>
5:13 pm - Thursday April 19, 8063

የ77 አመቱ የትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህመድ  (ጴጥሮስ አሸናፊ ከበደ)

በ1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ በአሜሪካን ግቢ አካባቢ የተወለደው ማህሙድ ሥራንም ሆነ ሕይወትን በራሱ መጋፈጥ የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነበር፡፡ አባቱ በሚሠሩበት ግሪክ ክለብ አብሮ በመሔድ በቅርጫት ኳስና የቴኒስ ሜዳዎች ላይ ይሠራም ነበር፡፡ በስድስት ዓመቱም ሊስትሮ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታው ብዙ ጐበዝ እንዳልነበር የተረዳው ማህሙድ ቤተሰቦቹንና ራሱን መርዳት እንዳለበትም የተረዳውም እንዲሁ በአፍላ ዕድሜው ነበር፡፡
የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚም ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት የነበረ ቦታ ነበር፡፡
በአንድ አጋጣሚም ሁሉም ድምፃውያን ወደ ድሬዳዋ ሔደው ሙዚቀኞቹ ያለ ድምፃዊ የተፈራ ካሣን ‹‹አልጠላሽም ከቶ››ን የተዘራን ‹‹ይሔም አለ ለካ››ንና የጥላሁን ዘፈኖች እየተለማመዱ ነበር፡፡ በድምፅ መዝፈን እንደሚፈልግም ጠየቃቸው ፈቀዱለትም። ‹‹አልጠላሽም ከቶ›› የሚለውን ዘፈን በሚዘፍንበት ሰዓት የኮንጐ ዘማቾች በቦታው ነበሩና አስደነቃቸው፡፡ እንደገናም እንዲዘፍን ተጠየቀ፡፡ የክለቡ ባለቤት በቦታው የነበረ ሲሆን አድናቆት በተሞላ ድምፅም ‹‹የአላህ ያለ መዝፈን ትችላለህ!›› እንዳለው ማህሙድ ያስታውሳል በዚህም አጋጣሚ ከአስተናጋጅነት ወደ ዘፋኝነት ተቀየረ፡፡ የቤቱ ባለቤትም ሙሉ ልብስ ገዛለት፡፡
ጥላሁንና ሌሎቹ ዘፋኞች በተመለሱበት ወቅት የእሱ መዝፈን በጣም ነው ያስገረማቸው ስለነበር፤ የግጥም ደብተር ሰጡት፡፡ የተለያዩ ዘፋኞችን ሙዚቃን በመዝፈን ጀመረ፡፡ በዚህም ክለብ ነበር ‹‹አላወቅሽልኝም›› የሚለው የመጀመሪያው ዘፈኑ የሆነው ግጥም ተሰጠው፡፡ ክብር ዘበኛ መቀጠር ፍላጐቱ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ግን ፖሊስ ኦርኬስትራና ምድር ጦር ለመቀጠር ጠየቀ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም እንደማይቀጥሩት ነገሩት፡፡ መቶ አለቃ ግርማ ሐድጉም (በኋላ ሻለቃ) ክብር ዘበኛ መቀጠር ይፈልግ እንደሆነ ጠየቁት፣ እሱም ተስማማ ከመቀጠሩ በፊት ግን በሕዝብ ፊት ዘፍኖ ማለፍ ነበረበት፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረውን እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በጥልቅ ያስታውሳል፤ የታምራት ሞላን ‹‹ተስፋ አትቁረጪ›› እንዲሁም ‹‹አላወቅሺልኝም›› ዘፈነ፣ ‹‹የኤልቪስ ፕሪስሊን ዳንስምንም ደነሰ፣ እናም የተመልካቹ መልስ የማይታመን ሆነ፡፡
መቶ አለቃ ግርማም ወታደር ሆኖ እንዳይቀጠር መከሩት፣ የክብር ዘበኛ ሰዎችም በወታደርነትና ሙዚቀኝነት 120 ብር እንክፈልህ ብለው ቢጠይቁትም እሱ ግን በሙዚቀኝነት ብቻ በ1955 ዓ.ም. አካባቢ ተቀጠረ፡፡ ለአሥራ አንድ ዓመታትም ያህልም በዚህ ቦታ ሠርቷል፡፡ ወርሃዊ ደመወዙም 60 ብር የነበረ ሲሆን በዚህ ደመወዝ አምስት እህቶቹና ወንድሞቹ በአጠቃላይ ቤተሰቦቹን ይደግፍ ነበር፡፡ በወቅቱ ወላጅ  አባቱ ሥራ ያልነበራቸው ሲሆን እናቱ ብቻ ቤተሰቡን ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎችን ይሰሩ ነበር ፤ መጨረሻ ላይ ከክብር ዘበኛን በለቀቀበት ወቅት ደመወዙ 250 ብር ደርሶ የነበረ ሲሆን በመቀጠልም  ከአይቤክስ ባንድ ጋር ተጠቃልሎ ራስ ሆቴል ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ።
ዛሬ ማህሙድ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን መጣል ከቻሉ ስመ ጥሩ ዘፋኞች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተደናቂነትን፣ ተፈቃሪነትን ማትረፍ የቻለ ፈርጥ እንደሆነም የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው ማህሙድ በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን ያዝናናል፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በላይ በቆየውም የሙዚቃ ሕይወቱ የተለያዩ ትውልድን በሙዚቃው አንድ ላይ ማምጣት የቻለ ትልቅ አርቲስት ነው፡፡ በተለያዩ ኮንሠርቶች በሚዘፍንበትም ወቅት በተለያዩ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል መልኩ አብረውት በመዝፈንም በዘፈኑ አንድነትንም ያሳያሉ፡፡
ማህሙድን የኢትዮጵያ የስነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ታህሳስ 24 ቀን 1991 ዓ.ም. “የረጅም ጊዜ ተሸላሚ” በሚል ዘርፍ ሸልሞታል። ከሰማኒያ በላይ በጉራጊኛና አማርኛ የዘፈነው ድምጻዊ ማህሙድ ተደናቂነትን ካተረፈባቸው መካከል፦ የሺ ሃረጊቱ፣ መቼ ነው አገሬን የማየው፣ አሽቃሩ፣ ኢትዮጵያና፣ የሠላሌዋ ይገኙበታል።
ድምጻዊ ማህሙድ በእሱ ዘመን ካሉት ድምፃውያን በተሻለ መልኩ በተለያዩ አገራት መድረክ ስራዎቹን በማቅረቡ ቢቢሲ 1999 ዓ.ም. “የአለም አቀፍ የሙዚቃ ተሸላሚ ከአፍሪካ” በሚል የሚታወቀውን የሽልማት ዘርፍ አበርክቶለታል። በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም 50 ዓመት የሙዚቃ ህይወቱም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮለታል።
ማህሙድ አሁን 77 አመት ሞላው። አሁንም ይዘፍናል፣ አሁንም በመድረክ ላይ ይወዛወዛል፣ ይደንሳል፣ ይጨፍራል ፣ ያስጨፍራል!  እንደመታደልም ሆኖ የዛሬ አመት 76 ኛ አመት የልደት በአሉን አብሬው ማክበር በመቻሌ ያቺ ዕለት  በህይወቴ ከተደሰትኩባቸው ዕለታት አንዷ ሆናለች።
አሁንም ለጋሽ ማህሙድ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር እመኝለታለሁ። 
መልካም ልደት !!!
Filed in: Amharic