>

አንዳርጋቸዉን ፍቺዉ!!  ጦቢያ ተለመኚኝ… (ሃራ አብዲ)

የወጣት አፍቃሪ ልቡ፤ በዉበትሽ ሲማረክ፣

በእቅፍሽ ዉስጥ ፣ስፍራ አገኘ፣

ቅብጥብጥ ያፍላ ጉልበቱ፣ለልእልናሽ ሲንበረከክ፣

የልብሽን ሊያደርስልሽ፣ ዘመኑን ሙሉ ተመኘ።

እንደ እድሜ እኩዮቹ፣ ኢትዮጵያን እንዳሉት ሁሉ፣

አንዲም በኢትዮጵያ ተለከፈ!

ይች ንግርታም ወይዘሮ፤ ከኦሪት እስከ አዲስ ኪዳን፤ ያላጠመደችዉ የታል?

የፍቅርዋ ንብ ያልነደፈዉ፤ ሰመመንዋ ስንቅ ያልሆነዉ፤

ጠኔዋ ያላጠገበዉ፤ ጥማትዋ እርካታ ያልሰጠዉ፣

ያልሞተላት ሞትዋን ነጥቆ፣ ሀፍረትዋንስ ያልሸፈነ፣

መግነዝዋን ከጣትዋ ፈትቶ ፤ ነዉርዋን በክብሩ ያልከደነ።

ማነዉ ??

እንደ ሰም እየቀለጡ፤ ለነፍስሽ ነፍስ እየሰጡ፣

ስንቶች በክብር አሸለቡ፤ ስንቶች ቀሩ እንደወጡ።

አኝኬም አልዘልቀዉ እንዲል፤ እኔም አስልቼ አልዘለቅሁት፣

አንዳርጋቸዉ ጽጌን ላሳየዉ፤ እንደጎጆ ቤት ጉልላት።

ከፍ ብሎ ምስሉ ያብራ፤ ደምቆ ይነገር ግብሩ፣

ኢትዮጵያ ወይም  ሞት ብሎ ፤

ከልጅነት እስከ እዉቀት፤ በፍቅርሽ እቶን ማረሩ፣

ላንድነትሽ መንሰፍሰፉ፤ ለእድገትሽ መባከኑ፣

በስደት መንገላታቱ፣ በሱዳን በረሃ መሸንቆጡ፣

ከሱዳን- እንግሊዝ፣ ከእንግሊዝ ከንፎ መምጣቱ፣

ከፍ ብሎ  ምስሉ ያብራ፤ ደምቆ ይነገር ግብሩ፣

የልጅነት ፍቅረኛዉን፣ ጎልምሶም አለመርሳቱ።

እንደ አምሃ እንደወንድሙ፤ ክንዱን እስክሚንተራስ፣

ቃል ኪዳኑን ላይሽረዉ፣ ላይዘነጋዉ ሲጎለምስ።

ሚስት ቢያገባ፤ ልጆች ቢወልድ፤አቅመደካማ አባት ቢጦር፤

መቼዉንም ያልለቀቀዉ፣ የዉድሽ ጦስ፤የነፍሱ ጣእር ፣

የልጅነት ፍቅር በኩሩ፤ ከልቡ ሰገነት ያልወረድሽ፣

ጀግናሽን ፍችዉ እባክሽ፣ የእድሜ ልክ አፍቃሪሽን፣

አሳሪዎቹን ደጅ አልጠናም፤ አንች ነሽ ባላስልጣን!!

አንች ነሽ የአንዲ አዙሪት፣ ነፍሱን እረፍት የነፈግሻት!!

የትዉልዱ ድልድይ ያደረግሽዉ ፤ የ «ያ ትዉልድ» መልከፍት ክፋይ፣

ዘመን – ጠገብ ክንድሽ ይነሳ፤ ሰንሰለቱ ወልቆ ይታይ።

ከሚስቱ እቅፍ መንጥቀሽ ፤ ኤርትራ በረሃ የመሸግሽዉ፣

የልጆቹን ጠረን ሳይጠግብ፤ በስስትሽ የጠለፍሽዉ፣

የዘመን ሃማምሽን ሊታመም፤ ሊዳስስሽ የፈለግሽዉ፣

ጦቢያ እባክሽ ተለመኚኝ፣ አንዳርጋቸዉን ፍቺዉ!!

Inspired by,

FREE ANDY TSEGE: A campaign to free and return to UK a British father Andargachew “Andy” Tsege who was kidnapped on 23rd June 2014 while in-transit in Yemen International airport and rendered to Ethiopia. He is still in illegal detention in Ethiopia! He is a man who is advocating democratic government in Ethiopia.

Filed in: Amharic