>
5:18 pm - Saturday June 15, 3907

የእሳት አደጋ ተከላከይ ወይስ የለውጥ ሐዋሪያ? (ጎበና ጉግሣ)

„ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ናት፡፡..የሓሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል፡፡….እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክረሲና ነጻነት ይስፈልገናል፣ይገባናልም፡፡….ነጻነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታም አይደለም፡፡ከሰበዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ ነው፡፡“ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ

…አብይ አህመድ „የእሳት አደጋ ተከላከይ ወይስ የለውጥ ሐዋሪያ !“ ይህ አሁን ከያለበት የሚሰማ ጥያቄ ነው፡፡ ሰውዬውም በሕዝብ ጥያቄና በወያኔ መካከል የቆመ ነው፡፡ እሱ ብቻውን ምንም የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ግን ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከተፈለገ  …አብይ እህአዴግን ወክሎ፣ ከተለያዩ የሕብረተሱ ክፍሎች የተወጣጣ የሽግግር መንግሥት በአስቸከኳይ አዲስ አበባ ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡“ የአንድ ጸሓፊ አስተያየት!

ምን ዓይነት „አዲስ“ አነጋገር ነው፡፡ እንዴትስ ያለ ግሩም አቀራረብ ነው፡፡ ለአለፉት 27 አመት በአገሪቱ ሚዲያ ቀርቶ ፣ከአንድም የመንግሥት ተወካይ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በጨረፍታ እንኳን ያልተሰማ ቃል ነው፡፡ ይህ፣ ያውም እንዳንዶቹ እንደሚሉት „..በወያኔዎች ተኮትኩቶ“ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ከወጣ ከአንድ ጎልማሣ ቀርቶ፣ተቃዋሚ ነን ብለው ከሚመጻደቁ „…ነጻ-አውጪዎችም አፍ“  እስከ ዛሬ ድረስ ያልተሰመ አነጋገር አብይ በየሄደበት ያሰማል፡፡

ዲፕሎማት ወይስ የተደበቀ አጀንዳ አራማጅ! የለውጥ ሐዋሪያ ወይስ አፍዝ አደንግዝ! የእሳት አደጋ ተከላካይ ወይስ የለውጥ እንቅስቃሴው መሪ!

ጊዜው ተቀይሮአል፡፡ በዚያውም አገሪቱን ለአለፉት ረጅም አመታት ሲያምስ የቆየው „የኮሚኒስቶቹ  የስታሊን“ የፖለቲካ ቲዎሪ እና ርዕዮተ ዓለሙም ፣ቢያንስ ከሦስት አመት ወዲህ ቀስ የእያለ አብሮ ተለውጦአል፡፡

የአገሪቱም ሊህቃን ለክፎአቸው ከሰነበተው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን „…የእብደት ፖለቲካ“ ወደ ተጨባጩ መፍትሔ ፍለጋ የተመለሱ ይመስላል፡፡

የዓይን ምስክር ሁነን እንደምናየውና እንደምንሰማው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሁን አንደኛውና ግንባር ቀደም ፖለቲከኛ መሆኑ ነው!

ግን እንደገና መልሶ ለመጠየቅ፣ …አብይ ምን ይፈልጋል! ወያኔዎችስ ምን ይፈልጋሉ! ሕዝቡስ ምን ይላል! ተቃዋሚ ኃይሎችስ ምን  ምን ይፈልጋሉ! ምንስ ይላሉ!

 ወዶ ሥልጣኑን የሚያስረክብ ቡድን የትም አልታየም፡፡ ያውም ደግሞ የአገሩቱን ሐብት ፣ከመሬት እስከ ባንክ፣ከሕንጻ እስከ የእርሻ ቦታ፣ከሠራዊት እስከ ጸጥታና ፖሊስ፣ከውጭ ጉዳይ እስከ አስመጪና ላኪነት …. ይህን ሁሉ በእጁ ላይ የሚገኘውን ንብረት ወያኔ ዝም ብሎ አስረክቦ ወደ አደዋና ወደ መቀሌ አንገቱን ደፍቶ አይመለስም፡፡

ሁለት ሁኔታዎችን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ደርግ እንዴት „ተጠናክሮ „ እንደወጣና ፣ሁለተኛው ሻቢያ፣ ወያኔ እና ኦነግ አዲስ አበባና አሥመራን እንዴት „ሊቆጣጠሩ ቻሉ“  የሚሉትን ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ብዙ ቦታዎች መሄድ አያስፈልግም፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱ ሆኑ፣ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ተቃዋሚ ነን የሚሉትም የአገሪቱ ምሁራን ያኔ „….ለጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት“ ትንሽ ዕድል ቢሰጡ ኑሮ ደርግ የሚባል ፍጡር መጥቶ አገሪቱን ለአሥራ ሰባት አመታት ባልገዛት ነበር፡፡

ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምም ከመፈርጠጡ በፊት „… ብሔራዊ እርቅ ብሎ ሁሉንም ለሚያሳትፍ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት“ ምሥረታ በሩን ከፍቶ ቢሄድ ወያኔና ሻቢያ ብቻቸውን አሥመራና አዲስ አበባን ይዘው 27 አመታት በተከታታይ በአልጨፈሩብንም ነበር፡፡

አሁንም ያለነው ከዚሁ ሁኔታ ፊት ነው፡፡

„አብይ ይህን አለ፣…አብይ ይህን ብሎአል፣…አብይ፣ለማ መገርሣና ቆሬዎችን የሚያሸነፍቻው የለም፣ ቆሬና ፋኖ፣ፋኖና አማራ…“ ይህ ሁሉ ግምት ምኞት ሁኖ ይቀራል እንጂ „ሁሉን ነገር“  ጠቅልሎ ከያዘው ከወያኔ እጅ ሥልጣኑን በቀላሉ ፈልቅቆ ማውጣት አይቻልም፡፡ አንድ መንገድ ግን አለ፡፡

እሱም  የቱኒዚያው መፍትሔ ነው፡፡

„…ሁሉንም የሚያሳትፍ …የክብ ጠረጴዛ ንግግር“ በአብይና – እሱ እንደ አለው „…በተፎካካሪ „ ቡድኖች መካከል የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ለ27 አመታት የቆየውን የወያኔን አምባገነን አገዛዝ ለማሰወገድ „ንግግር „ መጀመር ይኖርበታል፡፡

ይህ „…የክብ ጠረጴዛ ወይይትም“ ሰፋ ብሎ ሌሎቹን የሕብረተሰቡን ክፍሎችን ማሳተፍም ይኖርበታል፡፡

ግን አንድ ተዘሎ ሳይነሳ የማይታለፍ ነገር አለ፡፡

በ20ኛው እና በ19ኛው  ክፍለ ዘመን ፍልስፍና እና በዚያ  „…ሃይማኖት የተጠመቁና“ በእሱም አስተሳብ እና አመለካከት ላይ „ቆመው“ የቀሩ ሰዎችና ድርጅቶች አሁንም በአገሪቱ አሉ፡፡ ይህ ለማንም ምሥጢር አይደለም፡፡ እነሱን ምን እናድርጋቸው!!

ጠጋ ብለው ሲያዩአቸው ጽሑፎቻቸው ሲመረመሩ አብዛኛዎቹ በምንም ዓይነት ከአቋማቸው „ፈቀቅ „ የማይሉና የማይቀየሩ ናቸው፡፡ እነሱም አሁን አገሪቱ ለአለችበት ችግር የሚያቀርቡትም „…መፍትሔ“ የታወቀ ስለሆነ፣እነሱንም እንደአለ መርሣት ያስፈልጋል፡፡ ዱሮንም ከቁም ነገርም አይገቡም!

አቋማቸውን ቀይረው ለዲሞክራቲክ ሥርዓት ምሥረታ ከቆሙ የንግግሩ ተሳታፊዎች ማድረጉ ከጉዳቱ ጥቅሙ ይበልጣል፡፡

ሌሎቹስ!

የላይኖቹን ተክተለው „…አገሪቱ …ለሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በዕድገቱዋ አልደረሰችም „ የሚሉ ክፍሎች አሉ ፡፡ እነሱም ጥቂት አይደሉም፡፡ ግን ጊዜው ጥሎአቸው የሄደ ስለሆነ እንደ ትልቅ ነገር አመለካከታቸውን በአሁኑ ሰዓት ማዳመጥ ትርፉ ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡

በአለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያን ለማዳን „..የጦር ትግል „ያስፈልጋል የሚሉ „ኃይሎች“ ተነስተው እንደ ነበር ለማንም ግልጽ ነው፡፡እነሱን እና ደጋፊዎቻቸውን አብይ አህመድ ሸንጎ ውስጥ በአሰማው „ግሩም“ ንግግሩ ከጫዋታ ውጭ አድርጎአቸዋል፡፡

ከእነሱም ጋር „…እኛ የምርጥ ዘሮች ልጆች ነን“ እሰከ ማለት ድረስ የዘለቁ ወያኔዎች አሉ፡፡ሕዝቡ ግን „ይበቃችኋል! ውረዱ…!“  ከአላቸው ወዲህ ይህ የትግሬዎች ፣የአደዋና የአክሱም የመቀሌ ልጆች ስብስብ አሁን ይክበር ይመስገና „ለሦሰት“ ተከፋፍለዋል፡፡

ስለዚህ „ወያኔን“ አሁን እንደ አለፉት አመታት እንደ „…አንድ ወጥ ኃይል“ መመልከት ጊዜው ያለፈበት አመለካከት ነው፡፡

በዚህ የኃይል „አሠላለፉ“ በአገሪቱ ተቀይሮአል፡፡

አንደኛው ወገን በአንድ አረፍተ ነገር ለማስቀመጥ „… በመሣሪያ ኃይል፣ሁሉንም አንበርክከን „ እንደድሮው እንደ አለፉት 27 አመታት ሕዝቡን እንግዛው የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል„…በጥገናዊ ለውጥ ፣…በሪፎርም „ ቀስ እያለ፣የሕዝቡ ቁጣ „…እሰከሚበርድ ድረስ“ እናዝግም ባይ ናቸው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ቡድን ደግሞ „….ብሔራዊ እርቅን አውርዶ… የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቆ፣….በአንድ ዲሞክራቲክ ሥርዓት ውስጥ አብሮ መኖር ይቻላል“ ብሎ የሚያምን ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ንግግር በደንብ የተከታተለ፣ አስተዋይ ሰው እንደሚረዳው አብይ አህመድ  በአሁኑ ሰዓት ከየትኛው ወገን ጋር እንደቆመ ፣ብዙ ሳይደግም በቀላሉ ይረዳል፡፡

ይህ ከሆነ ደግሞ እሱና „ቁጥራቸው ቀላል ነው“  የማይባሉ የሸንጎ አባሎች እላይ የተጠቀሰውን „…ሦስተኛውን ክፍል“ የሚወክሉ „የለውጥ“ ኃይሎች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ማንም ሰው እንደሚያውቀው ጠቅላላውን የሸንጎ አባሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አልመረጣቸውም፡፡

ስለዚህ ሸንጎው ሕዝቡ ስለአልመረጣቸው „…መፍረስና መበተን“  አለበት፡፡ ጥለውት ወደ መጡበትም ወደ ሥራቸው ተመልሰው መሄድ ይገባቸዋል፡፡

ሸንጎው ፈርሶ „…የሚቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት“ አዲስ ምርጫ ከሁለት ወይም ሦስት አመት በኋላ ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

ወያኔ ይህን አይፈልግም፡፡

ወያኔ የሚፈልገው በአብይ ካቢኔ ውስጥ የእራሱን ሰዎች ሰግስጎ በጀመረው ለመቀጠል ነው፡፡ የመከላከያው ሚስትር፣የአገር አስተዳደሩ፣ ጄኔራሎቹና የጸጥታው ፖሊሶች፣….የውጭ ጉዳዩ፣…የባንክ ገዢዎች፣…ከንቲባዎቹና፣ቀበሌው…. በእነሱ እጅ ሁኖ አብይ እየተዘዋወረ „ጥሩ፣ጥሩ „ ሰው መስማት የሚፈለገውን ነገር እየተነጋገረ ወደፊት እንዲያዘግም ነው፡፡

„…በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ“፣እሱንም እንደማስፈራሪያ አድርጎ አብይንም ሆነ ጓደኛውን ለማን ፣እንዲሁም የሕዝቡን እንቅስቃሴ ጭምር „ ጊዜ ገዝቶ“ እሱን መሣሪያ በማድረግ እንደ አለፉት አመታት  አገሪቱን ከፋፍሎ „…መዝረፍ“ ይቻላል ብለው አክራሪ ወያኔዎች ድግሳቸውን አለጥርጥር ደግሰዋል፡፡

ግን ደግሞ አንድ እዚያ አውሮፓ እየታተመ የሚወጣ ዕለታዊ ጋዜጣ በትክክል አዲሱን ሁኔታ አይቶ እንደ ጻፈው  „….ከጠርሙሱ ውስጥ አንዳች መንፈስ አፈትልኮ ወጥቶአል፡፡ …ያ ! እንዳይወጣ ጥርቅም ተደርጎ፣ለዘመናት ታሽጎ ተቀምጦ የነበረው አንድ  መንፈስ „ – ጋዜጣው ይህን መንፈስ “…ጂኒ“ ይለዋል – „….ከሕዝብ የተቃውሞው ቁጣ ጋር ጠርሙሱን ለቆ አምልጦአል፡፡… ያንን በአራቱም ማዕዘን አሁን ተኖ፣ አፈትልኮ አገሪቱን ያዳረሰውን መንፈስ፣ እንደገና በቀላሉ ሰብስቦና ለቅሞ ጠርሙሱ ውስጥ  ከእንግዲህ መክተት – በኢትዮጵያ- አይቻልም…„ ብሎ ጋዜጠኛው ሓቁን በጥቂት ቃላት አስቀምጦአል፡፡

ጸሓፊው ዕውነት አለው፡፡

ከእንግዲህ ለጥያቄዎቻቸው ሕዝቡ መልስ ሳያገኝ ያ! „መንፈስ“ ተመልሶ ጠርሙስ ውስጥ  አይገባላቸውም፡፡

ግን የፈነዳው አብዮት በጥንቃቄ ከአልተያዘ እና የተደረጃ የተቀነባበረ አንዳች „ዝግጅት“ ከአልመራው በቀላሉ „…ሊከሽፍም“ ይችላል፡፡

ቢቀር ቢቀር ወያኔ አገር ከሚያበጣብጥ ተንኮል ከመሥራት አይመለስም፡፡„… እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል“ ብሎ አፈጅቶን ሊሄድም ይችላል፡፡ ግን ይህን ለማድረግ ከእንግዲህ ኃይል አለው!

እሱን ከግምታችን ውስጥ አስገብተን ከመዘርዘራችን በፊት በመጀመሪያ አብይ ምን አለ! ብለን ንግግሩን እንደገና እንመለከተው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአሁኑ ሰዓት „….በረሃብ አለንጋ ስለ ሚጠበሱት በሚሊዮን ስለሚቆጠሩት የአገሪቱ ልጆች „ በንግግሩ ላይ አላነሳም፡፡ የጡራታ ገንዘባቸው ስለማይበቃቸው ፣እንዲያውም ምንም ስለሌላቸው፣እንደዚሁ በሚሊዮን ስለሚቆጠሩት  እናትና አባቶች አንዳችም አረፍተ ነገር አልሠነዘረም፡፡

በየቤተ ክርሲቲያኑ ደጃፍና በየመንገዱ፣በልመና ስለሚተዳደሩት ዜጎቻችን ምንም ቃል ዞር ብሎ ለእነሱ አላሰማም፡፡

በቀን አንዴ በልተው ስለሚያድሩ፣የቤት ኪራይ መክፈል ስለማይችሉ፣….ለልጆቻቸው፣ልብስ ቀርቶ ለትምህርት ቤት የሚሆን ደብታርና እረሳስ፣  የምሰሳ ዳቦ እንኳን ማቅረብ ስለማይችሉት ቤተሰቦች ምንም አላለም፡፡

ከሁሉም „ሥራ እና ዳቦ ፣መሬትና ቤት“ አምጡልን ብለው ስለ ተነሱት ወጣቶች ጥያቄ አስቸኳይ „ማስታገሻ“ መልስ አላቀረበም፡፡

በሺህና በአሥር ሺህ „የኢትዮጵያ ባንዲራ አነሳችሁ „ ተብለው ወሕኒ ቤት ስለ ተወረወሩት እሥረኞችም እሱ አብይ አህመድ ምንም አላለም፡፡

50 ዶላር በማይሞላ የወር ደመውዝ ከአሥር ሰዓት በላይ በየፋብሪካው ለአውሮፓ ኩባንያዎች ስለሚሰሩት ሠራተኞች ጉዳይ አልተናገረም፡፡

ቤታቸው በአናታቸው ላይ ፈርሶ ፣እነሱ ተበትነው መሬታቸው ለቱጃሮች ስለተሸጠባቸው ቤተሰቦች ምንም አላለም፡፡

ያም ሆኖ ግን አብይ ስለ „….የሁላችንም ቤት ስለሆነችው ስለ ኢትዮጵያ „ አንስቶ ግሩም ድንቅ አረፍተ ነገሮችን ሸንጎው ላይ በአደረገው ንግግሩ አሥምሮበት ሄዶአል፡፡

በዚህም አንዱ የአውሮፓ ጋዜጠኛ እንደ ጻፈው „…ቡና ቤት ተቀምጠው ንግግሩን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎችም፣ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጭብጨባቸው“ አብይን ሲያጅቡት ያየውን ስሜት ተገርሞ አምዱ ላይ አሥፍሮአል ፡፡

ቀጥሎ አብይ„… ልዩነቶቻችን እናስተናግድ“ ብሎአል፡፡“….በሓሳብ ፍጭት መፍትሔ እናገኛል“ ብሎ እሱም ያምናል፡፡ „….የሓሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም“ ይለናል፡፡

„… እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ይገባናልም“ ብሎ „….መጪው ጊዜ የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው“ ብሎ … እቅጩን አብስሮአል፡፡

„…በአገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ“  ስለ ነጻነትና ስለ ፍትሕ፣ስለ የሕግ በላይነትም አንስቶ ስለ መተማመንና እና ስለ መግባባት ስለ በሠለጠነ መንገድ ቅራኔዎችን መፍታት ግሩም ሓሳቦችን አብይ በንግግሩ ላይ ሠንዝሮአል፡፡

ለመነሻ! ከዚህ የበለጠ ምን ያስፈልጋናል፡- ለመነሻ!!! ግን ይህን ተከትሎ ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ ለማምጣት፣እቅዶቹን በደንብ ሰብሰብ አድርጎ አላስቀመጠም፡፡

በሕዝብ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸሙትን ወታደሮች ፍርድ እንዲቀበሉ አደርጋለሁ ብሎ ቃል አልገባም!!

ለአንድ አገር ዕድገትና ለዜጎች በአንድነት በጋራ ቤት ውስጥ ተቻችለው አብረው ለመኖር ቢያንስ „…ሁለት ቁልፍ ነገሮችን“ አንድ መንግሥት – በመመሪያ ደረጃ – ቁልጭ አድርጎ በማያሻማ ቋንቋ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማስፈር አለበት፡፡ የሥልጣኔ ምንጩ ይህ ነው፡፡

አንደኛው „ሐሳብንና አመለካከትን በነጻ የመገልጽ መብት“  ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለማንም የማያዳላው „የሕግ በላይነት“ መኖር ነው፡፡

እነዚህ ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላሉ፡፡ ይህን የጨብጥ ሕዝብ ለገባበት ችግር „…ከፊል መፍትሔ“ አገኘ ማለት ነው፡፡

በአንድ በኩል፣ ….ነጻ ፍርድ ቤትን ፣ በሌላ በኩል…. ነጻ-ፐሬስን፣….በአንድ በኩል በነጻ ሕብረተስብ ውስጥ መኖርና መተንፈስን፣….በሌላ በኩል ተደራጅቶ መምረጥ እና መመረጥን….በአንድ በኩል መመራመርን፣ በሌላ በኩል ሠርቶ ጥሮ ግሮ፣ንብረትን ማፍራት….አንድ ሕዝብ የሚቻለው „….የሕግ በላይነት“  በአንድ አገር ሲሰፍንና፣“…..የፕሬስ ነጻነት …ሲረጋገጥ“ ብቻ ነው፡፡

የአውሮፓና የአሜሪካ ዕድገት፣የጃፓንና የህንድ … ሥልጣኔም የተገነቡትና የተመሠረቱት  በእነዚሁ „ጡቦች“ ላይ ነው፡፡

ሦስተኛው „የሥልጣን ክፍፍል“ ነው፡፡ ሥልጣን ተሸንሽኖና ተከፋፍሎ፣አንዱ ሌላውን ከመስመር እንዳይወጣ“ የመቆጣጠር“ መብቱን ሕገ-መንግሥቱ ላይ መሥፈር ይኖርበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን በአገሪቱ ለአለፉት ሺህ አመታት ያልታየውንና ያልተሰማውን „…. በሥራ ላይ ለማዋል ተነስቼአለሁ ተባበሩኝ“ የሚለውን ጥሪውን ሸንጎ ላይ ለአገሪቱ ዜጎች ፣ለተቃዋሚውም ጭምር አሰምቶአል፡፡ ይህን ጥሪ አሁን ዘሎ ማለፍ አይቻልም ፡፡ ይህን ጥሪ እንደ አልሰሙም  ችላ ማለት ስህተት ነው፡፡

„…በፖለቲካ ዓለም አርፍዶ የመጣውን“- ሚካኤል ጎርባቾቭ -„ ታሪክ ትቀጣዋለች..“ ብለዋል፡፡ እንደምናውቀው ይህን ያሉትንም ሰው ፣ጎርባቾቭን፣ ታሪክ ፍርዱዋን ሰጥታ ቀጥታቸዋለች፡፡

አብይ አቅጣጫውን ሰጥቶአል፡፡ አብይና የአገሪቱ ሊህቃን፣ ደግሞ በንግግሩ ላይ እንደተሰማው „…አንድ ላይ ሁነው“ ተባብረው፣ እንደ „አንድ ሰው“  ይህን ጥሪ „….በሥራ ለመተርጎምና ለማሳየት“ መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ግን በመጀመሪያ ምን መደረግ አለበት!!

ትልቁ ጥያቄ በአሁኑ ሰዓት ይህ ነው!….ምን መደረግ አለበት! መልሱ „ በቤተ – መንግሥት፣የራት ግብዣ ማካሄድ“ አይደለም፡፡

የአለፈው ስህተት እንደ ገና በሌላ መልኩ „ ተደግሞ“ ብቅ ብሎ በአናታችን ላይ እንዳይጨፍር ከምንስ መጠንቀቅ አለብን!

ለአቢይ „ጊዜ እንስጠው“ የሚል አነጋገር በአሁኑ ሰዓት ከብዙ አቅጣጫ ይሰማል፡፡ አንድ ቀን፣ ሁለት ሳምንት፣ ሦስት ወራት፣ወይስ አንድ አመት!

ይህን ማድረግ ስህተት ነው፡፡እንዲያውም ለወያኔዎች በቂ ጊዜ እንዲገዙ ዕድል መስጠት ነው፡፡

እንቅስቃሴው አለውጤት „… ተዳፍኖ፣ከሽፎ..“ እንዳይቀር ከተፈለገ፣ በመጀመሪያ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ በአስቸኳይ ለአንድ ጉዳይ መስጠት ይኖርብናል፡፡

ሁሉንም ወገን የሚያሳትፍ  „የራት ግብዣ ሳይሆን…የክብ ጠረጴዛ ስብሰባ „ መጥራት የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር  ንግግር ሲካሄድ -ምሥጢር መሆን የለበትም- ተመልካች „ሽማግሌዎች „ ፣ ዘጋቢ ጋዜጠኞች በቦታው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡

በዚያ! የክብ ጠረጴዛ ንግግርም ላይ ፣…የሃማኖት አባቶች፣ የሙያ ድርጅት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪዎች፣ አስተማሪዎች፣ተማሪዎች ጠበቆች፣ዳኞችና ደራሲያን ጸሓፊዎች….በጠቅላላው  የአገሪቱ ምሁራን እና የሲቪል ማህበርሰብ ተወካዮች በሚሉ ማሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡

የንግግሩ ውጤትም  ደግሞ – ሌሎች አገሮች እንደታየው- ለጊዜው በሁለት ነገሮች ላይ ብቻ ቢያተኩር ውጤቱ የተሳካ ይሆናል፡፡

አንደኛው አሁን ከአለው ሁኔታ ጋር አብረው የማይሄዱትን የሕገ-መንግሥቱን „አንቀጾች ማሻሻል“ ነው፡፡ አሻሽሎም በአዲስ እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡ ይህን የሚሠሩና የሚያስተካክሉ ጠበብቶችን መሰየም ይኖርበታል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የንግግሩ ውጤት፣ „ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት“ እንዲመሠረት መንገዱን ይጠርጋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ተገለው የነበሩትን የሕብረተስቡን ክፍሎች፣…የሃይማኖት አባቶች፣የተደራጁና ያልተደራጁ ምሁሮችን፣ተማሪዎችን፣ወጣቶችን… – እላይ የተባለውን እንደገና ለመድገም- ያቀፈ ከእነሱም የተውጣጣ አንድ„…..ጊዜያዊ …የሽግግር መንግሥት „ ኃላፊነቱን ተቀብሎ አገሪቱን ይመራል፡፡ ይህ „ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት“ ከሁለት፣ግፋ ቢል ከሦስት አመት በላይ መቆየት የለበትም፡፡

ከዚያ በሦስተኛው ደረጃ „…ነጻ-ምርጫን“ በአገሪቱ አካሂዶ ሥልጣኑን፣ለተመረጡት ድርጅቶች ያስረክባል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ „ …ዲሞክራሲ ለእኛ ባዕድ አይደለም“ ብለው የሚያምኑ ከሆነ „…ነጻ- ፔሬሱን“ ከመንግሥት ቁጥጥርና ከመንግሥት ሳንሱር ነጻ ሁነው እንዲንቀሳቀሱ „መብታቸውን“  በመንግሥት ደረጃ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ከእሱም ጋር እንደዚሁ የእህአዴግ የግል ቤትና ተቀጥላ ሆነ ይሰራ የነበረውን ፍርድ ቤት አስተካክለውና ሽረው„… ነጻነቱ „ በይፋ የታወቀ ፍርድ ቤትና ዳኞች በአስቸኳይ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማረጋገጥ፣ይኖርባቸዋል፡፡

ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ሥርዓት የሚደረገው ጉዞ እንዲሳካ፣ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች ደማቸውን ያፈሰሱበት አላማቸው እንዳይቀለበስ፣ እላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡እሱ ብቻ አይደለም፡፡ የሕዝቡም ጥያቄ በአስቸኳይ መልስ የሚያገኘው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፤

እነዚያ „ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ „ ….የሚያስፈራ ጦርና የስለላ ድርጅት፣እንዲሁም አንዴ በግዛት ዘመናቸው በሚሊዮን ይቆጠሩ የነበሩትን ካድሬዎችን ሰብስበው የነበሩት „…. የፖላንድና የሩሜንያ ፣የቡልጋሪያና የምሥራቅ ጀርመን፣የቼኮዝሎቫኪያና የሶቪየት ኮሚኒስት ፓርቲዎች“ ደም ሳይፈስ የሥልጣን ሽግግር በየአገራቸው ያካሄዱት „በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ“ ነው፡፡

ይህን መፍትሔ አንቀበልም ያሉት እንደ ቻውቼስኮ ዓይነቶቹ  ደግሞ ተይዘው – ለማስታወስ- በጥይት ተደብድበው ከሥልጣናቸው ወርደዋል፡፡

„…ለውጥ „ በአገሪቱ በኢትዮጵያ እንዳይመጣ የሚፈልገው አንደኛው የወያኔ ክንፍ „ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ „ ዕድሜአቸውን አራዝመው እንደገና ሊገዙን ይፈልጋሉ፡፡ ይህቺን ዓይነቱዋን ዕድል ግን እንደገና መልሰን ለእነሱ መስጠት የለብንም፡፡

ሌላም „ሕልምም“ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በሐምሌ እና ነሓሴ ወር „…እህአዴግ ተዋህዶ“ አንድ ፓርቲ ሆኖ ሊቀመንበሩንም አብይ አህመድ አድርጎ ተቀበሉኝ ሊለን ይፈልጋል፡፡

ምናልባት ስማቸውን ቀይረው „….የሶሻል ዲሞክራቲክ“ ብለው ብቅ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ወይም እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ „… የፍትህና የእኩልነት ፓርቲ „ የሚለውንም ስም ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ወይም….“ አዲሱ አብዮታዊ ዲሞክራቲክ ፓርቲ …“

ወያኔ በዝርፊያ ያካበተውን ሐብት እና ሥልጣኑን ከመዳፉ ለአለማስወጣት ገና „ብዙ „ የሚያደርጋቸው ነገሮች አይጠፉም፡፡

እንደ ቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ወይም እንደ ግብጹ ጄኔራል አዚዚ „ከሕዝቡ ቁጣ „ በአንዳንድ ብልሃቶች „….እናምልጣለን“ ብለው ለተመልካቹ አዲስ የሆነ „መላ ምትም „ ሊመቱ ይችላሉ፡፡

ግን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሆነ የግብጽ ሠራዊት …ጄኔራል አዚዚም እንደ ወያኔ „…በዘር ላይ የተሰባሰበ…. የተደራጀም“ ዘርንም መሠረት አድርገው፣ አገራቸውን  የዘረፉ ሰዎች አይደሉም፡፡

ወያኔ  … እንደ ቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ወይም እንደ አዚዚ „ተቀባይነት“ የሚኖረው፣ „….ከሥልጣኑም ፣….ከዘረፈውም ሓብቱም“ ለሕዝቡ መልሶ ሲያካፍላቸው ብቻ ነው፡፡

በአጭሩ የቻይና እና የግብጽ መሪዎች „…በዘር“ ተደራጅተው „እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች“ አገራቸውን አላራቆቱም፡፡ ከዚያም በላይ የሁለቱ አገር መሪዎች „…ዳቦና ሥራ፣…ብልጽግና እና ዕድገትን „ ለሕዝባቸው አምጥተዋል፡፡ ከተገኘውም ለዜጎቻቸው አካፍለዋል፡፡ የአገራቸውን መሬትም ለባእድ መንግሥታት፣….ለአውሮፓና፣ለአረብ፣….ለቻይናና እና ለቱርክ ቱጃሮች እንደ ወያኔ እነሱ አልሸጡም፡፡

የፈነዳው አብዮት ተኮላሽቶ እንደይከሽፍም ፣ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በጀመረው አላማ መቀጠል የሚችለው እላይ የተባሉትን እርምጃዎች በሥራ ተርጎሞ ሲያሳይ ብቻ ነው፡፡ አብይ ለእራሱም ሆነ፣ ሸንጎ ውስጥ የተናገረውን „ቃሉን ለማክበር“ ፣ከእሱም ጋር የቆሙትን ሰዎች ደህንነት ለመጠበቅ፣ „ ሁሉም በተቻለ መጠን አስተዋጽዎውን ለእናት አገሩ ለኢትዮጵያ እንዲያበረክት“ …የክብ ጠረጴዛ ስብሰባ „ ሲጠራ ብቻ ነው፡፡

ወደፊት መቋቋም ያለበት „አዲሱ የአብይ ካቢኔም „ ዱሮ የምናውቃቸው ሰዎች፣ ወያኔዎች መሆን የለባቸውም፡፡ „ አዲሱ ካቢኔ“ ከሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍል  የተወጣጣ ፣ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ነው፡፡

„ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና ታፍራ፣ተከብራና በልጽጋ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ“

ይህ አነጋገር በትክክል በሥራ ላይ የሚተረጎመው ደግሞ – ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲ የተሸጋገሩትን አገሮች መንገድ ስንከተል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ከሌሎቹ አገሮች  በምንም ዓይነት አትለይም፡፡ ዪኒቨርሳል መፍትሔ ነውና!

 

 

Filed in: Amharic