>

 እስኪ አንድ ጊዜ አብረውኝ አሜን ይበሉ  (ይልማ ኪዳኔ)

ሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጽያ መሪ ሆነው ሳሉ ኢትዮጽያ ብሎ መጥራት ይጠሉ ስለነበር በምትኩ አገሪቱና ሕዝቦችዋ እያሉ ሲናገሩ አንድም ቀን ተሳስተው እንኳን ከልባቸው የኢትዮጽያን ስም ሳይጠሩ ሞት በድንገት ያለ እድሜያቸው ይዛቸው ጠፋች። ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት ገላገለችን። በሌላ በኩል የዛሬው ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የአቶ መለስ ዜናዊ ግልባጭ የሆኑ እና አገሪቱና ህዝቦችዋ ብሎ ከማውራት ይልቅ ልክ እንደ አንድ አገሩን እንደሚወድ መሪ ኢትዮጽያና የኢትዮጽያ ህዝብ እያሉ የሚናገሩ መሪ አገራችን አግኝታለች። የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር የኢትዮጽያን ህዝብ ያስደሰተና አንጀት ያራሰ ነበር።
“ …ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት፡፡… ትናንት አባቶቻችን በመተማ፣ በዓድዋና በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት አገር አለችን፡፡… አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ አገር እንሆናለን፡፡ የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንሆናለን፡፡…ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች፣ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል፡፡… ገበታው ሰፊ በሆነባት፣ ሁሉም ሠርቶ መበልፀግ በሚችልባት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት የለም፡፡… ሁላችንም ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ፡፡… ወጣቶች ኢትዮጵያ የእናንተ ነች፣ መጪው ዘመን ከሁሉ በላይ የእናንተ ነው፡፡… የኢትዮጵያ ሴቶች በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያን ገንብታችሁ፣ ታሪክ ሠርታችሁ፣ ትውልድ ቀርፃችሁ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡… አገራዊ ማንነታችን ያለ እናንተ ያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምንም ነው፡፡… እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል፡፡ ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡… የላትም፡፡ በእናቴ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋና ምሥጋና እንደ መስጠት በመቁጠር ዛሬ በሕይወት ካገጠቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሠግናት እወዳለሁ፡፡… ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልፅጋ ለዘለዓለም ትኑር!” – ከጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር የተወሰደ
ሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ ኤርትራን ያስገነጠሉ፤ ኢትዮጽያን ያለ ባህር በር ያስቀሩ፤ የግዛት አንድነቷን ያናጉ፤ ህዝባችንን በጎሳ የከፋፈሉ፤ የማንነታችን መገለጫ የሆነችውን ባንዲራችንን፤ ታሪካችንንና የጋራ እሴቶቻችንን ያራከሱ፤ የኢትዮጽያዊነት እምነትና ስሜታችንን ያራከሱ፤ ተቃዎሚዎቻቸውን በጠላትነት የፈረጁ፤ ስልጣንና ጠመንጃቸውን ተማምነው ምሁራንን የዘለፉና አንገት ያሰደፉ፤ አገር ወዳድ ዜጎችን ከስራ ያፈናቀሉ፤ በምትካቸው ችሎታና ብቃት የሌላቸውን ሰዎች በአመራር ላይ በማስቀመጥ የአገር ሀብትና ንብረት ያዘረፉ፤ በተሳሳት ፖሊሲያቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ያስራቡ፤ ጠባብና የዘረኝነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ዘረኛ ሰው ነበሩ።
አብረውኝ አሜን ይበሉ!
Filed in: Amharic