>

ወልቃይት እና ራያ፣ ወደ ትግራይ የተካለሉበት ሂደት በአጭሩ (በወቅቱ ከነበሩ ተሳታፊዎች))

(ጊዮን መጽሔት)
በአማራ ህዝብ ዘንድ የሚሰማው ጩከት፤ ወልቃይት፤ጠገዴ ፣ጠለምት፣መተከል.እራያና ሌሎቹም ከባቢዎች ህዝቦቹ አማራ፣መሬቱም የአማራ ስለሆነ፤ ወደ አማራ ክልል ይመለሱ የሚል እንጅ እነዚህ ከባቢዎች ወደ ሌሎች ክልሎች ስለተካለሉበት ሁኔታ ግንዛቤ የለውም፡፡
ይህን ሁኔታ በዚህ ክፍል በአጭሩ እንመለከተዋለን፡
በሽግገረሩ ዘመን ስለነበረው አከላላል ሂደት እራሱን በቻለ ክፍል ቀደም ብየ “ግጨው ጠገዴ ራያ መተከል…” በሚል አንስቸዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ በተለየ ሁኔታ ደግሞ ወልቃይትን ወደ ትግራይ አከላላል እንመለከታለን፡፡
#የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ የክለላ ስራው የተሰራው #ከመንግስታዊ የመዋቅር አሰራር ወይም አካሄድ ይልቅ #ፖለቲካዊ ነበር፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም የጸደቀው የሽግግር ቻርተር ስለ ሚቋቋሙት ክልላዊ አስተዳሮች እንዲህ ሲል አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር፤-
በብሄሮች አሰፋፈር ላይ በመመርኮዝ ተመርጠው የሚቋቋሙ ክልላዊ የአስተዳደር ተግባሮችን ለማከናወን የሚረዱ ሪጅናዊ ክልላዊ ምክር ቤቶች እንዲኖሩ የሚያደርግ ህግ ይኖራል፡፡ ለእነዚህ ክልላዊ ሪጅናዊ ምክር ቤቶች የሚካሄደው ምርጫ ሁኔታዎቹ በፈቀዱበት ቦታ ሁሉ የሽግገር መንግስቱ በተመሰረተ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ይከናወናልይላል (ኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር፤ቁ1.፣አንቀጽ13)፡፡
ቻርተሩን መሰረት በማድረግ ክልሎችን አዋቅሮ ወደ ምርጫ ለመግባት በኢህአዴግ ደረጃ ለካድሬው ልዩ ልዩ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይቶች ተካሄዱ፡፡ እናም በህዳር ወር 1984 ዓ፣ም በጎንደ ከተማ በዚሁ አጀንዳ ዙሪያ ስለተካሄደው ውይይትና በወቅቱ ተነስተው ስለነበሩ ሃሳቦችና ስለተከናወነው ድራማ በወቅቱ ተሳታፊ ከነበሩ ነባር የኢህዴን ታጋዮች፤ የነገሩንን ድራማ በአጭሩ ላካፍላችሁ ወደድኩ ፡፡
ወቅቱ ህዳር 1984 ዓ.ም ነው ፤የስብሰባ ቦታው #ጎንደር ከተማ ፤አሁን #የከፍተኛው ፍ/ቤት ችሎት ማስቻያ ፡፡
♦የስብሰባው አጀንዳ #አስተዳደራዊ ክልሎች ስለሚደራጁበት ሁኔታ ለመወያየት ነበር፡፡
♦ተሰብሳቢዎች ደግሞ የኢህዴን ካድሬዎች ናቸው፡፡ ♦ሰብሳቢዎች የኢህዴንና ሕውሀት አመራሮች፡፡
♦ የመረጃ ምንጨ በወቅቱ ካስታወሳቸው አመራሮች መካከል በኢህአዴግ ደረጃ የመድረኩን የመሩት #አመራሮች የሚከተሉት ነበሩ፤
1. ሕላዊ ዮሴፍ- ከኢህዴን አመራር፤
2. አለሙ አየለ( ጡንቸ)- ከኢህዴን አመራር ፤
3. ሙሉ ታምራት( የታምራት ላይኔ ባለቤት)-ከኢህዴን አመራር፤
4. መስፍን ሚባል -የሕውሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ደደቢት ክ/ጦር አመራር የነበረ፤
5. ወዲ ቡርዲ የሚባል – የሕውሀት ታጋይ /አመራርና ፤
(…..አንባቢዎች የሌሎች ተሳትታፊ ስሞችን ብትጨምሩልን ፅሁፉ ሙሉ ይሆናል)
የመረጃው ባለቤትና ከሌላም ተጨማሪ ሰው እንዳረጋገጥኩት በወቅቱ ኮንፈረንሱን ከሚመሩት አካላት( አለሙ ጡንቸ መድረክ መሪ ነበር) በመግቢያ ላይ እንዲህ የሚል መንደርደሪያ ቀረበ፡፡
ባህልን ፤አፍ መፍቻ ቋንቋን፤ወግና ልማድን፤ታሪክን ፤ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥን ወዘተ….መሰረት ያደረገ የክልሎች አስተዳደደር እንደሚኖር አብራራ፡፡በዚህም ያለምንም ልዩነት ሁሉም ታጋይ አጠቃላይ የሆነ ስምምነቱን ገለጸ፡፡ቀጥሎ ወደ ተግባር ለመግባት ይቻል ዘንድ ፤ክልሎች፤ዞኖችና ወረዳዎች ሊደራጁ ስለሚችሉበት ሁኔታ #በኢህአዴግ ደረጃ የተዘጋጀ መሪ የክልል ፕላን ተብሎ ቀረበ፡፡ በዚሁ #መሪ ፕላን መሰረት ነበር ዛሬ ለውዝግበ የዳረጉን #የአማራ_ለም_መሬቶች ወደ #ትግራይ እንደሚካለሉ ፕሮፖዛል ተሰርቶ የቀረበው፡፡
በወቅቱ ይህን ፕሮፖዛል ያዳመጡ አንዳንድ የኢህዴን ካድሬዎች( በተለይም ከባቢዎቹን በደንብ የሚያውቁ ታጋዮች) በቁጣ የታጀበ ተቃውሞ ማቅረብ ጀመረው እንደነበርም ከተሳታፊዎች አረጋግጫለው፡፡ በተለይም ወደ ትግራይ በመካለላቸው ጠንከር ያለ ተቃውሞ የቀረበባቸው በጎንደር ከባቢ የሚከተሉት ነበሩ፤
((ወልቃይት፤ሁመራ፤ ፀለምትና አካባቢው በተለይም፤ አርማደጋ በረሃ፤ማይጸብሪ፤ደማምጨና ሰቆጣ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ወቅት ጠንከር ያለ ተቃውሞ ያቀርቡ ከነበሩት የኢህዴን ካድሬዎች መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ፡
1. ታጋይ አደራ- ክ/ ህዝብ፤ የወሎ ልጅ፤
2. ታጋይ ወርቁ ተገኝ- ክ/ህዝብ፤ የወሎ ልጅ ( በሂዎት የሌለ)፤
3. ታጋይ ጻዲቁ- ክ/ህዝብ- የጎንደር-ቆላ ወገራ ልጅ፤
4. ነጠረ ተቋሬ- ክ/ህዝብ ፤ጎንደር ልጅ- ጃኖራ፤
5. መሳፍንት በውቀቱ- ክ/ህዝብ፤ የጎንደር ልጅ( እስራኤል አገር ያለ)፤እና ሌሎችም ነበሩ፡፡
በወቅቱ የነበረው የእነዚህ ታጋዮች የተቃውሞ ነጥብ በምን አይነት ሂሳብ ነው እነዚህ ለም የጎንደር ቦታዎች ወደ ትግራይ የሚካለሉት? የሚል ነበር፡፡ከቦታው አቀማመጥ፤ ከህዝቦቹ ታሪክ ፤ባህልና ወግ፤ ልማድ፤የአኗኗር ዜቤ፤ ጅኦግራፊያዊ አቀማማጥ አንጻር ሲታይ እነዚህ ከባቢዎች የአማራ እንጅ የትግራይ አይደሉም በማለት በብርቱ ተከራከሩ፡፡ እንዲህ የሚል ጥያቄም አነስተው ነበር፤
<< ለመሆኑ ከተከዜ ወንዝ ወዲህ ባሻገር ለምን አስፈለገ ?የሚል።ይህን ጊዜ መድረኩን ሊመሩ በመጡት አመራሮች ዘንድ መደናገጥና ግራ መጋባት ተከሰተ፡፡ ባልተረጋጋ መንፈስ <<በእነዚህ አካባቢዎች የሕውሀት ታጋዮች ብዙ ደም አፍሰውበታል>> የሚል አስቂኝ እና በድንጋጤ የታጀበ መልስ ተሰጠ፡፡ በዚህ መልስ ታጋዩ እንደገና በመበሳጨት እንዲህ አለ “እንግዲያው ክለላ ሳይሆን የደም ዋጋ ይባልና እንወያይበት ” የሚል ጠንካራ ሃሳብ ተሰነዘረ ይላል በቦታው የተሳተፈው አንድ ወዳጀ።
<<አሁን ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡ ስለሆነም በእረፍት ስም መድረኩ እንዲቋረጥ ተደረገና ተሰብሳቢው ከአዳራሽ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ መድረክ መሪዎቹ በእረፍት ስአት መሰራት ስላለበት ነገር አዲስ ሰልት ነድፈው ተግባራዊ አደረጉ፡፡ እሄው ስልትም ጠንካራ ተቃውሞ ያሰሙ የነበሩትን ታጋዮች በተናጠል አወያይቶ ማሳመን ፤ካላመኑም እረፉ ማለት ነበር፡፡ በዚሁ አቅጣጫ የተናጠል ውይይት ተካሄደ ፤ ልጆቹ መለዘብ አልቻሉም፡፡ቀጥሎ ወደ ማስፈራራት ተገባ፡፡>> ይህ እንግዲህ እነ ወልቃይትን ራያን ለመንጠቅ የተደረገ ጦርነት እንጅ የህዝብን ሰላም ዲሞክራሲ ለማምጣት የተደረገ አይደለም።ቀድሞውን ለነፃነት ሲል ዋጋ የከፈለ ህዝብ ለሽያጭ ቀረበ።
ልብ በሉ ይህ ወቅት ለጠንካራ የኢህዴን ታጋዮች ጥሩ አልነበረም፤ ገዳያቸው እንኳን በውል ሳይታወቅ ሰዎች በየከባቢው ሞተው ይገኙ ነበርና።እነ ጉሴ ጺሞና ሙሉአለም አበበ መጥቀስ ይቻላል።((ይህንን ጉዳይ በስፋት ሌላ ጊዜ እኔም እመለስበታለው።))
በመሆኑም ማስፈራር ሲጀመር በኋላ በነዚህ ታጋዮች ዘንድ ትንሽ መደንገጥ ተጀመረ፡፡ ጠንከር ብለው ተቃውሞ ያሰሙትን ልጆች ለየብቻ ካወያዩ በኃላ በአንድ ላይ ሰብስበው የተነገራቸው ነገር እንዲህ የሚል ነበር፤
<<አሁን በዚህ መድረክ ከወደቅን ህዝቡ ይሰማል፤ ይህ ደግሞ ለድርጅታችን ውድቀት ነው፤ስለሆነም ሚስጥሩ ተጠብቆ እንዲቆይና ለወደፊቱ ድርጅቱ አጥንቶ ያስተካክለዋል፤እኛም ጉዳዩ እንዲታይ ሪፖርት እናደርጋለን ፡፡ እስከዛው ግን እነዚህን ከባቢዎች የህውሀት ታጋዮች ሲያስተዳድሯቸው ስለቆዩ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ እነሱው እየተቆጣጠሯቸው እንዲቆዩ>>በሚል የእነ ወልቃይት ጉዳይ ለጊዜው ተቋጨ።
ይህንን ሀቅ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ ቢወረድም ጫፉ ከተገኘ በኋላ መረጃውን ለማረጋገጥና ለማስፋት ግን ብዙ አላደከመንም።እናም እስኪ ለማስረጃ የሌላ ሰው ሀሰብን እናካት።
በግል ከተወያዩት ካድሬዎች መካከል የአንዱ ብቻ ላንሳለችሁ፡፡ ታጋዩ #መሳፍንት በውቀቱ ይባልል፤የጎንደደር( ዳባት ) አካባቢ ልጅ ነው፡፡ እርሱን በግል እንዲያወያይ የተመደበለት ደግሞ የሕውሀት ታጋይ የነበረ ለታይ ይባላል( #ለታይ አሁን የሕውሀት የልማት ድርጅት የሆነውን የጉና ሥራ አስኪያጅ መሆኑን ሰምቻለሁ)፡፡ ለታይ ለመሳፍንት የተመደበበት ምክንያት ነበረው፡፡ ለታይ በህውሀት ካድሬነቱ ዳባት ወረዳ ሲሰራ፤ከመሳፍነት ቤተሰብ ጋር ተቀራርበው ነበርና እንደቤተሰብ እስከመተያት ደርሰው ነበር፤ የመሳፍንት አባትም ለለታይ ዘወትር የልጀን ነገር አደራ ይለው ነበር፡፡እናም መሳፍንትን ለማግባበት ከለታይ የቀረበ ሰው አልነበረምና ለታይ ለመሳፍንት ተመደበ፡፡ ይሁን እንጅ ለመሳፍንት ለታይ አልከበደውም፤ በሁለቱ መካከል ቤተሰባዊ የሆነ መቀራረብ ስላለ መሳፍንት ለታይን አልቀበልህም አለው፡፡ ያኔ ለታይ ለመሳፍንት እንቅጩን ነገረው፤ እንግዲያው ወንድሜ እረፍ ፤እኔ ቁሜ እያየሁ አንተ ስትሞት አላይም፤የአባትህ አደራም አለብኝ፤ ጉዳዩ ከላይ ተወስኖ ስለመጣ አንተ ተከራክረህ የምታመጣው ነገር የለምና ሃሳብህን አንሳ ይለዋል፡፡ መሴ ወይ ፍንክች አለ፡፡ይህ ጉዳይ እንዳልሰራ ሲታወቅ ለመሳፍንት ሌላ ሰው ተመደበ፡፡ይህ ሰው ደግሞ በወቅቱ #የደደቢት ክ/ጦር አመራር የነበረውና ዚሁ መድረክ ተሳታፊ የነበረው የሕውሀቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል #መስፍን ነው( በኃላ መስፍን ጀኔራል መሆኑን ሰምቻለሁ፤አሁን ደግሞ ጡረታም እንደወጣ መረጃ አለ)፡፡ የመስፍን መኖሪያ ቤት በወቅቱ ጎንደር ከተማ ቀበሌ 2/3 በተለምዶ #የገዛከኝ ወርቄ ግቢ ከሚባለው ነበር፡፡ መስፍን መሳፍንት ጠራና በጉዳዩ ላይ ተወያዩ፤ማስፈራሪያም ቀረበለት፤ መሴ አሁንም አላምንም አለ፡፡ በመጨረሻም መስፍን ለመሳፍንት እንዲህ አለው ” እረፍ የበላይ አካል ውሳኔ ነው በቃህ፡፡” እሄኔ መሳፍንት ሆዱ መሸበር ጀመረ፡፡
አሁን የግል ውይይቱም፤ ማስፈራረቱም አልቋልና ፤ከሰዓት በኃላ፤ በእረፍት ስም ተበትኖ የነበረው መድረኩ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ አለሙ ጡንቸ መድረኩን ከፈተ፤ ቅድም ልዩነት የነበራችሁ ጓዶች ሃሳባችሁን መቀጠል ትችላለላችሁ አለ፡፡ አለሙ እንዲህ የሚለው ስራውን ካሰራ በኃላ መሆኑን ልብ በሉ፡፡በፖለቲካ ስብሰባ ይህ የተለመደ ስልት ነው።
ለአለሙ ጥያቄ መልስ ጠፋ፤ በሉ እንጅ ዝም፤ በሉ እንጅ ዝም፡፡ ሰው ገብቶታል ፤ ልጆቹ ለየብቻ መርፌ ተወግተው እንደገቡ ይታወቃል፡፡ እንዲያ በብስጭት ሲናገሩ የነበሩ ልጆች ሁሉም ለአለሙ ጥያቄ መልስ ከመስጠት ጸጥ አሉ፡፡ መጨረሻ ላይ አለሙ ጠንከር ብለው ይቃወሙ ከነበሩት ጎላ ብሎ ይደመጥ የነበረውን መሳፍንትን ስም ጠርቶ፤ መሳፍንት ሃሳብህን ለምን አትቀጥልም? ይለዋል፤ መሳፍንትም አይ ቅድም በእረፍት ስአት ጓዶች ስላሳዩኝ ሃሳቤን አንስቻለሁ አለ፡፡ በቃ ሁሉም ከተስማማና ልዩነት ከሌለ ይህን አጀንዳ በዚህ መልኩ ያለ ልዩነት አልፈነዋል ተባለ፡፡የእነ ወልቃይት የእነ ራያም ድራማም ተጠናቀቀ።የአማራ ህዝብ መሬት፤ አማራ ወንድሞቻችንም በዛቻና ማስፈራሪያ ምክንያት ከእኛ እንዲለዩን ተወሰነ።ያ ወቅት ማለት የአማራ ታሪክ በጥቁር የተፃፈበት አንዱ እለት ነበር።
እንዲህ ባለ ድራማ ነበር ዛሬ የአማራ ህዝብ የሚሞትላቸው ለም መሬቶቹ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ሁመራ፤ጠለምት፤ራያ፤መተከል ወዘተ…. ተላልፈው ለትግራይ የተሰጡበት፡፡
ሕውሀትና ኢህዴን እንዲህ ተባብረው የአማራን ጥቅም ጎድተዋል፤ በዛን ወቅት እንኳን ነገሩ ገብቷቸው ሁኔታውን ለመታገልና ለማስተካከል የሞከሩ የአማራ ልጆች እንዲህ ባለ መልኩ ነበር የሚታፈኑት፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰበቡ ኢህዴን/ብአዴን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
((#የከፋኝ ቅሪቶች እና ቀጣይ ጉዞ-….#የኢህዲን ታጋይ የነበረ ግለሰብ ትዝብቱን እንደሚተከውለ ይገልፃል))
በክፍል ሁለት እንደተገለጸው አብዛኛው የከፋኝ ጦር በጊዜ ሂደት በምህረት እጁን ለሕውሀት ሰጥቶ ሰላማዊ ኑሮውን ወደ መምራት ተሰማራ፡፡ነገር ግን ነገሩ ያልጣማቸው የተወሰኑ የከፋኝ ጦር አባለት በምህረት የተገኘውን እድል መጠቀም አልፈለጉም ነበር፡፡
<< እነዚህ ምህረት ለመጠየቅ ፍቃደኛ ያልነበሩና ምህረት ብለው ቢገቡም በቀላሉ እደማይለቀቁ የሚያውቁ አባላት በምህረት ከመግባት ፈንታ ወደ ኤርትራ እንደሄዱ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኤርትራ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ በኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ጦርነቱ ሲጀመር፤ በስደት መልክ ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የከፋኝ አባላት እንደ አዲስ በመደራጀት አርበኞች ግንባር የሚል ድርጅት አቋቁመው ፀረ- ኢትዮጵያ መንግስት (ፀረ ህወሃት) እንቅስቃሴ ውስጥ እንደገቡ ይነገራል፡፡ የአርበኞች ግንባር መፈጠር የኤርትራ መንግስትም ከራሱ ጥቅም አንጻር ይፈልገው ነበርና አዲሱ ድርጅት ተፈላጊውን ስነቅና ትጥቅም ከኤርትራ መንግስት በቀላሉ ማግኘት ጀመረ፡፡>>
አንዳንድ ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ ደግሞ አሁን የአርበኞች ግንባርን በኃላፊነት ከሚመሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ አመራሮች ቀደምት የከፋኝ ጦር አባላት የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡
ምህረት ያልገቡት የከፋኝ ጦር አባለት ሁኔታ ከላይ እንደጠቀስኩት ሁኖ በምህረት የገቡ የከፋኝ አባላት የኑሮ ሁኔታ ደግሞ በወቅቱ እገዛ ስላልተደረገላቸው ለስራ አጥነት ችግር ተጋለጡ፡፡ በሂደትም ከማህበረሰቡ እየተገለሉ ሄዱ ፤ በስበብ አስባቡ ሲታሰሩና ሲፈቱ አንዳንዶቹ ደግሞ እስራት ተፈረዶባቸው ወህኒ ተወረወሩ፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ምህረት ገቤዎቹ ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየተመናመነ ሄደ፡፡አንዳንዶቹ ደግሞ አማራጭ በማጣታቸው ለስደት ተዳረጉ፡፡ከዚህ ሁሉ የተረፉት ደግሞ ወደ ኤርትራ በመሻገር አርበኞች ግንባርን እንደተቀላቀሉ ይገመታል፡፡
በወልቃይት የአማራዎች ላይ ስለደረሱ በደሎች ሚሰሙ ክሶች
ሕውሀትና የወልቃይት ህዝብ ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ህውሀት በወልቃይትና ጠገዴ ህዝብ ላይ ከባድ የሆኑ ግፍና በደሎች መፈጸሙን የከባቢው ተወላጆች በምሬት ይናገራሉ፡፡በተለይም አሁን እድሜ ለማህበራዊ ሚዲያ እና ከሞት እና ጅምላ ግድያ የተረፉ እነዚህ የወልቃይት አማራዎች አሁንም ድረስ ያላቆመውን ህወሃትን በአማራው ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍ እየነገሩን ነው። ተወላጆቹ በሕውሀት ተፈጽመዋል ከሚሏቸው በደሎች መካከል ግድያና፤ አፈና፤ መሰደድ፤መፈናቀል፤ዝርፊያና አስገድዶ መደፈር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ደረሰ ስለሚባለው ግፍና በደል ሙሉ ቀን ተስፋሁን (2009 ዓ፣ም) ” የጥፋት ዘመን” በተሰኘው መጽሀፉ ከ1983ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት አመታት በአማራ ህዝብ ላይ ስለተፈጸመውበደል በዘረዘረበት ክፍል የወልቃይት ህዝብ ችግር መመልከት ይቻላል፡፡ ዋናዋናዎቹም፤ ግድያና አፈና፤ መፈናቀልና ስደት፤ የንብረት ዝርፊያና የሴት ልጆች መደፈር ፤ታሪክና ባህልን የማጥፋት ዘመቻ መሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የወልቃይት አማራ ግፍና በደል እንዲሁ በቀላሉ ሊገለጽ አይችልም፤እራሱን ችሎ ጥናት ይፈልጋል፡፡
ሲጠቃለልም፤ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች በህውሀት የደረሰባቸው በደል የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሏቸውን ጉዳዮች ይዘረዝራሉ፡፡ ከተዎላጆቹ ውጭ ያሉና አንዳንድ የተጻፉ ሰነዶችም በደሉን ዘር ማጥፋት ሲሉ ገልጸውታል፡፡ እንግዲህ በወልቃይት ጠገዴ ከባቢዎች የደረሰው በደልና ግፍ ዘር ማጥፋት ደረጃ ደርሷል ወይ የሚለው በሂደት የሚታይ ሆኖ እንደ እኔ ላለ መረጃውን በቅርብ ለሚከታተል ግን ሌላ ስም ካልተሰጠው በስተቀር አሁን ያለው “የዘር ማጥፋ” የሚባለው ትርጉም ራሱ የሚገልፀው አይመስለኝም።በደሉ ከዚያም በላይ ነው።ታሪክ አዋቂ ሰው ብቻ ሳይሆን ለታሪክ ምልክት ሊሆን ይችላል የተባለ ዛፍ ድረስ ማወደም የጀመረን ስርዓት በምን ህግ እንደሚዳኝና በምን ቃል እንደሚገለፅም ይከብዳል።
ብአዴን አማራን እንዴት አስጠቃው?….
የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጩኸት እሪ በከንቱ ሆኖ ለአመታት ቀጥሏል።በደሉ ዛሬም ከትናንት አልተሻለም።ዛሬ ግን በደላቸውን መውላ አማራ ይሰማዋል።
ከላይ ባመላከትኩት ሂደት መሰረት ወልቃይትና ጠገዴ ወደ ትግራይ ከተካለሉ ጊዜ ጀምሮ በአካባቢዎቹ ህዝብ እየታፈነም ቢሆን አቤት ብሏል፤ አማራነን ልቀቁን ብሏል፤ ሰሚ ግን የለም፡፡ምክንያቱም ታስቦበት የተሰራ ድርጊት ነውና፡፡ ለነገሩ ወልቃይት፤ ጠገዴና ጠለምት ፤ እንዲሁም ራያና አካባቢው ወደ ትግራይ የተካለለው ከ1984 ዓ.ም በኃላ ነውን? ብለን ስንጠይቅ መልሱ አይደለም ነው፡፡ሕውሀት እነዚህን የአማራ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ያከለለው በ1968 ዓ.ም ማኒፌስቶው ነው፡፡ በ1984 ዓ.ም የተከናወነው በድርጅት ደረጃ ያሰበውን ሃሳብ እርሱ ባዘጋጀው ህገ- መንግስት እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ ነው ነው ፡፡ እሂንን እውነታ ተ.ሓ.ሕ.ት( ሕውሀት) በ1968 ዓ.ም ማኒፌስቶው እንዲህ አስፍሮት እናገኘዋለን፤-
<<………የትግራይ ሕዝብ ማለት በትግራይ ውስጥ የሚኖሩትንና በተለያየ ምክንያት ከትግራይ መሬት ውጭ የሚኖሩትን ሕዝቦቿ በሙሉ ያጠቃለለ ነው። [ትግሮኛ ተናጋሪዎች፣ ኣፋር (ጠልጣል)፣ አገው፣ ሳሆ፣ ኩናማ፣ ወ.ዘ.ተ.] የትግራይ መሬት በደቡብ ኣለውና፣ በሰሜን መረብ ሲያካልሉት በምዕራብ በኩል ደግሞ ወልቃይትንና ፀለምትን ያጠቃልላል (ተ.ሓ.ሕ.ት፤መግለጫ፡ ገጽ V)>> ይላል
ስለዚህ በ1984 ዓ.ም የተካሄደው ድርጊት ይህንን ማኒፌስቶ ህገ-መንግስታዊ መልክ ማስያዝ እንጅ አዲስ የተፈጠረ ነገር አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሕወሀት ነገሩን የጨረሰ በ1968 ዓ.ም ነው፡፡ ይህንን ቀድሞ ያለቀለት አከላልለል የወልቃይት ጠገዴ ህዝብም አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለም ቢሆን ድርጊቱን ሲቃወም ኑሯል፡፡ ቅሬታቸውንም በተለያዩ ወቅቶችና በተለያየ መልኩ ሲያስሙ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም በጠገዴ ወረዳ የአምስት ቀበሌ ህዝቦች ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ አቤቱታቸውን ማድረስ ለሚገባቸው ሁሉ አድርሰው መልስ አጥተው መቅረታቸው ይታወሳል፡፡
የእነዚህ አማራዎች ጩኸት በወቅቱ ሰሚ ያላገኘው ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ የእነዚህ ወገኖች ጩኸት በወቅቱ ሰሚ እንዳያገኝ ያደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች እንደነበሩ (አሁንም እንዳሉ ) ቢታወቅም ከዋና ዋና ዎቹ ምክንያቶቸች መካከል የሚከተሉትን እንጥቀስ፦….
Filed in: Amharic