1. ለውጥ እና ሥርዓት
ጥሩ መሪ የለውጥ ሃዋሪያ ነው። ለለውጥ ያልተነሳሳ ሰው መሪ መሆን አይችልም። ለውጥ ደግሞ ነባር ህጎችንና ልማዶችን መቃወም እና በአዳዲስ ህጎችና ልማዶች እንዲተኩ መጣር ይጠይቃል። ለውጥ ማፍረስን ይጠይቃል።
በአንፃሩ፣ መሪ ህግን አክባሪ ነው፤ ባህል አክባሪ ነው። መሪ ያላከበረው ህግ መቸም ቢሆን ሊከበር አይችልም። ልማዶችንም ማክበር ከጥሩ መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነው። መሪ የሥርዓት ምንጭ ነው።
አንዳርጋቸው የለውጥ መሪ ነው። ሁሌ አዳዲስ አሰራሮች መሞከር ይወዳል፤ አዳዲስ ሀሳቦችን ያመነጫል። ለውጥ በአገር ብቻ ሳይሆን በድርጅት ደረጃም እንዲኖር ይፈልጋል። በአንፃሩ ደግሞ ሥርዓት ያጠብቃል። ለምሳሌ ጠዋት የመጀሪያ ሥራዉ በዕለቱ የሚሠሩ ሥራዎችን ዝርዝር (To do list ) ማዘጋጀት ነው። ከትናትናው ያደሩትን ወደዛሬ ያሸጋግራል፤ የዛሬዎችን ይጽፋል፤ ትናንሽ ነገሮችን ሳይቀር ይመዘግባል፤ ተራ የሚባል ነገር እንኳን – ለምሳሌ ኢሜሎችን ከፍቶ ማየት – በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል። አንዳርጋቸው ራሱን በሥርዓት ገድቦ የሚመራ ሰው ነው፤ በዚያው መጠን ደግሞ የለውጥ አቀንቃኝ ነው።
ይህ ባህርዩ በሌሎች ብዙ ነገሮች ይገለፃል። የለውጥ ሀሳብ ያመነጫል፤ ወዲያው ደግሞ ከለውጥ በኋላ ስለሚኖረው ሥርዓት ይጨነቃል።
2. መምሰል እና መለየት
ጥሩ መሪ ተከታዮችን መምሰል አለበት። ተከታዮች ሲራቡ መራብ፤ ሲታረዙ መታረዝ አለበት። ተከታዮች የሚሠሩትን ሥራ እሱም መሥራት አለበት። መሪ በሁሉም ረገድ ለተከታዮቹ አርዓያ መሆን አለበት።
በሌላ በኩል፣ መሪ ከተከታዮቹ መለየት አለበት። አለበለዚያማ ምኑን መሪ ሆነው? ተከታዮቹም ቢሆኑ መሪያቸው ከእነሱ በምንም የሚለይ አለመሆኑን ሲያዩ በመሪነት መቀበል ይቸግራቸዋል።
አንዳርጋቸው ይህን አስቸጋሪ ወለፈንዲ መወጣት የቻለ ነው። ከተከታዮቹ ጋር ይመሳሰላል፤ የሚበሉት ይበላል፤ የሚቸኙበት ላይ ይተኛል፤ ተራ ገብቶ ምግብ ያበስላል። አንዳርጋቸው በሁሉም ረገድ ለተከታዮቹ አርአያ ነው።
ይሆን እንጂ አንዳርጋቸው ከተመሪዎች የተለየ ነውም። የቅርቡን ብቻ ሳይሆን የሩቁን ያቅዳል፤ ግኑኝነቱ የሰፋ ነው፤ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ሩቅም ቅርብም ካሉት ወሳኝ ሰዎች ጋር ይገናኛል። አንዳርጋቸውን ከተመሪዎች መለየት በጣም ቀላል ነው።
3. የሥራ ሰው እና የሐሳብ ሰው
ጥሩ መሪ ተግባር ላይ እንዲያተኩርና የሥራ ሰው (The Doer) እንዲሆን ይፈለጋል። በሌላ በኩል ጥሩ መሪ የሐሳብ ሰው (The Thinker) መሆን ይኖርበታል። ሓሳብና ተግባር መደጋገፍ እንጂ መነጣጠል የለባቸው።
አንዳርጋቸው የተግባር ሰው ነው፤ አንዳርጋቸው የሀሳብ ሰውም ጭምር ነው። ጉድጓድ ሲቆፍር፣ እንጨት ሲፈልጥ፣ ምግብ ሲያበስል ለመጀመሪያ ግዜ ያየው ሰው እንኳንስ የፍልስፍና ሀሳቦችን ሊያውጠነጥን ይቅርና ማንበብና መፃፍ የሚችል መሆኑ ሊጠራጠር ይችላል። ሆኖም ግን የፍልስፍና ሙግት ከጀመረ ይህ ሰው መፃፍ ሲያነብ ብቻ የኖረ፤ ከማንበብ ውጭ ሌላ ሥራ ኑሮት የማውቅ ሊመስለው ይችላል።
4. በአንድ ጉዳይ ላይ ማትኮር እና ሁሉን ዓቀፍ እይታ
ጥሩ አመራር እና ጥሩ መሪ በአንድ አቢይ ጉዳይ ላይ ማትኮር ይኖርበታል። ያም ጉዳይ የድርጅቱ ግብና ወደዚያ ያደርሰኛል በሚለው ስትራቴጂው ላይ መሆን ይኖርበታል። በየጊዜው በሚፈጠሩ “የጎን ጉዳዮች” ትኩረቱ የሚዛባ ሰው ጥሩ መሪ መሆን አይችልም።
ይሁን እንጂ፣ መሪ ሁሉን ዓቀፍ እይታ እንዲኖረው ያሻል። ጥሩ መሪ ትኩረቱ መንገዱ ላይ ቢሆንም እንደጋሪ ፈረስ ግራና ቀኙን ላለማየት ዓይኖቹን የሸፈነ መሆን የለበትም። በየጊዜው የሚፈጠሩ እድሎችን በቸልታ የሚያሳልፍ ሰው ጥሩ መሪ መሆን አይችልም። እይታን ዓለም-ዓቀፍ፤ ተግባሮችን ግን አካባቢ-ተኮር ማድረግ እንደ መፍትሄ ይቀርባል። ይህንን በተግባር መተርጎም ግን ቀላል ነገር አይደለም።
አንዳርጋቸው አንድ ጉዳይ ይዞ እዳር ሳያደርስ እንቅልፍ የማይወስደው፤ ከያዘው ጉዳይ ላይ ዓይኖቹን የማይነቅል ሰው ነው። በዚያው መጠን ደግሞ ወቅት የሚፈጥራቸውን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም እና ወቅት ከሚፈጥራቸው አደጋዎች ለመከላከል አዟዙሮ የሚያይ ሁሉን ዓቀፍ እይታ ያለው ሰው ነው።
በአንድ ወቅት የሆነ ሰው በሱ ላይ እጅና እግር የሌለው ትችት ፃፈ። አንዳርጋቸው ጽጌ የሚለውን ስሙን “በትናቸው ጽጌ” እያለ ነበር የፃፈው። ጭብጡን ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ባዶ ጩከትና ስድቦች የታጨቁበት ጽሁፍ ነበር። ይዘቱን ትቼ (ይዘት ስላልነበረውም) ቅርጹን በሚመለከት “ቃላትን አለአግባብ ስንጠቀም ሊያሳዝኑን ይገባል” የሚል መልዕክት ያለው ”የቃላት ኢኮኖሚ“ የሚል ርዕስ የሰጠኹት አንድ ገጽ ጽሁፍ ምላሽ ፃፍኩ።
አንዳርጋቸው “ሥራ አጥተህ ነው ለዚህ ምላሽ የሰጠኸው?” ሲል ተቆጣኝ፤ “እንዲህ በእንዲህ ዓይነት ነገር ጊዜህን ታባክናለህ?” ሲል ተቸኝ። “አንተምኮ ጊዜ ሰጥተኽ የእሱንም የኔን ጽሁፎች አንብበሃቸዋ ማለት ነው” ስል ተከላከልኩ። “እየው በተቻለ መጠን እኛን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ማየት አለብን፤ ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ ስቀን፣ ንቀን፣ ተገርመን፣ ወይም ቸል ብለን የምናልፋቸው ናቸው። ማየትህን አይደለም የጠላሁት ምላሽ መስጠትህ ነው” አለኝ። አንዳርጋቸው ብዙነገሮችን ያያል፣ ይሰማል፤ ትኩረቱን የሚስቡት ነገሮች ግን ውስን ናቸው።
ስለአንዳርጋቸው ብዙ ማለት ይቻላል። ለጊዜው በዚሁ ይብቃኝ። አንዳርጋቸው ንቅናቄዓችን አርበኞች ግንቦት7 ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በጉጉት የምትጠብቀው ሰው ነው። በአንዳርጋቸው መታሰር የምትጎዳው የምንወዳት ኢትዮጵያ ነች።