ትላንት
በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አመራር ሙያ (Business Administration) የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት በምማርበት ወቅት “Operation Management” የሚባለውን ኮርስ ያስተማረኝ አንድ የውቅሮ ተወላጅ የሆነ መምህር ነው። ይህ ስሙን የማልጠቅሰው መምህር የሞሶቦ ሲሚንቶ የገበያ ስትራቴጂን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የተናገረው ነገር መቼም ከአዕምሮዬ አይጠፋም። ነገሩ እንዲህ ነው፤ የሞሶቦ ሲሚንቶ በመቐለ ከተማ የሚሸጥበት ዋጋ በአዲስ አበባ ከሚሸጥበት ዋጋ በሁለት ብር ይበልጣል። በዚህ መሰረት የሞሶቦ ሲሚንቶ መቐለ ላይ 300 ብር የሚሸጥ ከሆነ ከፋብሪካው 700 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ አበባ ደግሞ 198 ብር ይሸጣል። ይህ “dumping” እንደሚባልና ሕገ-ወጥ ተግባር መሆኑን ስናገር መምህሩና የአከባቢው ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በሙሉ ¨No” በማለት በአንድ ድምፅ ተቃወሙኝ። ቀጠልኩና “እሺ.. የመቐለ ከተማ ሲሚንቶ ተጠቃሚዎች ያለ አግባብ በድርጅቱ እየተበዘበዙ ነው” ስላቸው አሁንም በአንድ ተቃወሙኝ። በመጨረሻም መምህሩ ያነሳሁትን ጥያቄ ሆነ ሃሳብ በሚያጣጥል መልኩ “ይህ የሞሶቦ ሲሚንቶ የገበያ ስልት (Market Strategy) ነው” በማለት በተግሳፅ ተናገረኝ።
በመሰረቱ የሲሚንቶ ፋብሪካ ምርቱን የሚሸጥበት ገበያ ከ300 ከ.ሜትር በላይ የሚርቅ መሆን እንደሌለበት የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ። ምክንያቱም ሲሚንቶ በባህሪው ከባድ (Bulky) ምርት ስለሆነ ከ300 ኪ.ሜ በላይ በትራንስፖርት አጓጉዞ መሸጥ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ይዳርጋል። ሞሶቦ ሲሚንቶ ግን ምርቱን በመኪና 700 ከ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲስ አበባ አምጥቶ መቐለ ላይ ከሚሸጥበት ዋጋ የሁለት ቅናሽ አድርጎ ይሸጣል። በዚህ መሰረት፣ አንደኛ፡- ሞሶቦ ሲሚንቶ ምርቱን አዲስ አበባ ድረስ ወስዶ የትራንስፖርት ወጪውን ሳይጨምር በሁለት ብር ቅናሽ መሸጡ በሕገ-ወጥ ተግባር እንደተሰማራ ያሳያል፣ ሁለተኛ፡- መቐለ ላይ ያለው የሞሶቦ ሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ከአዲስ አበባው የመሸጫ ዋጋ በሁለት ብር የሚበልጥ ከሆነ ድርጅቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ያለአግባብ እየበዘበዘ መሆኑን ያሳያል።
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ሞሶቦ ሲሚንቶ የሚከተለው የገበያ ስልት (Market Strategy) ከሕግም ሆነ ከቢዝነስ አንፃር ፍፁም የተሳሳተ ነው። ከሕግ አንፃር የሞሶቦ የገበያ ስልት ሌሎች የሰሚንቶ ፋብሪካዎችን ቀስ በቀስ ከገበያ በማስወጣት የምርቱን ገበያ በበላይነት ለመቆጣጠር ያለመ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአከባቢው ማህብረሰብ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ይበዘብዛል። እንዲህ ያለ የገበያ ስልት የድርጅቱን ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ይልቅ ለኪሳራ ይዳርገዋል። ይሁን እንጂ ነባር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከገበያ ከመውጣት ይልቅ ብዛት ያላቸው አዳዲስ ፋብሪካዎች ተከፈቱ። የሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካም በሚፈለገው ደረጃ ተወዳዳሪ ባይሆንም እንኳን በኪሳራ ምክንያት ከገበያ አልወጣም። ለምን?
አስታውሳለሁ… ደርባ ሲሚንቶ ወደ ገበያ በገባበት ወቅት በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ምርት እጥረት ተከስቶ ነበር። በተመሳሳይ በመቐለ ከተማ ነዋሪዎች የሲሚንቶ ምርት ለመግዛት ለብዙ ቀናት ወረፋ የሚጠብቁበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ ደርባ ሲሚንቶ ምርቱን በራሱ ትራንስፖርት ለመቐለ ከተማ ተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ ያስታወቀው። ይህን ተከትሎ አብዛኞቹ ሲሚንቶ ፈላጊዎች ከድርባ ሲሚንቶ ጋር የግዢ ስምምነት ማድረግ የጀመሩት። በዚህ ምክንያት በወረፋና በሰልፍ ሲንያንገላታቸው የነበረውን ሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዞር ብሎ የሚያየው ጠፋ።
ሞሶቦ የትእምት (EFFORT) አባል ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ዋና ስራ አስኪያጁ ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣን ነው። ይህ ባለስልጣን ለኢትዮጲያ ንግድ ባንክ መቐለ ቅርጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። ትዕዛዙም “በሞሶቦ ሲሚንቶ ላይ ፊታቸውን በማዞር ከደርባ ሲሚንቶ የግዢ ውል ለሚገቡ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች የባንክ ሲፒኦ (CPO) እንዳይሰጣቸው” የሚል ነበር። በዚህ መልኩ በህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጣልቃ-ገብነት ምክንያት ሞሶቦ ሲሚንቶ የተሳሳተና ሕገ ወጥ የሆነ የገበያ ስልቱን ይዞ እንዲቀጥል ያደርጉታል።
ስለዚህ እንደ ሞሶቦ ሲሚንቶ ያሉ የትእምት (EFFORT) ድርጅቶችን መውረስና ወደ ግል እንዲዘዋወሩ ማድረግ ምን ፋይዳ አለው?
- 1ኛ፡- የትእምት (EFFORT) ድርጅቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነት ለመቆጣጠር በሚከተሉት ስልት ምክንያት በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ማስወገድ ይቻላል። በዘርፉ የሚታየውን የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ያስቀራል። በመሆኑም በዘርፉ አዳዲስ የቢዝነስ ተቋማት እንዲሰማሩ ያስችላል። እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።
- 2ኛ፡- ድርጅቶቹ ወደ ግል ሲዘዋወሩ በምርት ዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን የገበያ ስልት ይቀይሳሉ። በመሆኑም ምርቶቻቸውን ለአከባቢው ማህብረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ስለሚሆኑ ለአከባቢው ማህብረሰብ ሆነ ለሀገሪቱ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራሉ።
- 3ኛ፡- የትእምት (EFFORT) ድርጅቶችን ወደ ግል በማዘዋወር መንግስት ገንዘብ ያገኛል። በዚህ መሰረት፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታ አስተዋፅ ከማበርከቱ በተጨማሪ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ከማረጋገጥ አንፃር የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል።
ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ መንግስት የትእምት (EFFORT) ድርጅቶችን በመውረስ ወደ ግል ባለሃብቶች ማዘዋወሩ የህወሓት ባለስልጣኖች እያገኙት ያለውን ያልተገባ ጥቅም ያስቀራል። እነዚህ ድርጅቶች ቢወረሱ የሚጎዱት የተወሰኑ የህወሓት አመራሮች እና አባላት ናቸው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን እንደ ክልል የትግራይ ሕዝብ ይጠቀማል፡፡ እንደ ሀገር ደግሞ ለኢትዮጲያ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል። ሌላው ቢቀር የህወሓትን አድሏዊ ድጋፍ፥ ማጭበርበርና ኪራይ ሰብሳቢነት ያስቀራል፡፡ በአጠቃላይ “EFFORTን” መውረስ ከሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥገኛ ተውሳክን እንደማስወገድ ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እስካሁን ባሉበት ሁኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ ከጥገኛ ተውሳክ የተለየ ሚና የላቸውም፡፡
በመጨረሻም፣ አንዳንድ የትግራይ ልሂቃን “የትእምት (EFFORT) ድርጅቶች የሚወረሱት በእኛ መቃብር ላይ ነው” የሚል አቋም የሚያራምዱበትን በተመለከተ ቀደም ሲል የጠቀስኩትን መምህርና ተማሪዎች ማስታወስ ይበቃል። እንኳን የትግራይ ሕዝብን ጥቅምና ተጠቃሚነት የሚማሩትን ሆነ የሚያስተምሩትን ፅንሰ-ሃሳብ መገንዘብ የተሳናቸው ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም።