>

ነብሩ፣ ሊቀመንበሩ እና አያ ጅቦ (ስዩም ተሾመ)

አያ ጅቦ እና ቄሮ መስማማት ቀርቶ መግባባት አይችሉም፡፡ ዶ/ር አብይ ያደገው በአያ ጅቦ መንደር ነው፡፡ ነገር ግን፣ በቅርቡ በሁለቱ ባላንጣዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት አሳዳጊዎቹን ከድቶ ከነብሮች ጎን ቆመ፡፡ ነብሮችም ይህን ከግምት በማስገባት ከሰፈራቸው አልፎ የቀበሌው ሊቀመንበር ሆኖ እንዲመረጥ አስችለወታል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ነብሮ (ቄሮ)፣ ሊቀመንበሩ እና አያ ጅቦ (ህወሓት)

አሳዳጊዎቹ ጅቦች ግን ከድቷቸው ከቄሮዎች ጎን ስለቆመ፣ እንዲሁም ቀድሞ በቀበሌው ውስጥ የነበራቸውን የአድራጊ-ፈጣሪነት ስልጣን ስላሳጣቸው ሥር-የሰደደ ቂምና ጥላቻ አላቸው፡፡ እነሱን ከድቶ ሊቀመንበር መሆኑ ሳያንስ “ከቄሮዎች ጋር ተባብሮ ሊያጠቃን ይችላል” የሚል ስጋት በጅቦች ዘንድ አለ፡፡ ስለዚህ “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” በሚለው መርህ ሊቀመንበሩን በመንከስ በውስጣቸው የተጠራቀመውን ቂምና ጥላቻ ለመወጣት የሚያስችላቸው አሳቻ ግዜና ቦታ እያፈላለጉ ነው፡፡

ጅቦች በሊቀመንበሩ ላይ ጥቃት ከመፈፀም ያገዳቸው ብቸኛ ነገር ጥቃቱን ተከትሎ በነብሮች ሰፈር የሚፈጥረው ቁጣና የሚከተለው የአፀፋ እርምጃ ነው፡፡ ነብሮች አንዴ በቁጣና በእልህ የበቀል እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ የጅቦች ሰፈር ባድመ (ምድረ-በዳ) እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን፣ በሊቀመንበሩ የተፈፀመባቸውን ክህደትና የፈጠረባቸው  ስጋት ጨርሶ ከውስጣቸው አይወጣም፡፡

ሊቀመንበሩ ደግሞ የነብሮች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የቀበሌው መሪ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡  ይሁን እንጂ፣ በጅቦች ዘንድ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ለማግኘት የሚያደርገውን ነገር በሙሉ ነብሮች በዓይነ-ቁራኛ እየተከታተሉ ነው፡፡ በግጭቱ ወቅት ከእነሱ ጎን የቆመ ቢሆንም አሳዳጊዎቹ ጅቦች መሆናቸውን ነብሮች ፈፅሞ አይዘነጉም፡፡ ከቀንደኛ ጠላታቸው እጅ እየበላ ያደገ እንደመሆኑ “በቀውጢ ሰዓት ድንገት ሊከዳን ይችላል” የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ስለዚህ ሊቀመንበሩ በጅቦች ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገውን ነገር በነብሮች ሰፈር ስጋትና ጥርጣሬ ይፈጥራል፡፡

ጅቦች በነብሮች ላይ ጥቃት ከፈፀሙና ሊቀመንበሩ ይህን ማስቆም ከተሳነው ነብሮች ተባብረው ከስልጣን ያወርዱታል፡፡ በጅቦች ላይ እንደፈፀመው አይነት ክህደት በነብሮች ላይ ከፈፀመ ግን በተዓምር ከሞት አይተርፍም፡፡ ከቄሮዎች ጋር ሆኖ በጅቦች ላይ ጥቃት ከፈፀመ ጅቦቹ አሳቻ ሰዓት መጠበቃቸው ቀርቶ በአልሞት-ባይ ተጋዳይነት ሊቀመንበሩን ለማውረድ አሊያም ለማስወገድ ይሞክራሉ፡፡ ያው ይህን ባደረጉ ማግስት ሰፈራቸው ምድረ-በዳ መሆኑ አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ አሁን ባሉበት ሁኔታ በፍርሃትና ስጋት መኖር አይሹም፡፡

ከላይ  በተገለፀው መሠረት ሊቀመንበሩ ጅቦችን ሆነ ነብሮችን በአንድ ግዜ ወይም እኩል ማስደሰት አይችልም፡፡ የሁለቱንም ስጋት ጨርሶ ማስወገድ አይችልም፡፡ ሁለቱም ለዘለቄታው በስጋትና ፍርሃት መኖር አይሹም፡፡ ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ ደግሞ ሊቀመንበሩን ከመሃል በማስወጣት ነብሮች እና ጅቦች ፊት-ለፊት ይፋጠጣሉ፡፡ ባልተጠበቀ ምክንያት ወደ ለየለት ግጭት ያመራሉ፡፡ በግጭቱ ማን አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ ከሊቀመንበሩ የሚጠበቀው የማይታረቁ ወገኖችን ለማስታረቅ ከመሞከር ይልቅ ጎራውን መለየትና የደፈረሰውን ማጥራት ነው!!

Filed in: Amharic