>

 የጅማው ባለቅኔ ከድር ሰተቴ ማነው? (ኤርሚያስ ቶኩማ)

በቁም ለገደሏት ለሞተች ሀገሬ 
ባንድ አይኔ አነባለሁ አንዱን አሳስሬ፡፡
ከድር ሰተቴ 
 የጅማው ባለቅኔ ከድር ሰተቴ ማነው? አልከኝ ፅሁፉን አንብበህ ስትጨርስ ትረዳዋለህ፡፡
ገዢው ፓርቲ አቅዶ እንዲዳከሙ ካደረጋቸው የሀገራችን ከተሞች መካከል አረንጓዴዋ ጅማ ከተማ አንዷ ነች፡፡
ጅማ በተለይም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሌሎች ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታደርግ የነበረችና ዝናቸው እስከታንዛንያ የደረሰ እንድ ታላቁ አባጅፋር ያሉ ንጉሶች ያስተዳድሯት  የነበረች እና የምዕራብ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መናኸሪያ የነበረች ከተማ ነች፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ የነበሩት ገናና የንግድ ማዕከላት ቦንጋ፣ ሰቃ ወይም ሊሙ እና የጅማዋ ሒርማታ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጅማ እጅግ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባቷ የተነሳ በ1861 ዓካባቢ 150 ሺህ የሚደርስ ህዝብ ይኖርባት እንደነበረ ካርዲናል ማሳጃ ሲገልፅ ከተማዋ የደቡብ ምዕራብ የእስልምና ትምህርት ማዕከል ለመሆን በመብቃቷ ከጉማ፣ ሊሙ፣ ጌራ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ሐረርጌና ደሴ ጭምር ለሐይማኖታዊ ትምህርት ወደጅማ በርካታ ህዝብ ይነጉድ እንደነበረ Gwynn C.W. የተሰኘ ፀሀፊ  “A Journey in Southern Abyssinia ብሎ በ1911 ባሳተመው መፅሐፉ ይገልፃል፡፡
በጣልያን ወረራ ወቅት ተዳክሞ የነበረው የጅማ ኢኮኖሚ እድሜ ለእነፊታውራሪ ገረሱ ዱኪና አርበኛ ጃገማ ኬሎ ጣልያንን ከግዛቷ አባራ አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያ አውራጃ በመሆን በስሯ ጂረን፣ ሂርማታ፣ ቦሳና መንደራን አቅፋ የተለመደውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የቀጠለች ሲሆን ከ1941 ዓመተ ምህረት በኋላ ሂርማታን እንዲያስተዳድሩ ከተሸሙት መካከል አቶ ጅፋር ፈይሳና አባ ጋሮ አባዳለቻ የጅማ ኢኮኖሚ በተረጋጋ መንገድ እንዲጓዝ ያደረጉ ሲሆን የጅማ አውራጃ አስተዳዳሪዎች የነበሩት እነ ግራዝማች ክፍሌ ንጋቱ፣ እነቀኛዝማች ወልደማርያም ነመራ፣ ሻለቃ ሐይለማርያም ሌንጮ፣ ነጋድራስ ጀማነህ ይመኑ፣ እና ቀኛዝማች ዮሴፍ ሰርዳ ጅማን እየተፈራረቁ በመምራት ጥንካሬዋን ይዛ እንድትጥል በማድረግ የተሻለች ጅማን መፍጠር ተችሎ ነበረ፡፡
በካትሪን ግሬፍናው የተሰራው The political Economy of an African society in Transformation: The case of Macca Oromo ጥናት እንደሚያስረዳው ደግሞ  ጅማ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የነበራት ከተማ ስትሆን የቡና ምርት፣ የእንጨት ስራዎች እና ጅማ አጂፕ አካባቢ ይገኝ የነበረው የጅማ ጨርቃጨርቅ የጅማን ኢኮኖሚ ቀጥ አድርጎ ይዞ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡  ጅማ የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት እንኳን ከአዲስ አበባ፣ ከአስመራና ከድሬዳዋ በመቀጠል አህጉራዊ የስፖርት ውድድሮችን እስከማዘጋጀት የደረሰች ከተማ እንደነበረች ይታወሳል፡፡  ገዢው ፓርቲ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ግን የጅማ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ እየወደቀ መጥቶ ዛሬ ጅማ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን ያቀፈች ከተማ ሆናለች፡፡ ለጅማ ከተማ የኢኮኖሚ መዳከም ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
  ✔ የጅማን ከተማ ኢኮኖሚ ይደግፉ የነበሩት በጅማ ይገኙ የነበሩ ታላላቅ የቡና አምራች ማህበራት ፈርሰው ለመንግስት ቅርብ ወደሆኑ ግለሰቦች እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን ከቀደምት የጅማ ቡና አምራች ማህበራት መካከል አሁንም እየተንገዳገደ በህይወት የሚገኘው ቢፍቱ ጉዲና የቡና አምራች ህብረት ስራ ማህበር ሲሆን የተቀሩት በሙሉ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ከጅማ ህዝብ ንብረትነት ወጥተዋል፡፡
✔ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ ባለቤት ያደረገው የድሮው አጂፕ አካባቢ ይገኝ የነበረው ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞቹን በትኖ ተዘግቶ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ በአርባምንጭና በድሬዳዋ ከተፈፀመው ጋር ተመሳሳይ ነው)
✔ በጅማ ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች  ከለምለሙ የጊቤ ዙሪያ ጫካዎች እየለቀሙ ለነጋዴዎች ለሽቶ መስሪያነት እንዲውል የሚሸጡት ሲቬትስ ከገበሬዎች ንብረትነት ወጥቶ የአላሙዲን ንብረት ሆኗል፡፡
✔ ለጅማ ከተማ ጥሩ ገቢ ያስገኙ የነበሩት ከአጋሮ እስከበደሌ የሚገኙ ሰፋፊ የቡናና የሻይ ቅጠል ማሳዎች እንደአላሙዲን ላሉ ባለሀብቶች መተላለፋቸው፤
✔ ጫትን በብዛት ወደውጭ በመላክ የጅማን ኢኮኖሚ ይደግፉ የነበሩት የአጋሮ የጫት ላኪ ማህበራት የጫት ማሳቸውን ተቀምተው ከንግዱ ዓለም እንዲወገዱ መደረጋቸው
✔ የጅማን ወጣት ለማደንዘዝ ጫትና እና ሺሻን የመሣሠሉ የወጣት ጠር የሆኑ ነገሮችን በዘፈቀደ ወጣቱ እንዲዘፈቅባቸው ቁጥጥሩን ማላላት
✔ በ1931 ዓመተ ምህረት ለጅማ ከተማ ህዝብ መቅረብ የጀመረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሳይስፋፋ ዛሬም በርካታ የጅማ ገጠራማ ወረዳዎች በውሃ እጥረት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡
✔ በጅማ ከተማ ተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ የሚያጋጥም ሲሆን ከ1938 እስከ 1983 የተተከሉት የተለያዩ መጠባበቂያ ጀነሬተሮች በሙሉ ተነቅለው ከጅማ ተወስደዋል፡፡
ጅማን የጎበኘ ማንኛውም ሰው ስለሰተቴ ሳይሠማ የሚመለስ አይመስለኝም፤ ሰተቴ ሲበዛ ቀለድ አዋቂ እና በግጥም የደርግ ባለስልጣናትን ይናገር የነበረ ነው፡፡ ጅማ መንደራ ውስጥ  የተወለደው  `ከድር መሐመድ  ሐሠን  ቢላል` በብዙዎች አጠራር ከድር ሰተቴ፤  የጅማ ህዝብን በደል በአደባባይ በድፍረት ያሰማ የነበረ ብሩህ አዕምሮ የነበረው ግለሰብ እንደነበረ የከድር ሰተቴን የህይወት ታሪክ የፃፈው ደራሲ ዲራዓዝ በመፅፉ ይገልፃል፡፡ ስለከድር ሰተቴ ያነበብኩትን ላጫውታችሁና ላብቃ
ኮሎኔል ተድላ የተባሉ የጅማ ፖሊስ አዛዥ ነበሩ፡፡ ሰውዬው ከአብዮቱም በላይ ለሚስታቸው ቃል ታማኝና ታዛዥ ነበሩ ይባላል፡፡ ታዲያ ይህንን የተረዳው ሰተቴ እንደሚከተለው ይሸነቁጣቸዋል፡፡
……………….
 የፍርድዎ ውሳኔ፣ በጓሮ በር በኩል  ከጓዳ ከመጣ፤
ዳኛ ቤትዎ ይቅሩ!  ሚስትዎ ችሎት ትምጣ፡፡
……………….
ዛሬስ ማን ይሆን እንደከድር ሰተቴ የጅማን ህዝብ በደል በአደባባይ የሚያሰማ???????
Filed in: Amharic