>
5:13 pm - Saturday April 19, 6200

የወሎ ሙስሊምና ክርስቲያኖች ግንኙነት በዐጼ ዮሐንስ የማክፈር ዘመቻ ጊዜ፤ (ውብሸት ሙላት)

ከሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳዎች መካከል በአክሱም የሚኖሩ ሙስሊሞችና በዐጼ ዮሐንስ ዘመን በወሎ ሙስሊም አማሮች ላይ የተፈጸመው ግፍ ይገኙበታል፡፡
መቼም ዐጼ ዮሐንስ በወሎ ሙስሊም አማራዎች ላይ እንደፈጸሙት በደል ማንም ላይ አልፈጸሙም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ሙስሊሞችን በሚመለከት “የእስላም አገሩ መካ የወፍ አገሩ ዋርካ” የሚል ያልተጻፈ የተግባር ፖሊሲ ነበራቸው ይባላል፡፡ በመሆኑም ሙስሊሞችን ክርስቲያን ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን እውነት ነው ብሎ መቀበል አስቸጋሪ ነው፡፡ ለመቀበል የሚያዳግትበት ምክንያቱ ደግሞ የወሎ ሙስሊም አማራ ላይ የፈጸሙትን ግፍ ሙስሊም ትግራዋዮች ወይም አፋሮች ላይ አልፈጸሙም፡፡  ከዚህ አንጻር የተፈጸመውን ግፍ ረጋ ብሎ ላጤነ ሰው ስለምን ሙስሊም አማሮችን ብቻ ለማክፈር ፈለጉ ማለት አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ በዚያን የመከራ ዘመን ሙስሊምና ክርሰቲያን አማሮች ያደርጉት የነበረውን ትብብር የእኔን የአባቴን ቅድመ አያት ታሪክ ብቻ በማንሳት ልዘክር፡፡ የአባቴ ቅድመ አያት ግዛው ብርሌ ይባላሉ፡፡ በዐጼ ዮሐንስ ዘመን የነበሩ በአሁኑ አጠራር በደቡብ ወሎ ዞን በኩታበር ወረዳ ሩጋ አቦ አካባቢ ገዥ ነበሩ፡፡ በዚያ ክፉ ዘመን ለግዛው ብርሌም  ክፉ የንጉሠ ነገሥት ትዕዛዝ ደረሳቸው አሉ፣ሲወርድ ሲዋረድ እየተነገረን ያደግነው ታሪክ፡፡ ታሪኩ በቤተሰብ ብቻ የሚነገር ሳይሆን በአካባቢው ኗሪም የሚያውቀው ነው፡፡
ያቺ ክፉ የንጉሠ ነገሥት ትዕዛዝ በግዛታቸው ሥር የሚኖረውን ሙስሊም፣ ክርስቲያን እንዲያደርጉና ቦሩ ሜዳ ይዘው በመምጣት የክርስቲያን ሥጋ በማብላት ክርስቲያን መሆናቸውን (መክፈራቸውን) እንዲያረጋግጡ ነው፡፡ ይቺን የዐጼ ዮሐንስ  ቀጭን ትእዛዝ ግዛው ብርሌ እንዴት  እንደሚያደርጓት ጨነቃቸው አሉ፡፡ እሳቸው ካህን ቢሆኑም የሚያውቁት ሙስሊም እና  ክርስቲያንም አብሮ ተዋዶ፣ተፋቅሮ አብሮ በልቶ ጠጥቶ ሲኖር እንጂ አንዱ ሌላውን አስገድዶ ሲያሰልም ወይም ክርስቲያን ሲያደርግ አልነበረም፡፡
ግዛው ብርሌ  መፍትሔ ፍለጋ ማውጠንጠን ጀመሩ፡፡ እንዳይተውት  የንጉሥ ትእዛዝ ነው፡፡ አያስገድዱ ነገር አስገድዶ ክርስቲያን ማድረግ በራሱ ክርስቲያናዊ አይደለም፤በዚያ ላይ ለዘመናት  ኮሽ ሳይል አብረው የኖረ ሙስሊም ወገኖቻቸውን ነው አስገድዱ የተባሉት፡፡ ከዚያ ሕዝበ ሙስሊሙን ሰብስበው የንጉሠ ነገሥቱን ትዕዛዝ ነገሩ፡፡ እናም ምን እናድርግ ይላሉ፡፡ በግላቸው ይቺን ክፉ ትእዛዝ እንደማያምኑበት ለሕዝቡ አሳወቁ፡፡
ግዛው ብርሌ መፍትሔ ያሉትን አንድ ብልሃት አፈለቁ፡፡ ይሄንን የመፍትሔ ሐሳብ በልባቸው እንዲይዙ ሙስሊሞቹን ቃል አስገቡ፡፡ ቃልም ተገባ፡፡ ብልሃቱም፣ ማንኛውም ሙስሊም በኪሱ ዝግኒ (የበሰለና የተከተፈ ሥጋ) በኪሳቸው ይዘው በቀጠሮ ቀን ቦሩ ሜዳ መገኘት ብሎም የሚሰጣቸውን የክርስትና ስም በማስታወስ ስማቸውን መናገር ነው፡፡ ቦሩ ሜዳ ላይም ዝግኒ ሲሰጣቸው በመቀበል በሌላ በኪሳቸው   በማድረግ ከቤታቸው ይዘው የመጡትን ሥጋ መብላት ነው፡፡ በተባለውም መሠረት ተፈጸመ፡፡
ይኼ ተጠናቆ ወደየቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ሌላ ጭንቅ መጣ፡፡ ሲሞቱ መቀበር ያለባቸው ቤተክርስቲያን ነውና፡፡ ግዛው ብርሌ ለዚህም ሌላ ብልሃት አመጡ፡፡ ሙስሊም ሲሞት ቀን ላይ ሰንበሌጥን አስከሬን አስመስሎ በማዘጋጀት በይፋ ቀን ቀን ይቀብራሉ፡፡ ማታ ማታ ደግሞ እውነተኛውን አስከሬን በሟች የቅርብ ሰዎች በሙስሊም መቃብር ይቀበራል፡፡ ይህ የመቃብር ሥፍራ አሁንም ያለ ሲሆን ከላይ የሚታይ የመቃብር ምልክት የለውም፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ መቃብርነቱ ስለሚታወቅ አይታረስም፡፡
በዚያ የጭንቅ ወቅት ሌላም ነገር አስቸጋሪ ሆነ፡፡ በዚያን ዘመን እንዴት ዋላችሁ? እንዴት አደራችሁ? እንዴት አመሻችሁ? ሲባል እግዚአብሔር (እግዚሐር) ይመስገን ማለት ግድ ነው፡፡ ይህ ነገር በተለይ ለሼኮቹ ኅሊናን የሚፈታተን ሆነ፡፡ በዚህን ጊዜ ዐሊሞቹ መፍትሔ ዘየዱና ለቄስ ጓደኞቻቸው አማከሯቸው፡፡ ምክሩም ከዘጠና ዘጠኙ የአላህ (የፈጣሪ) ስሞች አንዱ አልዟሒር ነው፡፡ እናም እንዴት አደራችሁ/ዋላችሁ ሲባሉ እግዚሐር ይመስገን በሚለው ፋንታ አልዟሒር ይመስግን እንላለን አሏቸው፡፡ በዚህ የክርስቲያኑም የሙስሊሙም ጭንቀት መላ አገኘ፡፡ የዚያች  አካባቢው  ሙስሊም አማሮች ለንጉሥ ከሚያዋሽክ ሰውም ጭምር ተጠብቀው ያችን የጭንቅ ዘመን አለፏት፡፡
ስለግዛው ብርሌ ሲነሳ  እስካሁን ድረስ በሕዝቡ ዘንድ ከድርጊታቸው በተጨማሪ ሞታቸውም ይታወሳል፡፡ ለደጉ ለግዛው ብርሌ እንኳን ሰው ወፍ አልቅሷል ይባላል፡፡ ግዛው ሞተው ሊቀበሩ አስከሬኑ ከቤታቸው በግምት ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው ሩጋ አቦ (አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ) ቤተክርስቲያን ሲሄድ የጉዞ ጸሎተ ፍትሀት ይደረጋል፡፡ የተወሰነ ርቀት ከተጓዘ በኋላ አስከሬኑ አርፎ ጸሎት ይደረጋል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ሲጓዝ አጃቢው የሚወዳቸው ሙስሊምና ክርስቲያን ሕዝብ ብቻ አልነበረም፡፡ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ  ግሪሳ ወፍ አስከሬኑ ለፍትሃት የሚያርፈበት ቦታ ቀድሞ ያርፍና ለቀስተኛው ሲጠጋ ተነስቶ በመብረር ቀጥሎ ፍትሃት የሚደረግበት ቦታ ላይ ያርፋል ፡፡ በዚህ ሁኔታ ግሪሳው ወፍ አብሮ የግዛውን አስከሬን እየረበብ እየመራ ከዚያም እያረፈ አጅቦ ቤተክርስቲያን አደረሰ፡፡ በዚህም “ለግዛው እንኳን ሰው ወፍ አለቀሰ” ይባላል፡፡
መቼም ሙስሊም አማራ ላይ የደረሠው ግፍ ለከት የለውም፡፡ በዚያ ጭንቅ ውስጥም ሆነው ክርስቲያን አማራው ሙስሊም አማራ ወንድምና እህቱን እንዲህ በማድረግ ከግድያም ከማክፈርም ለመጠበቅ ጥሯል፡፡
Filed in: Amharic