>

የጣቢያ እስረኞች ማታ ማታ… ("የዱርዬው ባሕል") [በፍቃዱ ዘ ሀይሉ]

 ለኢትዮጵያ ክርስትያኖች ዛሬ “የቅዳሜ ስኡር” ነው። የፋሲካ ዋዜማ። የሚያሳዝን እና የሚያስቆጭ ወሬ አላወራላችሁም። ስለእስር ቆይታችን የጻፍኩትን አጭር ማስታወሻ ሰኞ (ወይ ማክሰኞ) አዲስ ስታንዳርድ ላይ ታነባላችሁ ብዬ እተነብያለሁ 😜። ለዛሬ ግን በየፖሊስ ጣቢያው ያሉ እስረኞች ቀን ጠያቂ በማስተናገድ፣ ፍርድ ቤት ደርሶ በመምጣት እና የመሳሰሉት ተጠምደው ውለው በጠባብ ክፍሎች ታጉረው ለማምሻ የሚጨዋወቱትን ነው የማስነብባችሁ። ጫወታው ከጣቢያ ጣቢያ ቢለያይም ተመሳሳይ ነው። የሚከተለው ታሪክ እኛ ባለፈው ሳምንት ንፋስ ስልክ (ላፍቶ) ክፍለከተማ ፖሊስ መምሪያ ያለው ጣቢያ ያሳለፍነው ነው።
አዲስ እስረኛ የገባ ካለ ማታ “ተነስ” ይባላል። አዛዡ ካፖው ነው። አዲሱ እስረኛ ይቆማል። እግሩን ገጥሞ፣ እጁን ወደኋላ አድርጎ እንዲቆም የታዘዛል። የእስረኞች ሁሉ ዓይኖች ሁሉ ወደ እርሱ ይፈጣሉ።
ካፖው፦ ሥምህ ማነው?
እስረኛው መደንገጡ ስለማይቀር ሥሙን ቀዝቀዝ አድርጎ ይናገራል።
ካፖው “ይሰማል?” ብሎ ቤቱን ሲጠይቅ። ቤቱ በሙሉ ድምፅ “አይሰማም” ብሎ ይጮኻል። ይሄኔ አዲሱ እስረኛ በድንጋጤ ድምፁን ጮክ አድርጎ ይናገራል። ይሄ የሚደረግበት መንገድ ‘ድራማቲክ’ ነው። የኛ ካፖ ለምሳሌ እግሩን አጣምሮ ተቀምጦ ባለአንድ መስታወት መነፅር አጥልቆ ከተጠያቂው ፊትለፊት ተቀምጦ ነው። ተመላላሽ እስረኞች ግን እምብዛም አይደነግጡም።
ጥያቄው ሲቀጥል “የገባህበት ወንጀል ምንድን ነው?” ይባላል። ደረቅ ቼክ ጽፌ፣ መኪና አደጋ አድርሼ፣ ወዘተ… ይላሉ። “ዱርዬውም” ያው በራሱ ቋንቋ ያወራል። ለምሳሌ አንድ የዐሥራ ምናምን አመት ጩጬ ልጅ “ወንጀል?” ሲባል “ሰተቴ” ብሏል። ለእንግዶች ሲብራራ የሰው ቤት ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶ መዝረፍ ነው። ከዚያም “መርማሪው እያጣራ ነው?” ተብሎ ይጠየቃል። “አዎ” ሲል። ካፖው “ቤቱስ?” ይላል። ቤቱም “ይጣራለታል” ይላል ባንድ ድምፅ።
ጥያቄው ይቀጥላል። ካፖው የሚከተለውን ጥያቄ በፍጥነት ነው የሚያነበንበው። መልሱ ላይ ብዙዎች ይሸወዳሉ።
ካፖው፦ “ብዙዎቻችን ፆታችንን ስንጠየቅ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ወዘተ እንላለን። አንተስ?”
መልሱ “ወንድ” ቢሆንም (የወንዶች ቤት በመሆኑ) ብዙዎች ግን ብሔራቸውን ይናገራሉ።
ወዲያው ካፖው “ፆታውን ያላወቀው” ሲል፣ ቤቱ “እራሱ” ይላል። (ፆታውን ቢያውቅም “ፃታውን ያወቀው” መባሉ አይቀርም።) አሁንም ካፖው “ቅልስልሱ” ሲል፣ ቤቱ “እራሱ” ይላል። ወንጀሉን ጠቅሶ ሲናገር፣ ቤቱ “ይጣራለታል” ብሎ በአንድ ድምፅ ያስገመግማል። ከዚያ በደንቡ መሠረት ለቤቱ ሦስት ዘፈን፣ ሦስት ቀልድ፣ ሦስት ገጠመኝ እንዲናገር ይፈረድበታል። እችላለሁ ያለ ይናገራል። አልችልም ያለ ይቀጣል።
ቅጣቱ በካፖው አገላለጽ “ለቤቱ አንድ የሙዚቃ አልበም መግዛት ነው”። የአንድ አልበም ዋጋ 200 ብር ነው። ካፖው እንደነገረን “ከሁለት ወር በፊት ኮማንድ ፖስት ከልክሎ ነው እንጂ ቅጂ በመቶ ብር ይሸጥ ነበር”። የቻለ ይከፍላል። ያልቻለ ለነገ ሊከፍል ዋስ ይጠራል። አለበለዚያ የማይቻል ስፖርታዊ ቅጣት ይቀጣል – ለመሳቂያነት።
የአልበም ለከፈሉ ሰዎች የሚዘፍንላቸው ካፖው ራሱ ነው። ገንዘቡን የሚወስደው እሱ ነው መሰለኝ።
የታዋቂ ዜማዎችን እየቀየሩ በዱርዬው ሥራ ማቀንቀን የተለመደ ነው። ካፖው ከሚዘፍናቸው ዘፈኖች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።
“ጨፍቅ” ይባላል ዘፈን ሲጀመር። ጣታችሁን በማፋጨት ዜማ ፍጠሩ (በጣታችሁ አጨብጭቡ) እንደማለት ነው፣ ዘፋኙን ለማጀብ። አንዳንድ ጣቢያዎች ውስጥ “ጭራሮ” ይሉታል።
(“ብሔር ብሔረሰቦች” በሚለው ኅብረ ዝማሬ ዜማ)
“ሌቦች፣ ሌቦች ለሌቦች
እኛ የሸገር ልጆች
የምንሰርቅበት ወደ ቦሌ
መገናኛችን ያው ከርቸሌ
ታርመን ደግሞ እንወጣለን
ወጥተንም ደግመን እንሰርቃለን…” ይላል። (የመጨረሻዎቹን ሁለት መሥመሮች ትንሽ ሳላሳስታቸው አልቀርም። ይህ ዜማ ሲያልቅ “እኛ ልጆችሽ… እንዘርፍሻለን ተደራጅተን” እያለ መሆኑ ትልቅ ምፀት ነው።)
(“ፍቅርህ በረታብኝ” በሚለው ዜማም ይቀጥላል)
“ሱሴ በረታብኝ ተጨነቀ ሆዴ
በልክ አይሆንም ወይ ጭሳጭስ መውደዴ
እቅማለሁ እንጂ እቀመቅማለሁ
ጨብሲ ማንን ገሎ እሞትብሻለሁ?” እያለ ይቀጥላል።
ይሄ ብቻ አይለም። አሁን እዚያ ጣቢያ የሚበዙት ከሰበታ አካባቢ የታፈሱት የአስቸኳይ ግዜ ዐዋጁ እስረኞች ስለሆኑ የኦሮምኛ (የተቃውሞ) ዘፈኖችን ያንጎራጉራሉ። በዚህ ፈልመታ አመኑን የሚያክለው የለም። በሱ ፊታውራሪነት በጋራ ሲዘፍኑ ሙዚቃ ቋንቋ እንደማይፈልግ ትረዳላችሁ። “ሶሎሎ ኦሮሚያ” የምትል ደጋግመው የሚዘፍኗት ዘፈን ደግሞ አንጀትን እንደማሲንቆ ገመድ ትገዘግዛለች። እነፈልመታ እኛ ሳንታሰር እዚያው ነበሩ። ከተፈታንም በኋላ እዚያው ናቸው። በዐሉንም በዚህ መልኩ እዚያው ነው የሚያሳልፉት።
Filed in: Amharic