>

ስለወቅታዊ የፖለቲካ ሃይሎች አጀንዳ አጭር መልዕክት  (ዮናታን ተስፋዬ)

በኢትዮጵያ ስንት ፓርቲ ያስፈልገናል?

ግርማ ሰይፉ

በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ እና ሲቪል ማህበራት ሚና ተደበላልቀው ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳቸውም ቢሆን ተገቢ ሚናቸውን ለመጫወት በሚያስችል ቁመና ላይ አይገኙም፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እና የሲቪል ማህበራት የመኖርን አሰፈላጊነት በግልፅ አስቀምጠውታል፡፡ “የሃሣብ ልዩነት መርገምት አይደለም፤ በአግባቡ ከተጠቀምንበት በረከት ነው፡፡” በማለት፡፡ የሃሣብ ልዩነቶች በረከት የሚሆኑት ደግሞ በአግባቡ ስንጠቀምባቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን የመቶ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ሰለሆነች መቶ ሚሊዮን ህዝብ ማሰብ ይችላል፡፡ ይህን የሃሣብ ብዝዓነት በተወሰኑ ማዕቀፎች በማስቀመጥ የሃሣብ መሸጋሽግ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዜጎች በመሰላቸው መስመር በፖለቲካ ፓርቲ ወይም በሲቪል ማህበርነት የሚደራጁት፡፡
በዓለም ማንነትን መሰረት አድርጎ መደራጀት የተለመደ ባይሆንም የሌለ አይደለም፡፡ በዴሞክራሲ የላቁ ከሚባሉት ግንባር ቀደሟ እንግዚ የአይሪሽ፣ የሰኮትላንደ፣ ወዘተ እያሉ በፖለቲካ ፓርቲነት ይደራጃሉ፡፡ ለበኢትዮጵያ አገራችን አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ አስተሳሰብን ማንነት ላይ መሰረት በማድረግ ነው፣ መደራጀት አንዱ ቅርፅ ሆኖ ከወጣ ሰንብቷል፡፡ በአገራችን ከሰማኒያ በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ የትኛው ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ እንደሆነ ግልፅ መሰፈርት የለም፡፡ ማንነትን መሰረት ያደረገ የሃሣብ መሸጋሸግ ደጋፊዎችም ቢሆኑ በዚህ መስመር ግልፅ ሃሣብ የላቸውም፡፡ የእኛ የሚሉት (ካለ) መበደሉን፣ ሌሎችም እንዲሁ መበደላቸውን በመተረክ ላይ ብቻ የተመሰረተ የሃሣብ ስብስብ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መሄድ ሳያስፈልግ፣ በዚህ መስመርም ቢሆን መደረጃት መብት መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡
ኢትዮጵያችን ውስጥ በብሔር መደራጀት የተፈቀደ ነው፡፡ ሰለዚህም በዚሁ መስመር መሰባሰብ ቢያስፈልግ ከሰማኒያ በላይ ፓርቲዎች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መረዳት የሚኖርብን አንድ ሀቅ ግን አንድም ብሔር ብቻውን ቆሞ ፌዴራል መንግሰት ሊመሰርት ያለመቻሉ ነው፡፡ ሰለዚህ የኢህአዴግ ዓይነት ግንባር የግድ ይለዋል፡፡ በዚህ መስመር ተሰባስቦ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ያልጣመው ደግሞ ሌላ አማራጭ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለዚህ ምሣሌ የሚሆነው ደግሞ መድረክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዚህ ዓይነት ለመሰባሰብ ከእነዚህ ውጭ ተጨማሪ ፓርቲ የሚያስፈልግበት ምክንያት ቢኖር የግለሰቦች የንግሥና ፍላጎት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በክልል ደረጃ በየክልሎች ባሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብዛት ፓርቲ ሊኖር ይችላል፡፡ የመጨረሻ ግባቸውም በክልለ ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት ብቻ ነው፡፡ የክልል ግንባር ከፈጠሩ ደግሞ የክልል መንግሰት ለመሆን ነው፡፡ ለምሣሌ የኮንሶ ሕዝብ ፓርቲ ከደቡብ ክልል ውጭ ለመደራጀት ምንም ምክንያት ሊኖረው አይችለም፤ እንዲሁም ሀወሓት ከትግራይ ውጭ ለመደራጀት ምክንያት አይኖረውም፡፡ ወዘተ …
ከላይ የተገለፁት ፓርቲዎች በአብዛኛው የሶሻሊስት ቅኝት ያለባቸው ሰለሆኑ ሌላ ተጨማሪ ሶሻሊስት ፓርቲ አስፈላጊነት አልታየኝም፡፡ ሰለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ መሰመር የሚከተሉ ፓርቲዎች ሊኖሩ የሚችሉበት እድል ይኖራል፡፡ ሶሻል ዴሞክራት የሚባሉት በዋነኝነት ብዙ የመንግሰት ጣልቃ ገብነት የሚደግፉ ሆነው ግን በመሰረታዊነት የሊብራል ዴሞክራሲ ነፃ ገበያ መርዕን የሚያከብሩ እንዲሁም በግለሰብ መብት ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህ መስመር አንድ ወይም ሁለት ፓርቲዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሁለት ከሆኑ አንደኛው ወደ መሃል የሚመጣ ሊሆን የሚችል ይሆናል (ሴንተር ራይት የሚባለው ዓይነት) ተብሎ ሊገመት ይችላል፡፡
በተመሳሳይ ቀኝ ዘመም የሆኑ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እጅግ ማነስ አለበት የሚሉ ፓርቲዎች የመኖር እድል አላቸው፡፡ በኢትዮጵያችን ይህ እሩቅ ቢሆንም በሃሣብ ደረጃ ዝግ የሚሆን አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የሚላቸው ኒዎ ሊብራል ማለት ሳይሆን ከዚህ መለስተኛ የሆኑ አስተሳሰብ ያለቸው ሊሆኑ ነው የሚችሉት፡፡ በዓለማችን መንግሰት ከጥበቃ እና ህግ ከማስከበር መዝለል የለበትም የሚለው ዘዬ ተቀባይነት ያገኘ አይደለም፡፡ መንግሰት ብዙ ሚና ይኖረዋል፡፡ ጉዳይ ምን ያህል ብዙ የሚለው ብቻ ነው፡፡ ከቀኝ ዘመሞች መለስተኛ የሆኑ ወደ መሃል የመምጣት ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች ቢኖሩም አንድ አማራጭ ነው፡፡ እነዚህ ሌላ አማራጭ አላቸው ሴንተር ራይት ከሆኑት ሊብራል ዴሞክራቶች ጋር መገናኘታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ሰለዚህ በአገራችን ኢትዮጵያ በሃሣብ መሰባሰብ ቢጀመር እና አሁን ያለውን በብሔር የመደራጅት መብትን ሳይቃወሙ መስራት ቢቻል አምስት ወይም ሰድስት ዋንኛ ፓርቲዎች በፌዴራል ደረጃ ሊኖሩን ይችላሉ፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ መንግሰት የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ካሮትና አርጩሜ ማዘጋጀት፡፡
ካሮት ለእነዚህ ስድስት ፓርቲዎች በስብስባቸው ልክ የሚሆን በአዲስ አበባ ቢሮ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት (ደረጃውን የጠበቀ የመንግሰት መስሪያ ቤት ደረጃ ያለው መሆን ይኖርበታል)፣ ተመጣጣኝ በጀት መመደብም ያስፈልገዋል፡፡
አርጩሜው ለፓርቲ ምስረታ የሚያስፈልጉትን ዝቅተኛ መመዘኛ እና አመራር ማሟላት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ማንኛውንም ህጋዊ ግዴታ የማይወጡ አመራሮች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረrግ፡፡

ስለወቅታዊ የፖለቲካ ሃይሎች አጀንዳ አጭር መልዕክት

ዮናታን ተስፋዬ
የአቶ ግርማ ሰይፉ
ምክረ ሀሳብ ተቀባይነት ያለውና አንገብጋቢ ወቅታዊ ጉዳይ ቢሆንም አንድ መሰረታዊ ጉዳይ የተዘነጋ መሆኑን ግን ሳልጠቁም ማለፍ አልፈለግኩም። እርግጥ አቶ ግርማ ይዘነጉታል ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ እንዳይሆን ለማስታወስ ነው።
ዝርዝሩን ትቼ – የባህርዳሩን የጠሚ አብይን “ተደራጅታችሁ በምርጫ አሸንፉን – በደስታ ስልጣን እንለቅላችሇለን” የሚል ሀሳብ ተመርኩዘው በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ሃይሎች (በተለይ በቅርብ ከግፍ እስር የተፈቱትን) በቶሎ እንዲደራጁ አሳስበዋል። መልካም። ይህ የሚወደድ ሀሳብ ነው።
በኔበኩል ግን መሰባሰብ፣ መጠናከሩና መደራጀቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከሀገር ውጪ ያሉ አካላት እና በኤርትራ በረሃም ይሁን በሀገር ውስጥ በተለያየ ቦታ የሃይል ትግል ላይ ያሉ የነፃነት ታጋዮችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ድርድር እንዲደረግ ግፊት ማድረግ ወሳኝ እና ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ካለነዚህ ሃይሎች ተሳትፎ የሚኖር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማንም ጠቃሚነት ይኖረዋል ብዬ አላምንም። ምርጫም ይሁን ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ቀጥተኝ፣ ቀናነት የነገሰበት እና ሁሉን አካታች ካልሆነ አጠቃላይ ሂደቱ ተአማኒነት እና ቅቡልነት የሚኖረው አይሆንም።
ያብቻም ሳይሆን በርካቶች ተገፍተው ገለል የተደረጉበትን የፖለቲካ ሜዳ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስፈት የሚቻለው የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችን ባካተተ መልኩ ከገዢው ሃይል ጋር አስገዳጅ ድርድር ማድረግ ሲቻል ነው።
ባጠቃላይ በሀገር ውስጥ የተበተነው የለውጥ ሃይል ማሰባሰብና ማደራጀት፤ ተፎካካሪ ለመሆን ራስን ማዘጋጀት አስፈላጊና ወቅታዊ ቢሆንም በዚህ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የሚኖራቸው የተገፉ እና የትግል ስልት የቀየሩ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሀገር ተመልሰው መሳተፋቸው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ሊታወስና ሊታመንበት ይገባል። በተገኘው አጋጣሚና መንገድ ሁሉ ለገዢው አካል ማሳሰብና ጫና መሳደርም ከሁሉም ወገን ይጠበቃል።
መልካሙን ተመኘሁ
Filed in: Amharic