>
5:33 pm - Saturday December 5, 3046

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዘነጋቸው የቤት ሠራተኞችና መብቶቻው፤ (ውብሸት ሙላት)

በኢትዮጵያ የሠራተኞች ቀንም የማያስታውሳቸው፤

በኢትዮጵ የወራት እና ቀናት አቆጣጠር ሚያዚያ 23 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠራተኞች ቀን የሚከበርበት ነው፡፡ ይህ ዕለት በጥንት አዋማዊ አውሮፓውያን ዘንድ የበጋው መንፈቅ አንድ ብሎ የሚጀምርበት ስለሆነ የፈንጠዝያ ቀናቸው ነበር፡፡ ‘ሜይ ዴይ’ ብለውም ይጠሩታል፡፡ ከሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም መምጣት በኋላ ግን ይህ ዕለት ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (International Workers’ Day) ሆነ፡፡
በመሆኑም የሠራተኛው መደብ በዓል የሚያደርግበት፣የሚያርፈበት ሆነ፡፡ ‘ስምንት ሰዓት ለሥራ፣ስምንት ሰዓት ለመዝናኛ፣ስምንት ሰዓት ለማረፊያ’ የሚለውንም ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግም አስተዋጽኦ ስላለው ለሠራተኛው የድል ቀን ነው፡፡ በርካታ አገራት ከዚህ በተጨማሪ የሥራ ቀን (Labour Day) ብለውም ከብራሉ፡፡ ዕለቱ ግን ሚያዚያ 23 አይደለም፡፡
ይህ ቀን ሁሉንም ሠራተኛ የሚመለከት ነው፡፡ በኢትዮጵያም እንደሌሎቹ አገራት ሁሉ ዕለቱ ያው መከበሩ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ቀን ለበርካታ ሠራተኛ እንደ ድል ቀን ቢቆጠርም በኢትዮጵያ ግን አሁንም ለዚህ ድል ያልታደሉ፣ የማይታደሙ፣ የሌሎቹ ድል ድላቸው ያልሆነላቸው የሠራተኛ ክፍሎች አሉ፡፡ የእነሱም ጭምር ይሆን ዘንድ፣ ‘የእኛም ቀን ነው’ የሚያስብል ጥበቃ አልተደረገላቸውምና፡፡ እነዚህም በዋናነት የቤት ሠራተኞች ናቸው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የቤት ሠራተኞች በሚመለከት ያሉትን ሕጎች በመዳሰስ ለወደፊት ምን መሆን እንዳለበት ማመልከት ነው፡፡
የቤት ሠራተኛ 
የቤት ሠራተኛ መቅጠር በአገራችንም ይሁን በየትም፣ጥንትም የነበረ ልማድ ነው፡፡ የተለያዩ የቤት ውስጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎችን በግዥ ወይንም በቅጥር መያዝ የተለመደ ነው፡፡ በግዥ የሚፈጸመውን በሕግም በተግባርም ማስቀረት ቢቻልም በቅጥር የቤት ሥራ ማሠራትን ግን በአግባቡ ፈር ማስያዝ ላይ በርካታ አገራት ዳተኞች እንደሆኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት ጥረቶች፣ የቤት ሠራተኛ የሚባል ይቀር ሳይሆን በተገቢው ሁኔታ መብታቸው ይጠበቅ፤ የአሠሪዎችም መብትና ግዴታዎችም ተለይተው  ይታወቁ፤ የሚል አዝማሚያ ነው ያለው፡፡
የቤት ሠራተኛ የሚባሉት ከአሠሪው ጋር በመኖር አልበበለዚያም በተመላላሽነት የተለያዩ የቤት ሥራዎችን የሚያከናውኑት ግለሰቦችን ይመለከታል፡፡ ስለሆነም፣ምግብ የሚዘጋጁ፣ልብስ የሚያጥቡ፣ ቤት የሚያጸዱና የሚጠብቁ፣ሕጻናቶችን እና አቅመ ደካሞችን የሚንከባከቡ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከሚሠጡት ግልጋሎት እና ከሥራቸው ባሕርይ አንጻር ቤተሰባዊ ሁኔታ አለበት፡፡ ግንኙነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ታማኝነትን እና መቀራረብን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት የሚመለከቱ ሕጎች ሲወጡ ይሄንን ሁኔታም ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡
ከጾታ አንጻር ሲታይ የቤት ሠራተኞች በአብዝኃኛው ሴቶች ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እነኳን  85 በመቶ ገደማ ሴቶች መሆናቸውን በጥናት የተረጋገጠ ነው፡፡ በተለያዩ አገራት በመጓዝም ስለሚሠሩ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦቸውም ከፍተኛ ነው፤ቢያንስ ወደ አገራቸው ገቢ በመላክ፡፡
ይሁን እንጂ የተሰጣቸው ዕውቅናና ጥበቃ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ እንደ መደበኛ ሥራም አይቆጠርም፡፡ የቅጥር ሁኔታው እንኳን በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ወይንም እንደሌሎች ሠራተኞች ጥበቃ አያደርግላቸውም፡፡ የመብት ጥሰቱ የበረታ መሆኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጥናቶች ለዚህ አስረጂ ናቸው፡፡ መብታቸውን መጋፋት ሲጠናም በጭራሽ የሠራተኛ መብት እንደሌላቸው መውሰድ የተለመደ ነው፡፡
አድልኦ መፈጸም፣ደመወዝ አለመክፈል፣ዕረፍት አለመስጠት፣ለጾታዊ ጥቃት መጋለጥ የቤት ሠራተኞች የኑሯቸው አካል ነው፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ስደት እና ስደትን ተከትሎ ለሚመጡ ችግሮች  እንዲሁ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ይህንን ችግር በመገንዘብ ዓለም አቀፉ ሥራ ድርጅት አገራት ተቀብለው ይተገብሩት ዘንድ አንድ ስምምነት ከስድስት ዓመታት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡ እ.አ.አ. ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮም በሥራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬ መቶ ዓመታት ገደማ ድርጅቱ ሲቋቋም ከነበሩት መሥራቾች አንዷ ብትሆንም፣ እጅግ በርካታ የቤት ሠራተኞችን በአገር ውስጥም ይሁን ወደሌላ አገር ብትልክም ስምምነቱን ለማጽደቅ አለከጀለችም፡፡ ሌላ እዚህ ግባ የሚባል ሕግም አላወጣችም፡፡ ለቤት ሠራተኞች ጭምር የሚሆኑትን የሕግ ማዕቀፎች ከሕገ መንግሥቱ በመጀመር እንመለከታቸው፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፉ
ሕገ መንግሥቱ በተናጠል ስለ ቤት ሠራተኞች ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም፡፡ እንዲኖርም አይጠበቅም፡፡ በአጠቃላይ ሠራተኞችን ከሚመለከቱት አንቀጾች መካከል ስለ ግል ሠራተኞችም የሚሆኑ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ እነዚህንም በሦስት በመክፈል እንመልከታቸው፡፡
የመጀመሪያው እንደማንኛውም ሠራተኛ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችን ይመለከታል፡፡ የግል ሠራተኞች እንደማንኛው አገልግሎት እንደሚሠጥ እና እንደ አንድ ዘርፍ (ወይንም እንደሥራው ዓይነት) የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ በማኅበራቸውም አማካይነት ጥቅሞቻቸውን እና መብቶቻቸውን ከአሠሪዎች ጋር በመደራደር በተሻለ ሁኔታ ሊስከብሩ ይችላሉ፡፡ ይህንን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 መረዳት ይቻላል፡፡
ይህንን መብት ለማረጋገጥ ደግሞ ሌላ ዝርዘር ሕግ ሊኖር እንደሚገባ ከዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መረዳት ይቻላል፡፡ በምን መልኩ እና ሥርዓት መደራጀት ብሎም መደራደር እንደሚችሉ በሕግ ሊገለጽ ይገባል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ የሚተዳደሩት ሠራተኞችን ከዚህ አንጻር ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም የግል ሠራተኞችም እንደማንኛውም ሠራተኛ ሁሉ የሥራ ሠዓታቸው ውስን መሆን አለበት፡፡
የተለያዩ ዓይነት ዕረፍቶችን የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ለምሳሌ የወሊድ፣የሕመም፣የሳምንት፣የበዓል፣የዓመት ዕረፍትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም የሚሠሩበትን ቦታ እና ሁኔታ ጤናማ እና አደጋ የማያስከትልም መሆን አለበት፡፡ እነዚህ እንግዲህ በአንቀጽ 42 ላይ የምናገኛቸው ናቸው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ አብዝኃኛውን ቁጥር የሚይዙት የግል ሠራተኞች ሴቶች ስለሆኑ በሴትነታቸው ያላቸው መብቶች እና ተጨማሪ ድጋፎች ናቸው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 በተለይ ስለሴት የቤት ሠራተኞችም ጭምር የሚሆኑ በርካታ መብቶችን አካትቷል፡፡ መንግሥት፣ ሴቶች በበታችነት እና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ጠባሳ እንዲታረምላቸው የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ጨቋኝ ከሆኑ ልማዶች እና ሕጎች እንዲላቀቁ ብሎም በአካላቸውም ሆነ በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ማድረግ አለበት፡፡ የወሊድ እና የእርግዝና ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ሊሠጣቸው እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ የቤት ሠራተኞች ግን የወሊድ ፈቃድ መጠን የሚገለጸው ደግሞ በሌላ ሕግ ስለሆነ እና እነሱን የሚመለከት ሕግ ስለሌለ እንደሌሎች ሠራተኞች የሚሠጣቸው የወሊድ ፈቃድ የለም፡፡ በሌላ አገላለጽ አሠሪው የወሊድ ፈቃድ እንዲሠጥ የሚስገድደው ሕግ የለም፡፡
ሦስተኛው፣ መብት እንኳን ባይሆኑም መንግሥት ሠራተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በሚመለከት ሊከተለው የሚገባ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ነክ ዓላማዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በአንቀጽ 89 መሠረት መንግሥት ሠራተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጤንነቱና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ የኑሮ ደረጃው እንዲሻሻል የሚያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል አለበት፡፡ ይህንንም ለማሟላት መጣር አለበት፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሠራተኞችም ጤንነታቸው የሚጠበቅበት፣አካላዊና አዕምሯዊ ደኅንነታቸው ጉዳት እንዳይደርስበት ከደረሰም የሚታረምበትና የሚካሱበትን ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡
የኑሮ ድረጃቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሕጋዊ ማዕቀፍ ያስፈልጋቸዋልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከላይ ከተገለጸው አንቀጽ ቀጥሎ  የምናገው የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን የዜጎች ጤንነት እና ማኅበራዊ ዋስትና የሚሻሻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባት እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ የቤት ሠራተኞችን ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ እና ከማሕበራዊ ዋስትና ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት የለም፡፡ በመሆኑም በሥራቸው ምክንያት እኩል ጥበቃና እና ዋስትና አላገኙም ብሎ መደምደም ብዙም የሚያከራክር አይደለም፡፡
የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለ ቤት ሠራተኞች
በ1952 ዓ.ም.የወጣው እና አሁንም በሥራ ላይ ያለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ከአንቀጽ 2601 እስከ 2604 ድረስ ከቀጣሪው ጋር አብሮ ስለሚኖሩ የየቤት ሠራተኞች የተወሱ ጉዳዮችን ሕጋዊ መሠረት አስይዟል፡፡ እነዚህ አንቀጾች ሠራተኛው ከቀጣሪው ጋር በመኖር የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን ሲባል የሚደረግ ውልን የሚመለከቱ እንጂ በተመላላሽነት ወይንም ሠራተኞቹ በራሳቸው መኖሪያ እየኖሩ ነገር ግን የተወሰነ ሠዓት ሥራ የሚሠሩትን አይመለከትም፡፡
የድንጋጌዎቹም ርዕስ “በቤተሰብ አስተዳር ውስጥ ስለሚኖር አሽከር የሥራ ውል” የሚል ነው፡፡ በአንቀጾቹ ውስጥ ሠራተኞው ‘አሽከር’ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን የቅጥር ውሉም ‘የአሽከርነት ውል’ ነው ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ‘አሽከር’ የሚለው ቃል ቢያንስ በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት ስለሌለው እና ክብረ ነክም ስለሆነ ስያሜውን በመቀየር ዝርዝር ሕግ ማውጣትም ይገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በደርግም ዘመን ይሁን አሁን ባለው ምንም የተጨመረ ነገር የለም፡፡ እስካሁን ድረስ ሕግ አለመውጣቱን ስናይ ጎደሎም ቢሆኑ ጭራሹን ከመተው እና ከመዘንጋት እንደሚሻሉ ማስተባበል አይቻልም፡፡
የፍትሐ ብሔር ሕጉ ዕልባት ለመስጠት የሞከረባቸውን ጉዳዮች እንመለከት፡፡ ሠራተኛውን በሚመለከት አሠሪው ያሉበትን ግዴታዎች በቀዳሚነት አስቀምጧል፡፡ በመጀመሪያው ከተቀመጡት ግዴታዎች ውስጥ የሠራተኛውን የመኖሪያ ቦታ፣ ምግብ፣ የሥራ እና የዕረፍት ጊዜ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር የአሠሪው ግዴታ የሠራተኛውን ጤንነት እና ግብረገብነት ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ በአዕምሮ ግምት ተገቢ የሆኑ ዝግጅቶችን ማድረግ ነው፡፡
በመሆኑም፣አሠሪው ለሠራተኛው የሚኖርበትን ቤት ለጤንነቱ ምቹነት፣ የምግቡን መጠን፣ዓይነት እና ጥራት ወዘተ የራሱ አዕምሮ በፈቀደው መጠን ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ ይህ እንግዲህ የሞራል ግዴታ እንጂ ብዙም በሕግ አይመስልም፡፡
የፍትሐ ብሔር ሕጉ የደነገገው ሌለው ጉዳይ ሕክምናን የሚመለከት ነው፡፡ ሠራተኛው ውሉ ጸንቶ ባለበት ጊዜ ከታመመ አሠሪው በቤቱ ወይንም በሕክምና ቦታ የማሳከም ግዴታ አለበት፡፡ ሠራተኛው ከተቀጠረ ሦስት ወር ከሞላው አስራ አምስት ቀናት፣አንድ ዓመት ከሞላው ደግሞ ለአንድ ወር የማስታመም ግዴታ አለበት፡፡ ሦስት ወር ሳይሞላው ቢታመም የአሠሪው ግዴታ ምን እንደሆነ አልተገለጸም፡፡ ለተወሱ ቀናት ማስታመም ወይንም ጭራሹን ግዴታ ስለመኖር አለመኖሩ ሕጉ አልነገረንም፡፡ ሠራተኛው በታመመበት ወቅት ውሉን ማቋረጥ ግን አይቻልም፡፡
ይህ ማለት ግን እስከሚድን ድረስ ሲያስታምም ይቆያል ማለት አይደለም፡፡ ሊቆይ የሚችለው ከላይ በተገለጹት መጠን እንጂ እስከሚድን ድረስ ውሉን ሳያቋርጥ የማስታመምን ግዴታ አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም ሦስት ወር የሞላውን ለአስራ አምስት ቀናት፣ አንድ ዓመት የሆነውን ለአንድ ወር ብቻ የማስታመም ግዴታ በአሠሪው ላይ ግዴታ የጣለ በመሆኑ፡፡
ይሁን እንጂ፣ አሠሪው ለሕክምና ያወጣውን ወጪ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የመቀነስ መብትንም ይሠጠዋል፡፡ ሠራተኛው በራሱ ጥፋት ያመጣው በሽታ ከሆነ ግን አሠሪው የማሳከም ግዴታ አይኖርበትም፡፡
ሌላው ሕጉ ያስቀመጠው የደመወዝ አከፋፈልን የሚመለከት ነው፡፡ በውላቸው ላይ በተለየ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር አሠሪው ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ያለበት በየሦስት ወሩ መጨረሻ ነው፡፡ ሁለቱ ከተስማሙ ግን በአንድ ወርም ይሁን በሁለት መክፈልን አይከለክልም፡፡ እንግዲህ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ያካተታቸው ከሞላ ጎደል እነዚህ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ እስካሁን ድረስ የቤት ሠራተኞችን የሚመለከት ሕግ አልወጣም፡፡
የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉም ካገለላቸው መካከል የቤት ወይንም የግል ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ዋና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የቤት ውስጥ ወይንም የግል ሠራተኞች የሚባሉት  ከላይ የገለጽናቸው በዋነኛነት በአሠሪው መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ  ወይንም ለአሠሪው ለግል ኑሮ የሚያስፈልጉ  ተግባራትን የሚናውኑ ናቸው፡፡ ምግብ አብሳዮች፣ የጽዳት ሠራተኞች፣ አትክልተኞች፣ ጥበቃዎች፣ የግል ሹፌሮች፣ አጃቢዎች እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለአሠሪው እና/ወይንም ለቤተሰቡ ፍጆታ ብቻ የሚሆኑ ጉዳዮችን የሚከናውኑ መሆን አለባቸው፡፡
የሥራቸው ዓይነት ተመሳሳይ ሆኖ በመንግሥት ወይንም በሌላ ማናቸውም ድርጅት የተቀጠሩትን ግን የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ውጭ አልሆኑም፡፡ እንደ ቀጣሪው ዓይነት በሲቪል ሠርቪስ ወይንም በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ከአሠሪዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ይታያል፡፡ በመሆኑም የቤት ሠራተኞችንም አይመለከትም ማለት ነው፡፡
ጎደሎነታቸውን ለመሙላት
እንግዲህ ከላይ የተገለጹት ብዙ ነገሮች እንደጎደሏቸው መታዘብ አይገድም፡፡ ቢያንስ ከሌሎች ሠራተኛን ከሚመለከቱ ሕጎች ጋር በማነጻጸር ጎደሎነታቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ የግል ሠራተኛ ሆኖ ለመቀጠር ዝቅተኛው ዕድሜ አይታወቅም፡፡ በሌሎች ሁኔታ 14 ዓመት የሞላውን መቅጠር ይቻላል፡፡
በተለይ ተመላላሽ ያልሆኑትን በተመለከተ በአንድ በኩል ቤተሰባዊ ትስስርን እና ግንኙነትን ከግምት በማስገባት በሌላ በኩል ደግሞ ቢያንስ መሠረታዊ የሆነውን እስከ ስምንተኛ ክፍል የመማር መብት ከግምት የሚያስገባ ሕግ ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም ብዙ የመብት ጥሰቶች የሚከሠቱት ደመወዝ ካለመክፈል ጋር የተያያዙ ስለሆኑ ተሻለ ሁኔታ ውል የሚደረግባቸውን መንገዶች ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በጽሑፍ እና በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በኩል እንዲፈጸሙ ማደርግ እንደ አማራጭ መያዝ ይገባል፡፡ በርካታ አገራት ይሔንን መንገድ የተከተሉትም የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ሲሉ ነው፡፡
የአሠሪውና የሠራተኛውን ግዴታዎች፣ ውሉ ጸንቶ ሊቆይ የሚችልበትን ጊዜ ማለትም ለተወሰነ ጊዜ ስለመሆን አለመሆኑ፣ውል የሚቋረጥባቸውን መነሻዎችና የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣ውል ሲቋረጥ ሊኖር ስለሚገባው የስንብት ክፍያ እና ውሉን ላላከበረ የሚከፈል ካሳ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን፣ በቀን እና በሳምንት ሊኖር የሚገባው የሥራ ሰዓት እና የዕረፍት ጊዜያት ወዘተ የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የፍትሐ ብሔር ሕጉ የሉትም፡፡ ተመላላሽ እና አብረው የሚኖሩ ሠራተኞችን ሁኔታ በመለየት፣ለማኅበራዊ ዋስትና በሚያመች መልኩ ሕግ ማውጣት ይገባል፡፡
የሥራ ስምሪት ፖሊሲው ስለቤት ሠራተኞች
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥራ ስምሪት ፖሊሲ” ስለ ቤት ውስጥ ሠራተኞች ሁኔታ በተለይም መብታቻውን በማኅበራት አማካይነት ማስከበርን በተመለከተ “አሁን ተግባራዊ እየሆነ ያለው የሠራተኛ ማህበራት እንቅስቃሴ ለመብት ጥስት ተጋላጭ በሆኑ ሥራዎች ከተሰማሩት (ማለትም መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ፣በቤት ውስጥ ሥራና ተዘዋዋሪ ሠራተኞች) ይልቅ በመደበኛው ኢኮኖሚ ውስጥ በተሰማሩት የማተኮር ዝንባሌ አለው፡፡” ይላል፡፡ የፖሊሲው ዓላማዎችም የዜጎችን ማኅበራዊ ዋስትና ማረጋገጥ፣ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣት እና ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡
ፖሊሲው ይሄንን ይበል እንጂ ከላይ የተገለጹትን ለማስፈጸም የሚያግዝ ሕግ የለም፡፡ እንዲወጣም አስተያየት አልሰጠም፡፡ የቤት ውስጥ ሠራተኞችንም በማኅበር የሚደራጁበትን እና እና የተሻለ የሕግ ጥበቃ ማድረግ ይገባል፡፡
ወደ ሌላ አገራት በመሔድ የሚሠሩትን በተመለከተ ምን መደረግ እንዳለበት ፖሊሲው ሲያትት፣ በአገር ውስጥ መደበኛ ባልሆነው በተለይም ስለ ቤት ውስጥ ሠራተኞች ብዙም ትኩረት አልሠጠም፡፡
የቤት ሠራተኛ ጉዳይ ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ዝቅተኛው የዕድሜ መጠን አልተወሰነም፡፡ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ በሰፊው ስለመኖሩ ጥናት ማድረግ አያስፈልግም፡፡ ከመሠረታዊ ትምህርት መዳረስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የግዳጅ ሥራንም ይመለከታል፡፡ ይሁን እንጂ ፖሊሲው የቤት ሠራተኞችን በተመለከተ ጎደሎው ብዙ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ስለቤት ሠራተኞች
ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ስለ ቤት ሠራተኞች ያወጣውን ስምምነት የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ስምምነቱ በመሠረታዊ መርሕነት ያስቀመጣቸው ወይንም ለማሳካት በማሰብ በግብነት ካስቀመጣቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
የቤት ሠራተኞች እንደማንኛውም ሰው ያላቸውን ሰብኣዊ መብቶች ማስጠበቅና እንዲሻሻል ማድረግ የመጀመሪያው መርሕ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የመደራጀት፣ማኅበር የማቋቋም፣ዕውቅና የማግኘትና መደራደር መብትን የሚመለከት ነው፡፡ ዘርፉ ለሕጻናት ጉልበት ብዝበዛና ቅጥርም የተጋለጠ ስለሆነ ይህንን ማስቀረትም ሌላው መርሕ ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ በመሆናቸው ብቻ የተነሳ ጥበቃ እና የሕግ ማዕቀፍ በማጣት የሚደርስባቸውን መድልኦ ማስወገድም ግቡ ነው፡፡
በማናቸውም መልኩ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማስወገድ እና ለሚሠሩት ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ ማግኘት እንዲችሉ የሚያግዝ የቅጥር ግንኙነት ማስፈንም እንዲሁ ስምምነቱ ለማሳካት ያሰበው ግብ ነው፡፡ ከላይ የተገለጹት ለማሳካት ደግሞ በርካታ ግንኙነቶችን በሕግ እንዲገዙ ወይንም መብት እና ግዴታ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፈራሚ ስላልሆነች የማስፈጸም ግዴታ የለባትም፡፡
ለማጠቃለል የቤት ሠራተኛን በሚመለከት ጎደሎነቱ ቀድሞም ይታወቃል፡፡ የሥራ ሠዓት፣የደመወዝ ጉዳይ፣የግብር እና ማኅበራዊ ደኅንነት፣ የሠራተኞቹና የአሠሪዎች መብትና ግዴታ፣የሥራ ስንብት ክፍያ እና ማስጠንቀቂያ፣ዕረፍትን በተመለከተ፣የሥራ ላይ ደኅንነት ወዘተ በርካታ ጉዳዮች ሕጋዊ መፍትሔ አልተበጀላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ የግል ሠራተኛ መያዝ የተለመደ ነው፡፡ በቀድሞ ዘመናት በሰፊው የተዘወተረው ባርያ በመግዛት የቤት ሥራ ማሠራት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ባርያ ያልሆኑ ሰዎችም በቤት ሠራተኛነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ይህንን የሥራ ግንኙነት የፍትሐ ብሔር ሕጉ በተወሰነ መልኩ ቅርጽ ለማስያዝ ሞክሯል፡፡ ደርግ ሲመጣም ከሴተኛ አዳሪዎች እና ከቀን ሠራተኞች ጋር በአንድነት ማኅበር እንዲያቋቁሙ ከማድረግ የዘለለ ብዙም ጥረት አልተደረገም፡፡
 በሽግግሩ ወቅትም የወጣውም አሁን በሥራ ላይ ያለው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ቁጥር 377/1996  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ እንዲያወጣ ግዴታ ቢጥልበትም ሕጉ አስካሁን አልወጣም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም የሰጠውን ኃላፊነት ስላለመወጣቱ ቁጥጥርም አላደረገም፡፡ ቢያደርግ ኖር ቢያንስ 25 ዓመታት ገደማ ሊዘገይ አይችልም፡፡
 የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሴቶችና እና ሕጻናት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችም አያስታውሷቸውም፡፡ ሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም ጭምር እንዲሁ፡፡ ምናልባት ሕግ አውጭዎቹም ሆኑ ሌሎቹ የሚመለከታቸው አካላት የቤት ሠራተኛ ቀጣሪ ስለሆኑ ራሳቸው ላይ ግዴታ ላለመጫን ይሁን አይሁን ግን አልታወቀም፡፡
Filed in: Amharic