>
5:18 pm - Thursday June 15, 9426

ሜይ ዴይ እና ካርል ማርክስ (ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

ሚያዚያ 23 ( May 1) በየዓመቱ የዓለም ሰራተኞች ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ቀን ሊታወስ የሚገባው ታላቅ ሰው ደግሞ ጀርመናዊው የዲያሌክቲክ ንድፈ-ሃሳብ ቀማሪ ካርል ሄንሪክ ማርክስ ነው፡፡ እነሆ ማርክስን ልንዘክረው ነው፡፡ ሜይ ዴይንም እናነሳዋለን፡፡

===ማርክስን በጨረፍታ==

ማርክስ ማን ነበር?. ሰፊ ባህር ነው ሰውዬው!! የደሃ ወዛደሮች አሰቃቂ ህይወት አዕምሮውን ቢበጠብጠው “መፍትሔው በሶሻሊስታዊ አብዮት የከበርቴውን መደብ ፈንቅሎ መጣል ነው” በማለት ያወጀ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮጳ ምንዱባን የህይወት ጠበቃ ነበር፡፡ በሰራተኛው መደብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ጭቆናና ግፍ ዓይነትና ብዛት፣ እንዲሁም ወደፊት በሰራተኛው መደብ መሪነት የሚመሰረተው ስልተ-ምርት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ ለማስረዳት Das Kpital የሚባለውን ዝነኛ መጽሐፍንም የጻፈ ልብ ብርቱ ጠቢብ ነው፡፡ ይህ ሰው በህግ የዶክትሬት ዲግሪ ነበረው፡፡ በሙያውና በጋዜጠኝነቱ በገነባው ትክለ ቁመና ሰፊ ገቢ ዝቆ የተንደላቀቀ ህይወት መኖር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ከራሱ ህይወት ይልቅ የሰራተኛው ሰቆቃ ነበር ሲያስጨንቀው የነበረው፡፡ በመሆኑም ለሰራተኛው ኑሮ መሻሻል መታገሉን መርጦ ዕድሜውን በሙሉ በድህነት እየተቆራመደ ኖሯል፡፡ ታዲያ ለነፍሲያው አንድም ነገር ጠብ ያላደረገለት ይህ የመከራ ህይወቱ የኋላ ኋላ የዓለምን ታሪክ ከስረ መሠረቱ ቀይሮታል፡፡

የማርክስ ዲያሌክቲካዊ ፍልስፍና የተዋቀረው “የመደብ ትግል” (class struggle) በሚል ዐቢይ አስተርዮ ዙሪያ ነው፡፡ በማርክስ አረዳድ መሠረት የሰው ልጅ ታሪክ የመደቦች ታሪክ ነው፡፡ ሰዎች ለብዙ ሺህ ዘመናት ሲጓዙበት የነበረው ሂደት ደግሞ “የመደብ ትግል” ይባላል፡፡ በያንዳንዱ ዘመን የሚኖር አንድ ህዝብ በመደቦች የተከፋፈለ ነው፡፡ ከነዚህ መደቦች መካከል አንደኛው ጨቋኝ ሲሆን ሌላኛው ተጨቋኝ ነው፡፡ ጨቋኙ መደብ ተጨቋኙን እንዳሻው ይገዛዋል፣ ይረግጠዋል፣ ሀብቱን ይቀማዋል፣ ጉልበቱን ይበዘብዘዋል፡፡ ተጨቋኙ መደብ እነዚህን ሁሉ እየቻለ ይገዛል፡፡ ጭቆናው ሲባባስ ግን ተጨቋኙ መደብ “እምቢ፣ አልገዛም” ማለት ይጀምራል፡፡ በዚህም የተነሳ በሁለቱ መደቦች መካከል ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ ጨቋኙ መደብ ተጨቋኙን ዝም ለማሰኘት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ቅራኔውን የበለጠ ያባብሱታል፡፡ በስተመጨረሻም ተጨቋኙ መደብ በገዥው ላይ ያምጽና ስልጣን ይቆጣጠራል፡፡ በዚህም መንገድ ድሮ የነበረው ስልተ ምርት (ስርዓተ ማህበር) በአዲስ ስልተ ምርት ይተካል፡፡

በማርክስ ትንታኔ መሠረት እስከ 1850ዎቹ ድረስ በነበረው ጊዜ በምድር ላይ አራት ስርዓተ ማህበሮች ታይተዋል፡፡ እነዚህም የጥንታዊ ጋርዮሽ ስርዓ ማህበር፣ የባሪያ አሳዳሪ ስርዓተ ማህበር፣ የፊውዳል ስርዓተ ማህበርና የካፒታሊዝም ስርዓተ ማህበር ናቸው፡፡ በ1850ዎቹ በርካታ የአውሮጳ ሀገራት በካፒታሊዝም ውስጥ ነበሩ፡፡ በዚህ ስርዓተ ማህበር ያሉት ሁለት መደቦች የከበርቴው መደብ እና የሰራተኛው መደብ ናቸው፡፡ በሁለቱ መደቦች መካከል ሃይለኛ ፍጥጫና ቅራኔ ነበር፡፡ ማርክስ በሁለቱ መካከል የነበረውን ግብግብ የወደፊት አቅጣጫ ሲተነብይ እንዲህ ነበር ያለው፡፡

“በሰራተኛው እና በከበርቴው መካከል ያለው ቅራኔ እየተካረረ ሲሄድ ሰራተኛው የባርነት ቀንበሩን ጥሎ የራሱን ነጻ መንግሥት ማወጁ አይቀርም”

ማርክስ የሰራተኛው መደብ ድል የሚቀዳጅበትን መንገድ ሲገልጽ “የስራ ማቆም አድማ መምታት፣ ተጨማሪ መብቶችን መጠየቅ፣ የከበርቴው መደብ የሚያወጣቸውን ደምቦች እምቢ ማለት፣ የከበርቴዎች ጠበቃ የሆነውን መንግሥት አለመታዘዝ፣ በመጨረሻም ሁሉን አቀፍ አብዮት በማካሄድ የመንግሥትን ስልጣን መቆጣጠር” በማለት አስረድቷል፡፡

በሰራተኛው መደብ መሪነት የሚመሠረተው አዲሱ ስርዓተ ማህበር “ሶሻሊዝም” ይባላል፡፡ በዚህ ስርዓተ ማህበር ስልጣኑን የሚይዘው የሰራተኛው መደብ ነው፡፡ ይሁንና የሰራተኛው መደብ መንግሥቱን ካደላደለ በኋላ በመጣበት መንገድ አይቀጥልም፡፡ ማንም ሊፈጽመው የማይችለውን አንድ ታላቅ ትንቢት ተፈጻሚ እንዲያደርግ ታሪካዊ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህም “መደብ” የሚባለውን የማህበረሰብ ክፍፍል ማጥፋትና እጅግ የላቀ አዲስ ስርዓተ ማህበር መፍጠር ነው፡፡

በዚህ መንገድ የሚመሠረተው ስርዓተ ማህበር “ኮምዩኒዝም” ይባላል፡፡ የዚህ ስርዓት መለያዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛ ስርዓቱ “መደብ አልባ” ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ጨቋኝም ሆነ ተጨቋኝ የሉም፡፡ ሁለተኛ ስርዓቱ መንግሥት አልባ ነው፡፡ መንግሥት የሚያስፈልገው መደቦች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ኮሚኒዝም ግን መደብ አልባ ስርዓት በመሆኑ መንግሥት አያስፈልገውም፡፡ ህግ፣ ደምብ፣ አዋጅ፣ ድንጋጌ፣ መመሪያ፣ ፓርላማ፣ ምርጫ፣ ወዘተ… የሚባሉት አሰራሮች ሁሉ ይጠፋሉ፡፡

የታላቁ ሶሻሊስት ታላቁ ትንቢት ይህ ነው፡፡ የዲያሌክቲኩ የመጨረሻ ጥግም ይህ ነው፡፡ የማርክስ ትንቢት ግብ በሰራተኛው መደብ ላይ ሲደርስ የነበረው ጭቆና ተወግዶ ማየት ነው፡፡ ይህ የሚቻለው ደግሞ የሰራተኛው መደብ ስልጣን ሲቆጣጠር ነው፡፡

==ከማርክስ በኋላ== 

ማርክስ ከሞተ በኋላ በርሱ ስም የሚምሉ ፈላስፋዎችና ፖለቲከኞች ተነስተዋል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ራሳቸውን በርእሰ ብሄርነት ከሰየሙ በኋላም “ማርክሲዝምን መሥርተናል” ብለዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ማርክሲስት ነን ባዮችና የማርክስ ትንቢት በጣም ነው የሚራራቁት፡፡ ለምሳሌ ከማርክስ ሞት በኋላ የተቋቋሙት የኮሚኒስት ንቅናቄዎችና በብዙ ሀገራት የተካሄዱት የሶሻሊስት አብዮቶች የተመሩት በሰራተኛው መደብ ሳይሆን በንዑስ ከበርቴውና በወታደሩ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም ስለርሱ ይለፍፉ የነበሩት አመራሮች ሁሉ ማርክሳዊያን ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል ማርክስ ከጥንታዊው ጋርዮሽ ጀምሮ እስከ ሶሻሊዝም ያሉት ስርዓቶች በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ እየተተካኩ እንደሚሄዱ ነበር የጻፈው፡፡ በርሱ ግንዛቤ መሰረት በፊውዳሊዝም ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ወደ ሶሻሊዝም ለመድረስ ካሻው በቅድሚያ በካፒታሊዝም ውስጥ ማለፍ ይገባዋል፡፡ ካፒታሊዝምን ሳይመሠርቱ ከፊውዳሊዝም በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም ለማለፍ አይቻልም፡፡ ይሁንና በማርክስ ስም ከተካሄዱት አብዮቶች መካከል አንዳቸውም በዚህ ሂደት ውስጥ አላለፉም፡፡ ሁላቸውም ከፊውዳሊዝም በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም ለማለፍ ነው የሞከሩት፡፡ በመሆኑም ነው የማርክስ ንድፈ-ሃሳብ አዋጭነት በትክክል አልተፈተነም የሚባለው፡፡

የማርክስ ንድፈ-ሃሳብ ከአሁኑ ዘመን ጋር ያለው ተዛምዶ ሲፈተሽ ግን ብዙም ላያስኬድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ከሰራተኛው ጉልበት ይልቅ የማሽን እና የሮቦት ጉልበቶች በምርት ሂደት ውስጥ ያላቸው አስፈላጊነት በጣም ጎልብቷልና፡፡ ማርክስ የተከራከረላቸው የፍትሐዊነትና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ግን ዛሬም ድረስ ህያው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በልዩ ልዩ ሀገራት የኢኮኖሚ ቀውስ በሚያጋጥምበት ጊዜ ማርክሳዊ እይታ ያላቸው ምሁራን ከትንታኔና ከመፍትሔ ሃሳቦች ጋር በየመድረኩ ላይ ብቅ የሚሉት፡፡

==የማርክስ ስራዎች==

ካርል ማርክስ የብዙ ታላላቅ ስራዎች ባለቤት ነው፡፡ ከስራዎቹ ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ግን “Das Kapital” ነው፡፡ ማርክስ ይህንን መጽሐፍ ያዘጋጀው በሶስት ቅጾች ቢሆንም እርሱ በህይወት እያለ ለኅትመት የበቃው የመጀመሪያው ቅጽ ብቻ ነው፡፡ ሁለቱ ቅጾች ከእርሱ እልፈት በኋላ የምንጊዜም ታማኝ ጓደኛው በነበረው ፍሬድሬክ ኤንግልስ ነው የታተሙት፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በሀገራችንም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅጾች በአማርኛ ተተርጉመዋል፡፡

የማርክስ ታላቅ ስራ የሆነው “ዳስ ካፒታል” በውስጠ ይዘቱ ምን ይመስላል? በዚህ ጽሑፍ አቅም ለመመለስ አይቻልም፡፡ ሆኖም ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ በዚህ ዙሪያ ከጻፈው ትንሽ ቀንጨብ ብናደርግ ስለመጽሐፉ በመጠኑ ሊያስረዳ ይችላል፡፡

“Marx’s masterpiece, Das Kapital, the “Bible of the working class,” as it was officially described in a resolution of the International Working Men’s Association, was published in 1867 in Berlin and received a second edition in 1873. Only the first volume was completed and published in Marx’s lifetime. The second and third volumes, unfinished by Marx, were edited by Engels and published in 1885 and 1894. The economic categories he employed were those of the classical British economics of David Ricardo; but Marx used them in accordance with his dialectical method to argue that bourgeois society, like every social organism, must follow its inevitable path of development. Through the working of such immanent tendencies as the declining rate of profit, capitalism would die and be replaced by another, higher, society. The most memorable pages in Das Kapital are the descriptive passages, culled from Parliamentary Blue Books, on the misery of the English working class. Marx believed that this misery would increase, while at the same time the monopoly of capital would become a fetter upon production until finally “the knell of capitalist private property sounds. The expropriators are expropriated.”

ከማርክስ ስራዎች መካከል በዓለም ዙሪያ በስፋት የተሰራጨው ደግሞ “የኮሚኒስት ፓርቲ ማኒፌስቶ” የተሰኘው ጥራዝ ነው፡፡ ማርክስ ይህንን ስራ ያዘጋጀው ከኤንግልስ ጋራ በመተባበር ሲሆን በጊዜው በመቋቋም ሂደት ላይ የነበረ Communist League የተሰኘ ህቡእ ማህበር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው የተጻፈው፡፡ “የሁሉም ሀገር ሰራተኞች ተባበሩ” የሚለው ዝነኛ የኮሚኒስቶች መፈክር የተወሰደው ከዚህ ታዋቂ ጥራዝ የመጨረሻ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡

=== ሜይ ዴይ==

May 1 (ሚያዚያ 23) የሰራተኞች ቀን ሆኖ መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1889 ነው፡፡ ይህም ካርል ማርክስ ከሞተ ከስድስት ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው (ማርክስ የኖረው ከ1818 እስከ 1883 ነው)፡፡ ይሁንና ለዕለቱ መከበር ዐቢይ መነሻ የሆነው ማርክስ ከታገላለቸው ግንባር ቀደም የሰራተኛው መደብ ጥያቄዎች አንዱ የሆነው የስምንት ሰዓት የስራ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ዕለት ከሌሎች የዓመቱ ቀናት ተመራጭ የሆነው ደግሞ በሰራተኛው መደብ ትግል ውስጥ የማይረሳ አጋጣሚ የተፈጠረበት በመሆኑ ነው፡፡ ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡፡

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሶሻሊስቶች ሲያነሱት የነበረው የስምንት ሰዓት የስራ ጊዜ በበርካታ የአውሮጳ ሀገራትና በአሜሪካ ግዛቶች ተከታታይ የስራ ማቆም አድማዎች እንዲጠሩ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ የየሀገራቱ መንግሥታት ጥያቄውን ለረጅም ጊዜ ሲገፉት ቆይተዋል፡፡ በሜይ 1 ቀን 1867 ግን የአሜሪካዋ አሊኖይ ግዛት መንግሥት ለጥያቄው ህጋዊ እውቅና ሰጠ፡፡ ሆኖም ይህ መብት ለሃያ ዓመታት ያህል ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም፡፡ የዚህም ምክንያት የዘመኑ የኢንዱስትሪ ከበርቴዎች መብቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚጠይቁ ሰራተኞችን ከስራ የሚያባርሩ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም ሰራተኛው የስራ ዋስትና ላለማጣት ሲል ለረጅም የስራ ሰዓታት በፋብሪካዎች መስራቱን ቀጥሏል፡፡

በሜይ ወር 1886 ግን ታሪካዊ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ በዚህ ዕለት በቺካጎ ከተማ የሚገኘው የማኮርሚክ የእርሻ ማሽነሪዎች ፋብሪካ ሰራተኞች የስራ ጊዜን በስምንት ሰዓት የሚገድበው መብት ተፈጻሚ እንዲሆን ለመጠየቅ ከሜይ 1-4/1886 የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ጠሩ፡፡ ብዙሃኑ ሰራተኞችም የአድማው ተሳታፊ ሆኑ፡፡ በሶስተኛው ቀን (ሜይ 3/1886 ) ግን ከሰራተኞቹ መካከል አድማውን የሚቃወም ቡድን ተፈጠረ፡፡ የቺካጎ ፖሊስ የአድማውን ተቃዋሚዎች ከብዙሃኑ ሰራተኞች ለመከላከል በሚል ባደረገው ጣልቃ ገብነት የስድስት ሰራተኞች ህይወት ጠፋ፡፡ ይህም ብዙሃኑን ሰራተኞችና የሰራተኛው መደብ ደጋፊዎችን አበሳጫቸው፡፡

ሰራተኞችና ግራ ዘመም ደጋፊዎቻቸው በተከታዩ ቀን (May 4/1886) የፖሊስን የጭካኔ እርምጃ የሚቃወም ሰልፍ ጠሩ፡፡ ሰልፉም በከተማዋ እምብርት ላይ በሚገኘው የሄይማርኬት አደባባይ (Haymarket Square) መካሄድ ጀመረ፡፡ በርካታ የሰራተኛ መደብ መሪዎች ሲደርስባቸው የነበረውን የጉልበት ብዝበዛ እየተነተኑ ተናገሩ፡፡ በፖሊስ የተወሰደውንም ጥቃት አወገዙ፡፡ ሰራተኞችም የመሪዎቻቸውን ቁጭት በጭብጨባና በመፈክሮች እያጀቡ አስተጋቡት፡፡ ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱን ቀጠለ፡፡ ከሰዓት በኋላ ግን ያልታወቀ ሰው በሰልፈኞቹ ዙሪያ በነበሩት ፖሊሶች ላይ ቦምብ በመወርወር ሰባት ፖሊሶችን ገደለ፡፡

በዚህ እርምጃ የከበርቴው ወገንና ደጋፊዎቻቸው በጣም ተቆጡ፡፡ የአሜሪካ ጋዜጦች ወሬውን እየተቀባበሉ የሰራተኛ መብት ታጋዮችን አብጠለጠሏቸው፡፡ “ከአውሮጳ (በተለይም ከጀርመን) የመጡ ሶሻሊስቶች ሀገራችንን ሊበጠብጧት ነው” እያሉ ነገሩን አሟሟቁት፡፡ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች “የአሜሪካን አንድነት ለመናድ በሚፈልጉት ሶሻሊስቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ይወሰድ” እያሉ ወተወቱ፡፡ ቦምቡን የወረወረ አካል ማንነት እስከ አሁን ድረስ ተለይቶ አልታወቀም፡፡ የታሪክ ምሁራን ግን የቺካጎ ከተማ ከበርቴዎች በላኳቸው ቅጥረኞች እንደተወረወረ ይጠረጥራሉ፡፡

የወቅቱ የኢሊኖይ ግዛት መንግሥት “ወንጀለኞቹን በነጻ ፍርድ ቤት እቀጣቸዋለሁ” በማለት ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እርሱም እንደ ከበርቴዎቹ ጣቱን የቀሰረው በሶሻሊስቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ኦገስት ስፓይስ” የሚባለውን የሰራተኛ መብት ታጋይና የጋዜጣ አዘጋጅን ጨምሮ ስምንት ሰዎችን ተጠያቂ በማድረግ ፍርድ ቤት አቀረባቸው፡፡ የታሪክ ምሁራን እንዳስረዱት ከነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በተጠቀሰው ዕለት በሄይማርኬት አደባባይ አልነበሩም፡፡ ኦገስት ስፓይስም በሰልፉ ላይ ንግግር ካደረገ በኋላ በጊዜ ከአካባቢው ሄዶ ነበር፡፡ በመሆኑም ሰዎቹ የተወነጀሉት የግራ ዘመም ርዕዮት አራማጆች ስለነበሩ ብቻ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ የስምንቱን ሰዎች ጉዳይ ለአንድ ዓመት ካንከባለለው በኋላ ኦገስት ስፓይስን ጨምሮ አምስት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ወሰነ፡፡ በሦሥት ሰዎች ላይ ደግሞ የእስር ቅጣት ተበየነ፡፡ ከአምስቱ ሰዎች መካከል አንዱ በእስር ላይ እያለ ህይወቱን አጠፋ፡፡ አራቱ ሰዎች ግን November 11/1887 በስቅላት ተገደሉ፡፡

ይህ ፍርድ ገምድል ውሳኔ የሰራተኛው መደብ ለመብቱ የሚያደርገውን ትግል የበለጠ እንዲያቀጣጥል አደረገው፡፡ በርካታ የአውሮጳ ሀገራትና አሜሪካ በስራ ማቆም አድማዎችና በሶሻሊስቶች ሰልፍ ተመቱ፡፡ በ1889 ደግሞ Second International የሚባለው የሶሻሊስት ፓርቲዎችና የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ዓለም አቀፍ ማህበር የቺካጎው አድማ የተጠራበት May 1 (ሚያዚያ 23) የሰራተኛው ቀን ሆኖ እንዲከበር ወሰነ፡፡ የሩሲያ አብዮተኞች በጥቅምት 1917 የዛሩን መንግሥት አስወግደው የሶቪየት ሶሻሊስቶች መንግሥትን ሲመሠርቱ ደግሞ “ሜይ ዴይ” የሶሻሊዝም ዐርማ እና የሠራተኞች አንድነት ምልክት ሆኖ ታወጀ፡፡ ከሁሉም በዓላት በላቀ ደረጃ እንዲከበርም ተወሰነ፡፡ ሌሎች ሶሻሊስት ሀገራትም ይህንኑ ደምብ በስራ ላይ አዋሉ፡፡

የሶቪየት ህብረት መንግሥት በ1991 ፈርሷል፡፡ ሩሲያም ኮሚኒዝምን እርግፍ አድርጋ በመተው በዲሞክራሲ የሚመራ የመንግሥት ፍልስፍናን ተከትላለች፡፡ እርሱን ይከተሉ የነበሩ በርካታ ሀገራትም የፖለቲካ ፍኖታቸውን ለውጠዋል፡፡ ሆኖም ዛሬም ሜይ ዴይ በብዙ ሀገራት የሰራተኞች ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡

==ብቸኛው ሶሻሊዝም=

ከላይ እንደጠቀስኩት በ1917 የተካሄደው የሩሲያው የጥቅምት አብዮትም ሆነ ከርሱ በኋላ የመጡት የሶሻሊስት አብዮቶች በሙሉ ካርል ማርክስ በ“ኮሚኒስት ማኒፌስቶ” እና በDas Kapital የጻፋቸውን ንድፈ-ሃሳቦች ተከትለው የተካሄዱ አልነበሩም፡፡ በማርክስ እይታ መሰረት ወደ ሶሻሊዝም የሚያስገባው መንገድ በከበርቴውና በወዝ አደሩ መካከል ያለው ቅራኔ ሲካረር የሚፈጠረው አብዮት ነው፡፡ ይህም አብዮት ያለማንም ጣልቃ ገብነትና አነሳሽነት በሰራተኛው መደብ ብቻ ይመራ ዘንድ የተገባ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ1871 የተካሄደው ዝነኛው የፓሪስ ኮሚዩን (Paris Commune) በማርክስ አንደበት “ትክክለኛ የወዝ አደሩ መደብ ንቅናቄ” ተብሎ ተወድሷል፡፡ ይህ የፓሪስ ኮሚዩን ከ71 ቀናት በኋላ በከበርቴው ሃይል ተጨፍልቆ ሲደመሰስ ማርክስ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

History has no comparable example of such greatness. Its martyrs are enshrined forever in the great heart of the working class.

የፓሪስ ኮምዩን በሁለት ወራት ቢቀጭም በዓለም ሶሻሊስቶች ዘንድ የማነቃቂያ መንፈስ ሆኖ ሲያገለግል ከርሟል፡፡ በዚህም ንቅናቄ ወቅት ነው የዓለም ሶሻሊስቶች ህብረ-ዝማሬ ሆኖ የሚያገለግለው “ኢንተርናሲዮናል” የተጻፈው፡፡ እኔም ጽሑፌን የማሳርገው በፕሮፌሰር አሰፋ ገብረማሪያም አማካኝነት ወደ አማርኛ የተተረጎመውን የኢንተርናሲዮናልን ግጥም በመጋበዝ ይሆናል፡፡

ተነሱ እናንተ የረሃብ እስረኞች
ተነሱ የምድር ጎስቋሎች
ፍትሕ በሚገባ ይበየናል
ሻል ያለ ዓለምም ይታያል፡፡

ከእንግዲህ ባለፈው ይብቃን እስር
ተነሱ ባሮች ጣሉ ቀንበር
የዓለም መሰረት አዲስ ይሁን
ኢሚንት ነን እልፍ እንሁን፡፡

የፍጻሜው ጦርነት ነው
ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው
የሰው ዘር በሙሉ
ወዛደር ይሆናሉ

የፍጻሜው ጦርነት ነው
ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው
ኢንተርናሲዮናል
በዓለም ይሆናል!!
—-
(ኢንተርናሲዮናል በግጥሙ እንደየ ቋንቋው ቢለያይም በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ዜማ ነው የሚዘመረው፡፡ ዜማውን ለመስማት የሚከተለውን የዩ-ቲዩብ ማስፈንጠሪያ/link ይጫኑ)፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=UXKr4HSPHT8&spfreload=10
——
አፈንዲ ሙተቂ
• መጀመሪያ ሚያዚያ 23/2007 ተጻፈ፡፡
• እንደገና ተሻሽሎ ሚያዚያ 23/2008 ተጻፈ፡፡
(ሀረር – ምሥራቅ ኢትዮጵያ)

Filed in: Amharic