደዳል? አንድ የሚያስደስት ነገር የሌለበት አገር ምኑ ይወደዳል? እኔ ልንገርህ ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ጋር ጦርነት ገጥማ ሌላው አገር በቲማቲም ኢትዮጵያ በመሳሪያ ቢገጥሙ እንኳን ‹ኧረ ንኩት› ነው የምለው፡፡ ምነው በየአገሩ የሚፈነዳው እሳተ ጎመራና መሬት መንቀጥቀጥ እዚህ ጠፋ? ይሄን ሕዝብ አንፈቅፍቆ ቢቀቅልልኝ ምን አለበት? …››

አይ አቡሽ …

ያልፋል ደግሞ ትዝ አለኝ፡፡ ትንሹ ያልፋል፡፡ የቆሼው ልጅ ያልፋል፡፡ ‹‹ሚስቴ ስትናፍቀኝ፡

‹‹የጎጃም ወተት፤ የወሎ ብስኩት፣
እኔ እወድሻለሁ፤ አባቴ ይሙት፡፡››

እያልኩ ግጥም እፅፍላት ነበር፤ አሁን ከታሰርኩ በኋላ ሌላ ልጅ መጥበሷን ሰምቻለሁ፡፡ ወዮ ለጠባሽ፡፡ ልፈታለት ብቻ … ›› ይል ነበር፤ በእጅ የተሳለ ‘የኒኪ ሚናጅን’ ስዕል በራስጌው የለጠፈው ትንሹ ያልፋል፡፡

አይ ያልፋል …

የመግጠም ነገር ሲነሳ አንድ ሔኖክ የተባለ ለትንሽ ጊዜያት ከእኔ አልጋ በላይ የሚተኛ፤ ቀኑን ሙሉ ከአልጋው የማይወርድ መጠጥ አዕምሮውን ያሳጣው ልጅ ትዝ አለኝ፡፡ ቀስ እያለ ነው የሚያወራው፡፡ ቀኑን ሙሉ ስለወሲብ ነበር የሚያወራው፡፡ የማያመጣው ወሲባዊ ግጥም አልነበረም፡፡ አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ ሔኖክ ከእንቅልፉ እንደነቃ፡

‹‹አሰላም አሊኩም ብዬ ቤት ስገባ፣
እግሮቿን አንስታ አለችኝ ጀባ፣
እኔም ደፈንኩላት ዝንብ እንዳይገባ፡፡››

በማለት ቀኑን ሲጀምር ሰማሁ፡፡ ‹‹ጀመረህ እንግዲህ›› ይሉታል ከጎኑ ያሉ ወዳጆቻችን፡፡

አይ ሔኖክ …

ኢትዮጵያ ውስጥ የማሰቃየት ተግባር (ከዚህ በኋላ የእንግሊዘኛውን ‘ቶርቸር’ እጠቀማለሁ) የማይፈፀምበት ቦታና ሁኔታ ማግኝት አዳጋች ነው፡፡ በአብዛኛው የፖለቲካ እስረኞች ስቃይና እንግልት ስለሚዘገብና ስለምንሰማ ‹የደረቅ ወንጀል ተጠርጣሪዎች› ላይ ስለሚደርሰው እንግልትና ‘ቶርቸር’ ብዙም ትኩረት አንሰጠውም፡፡ እውነታው ግን አሁን ባለው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ በማንኛውም አይነት ወንጀል የተጠረጠረ ሰው ‘ቶርቸር’ ሳይፈፀምበት ያልፋል ማለት እጅግ እድለኛ መሆንንን ይጠይቃል፡፡ ‹ማዕከላዊን› የምናውቀውን ያህል ‹ወንጁካን› አናውቀውም፡፡ ወንጁካ ከማዕከላዊ ጎን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ነው፡፡ በጣም በተደጋጋሚ ሲታሰሩ ሲፈቱ የነበሩ ደጋጋሚ ወንጀለኞች ሳይቀሩ ወንጁካን እጅግ ይፈሩታል፡፡ አንድ ሐዋላ በማጭበርበር የተከሰሰ የማዕከላዊ ወዳጄ፡ ‹‹ሲይዙን ወንጁካ ሊያስገቡን መስሎኝ በጣም ፈርቼ ነበር፤ ወደ ማዕከላዊ ሲያሳልፉን እፎይ ነበር ያልኩት›› ሲለኝ፤ ‹‹ወንጁካ እንዲህ አስፈሪ ነው እንዴ?›› ማለቴ አልቀረም ነበር፡፡

ቂሊንጦ ስንወርድ ነው ስለወንጁካ በሰፊው መስማት የጀመርኩት፡፡ የሦስት የእስር ወዳጆቻችን ታሪክ መንገሩ ስለወንጁካ ብዙ ይነግረናል፡፡

ፋንትሽ

ፋንትሽ ከብዙ የእስር ቤት ወዳጆቻችን አንዱ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ እስረኞች ምርመራ ከጨረሱ በኋላ የተጠረጠሩበትን ወንጀል እውነታውን ለታሳሪዎች የመንገር ችግር የለባቸውም፡፡ ሰው ገድለው ከሆነም ‹‹አዎ ገድየዋለሁ፤ ግን ጣቢያም ፍርድ ቤትም ክጃለሁ›› ማለት አይፈሩም፡፡ ፋንትሽ ግን ሁሌም እንዳልገደለ ይናገራል፡፡ ብዙው እስረኛም ያምነዋል፡፡ ፋንትሽ ‹ሰው ገድለሃል› ተብሎ ተይዞ ወንጁካ ሲገባ በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መታሰሩ ነው፡፡ እንደገባ ወዲያውኑ ወደምርመራ ክፍል ተጠርቶ ነበር መቀጥቀጥ የጀመረው፡፡ ሁሉም ነገር አሰደንግጦታል፡፡ ለሰዓታት ከተቀጠቀጠ በኋላ ሁሉም ደብዳቢዎች ወጥተው አንድ ሰው ወደ ክፍሉ ገብቶ፤ ‹‹ ‹እኔ ነኝ ዋነኛ መርማሪህ፡፡ ትብብር ካደረክ በሕይወት ትወጣለህ፤ ያለዛ በራስህ ላይ ፍረድ›፤ ሲለኝ ‹መርማሪህ ነኝ› ስላለኝ ደስ ብሎኝ፤ ‹መርማሪ ከሆነማ በሆነ የቴክኖሉጅ መሳሪያ እውነቱን ሊያገኝው ነው› ብዬ ደስ አለኝ›› ይላል ፋንትሽ፡፡ ምርመራ ማለት ድብደባ መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡ የሕይወት ታሪኩን ተናግሮ የተጠረጠረበትን ወንጀል ሲጠየቅ ምንም እንደማያውቅ በገለፀ ጊዜ ነው ምርመራ ምን እንደሆነ የተረዳው፡፡ ‹‹ዋናው መርማሪ ከሌሎች ሁለት መርማሪዎች ጋር በመሆን ‹ወፌ ይላላ› ሰቅለው ያልደበደቡኝ አካል የለም›› ይላል፡፡ ጥፍሩ በድብደባው ብዛት ተነቅሎ ወደ ቂሊንጦ በወረደበት ወቅት ያነክስ እንደነበር ጓደኞቹ ምስክሮቹ ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ‹ወፌ ይላላ› ከተገለበጠ በኋላ ‹‹አዎ ገድየዋለሁ›› ብሎ ፈረመ፡፡ አራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤትም ቀርቦ ይሄኑ ቃል ደገመ፡፡ በዚሁ ምክንያት ፋንትሽ በእስር ቤት ቋንቋ 16 ዳገት ጠጣ፡፡ 16 ዓመታት ፅኑ እስራት፡፡ አሁን ፋንትሽ ቃሊቲ ነው፡፡

ገሬ

ገሬ ጥሩ የእስር ቤት ወዳጃችን ነው፡፡ በጣም ሲበዛ ትሁትና ጨዋ ነው፡፡ ገሬም እንደ ፋንትሽ በሰው መግደል ወንጀል ነበር የተከሰሰው፡፡ ገሬ ግን በትክክልም ሰው መግደሉን ይናገራል፡፡ አገዳደሉ ግራ አጋቢ ቢሆንም፡፡ አንዲህ ነበር የሆነው፡ አንድ የተረገመች ቀን ገሬ ሰፈሩ ግሮሰሪ ብቻውን ይጠጣል፡፡ አንድ የሰፈሩ በጠባጭ ወደገሬ ይመጣና ብር እንዲያበድረው ይጠይቀዋል፡፡ ገሬ እንደሌለው ሲነግረው፤ ጠያቂው ገሬን አበሻቅጦ ሰድቦ ተፍቶበት ይሄዳል፡፡ ሞቅ ያለው ገሬ በሰው ፊት መዋረዱ እያንገበገበው ከግሮሰሪው ወጥቶ ቤት በመሔድ እቤት ያገኝውን የበር መደገፊያ እንጨት አንስቶ ያዋረደውን ሰው ይጠብቅ ያዘ፡፡ ብዙም ሳይቆይ አንደ ሰው በጨለማው ውስጥ ሲሔድ ይታየዋል፡፡ ከጀርባው ሲያየው ያዋረደው ሰው ነው፡፡ ማጅራቱ ላይ በያዘው እንጨት ይመታውና ምንም እንዳልተፈጠረ ቤቱ ገብቶ ይተኛል፡፡ ጠዋት ሲነቃ ጎረቤቱ ዳንኤል መሞቱን ይሰማል፡፡ ለካ ማታ የመታው ሰው በጥባጩን ሳይሆን ወዳጁን ጎረቤቱን በስህተት (በሕግ አነጋገር ‘Mistake of Fact’ እንደምንለው) ነው፡፡ ገሬ በራሱ ፈቃድ ለፖሊስ እጁን ሰጠ፤ ወንጁካ ገባ፡፡ ምንም እንኳን ድርጊቱን መፈፀሙን ቢያምንም ወንጁካ ገብቶ ሳይሰቃዩ መውጣት ነውር ነውና፤ መርማሪዎቹ ‹‹ ‹የገደልኩት ለመዝረፍ ነው› በለህ እመን›› እያሉ ቁም ስቅሉን አሳዩት፤ በድብደባ፡፡ አልቻለም ፈረመ፡፡ ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ ወስደው ሊዘርፍ እንደነበር የሚያሳይ ፎቶ አነሱት ‹(ክሊፕ ማሰራት› ይባላል እስር ቤት)፡፡ ‹‹ የግፋቸው ግፍ፤ የገደልኩበትን እንጨት ሲያጡት ለክሊፕ መስሪያ የፋዘርን ከዘራ ከቤት ወስደው በኤግዚቢትነት አስመዘገቡት›› ይላል ገሬ እየሳቀ ስለ ሁኔታው ሲናገር፡፡ በመጨረሻም ገሬ ‹ለመዝረፍ ገደለ› ተብሎ 18 ዓመታት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ አሁን ገሬ ቃሊቲ ነው፡፡

አይመኔ

አይመኔ እስር ቤት እንግሊዝኛ ከሚናገሩ ጥቂት እስረኞች አንዱ ነበር፡፡ ተወልዶ ያደገው ኬንያ ነው፡፡ ኬንያ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ዘመዶቹን ለመጠየቅ መጥቶ እንደዋዛ ቀረ፡፡ ኢትዮጵያ መጥቶም አገልግሎት ላይ የዋሉ እቃዎችን (በተለይም ኮምፒውተሮችን) በርካሽ ገዝቶ በመሸጥ ስራ ውስጥ ተሰማራ፡፡ አንድ ቀን አንድ ወዳጁ ‹‹አንድ ላፕቶፕ አለኝ፤ ግዛኝ›› ይለውና እዛው ሰፈሩ ይቀጥረዋል፡፡ አይመኔ ላፕቶፑን ለመግዛት የተቀጣጠሩበት ቦታ ሲደርስ ያለው ልጅ ከሩቅ የአንድ መኪናን መስታዎት ፈልቅቆ እቃ ሲያነሳ ያየዋል፡፡ ልጁ የተባለውን ላፕቶፕ ለአይመን ሰጥቶ ከአካባቢው ወዲያውኑ ይጠፋል፡፡ አይመንም በክትትል ፖሊሶች ‹‹አንተ ነህ የመኪናውን መስታዎት ፈልቅቀህ የዘረፍከው›› ይባላል፡፡ የተለያዩ ጣቢያዎች ለቀናት ከቆየ በኋላ ‹‹ብር ስጠኝና ልፍታህ›› ካለው ፖሊስ ጋር ባለመስማማቱ መርማሪው ለበቀል ወደ ወንጁካ ይለከዋል፡፡ ወንጁካ ሲደርስ፡ ‹‹አዲስ አባባ ከተማ ውስጥ የመኪና መስታዎት በመፈልቀቅ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ሁሉ አንተ ነህ የፈፀምከው›› በሚል፤ ከሐያ በላይ ተጨማሪ ክሶች ላይ ‹አምነህ ፈርም› ይሉታል፡፡ እንኳን ሐያውን መጀመሪያም የተጠረጠረበትን አንድ ክስ ያልፈፀመው አይመን ግራ ተጋብቶ ‹እንዴት?› ይላል፡፡ ድብደባው ተጀመረ፡፡ ቶርቸሩ ለቀናት ቀጥሎ ከቀናት በኋላ የአይመን ቀኝ እጅ አልሰራ ስላለ አይመን ‹ከምሞት› በሚል ምክንያት ሐያ አምስት የተለያዩ የእምነት ቃሎችን ፈረመ፡፡ አይመን አማርኛ ማንበብና መፃፍ አይችልም፡፡ ባዶ ወረቀት ላይ ይፈርማል መርማሪዎቹ ቀኑንና ቦታውን እየቀየሩ ይሞላሉ፡፡ በመጨረሻም አስራ ዘጠኝ የተለያዩ ክሶች ተመሰረቱበት፡፡ የአይመን ቀኝ እጅ አልንቀሳቀስ በማለቱ ቂሊንጦ ከመጣ በኋላ ፖሊስ ሆስፒታል ለአንድ ወር ተኝቶ ቀዶ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ አይመኔ እኔ በተፈታሁበት ወቅት በመጀመሪያው ክስ 8 ዓመት ተፈርዶበት ወደ ቃሊቲ ተወስዶ ነበር፡፡ ገና አስራ ስምንት ክሶች ይቀሩታል፡፡ አይመኔ አሁን ቃሊቲ ነው፡፡

የወንጁካ ታሪክ አያልቅም፡፡ ግፉ በጣም መጠነ ሰፊ ነው፡፡ እንዲሁ የስቃይ ሰለባዎችን ስናስብ ‹እንዲህ ያለ የከበደ መከራን ያሳለፉ ወዳጆችን ማሰቡም ጥሩ ነው› በሚል ይህ ተፃፈ እንጅ፡፡

*ይህ ጽሑፍ በሰኔ 2009 ‹ዓለማቀፍ የማሰቃየት ተግባር ሰለባዎች የድጋፍ ቀንን› አስመልክቶ የፌስቡክ ገፄ ላይ ተለጥፎ የነበረ ጽሑፍ ነው፡፡

Filed in: Amharic