>
5:30 pm - Thursday November 2, 3567

ፕሮፌሰሩ እና የመርከቡ ተሳፋሪዎች (ታምራት ነገራ)

ፕሮፌሰር መስፍንን እስከ ምርጫ 97 ድረስ የማውቃቸው ከውጭ እና በሩቁ ነበር፡፡

ምርጫ 97 ሲመጣ እርሳቸው እና ጓደኞቻቸው የመሠረቱት ቀስተ ዳመና ፓርቲ ከሌሎቹ ሦስት ፓርቲዎች ጋራ በመኾን ቅንጅትን የመመሥርት ጥሪ ማድረጉ ፕሮፌሰርን የማወቅ አጋጣሚ ፈጠረልኝ።

በወቅቱ እኔ የኢዴሊ አባል ነበርኹ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፕሮፌሰርን እንደ ፖለቲከኛም፤ ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ እንደ አዲስ ነገር ጋዜጠኛ (አዲስ አበባ ሳለች) በቅርበት ለማየት እና አብሬያቸው ለመሥራትም ዕድል ፈጥሮልኛል።

በእነዚህ ዓመታት ስለ ፕሮፌሰር ሐሳቦች እና ጽሑፎች ያለኝ አመለካከት ተለዋውጧል፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወሳኝ ወሳኝ የሚባሉት የፕሮፌሰር መስፍን ሐሳቦች ግን አልተለወጡም፤ እርሳቸውም መጻፍ አላቋረጡም፡፡

ከቅንጅት በፊት ፕሮፌሰር በተለያዩ ጋዜጦች የሚያሳትሟቸውን ጽሑፎች አልፎ አልፎ ገረፍ ገረፍ ከማድረግ በስተቀር ቋሚ አንባቢያቸው አልነበርኩም፡፡

በወቅቱ በአይዲዮሎጂ ልዩነት ምክንያት ፕሮፌሰር መስፍን የሚጽፉትን ጽሑፍ ማንበብም ኾነ ሐሳባቸውን ማስተናገድ ለእኔ የሚዋጥልኝ አልነበረም፡፡

ኢዴሊ ለቅንጅት መሥራችነት ሲጋበዝ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ለማስተላለፍ በጠራው ስብሰባ ላይ “ብርሃን ከጨለማ ጋራ ምን ኅብረት አለው?!” ለማለት እስኪዳዳኝ ድረስ ከእነ ፕሮፌሰር መስፍን ጋራ ተባብረን መሥራት እንደሌለብን ወጥሬ ተከራከርኩ፡፡

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ጀምሬው ወደ መሀል ለማፈግፈግ ኢዴሊን እንደቤቴ ብመርጥም፤ ተዐምር ካልተፈጠረ በቀር ከፕሮፌሰር መስፍን ጎን የሚሰለፈውን እኔን ማየት አልኾነልኝም።

በወቅቱ የፓርቲያችን ሊቀመንበር የነበረው ዶ/ር ዓለማየሁ አረዳ እና ሌሎች ጠና ያሉት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ግራ ዘመም ኾነን ያስቸገርነውን ወጣቶች ወደ ቅንጅቱ እንግባ ብለው ማሳመን አቃታቸው።

ውሳኔ ለማሳለፍ በጭንቅ በተወጠረው ስብሰባ መካከል ከእኛው (ከረባሾቹ ወጣቶች) ወገን የኾነው ስለሺ ጠና ያመጣው ሐሳብ ውጥረቱን ረገብ አደረገው። ስለሺ ያመጣልን ሐሳብ ቀላል ነበር፡፡

“እነዚህ ሰዎች ቀኝ ናቸው ብለን ብንተዋቸው፤ ያላቸውን ፖለቲካዊ ሐይል ግን ችላ ማለት የለብንም፡፡ ከእርነሱ ጋራ ባንሠራ ወያኔ ብለው ይፈርጁናል፤ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜም ኢዴሊ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ይወገዳል።

ስለዚህ የዛሬው ምርጫችን ፍጻሚያችንን ይወስናል።” አለና አረፈው፡፡

ኢዴሊያውያን ያኔ ከፍተኛ የኾነ የመታወቅ ረኀብ ውስጥ ነበርንና “ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ፓርቲው ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊወገድ ይችላል” የሚለውን የስለሺን ማስጠንቀቂያ በቀላሉ ልናልፈው አልቻልንም።

በስለሺ መከራከሪያ ደስ የተሰኘው ዶ/ር ዓለማየሁም አዲስ ሐሳብ አቀረበ፡፡

“ይህን ከእነፕሮፌሰር መስፍን ጋራ የምንመሠርተውን ቅንጅት እንደ ጀልባ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደግሞ እንደመርከብ እንየው፡፡

ይህን ቅንጅት እንደ ጀልባ ተጠቅመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ስንደርስ መርከቡ ላይ ተሳፍረን ስናበቃ ጀልባውን እንሰናበታለን፡፡

” ቅንጅትን እንደ ጀልባ ሕዝቡን እንደመርከብ አስበን፤ እንደ ለምፃም እንንገሸገሽባቸው ከነበሩት ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ለመሥራት ከጀልባው ተሳፈርን፡፡

ድንቄም ጀልባ! ድንቄም መርከብ! ታሪክ ተገለባበጠና ይኼው መርከቡም፤ ጀልባውም፤ ጠላቱም፤ ወዳጁም፤ ግራውም፤ ቀኙም ተተረማመሶ ጫዎታው አበቃ።

ገና መርከቡም፣ ጀልባውም፣ ባህሩም እንዲህ ሳይተረማመስ፤ ቅንጅትን ተሳፍሮ መርከቡ ላይ መውጣት የምትለዋ የዶ/ር ዓለማየሁ አረዳ አናሎጂ አስቂኝ ኾና ስላገኘናት የኢዴሊ ወጣት ክንፍ አባል የነበርነው እኔ፣ ስለሺ፤ ሙሉነህ እዮኤል እና ታሪኩ ደመላሽ ለአንዳንድ ወቅቶች እና ግለሰቦች የምታመች ‘መርከቡ’ የምትል ስም አወጣን።

ፕሮፌሰሩን መተዋወቅ

በርዕዮተ ዓለም ምክንያት አፍንጫዬን ይዤ የተጠጋኋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ግን ፈጽሞ እንደገመትኳቸው ኾነው አላገኘኋቸውም፡፡

አንደኛ፦ በጣም! በጣም! በጣም! ወጣት ይወዳሉ፡፡ የሐሳብ ድግግሞሻቸውን እና ሌክቸራቸውን ታግሶ የሚሰማቸው ከተገኘማ በጣም ደስታቸው ነው፡፡

ዝም ብለው ለሰሟቸው ወይንም ካርታ ከሚያጫውቷቸው እኩዮቻቸው ጋር ከመዋል ይልቅ ከሚጣላቸው ወጣት ጋራ ሲጨቃጨቁ መዋልን ይመርጣሉ እላለሁኝ፡፡

የእኛ ቢጤ እብሪተኛ የኾነን ወጣትን ማልመድን ደግሞ ልክ ፈረስ እንደመግራት ተክነውበታል፡፡ ለምን አይችሉበት!?

ስንት ትውልድ በስራቸው አለፈ? እንዲያው ሳናውቅ፣ ዐይናችን ሳያየው፤ ግንኙነታችን ከፕሮፌሰር መስፍንነት ወደ “ፕሮፍነት” ተለወጠ፤ ከእኛ ጋር ተቀላቅለው ቡና መጠጣትና የቆጥ የባጡን ማውራት ተጀመረ፡፡

ሁለተኛ፦ በጤንነት እና በዕድሜ ምክንያት እንደ ዔሊ ለማዝገም ቢገደደዱም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እና ሳይታክቱ በእጅጉ ይሠራሉ፡፡

መጽሐፎቻቸውን ሙሉ በሙሉ አሊያም የመጀመሪያውን ድራፍት ራሳቸው ይተይባሉ፡፡

ሦስተኛ፦ በአደባባይ መናገርም ኾነ መጻፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ፈፅሞ ያልለወጧቸው ዋና ዋና አቋሞች አሏቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ሰላማዊ ትግል፤ ስለ ስደት፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ስለ ሕግ የበላይነት፤ ስለ መሬት ፖሊሲ፤ ስለ ኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያሏቸውን አቋሞች ከፈለጋችኹ 50 ዓመት ወደኋላ ተመልሳችኹ ሂዱና አጥኑ፤ አሁንም ያኔም ፕሮፌሰር መስፍን ያው ናቸው፡፡

ይኼን እንደ ክፋት ከማየታችን በፊት በእነዚህ ሐሳቦች ዙሪያ {ለፖለቲካ፤ ለሕልውና፤ ለጥቅም፤ በአዲስ እውቀት ለመፈንደቅ እና ለሌሎች ምክንያቶች} ስንል ስንቴ አቋም እንደምንቀያይር አስተውሉ፡፡

በእነዚህ ሐሳቦች ዙርያ ኢትዮጵያ ስንቴ ተተራመሰች? ፕሮፌሰር መስፍን ግን ወይ ፍንክች፡፡

አራተኛ፦ ፕሮፌሰር መስፍን እጅግ ጨዋታ አዋቂ ናቸው፡፡ በቲቪ እና በጽሑፍ የምታውቋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ካድሬ ካድሬ ሊሸቱ ይችላሉ።

ጠጋ ስትሉ ግን ፕሮፍ አዲስ አበባ አሉኝ ብላ ልትኮራባቸው ከሚገቧት አራዶች አንዱ ናቸው፡፡ ያውም ለዛ ያላቸው አራዳ፡፡

አንድ ቀን ቤታቸው ሻይ ልንጠጣ ሄድንና ስለ ፍቅር እና ፍቅር እንዴት ለጽሑፍ እንደሚያነሳሳ ጫዎታ ተጀመረና እንዲህ አሉ “ይገርማችኋል አንድ ጊዜ ኮሌጅ ሳለሁ ፍቅር ይዞኝ 48 ገጽ የፍቅር ደብዳቤ ጽፌ ነበር”፡፡

እዚያ ከነበርነው አንደኛዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ነበረች፤ በመገረም “ፕሮፍ 48 ገጽ ሙሉ!?” በማለት ጠበቅ አድርጋ ጠየቀቻቸው።

“አንቺ ደግሞ፤ እሱንም ያቋረጥኩት ዶርም ሜቴ ዘሎ ሲገባ ከምናቤ ስለነቃሁ ነው” ብለው ቤቱ ውስጥ የነበርነውን ሁሉ ሳቅ በሳቅ አደረጉን፡፡

በሕይወት ገጠመኝ ትልልቅ ኢትዮጵያውያን (በርከት ያሉትን ለማግኘት ዕድል ገጥሞኛል) የፕሮፍን ያህል ለዛ ያለው ጨዋታ አዋቂ ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ (ቤፍ) ብቻ ነው። ፕሮፍ ከሲጋራ ምርጫ እስከ ፍልስፍና፤ በጨዋታ አድማጫቸውን ማስመጥ ያውቁበታል፡፡

አዲስ አበባ ያላችሁ ወጣቶች እስኪ እባካችኹ ኤድና ሞል ጊዜ ከምታጠፉ ሰብሰብ በሉ እና ፒያሳ ፕሮፍን ለማየት ጎራ በሉ፡፡ የኤድናው ፊልም በዲቪዲ መልክ መጥቶ ለዘላለም የእናንተ ይሆናል፡፡

ፕሮፍ ግን ለሁልጊዜም ከእናንተ ጋራ አይኾኑም፡፡ ከዕድሜ፣ ከትምህርት፣ ከንባብ ያገኙትን በማርልቦሮ ጭስ እያዋዙ ለዘላለም የማትረሱትን ጨዋታ ያጫውቷችኋል፡፡

ይሄ ደግሞ በተለይ በተለይ ፖለቲካ እንወዳለን ለምትሉ ጥብቅ ምክሬ ነው፡፡

እኔ እና አብይ በኦባማ ፍቅር እንደጀማሪ ፍንዳታ ብን ባልንበት ሰዓት ስለአሜሪካ ምርጫ ከእሳቸው ጋር ጨዋታ ገጠምን እና “ኦባማን እንዴት ያዩታል?” ብለን ጠየቅናቸው፡፡

እኔ እና አብይ ከ2006 የኮንግረስ ምርጫ ጀምሮ የእያንዳንዷን ካውንቲ (ወረዳ) ውጤት መከታተል ተለማምደናል እና የ2008 ምርጫ ኤክስፐርት አድርገን እራሳችን በራሳችን ሾመናል ስለዚህ በጥያቄያችን በውስጧ ፕሮፍ ምን ያህል ያውቁ ይሆን የምትል መገምገሚያ ቢጤ አዝላለች፡፡

“ እንደ ኤድላይ ስቴቨንሰን እንዳይሆን እሰጋለታለሁ” አሉን፡፡ እ.ኤ.አ 1958 ጀምሮ ስለነበረው የአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ጠለቅ ጠለቅ እና ጠበቅ ያሉ ሀሳቦችን እየሰጡን አንዳነዶቹን ምርጫዎች እሳቸው አሜሪካን ስለነበሩ የነበረውን ክርክርም እየዳሰሱ አጫወቱን፡፡

እኔ እና አብይ በአንናቆት ተያየን ፕሮፍ በወቅቱ ያጫወቱን ሀሳቦች የአሜሪካንን ፖለቲካ ለእኛ የተነትኑልን ከነበሩት አንዳንድ ጋዜጠኞች በእጅጉ የተሻለ እና መዓዛ ያለው ነበር፡፡

በቅንጅት የተዋወቅኋቸውን ፕሮፍ አንዴ የቅንጅት የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ጸሐፊ ኾኜያለሁና ለሥራም ለወዳጅነቱም ብዬ ጽሑፎቻቸውን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ በጽሑፎቹ ጥራት ተገረምኩ፡፡

ሐሳቦቹ ለእኔ ብዙም እንግዳ አይደሉም። ነገር ግን የፕሮፍ የአማርኛ አጣጣል፣ ለዛ እና በጽሑፍ የፓርቲውን (የውስጡንም የውጭውንም ሰው) የመጎንተል ችሎታቸው አስገራሚ ነበር፡፡

ለምሳሌ፤ አቶ በረከት ስምዖን የኢንተር ሀሞዌን ስብከት እንደጀመረ በወቅቱ ከነበሩት ጋዜጦች በአንዱ ላይ ለበረከት መልስ አንድ ጽሁፍ ጣል አደረጉ፡፡

ከዛ ፅሁፍ ውስጥ አንዲት አረፍተነገር እስከአሁን አትረሳኝም፡፡ “ከበረከት አፍ የሚወጣው እሳት ነው፡፡

ደረቀ እንጨት የለም አንጂ ደረቅ እንጨት ቢያገኝ አገር ያጠፋል” ተመልከቱ ስልጣንን አና የድራጎኑን ምስል እነዴት በአንድ አረፍተነገር አንዳንሰላሰሉት?

ፕሮፍ ከሚጽፏቸው መጻሕፍት በማይተናነስ እንዲያውም የሚልቁ ሐሳቦች በብዛት በተሸለ ጥራት በጋዜጣዎቹ በሚያቀርቡት ትንንሽ ጸሑፎች ውስጥ ታጭቀው ነበር፡፡

በእነዚህ ጽሑፎች ስለተማረክኹ እርሳቸው እስር ቤት ሳሉ {የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መጸሐፍ እንደወጣ} በቀጣይነት በአንድ ላይ ተሰብስበው በአንድ ጥራዝ እንዲታተሙ ለማድረግ ከልጃቸው ከዶ/ር መቅደስ መስፍን ጋራ ተነጋግረን ነበር፡፡ ሌላ የሚቆጭ የከሸፈ ውጥን።

ከጽሑፎቻቸው ባሻገር የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ቼዝ በግራንድ ማስተር ደረጃ ተክነውበታል፡፡

ማን ወዴት? እንዴት? ለምን? እና መቼ? እንደሚንቀሳቀስ ያን የቶሞካ ወፍራም ቡና ፉት እያሉ ማርልቦሮ ሲጋራቸውን ሳብ ለቀቅ እያደረጉ ሲተነትኑ ለሚሰማቸው፤ ለትንታኔያቸው ምሁራዊ ብቻ ሳይኾን የኾነ ውቃቢያዊ ሞገስም ይለግሱታል፡፡

ቅንጅት እንደማይኾን ኾኖ እኔም ፖለቲካውን ትቼ ወደ ጋዜጠኝነቱ ስመጣ ፕሮፍን በሌላ ዐይን የማየት ዕድል ገጠመኝ።

ምንኛ ትንሽም ብትኾን ትችት እንደማይችሉ፤ ምንኛ ቀላልም ብትኾን ለመተነኳኮስ ወደኋላ እንደማይሉ ዐየሁኝ፡፡ ወዳጄ መስፍን ነጋሽ “ፕሮፍ ምን ነካቸው?” ብሎ ለጻፋት አስተያየት የሰጡትን ምላሽ ወደ ኋላ መለስ ብላችኹ ቃኙ፡፡

ገና እንደመጣሁኝ ከአገርቤት ብዙ ነገር ይናፍቀኝ ነበር፡፡ አሁን አሜሪካንንም ለመድኩት የተሻለውን ነገር አየሁኝ የአዲስ አበባን ካፌዎች ጨዋታ አለመናፈቅ አልሆነልኝም፡፡

የፕሮፍ እና የቤፍ ጨዋታዎች ደግሞ መናፈቅ ብቻ ሳይሆን ማንነትን የሚቀርፁ ናቸው፡፡ እንደው ሳስበው እኔ እና ፕሮፍ ደግመን አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተን የምንጨቃጨቅ የምንሳሳቅ አይመስለኝም፡፡

እስከዛው ግን እንኳን ለ85 ዓመታቸው አደረሳቸው፡፡ ያወኳቸው ለጥቂት ጊዜ ቢሆንም ያቺው ጊዜ ግን እጅግ ጣፋጭ ነች፡፡

Filed in: Amharic