>

ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቃዮች እና የህገ-መንግስቱ አንድምታ!?! (ዘላለም እሼቱ)

በሀገሪቱ የመዘዋወር መብት እንዲሁም ቋሚ የመኖሪያ ቦታ የመመስረት ለሁሉም ዜጎች በዘር በሀይማኖት በብሔር ልዩነት ሳይደረግ የተሰጠ ሰፊ መብት መሆኑን ከህገመንግስቱ አንቀፅ 32 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል። ይህ መብት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም በህጋዊ መንገድ የገቡ የውጭ ሀገር ዜጎችን ሁሉ የሚያጠቃልል መብት ነው። የዚህ ፁሑፍ አላማ ግን በተለያዬ ጊዜ ስለሚፈናቀሉ ህዝቦች በተለይም የአማራ ህዝብ ስለደረሰባቸው የመብት ጥሰት እና በዚሁ ምክነያት ስለደረሰው ጉዳት መፍተሔ እና ስለተጠያቂ እንዲሁም ጠያቂ አካላት የሚዳስስ ነው። የአማራ ክልል ህዝቦች በተለያዬ ጊዜ በየቦታው በየጊዜው ሲፈናቀሉ ማየት እንደልምድ በመቆጠሩ ሰሞኑን ከቤንሻንጉል ክልል ስለተፈናቀሉት 527 አባውራዎች መንግስት ዝም ማለቱ ለቅሶ ሲደጋገም እንደ ዘፈን ተቆጥሮብናል።
እነዚህ ሰዎች የተፈናቀሉት መነሻው በሁለት ግለሰቦች የግል ግጭት መሆኑን መረጃ በተፈናቀሉት ሰዎች በኩል ልናገኝ ችለናል።
የእነዚህ ሰዎች የደረሰባቸው መብቶች የህገመንግስቱን አይነኬ የተባሉትን እና ባስቸኳይ ጋዜ አዎጁ እንኳን የማይታገዱ መብቶች ተጥሰዋል።
እነዚህ ተፈናቃይ ሰዎች የተጣሱባቸው እንዲሁም በጥቅሉ የአማራ ብሔር የደረሰበት የመብት ጥሰቶች።
1) መዘዋወር ነፃነት
የኢፌድሪ ህገመንግስት በጊዜ በቦታ በዘር እንዲሁም በሀይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለማንኛውም ኢትዮጰያዊ በኢትዮጰያ ውስጥ ተንቀሳቅሶ የመስራት እንዲሁም መኖሪያ ቦታ የመመሰረት መብት በአንቀፅ 32(1) ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል ነገር ግን ቤኒሻንጉል ላይ አማራዎቹ ግን የዚህ ሰፊ መብት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም።
2) የእኩልነት መብት
አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው ከቤኒሻንጉል ክልል እንዲፈናቀሉ የተደረጉት። በዚህም አማራ ከሌሎች ጋር እኩል እንደማይታይ፣ የእኩልነት መብቱ እንደተጣሰ ያሳያል።
3) በህይወት የመኖር መብት
 በህጋዊ መንገድ የክልሉን እንዲሁም የሀገሪቱን ህጎች አክበረው የሚኖሩ ብዙ አማራዎች በ2010ዓም ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። እነዚህ ሰዎች የተገደሉበት መንገድ እጅግ አሰቃቂ እና ነውረኛ በሆነ መንገድ አንዳንዶቹ አንገታቸው ተቀልቶ መገደላቸው ታውቋል።
ይህ ስቃይ ግን ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዎጅ እንኳ የማይጣስ ሙሉ መብት እንደሆነ ከህገመንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ በግል ተቀምጧል።
4) የንብረት መብት 
እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች ህይወታቸውን ሙሉ የደከሙባቸው ንብረቶች በዛረፋ እና በቃጠሎ አጠዋቸዋል። የመሬት የመጠቀም መብታቸውንም ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያላቸው ቢሆንም በመሬቱ የመጠቀም መብታቸው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ተግደዋል።
 ከዚህ በላይ የደረሱት ችግሮችን የፈጠሩ አካላት እንዲሁም ሰብዐዊ መብቶችን መንግስት ሳይወጣ በመቅረቱ በህገመንግስቱ አንቀፅ 13 ላይ የተቀመጠውን ሰባዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ ባለመወጣቱ ሊጠየቅ ይገባል።
ይህ ብሔርን መሰረት ያደረገ የመብት ጥሰት የመጨረሻ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል። ተፈናቃዮችም በቂ ካሳ እና በቂ የመኖር ዋስትና ሊያገኙ ይገባል።  ክስ ሲመሰረት በቂ የሰው እንዲሁም የሰነድ ማስረጃ የምናቀርብ ይሆናል።
Filed in: Amharic