መቼም እራሱን የቻለ የዘመን አውድ ቢኖረውም አፄ ቴወድሮስ በዘመናቸው ብዙ የጭካኔ ተግባራት መፈፀማቸውን ግን አንክድም፡፡ ነገር ግን አፄ ቴወድሮስን እንዳከብራቸው ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ ልጥቀስ፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ሙሴ አንድ ለማመን የምቸገርበትን ነገር ተናግሮአል፡፡ “እነዚን በጐች ወይንም የዋህ እስራኤልአውያን ከምታጠፉ እኔን ከህይወት መፅሃፍ ደምስሰኝ” ብሎ ነበር፡፡ ለአንድ አማኝ ከፈጣሪ የሕይወት መዝገብ መደምሰስ የመጨረሻው የመስዋትነት ጥግ ነው፡፡ አፄ ቴወድሮስም አንዲት ወይዘሮ እንዳሉት ጥልቅ የሀይማኖት ትምህርት ዕውቀት የነበራቸው ነበሩ፡፡ እናም በመጨረሻዋ ሰዓት የገዛ ህይወታቸውን ሲያጠፉ በራሳቸው ላይ የምድርን ብቻ ሳይሆን የሰማይንም በሮችና መስኮቶች እየዘጉ እንደነበር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ የዜጐችን ሕይወት ሲያጠፉና ሲቀጥፉ ኑረው ሀገርን ጥለው አልኮበለሉም፡፡ እንደአንዳዶቹም ሞትን ለማምለጥ ሲሞክሩ ትቦ ውስጥ በሞት ሰይፍ አልተቀሉም፡፡ ይልቅስ ሀገርን ከሚያሳንስ፣ ሕዝብን ከሚያኮስስና ትውልድንም አንገት ከሚያስደፋ ታሪክ ለትውልድ ጥለው ከማለፍ ይልቅ በመለኮታዊ ችሎትም ሳይቀር ተጠርቀው ወዳሲኦል ጥልቅ መወርወርን መርጠዋል፡፡ ይህ የሀገርንና የህዝብን ክብር ያስቀደመ የመስዋዕትነት ጥግ ነው፡፡ ዛሬ የዚህ ዘመን ትውልድ ከአፄ ቴወድሮስ የወረሰውም ይሄንን ከፍ ያለ የመሰዋትነት ታሪክ ነው፡፡
ከ1935 ዓ.ም. በኋላ በባላባታዊና ባህላዊ ባለስልጣኖች ባንድ ወገን የውጭ ሀገር ትምህርት የቀሰሙና በሀገራቸው ለከት ያጣ ድህነት ቁጭት የተቃጠሉ ወጣት ኢትዮጵያን ባለስልጣኖች በሌላ ወገን መካከል የነበረው ትንቅንቅ ከቴወድሮስ ሀገርን የማዘመን ህልም ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገስት ኃይለስላሴ ሚዛን ለመጠበቅ ሲሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው ፍትጊያ እንዲቀጥል ቢፈልጉም ውሎ አድሮ ግን ዳፋው ህልውናቸውን ጭምር የሚጠይቅ ሆኖዋል፡፡
ከመቶ ዓመት በኋላ የሥጋና ደም ብቻ ሳይሆን የዕምነትም ወንድም አማቾቹ ገርማሜና መንግስቱ ንዋይም ቴወድሮስ ያማጡትን ሀገርን የማዘመን ምጥ ያምጡ ዘንድ ተገደው ነበር፡፡ ቴወድሮስ በመጨረሻዋ ሰዓት ለእንግሊዞች እንዳሉት “እናንተ ያሸነፋችሁኝ በስርዓት የሚመራ ህዝብ ስላላችሁ ነው” ብለው ነበር፡፡ ቀደም ብለው ይኸንን ቁጭታቸውን የሚያስታግስ የትምህርት ሥርዓትንም ሆነ የተግባቦት መስመር መዘርጋት አልቻሉም፡፡ ይልቅስ ህዝቡ ለምን ህልሜን አያልምም? ለምንስ ምጤን አያምጥም? ሲሉ ጨከኑበት፡፡ ጭካኔያቸውም ይገባቸው ነበርና መልሰው “ፈጣሪዬ ሆይ ምነው ወሰደኸኝ ህዝቡን ብታስርፈው” ይሉ ነበር፡፡
እንደ አፄ-ተዎድሮስ የከፋ ባይሆንም እነ-ጄኔራል መንግስቱም የገጠማቸው ተመሣሣይነት ነበረው፡፡ ሕዝቡ ብዙም ህልማቸው የገባው አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ጄኔራል መንግስቱ ይግባኝ እንደማይጠቅ በፍርድ ቤት ባደረገው ንግግር የሚያስገርም ትንቢታዊ ንግግር የተናገረው፡፡ “ወዮ ለእናንተ፣ ወዮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳቤ የገባው ቀን ወዩ ለእናንተ” ብሎ ነበር፡፡ ጄኔራል መንግስቱ ወደ ንጉሠ ነገስቱ ይግባኝ እንደማይልና ይልቅስ እንደእርሱ ለዓላማ ሲሉ ወደተሰው ወንድሞቹ ለመሄድ እንደናፈቀ ገልፆ ከሞት ከማፈግፈግ ይልቅ ወደመት ሲቸኩል ታይቷል፡፡ ሰቅራጥስ ለእውነት ሲል ከሞት ጋር እንደተጠበቀ ጀኔራል መንግስቱም ወደ ሞት ናፈቀ፡፡
ዛሬ ድረስ አያሌዎች የመደራጀትን አስፈላጊነት አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ገርማሜ ንዋይ ምንአልባትም የመደራጀትን አስፈላጊነት ቀድሞ በመረዳት ማህበሮችን በመፍጠር የመደረጃት ሙከራ ቢያደርግም “አሁን ድረስ የዘለቀው የመሰነጣጠቅ አባዜ በጊዜው ችግር ሆኖበታል፡፡ ቴወድሮስ ህዝብ ህልማቸውን አልረዳ ሲል በብስጭት እርምጃ ይወስዱ እንደነበረው ሁሉ እነጀነራል መንግስቱም መፈንቅሉ መንግስቱ መክሸፉን ሲረዱ በብስጭት የሥርዓቱ ጐምቱ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ወስደዋል፤ ያልተገባ ቢሆንም፡፡
ቴዎድሮስ በፀጋዬ ገብረ መድህን ተወኔት “እውነት ትውልድ ይፋረደኝ” እያለ እንደቃተተው ሁሉ እነጀኔራል መንግስቱም የተስፋ አይኖቻቸውን በለጋ ተማሪዎች ላይ ያሳረፉ ይመስላሉ፡፡ ከመንፈቅለ መንግስቱ ሙከራ በፊት በ1951 ዓ.ም. የኮሌጅ ቀን ሲከበር የሕዝብን ብሶት ማንሳት የጀመሩት ተማሪዎች የእነርሱን ዓላማ አንግበው እንደሚንቀሳቀሱ በልባቸው የማይናወፅ እምነት ያሳደሩ ይመስላል፡፡ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በኢትዮጵያ በሕግ የተገደበ (Constitutional Monarch) ለማቋሟም ብሎም ልማትን ለማፋጠን በይፋ ከመናገራቸውም በላይ ከተማሪዎች ጋር ትግላቸውን የማስተሳሰር ሙከራም አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ሲቀጣጠል ከእነጀነራል መንግስቱ መገደል በኋላ ብዙ ዓመታትን አልጠየቀም፡፡ የኮሌጅ ቀንን በማክበር የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ እየተቀጣጠለ መጣ፡፡ አፄ-ኃይለ ስላሴ በትምህርት የለውጥ መሣሪያነት በማመን ከየአካባቢው ለጋ ኢትዮጵያውያንን ወደ ትምህርት ማዕድ ሲሰበስቡ አንዳንዶች” ይኸንን የደሃ ልጅ አስተምረህ አስተምረህ በራስህ ላይ መዘዝ እንዳታመጣ” ብለዋቸው ነበር፡፡ ትንቢቱ ሰመረ፡፡ የተማሪዎቹ ትግል በንጉሡ ላይ አነጣጠረ፡፡ ለንጉሱ የኮሌጅ ቀን የውርደትና የዘለፉ ቀን ሆኖ ይታያቸው ገባ ፡፡
ይኸ ሁሉ ሲሆን ግን የተማሪወቹ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ የሚያሰኝ መልክ አልነበረውም፡፡ ምን አልባት የዴሞክራሲን ጉዳይ በሚመለከት ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አለማየሁ ለንጉሠ ነገስቱ የፃፉት ደብዳቤ የመጀመሪያዋ የፖሊቲካና የዴሞክራሲ ሰነድ ተደርጋ ልትቆጠር ትችል ይሆናል፡፡ ይልቅስ በወቅቱ የዓለማችንን ሰማይ እያመሰቃቀለ የነበረው የሶሻሊዝም አውሎ ነፋስ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተንሰራፋው የአገዛዝ ጥቅጥቅ ደመና ላይ ይነፍስበት ገባ፡፡ ተማሪዎቹ በሀገራቸው ሥር የሰደደ ድህነትና የአፈና ስርዓት በአንድ ወገን፣ ዓለምን እያካለለ ባለው የሶሻሊዝም ርዮተ ዓለም በሌላ ወገን መናጥ ጀመሩ፡፡ የተቃውሞ ጡጫቸው በንጉሡ ላይ ብቻ ሳየሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም አነጣጠረ፡፡
አፄ ቴወድሮስም ሆኑ እነገርማሜ ያለውን ታሪክ አክብረው ሲነሱ ተማሪዎቹ ግን ለኢትዮጵያ ታሪክ ክብር አጡ፡፡ ቢያንስ ኦሮሞዎች፣ አጋዎችና፣ ትግሬዎች ያልተሣተፉበትን ታሪክ ለማስታወስ ያስቸግራል፡፡ ተማሪዎቹ ግን የኢትዮጵያ ታሪክ የፊውዳልና የአማራ ታሪክ ብቻ አድርገው ገነዙት፡፡ አሁን ድረስ የሀገራችንን መሠረት እያናጋ ያለው ዘረኝነት የትውልድ ክር የሚመዘዘውም ከተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ምንም እንኳን የስልጣን ማማ ላፍ ለመውጣት ሲባል እና ልዩነትን ለመፍታት የሀይል ፍጥጫ ለዘመናት በኋላም የላንጋኖ እንደሁነኛ መሣሪያ ተቆጥሮ ጥቅም ላይ ቢውልም በሥነ-ፅሁፍ አማካኝነት መዘላለፍ ግን ምን አልባትም በተማሪዎች የተቃውሞ ትግል ውስጥ ሳይወለድ አልቀረም፡፡ በተለይም አንዳንዶች እንደሚሉት በብሔረሰቦች ጉዳይ ላይ የተፃፈው የጥላሁን ታከለ ፅሁፍ ተጠቃሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ረገድ በመዘላለፍ የተጀመረው የተማሪዎች ትግል በመገዳደል ተደመደመ፡፡
“ከእኛ ጋር ካልሆንክ ከእነርሱ ጋር ነህ” ብሎ ሌላውን ማጥቃትና መዝለፍ፣ ተመሣሣይ ዓላማና ፕሮግራም ይዞም ለስልጣን ሲባል በውሃ ቀጠነ እርስ በእርሱ መባላት የተለመደ የፖለቲካችን አካል ሆኖዋል፡፡ የተማሪውን እንቅስቃሴ ስንቃኝ በጣም ብዙ ህፀፆችን በትችት ወረጦ መርጠን መልቀም ብንችልም ለዓመኑበት ነገር ሁለንተናን አሳልፎ የመስጠት ደረጃቸው ከድክመቶቻቸው በተጓዳኝ ጐልቶ የሚቆም ትልቅ የመስዋዕትነት ማማ ሆኖ ይታያል፡፡ በለጋ እድሜያቸው ለአመኑበትና እውነት ብለው ሞትን እስከመናቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት በጣም ያስደምመኛል፡
የፖለቲካ ባህላችን የቀረጹ የተለያዩ ነገሮችን ማንሣት ቢቻልም ይኸንን በመሠለ አጭር ፅሑፍ ላይ መነካካት ግን አደጋው ከጥቅሙ ያመዝናል፡፡ ነገር ግን ጥቅል የሆነውን የፖለቲካችን ንጣፍ ላይ ጥቂት ነገር ማለት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ዘመናችን ድረስ የዘለቀው የህዝብና የገዥወች ግብግብ መሠረት አንድ ጉዳይ ላይ ይመረኮዛል፡፡ ህዝብ ሊኖረው የሚሻው የአስተደደር አይነት ገዥዎች ሊጭኑበት ከሚፈልጉት የአገዛዝ ቀንበር ጋር መጣጣም አልቻለም፡፡ ይህ በገዥዎችና በተገዥዎች መኮከል ያለውን ልዩነት ያሰመረና የተቀውምና የድጋፍ መሠረትም ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ ገዥዎችም ህዝብም አንዱ በሌላው መገልገል ይፈልጋሉ፡፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የሉዓላዊ ስልጠን ባለቤትነቱን፣ የሀገሩና የህልውና ባለቤት መሆኑን ማስረገጥ ይሻል፡፡ እስካሁን የዘለቀው የፖለቲካችን ችግር መሠረቱ በዋናነት ይኸው ነው፡፡ የህዝብ ሉዓላዊነት ሳይወለድ ዘመን ጠገቡ የአገዛዝ ልዕልና ቀንሷል፡፡
ፖለቲካ የተለያዩ የሕዝብ ጥቅሞችና ፍላጐቶች ታርቀውና ተቻችለው እንዲሄዱ ሁነኛ መሣሪያ ቢሆንም ተግባር ላይ ማዋል አልተቻለም፡፡ ፖለቲካ የመወጋገዣና የተቀርኖ መፈልፈያና የጥላቻ ግንብ መሰረት ከመሆን እንዲዘል አልፈቅድንለትም፡፡
ለዚህም ይመስላል በአገዛዞችና በህዝብ መካከል ፍርሃትና አለመተማመን የነገሠው፡፡ ፖለቲካችን ህዝቡ መብቱን እንዲጠይቅ የሚያበረታታ ሳይሆን ወገቡን ሰብሮ ለገዥዎች ዙፋን ይሆን ዘንድ የሚገፋፋ ነው፡፡ ገዥዎች እንዲገዝፉ ህዝብ ለእነርሱ እንዲነጠፍና እንዲኮስስ የሚያደርግ ግንኙነት ነው፤ ከጥንት እስከ አሁን፡፡ ለዚህም ነው በአምናችን፣ በዘንድሮአችንና በከርሞአችን መካከል ብዙም ልዩነት የማናየው፡፡
ምን አልባት የከፋ የከፋውን ብቻ እያየን ከበጐ ነገራችን ጋር እንዳንተላለፍ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የእይታ መነፅራችንን የኢትዮጵያ አገዛዞች ከህዝብ ጋር የነበራቸውን የግንኙነት መስመር በህገ-መንግስት መሠረት ላይ ለመዘርጋት ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ ወደዚያው እናዙር፡፡ ይህ ተግባር እንደበጐ ሙከራ ቢወሰድ ክፉት የለውም፡፡ በቀደመው የታሪካችን ክፍል ከ13ኛው እስከ 20ኛ ክፍለ ዘመን ክብረ-ነገስትና ፍትሀ-ነገስት በሚሉ ሁለት ድርሳናት ላይ ተመስርተው ህግና ሥርዓትን ለማስፈን ሙከራ ያደረጉ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን በተለይም በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በዘመኑ ከነበረው የጃፖን ህገ-መንግስት እንደተቀዳ የሚነገርለት ህገ-መንግስት በ1923 ዓ.ም. መውጣቱን እናያለን፡፡ ይህ ህገ መንግስት ሀገሩንም ህዝቡንም ጠቅሎ ለንጉሡ የሚያስረክብ ሲሆን ለህዝብ ያጐናፀፈው መብት ዜግነትን ብቻ ይመስላል፡፡ በ1947 የወጣው ህገ-መንግስትም ቢሆንY የስልጣን ምንጩ ሕዝብ ሳይሆን መለኮት መሆኑን ያስቀጠለ ቢሆንም ተግባር ላይ በሚገባ አልዋለም እንጂ የተለያዩ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን የተካተቱበት ነበር፡፡
ብዙዎች በቁጭት የሚያነሱት በአገዛዙ ላይ የተቃውሞው አንቅስቃሴ ተፋፍም በቀጠለበት ወቅት በሀምሌ 30/1966ዓ.ም ተረቆ የበረው ህገ-መንግስት ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ ምን አልባትም ከዚያ ዘመን እስከአሁን ከምንዳክርበት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር አረንቋ ሊያወጣን የሚችል ወይንም እንዳንዘፈቅ የሚያደርግ መሣሪያ ይሆን ነበር፡፡ ይሁን እንጁ ተፋፍሞ የነበረው የአቢዮት እሳት የረቂቅ ህገ-መንግስቱን ህልውና ብቻ ሳይሆን የገዥዎችንም ህልውና አከሰመው፡፡ የህልመኞቻችን የሊበራል ዲሞክራሲ ህልም በህልምነት ቀረ፡፡
የደርግ ህገ-መንግስትም የስልጣን መሠረት እግዚዓብሔር ሳይሆን ሰፊው ህዝብ ነው አለ፡፡ አክሎም በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀስ 1 በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስልጣን ከህዝብም የሰርቶ አደሩ ነው ሲል ደነገገ፡፡ በሰራተኛው ስም ደርግ የአፈ ሙዝን ልዕልና ከፍ አድርጐ አውለበለበ፡፡ የአሁኑ የኢህአዴግ አገዛዝ ደግሞ የስልጣን ምንጭ እግዚአብሐር ወይንም ህዝብ ነው አላለም፡፡ ካስማውን ጐሣ ላይ ተከለ፡፡ የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የተሰጠው ለህዝብ ሳይሆን ለየብሄሩ በየግል የሚታደል ሆነ፡፡ ኢህአዴግ ደጋግሞ ሊነግረን እንደሞከረው ህዝብ የመከረበትና ያፀደቀው ህገ-መንግስት አይደለም፡፡ የሕገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሦ እንደሚሉን ውይይቱ የተደረገው በኢህአዴግና በአንዳንድ ገለሠቦች መካከል ነበር፡፡ ያም ሆኖ እንኳን አጠቃላይ የህገ-መንግስቱ ረቂቅ ለህዝብ ቀርቦ ውሳኔ ህዝብ አልተሰጠበትም፡፡ የህዝብ የሉዓላዊነት የስልጣን ባለቤትነት ሳይሆን የገዥዎች ልዕልና ቀጠለ፡፡
ቃልና ተግባሩ ተጣጥመው ባያውቁም በኢህአዴግ ሕገ መንግስት አያሌ የመብት ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደሌሎቹ ህገ-መንግስቶች ሁሉ ዜጐችን ይቅርና ህገ-መንግስቱ እራሱንም ከዘመኑ አንጋቾች መታደግ አልቻለም፡፡ አሁንም ዜጐች ከወረቀት በዘለለ የሉዋዓላዊ ሰልጣን ባለቤት መሆን አልቻሉም፡፡ አገዛዝም የአፈና እንጂ የነፃነት ምኩራብ ሊሆን አይችልም፡፡ አልቻለም፡፡
ከ13ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ክብረ ነገስት ፤ ፍትሀ ነገስት ፤ ጉባኤ ሊቃውንት እና ህገ ስርዎ መንግስት ( የመንግስት አስተዳድር መመሪያ ) የሚባሉ ሰነዶች የሰላምም ሆነ የጦርነት መመሪያ ሆነው እንዳገለገሉ ሁሉ ህገመንግስቶችም በዋናነት የህዝብን መብት ለማክበር ሳይሆን የአገዛዞችን ህልውና ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ጥቅም ላይ ውለዋል ፡፡ የህዝብን ጥቅምና መብቶች የሚያስከብሩ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ብዙውን ጊዜ ውቅረ መንግስቱ የመርጋት ችግር ታይቶበታል -ይታይበታል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው አጼ ቴድሮስ ትልቅ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ የአረጋውያንና በየጎጡ የመቧደን አዙሪት ውስጥ የወደቀውን ሀገር በማዋሃድ የተሻለ ውቅረ መንግስት ላይ ጠንካራ ሀገርን መገንባት ነበር፡፡ ይህ ህልምም ቢሆን በሙላት አልተወለደም፡፡
አገዛዞቹ የቅርጽ እንጂ የይዞት ልዩነት አልነበራቸውም ፡፡ ህዝብ ሁልጊዜም ለአገልጋይነት እንጂ ለተገልጋይነት አይታጭም ፡፡ በዜጎች እና በአገዛዞች መካከል የግንኙነት መስመሩን ለመዘርጋት የሚዘጋጁ ሰነዶች ህዝብ ያመነባቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ሳይሆኑ ህዝብ እንዴት መገዛት እንዳለበት አበክረው የሚያሳዩ ናቸው ፡፡ ያ ማለት በሀገራችን ውስጥ ምንም አይነት የዲሞክራሲ ተሞክሮ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም፡፡ የሚገባውን ያህል ያልዘመርንለትና ለዓለም ያላስተዋወቅነው የገዳ ዲሞክራሲ እና በደቡብ በሀገራችን ክፍሎች አንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረቱ አስተዳድራዊ መስተጋብሮች ነበሩን ፡፡ የህዝብ ፈቃድ መኖር እና አለመኖር አገዛዞች የሚያወርዱት አስተዳድራዊና ፖለቲካዊ መመሪያዎች እንዲሳኩ ወይንም እንዳይሳኩ የማድረግ አቅም አለው ፡፡ ለዚህም ነው ሀገራችን ለዘመናት ባለችበት የምትረግጠው፡፡ ህዝብ ስለችግር፣ ጥቅሞቹ፣ መብቶቹና ተስፋዎቹ መምከር በእነርሱም ላይ መወሰን ባልቻለባት ኢትዮጵያ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ከባብ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የዛሬ 60 እና 70 አመት ከዚያም በቀደሙ አመታት ያነሳናቸው አጀንዳዎች ዛሬም አጀንዳዎቻችን ናቸው ፡፤ የትላንቱን ከዛሬ የዛሬውን ከነገ የምናስተሳስርበት የርዮት ድር የለንም ፡፡ አምናችንን እና ዛሬያችንን ተደባልቀዋል ፡፡ ነገአችንስ እንዴት ይሆን? ካለፈው እና ከዛሬው ባልተማርን መጠን ነጋችንን ከትናትና ከዛሪያችን ጋር መመሳሰሉ አይቀርም ፡፡
ከአላሚዎቻችን በመማር ነገአችንን የተሻለ ማድረግ ይገባል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው የቴድሮስ ሀገሩን ከዘመነ መሳፍንት አዙሪት በማውጣት ጠንካራ፣ የረጋ እና የዘመነ ሀገርን የመፍጠር ህልም ነገን የተሻለ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከዚያም በኋላ ከአድማሳቸው ባሻገር ያለውን አለም ስልጣኔ ምን ላይ እንደደረሰ በአካል በመገኘት ያረጋገጡ ኢትዮጲያውያን ህልምም ኢትዮጵያን የማዘመን ህልም ነበር ፡፡ እነጀነራል መንግስቱ ንዋይ አያሌ ዘመናትን ካስቆጠረው ዘውዳዊ አገዛዝ ጋር ግብግብ የገጠሙት ነገን የተሻለ ለማድረግ ከሰነቁት ህልም ጋር የተቆራኘ ነው ፡፡ የኢትዮጲያ ተማሪዎች መሬት ላራሹ፣ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ይከበርና ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም የሚሉ መፈክሮችን አንግበው የወጡት በራሳቸው አውድ መሰረት ነገን ለህዝባቸው የተሻለ ለማድረግ ነው ፡፡
በእርግጥ ጊዜና ሁኔታ ተመቻችተውላቸው ያሰቡትን እርምጃ በዘመናቸው መራመድ ቢችሉ ምን ይፈጠር ነበር? የሚለውን መመለስ እንዳንችል ሁኔታዎች አይፈቅዱም ባልተፈጸመ ነገር ላይ ፍርድ መስጠት ተገቢ አይሆንም ፡፡
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን የማስፈን ህልም ካልተወለዱ ህልሞቻችን አንዱ ነው ፡፡ እነጀነራል መንግስቱ የንጉሳዊ ስርአቱን ስልጣን በመገደብ የተሻለ መንግስት ለመመስረት ቢያልሙ ቢሳካላቸው ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊት ያደርጓት ነበር ወይ ? የሚለውን ጥያቄ በአውንታ ለመመለስ የሚያበቃ ማስረጃ የለንም፡፡ የሀምሌ 30/1966ቱ ሊብራል ህገ መንግስት ቢታወጅ ኢትዮጲያን የዲሞክራሲ ምድር ያደርጋት ነበር ወይ ? ከግምት ያለፈ መናገር አንችልም ፡፡ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም የሚለው መፈክር ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን እንመስርት ማለት ነበር ? ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ በሶሻሊዝም እርእዮት አለም ፍቅር የተነደፉ ወጣቶች የህዝብን ሉአላዊነት የሚያረጋግጥ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ይፈጥር ነበር ብዬ መቀበል ከፍ ያለ የዋህነት ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ማርክሊዝም ህዝብን በሀይል ለአንድ ዓላማ ማስገዛት እንጂ የህዝብን ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ማድረግ አይደለም ፡፡
የተማሪዎች ትግል ካፈራቸው የፖለቲካ ቡድኖች አንዱ የሆነው ህዝባዊ ሃርነት ትግራይ ( ህውሀት ) ስለዲሞክራሲ ሲባል አያሌዎች ዋጋ ከፍለዋል ቢልም በተግባር የምናስተውለው የቀድሞው የአገዛዝ ስርአት በአዲስ ትረካ (narration) ሲቀጥል ነው ፡፡ በትግሉ ወቅት ህይወታቸውን የከፈሉ የህውሀት ታጋዮች ዛሬ ጓደኞቻቸው በኢትዮጲያ ህዝብ ጫንቃ ላይ የጫኑትን የአገዛዝ ቀንበር ቢያዩ ምን ይሉ ነበር? ምን አልባት የተማሪዎች ትግል በጥቂት የደርግ ወታደሮች እንደተነጠቀ ሁሉ የህውሀት ትግልም የጥቂት አጤዎች መጠቀሚያ ከመሆን አልዘለለም፡፡
በ1983 ዓ.ም በአብዮት የመጣው አገዛዝ ሌላ አብዮት ባፈረጠመው አገዛዝ ሲተካ በእርስ በእርስ ጦርነት የተዳከመችው ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ወዴት ያመራሉ? የሚለውን ጥያቄ ቁርጥ መልስ አልነበረውም፡፡ ብዙዎች የኢትዮጵያን እጣ በአውንታዊ ይወስናል የተባለው የሽግግር መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች ያላካተተ ከመሆኑም በላይ የየብሄሩ ተወካዮችን በመደርደር በዲሞክራሲ ላይ የሚሰራ የአገዛዞች የሸፍጥ ጉዞ ተጀመረ፡፡ የሽግግር መንግስቱ ሁነኛ አካል ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ወጣ ፡፡ በመጣንበት መንገድ መርገጣችን ቀጠለ ፡፡
አገዛዙ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተነስቶ ወደ ሊብራል ዲሞክራሲ አመራለሁ ሲለን ለመሞኘት ተዘጋጅተን ጠብቀነው፡፡ ጋዜጠኞች ጋዜጣዎችን ማተም ጀመሩ፡፡ እንዲያውም አገዛዙ አውቆ በነፃነት እንዲጽፉ እያደረገ ነው እስኪባል ድረስ በጎ ጅማሪዎች ታዩ፡፡ ፓለቲከኞች የፓለቲካ ማህበሮችን ፈጠሩ፡፡ አለም አቀፍ ማህበረሰቡም በተግባራዊ ሂደት አገዛዙን ለመቀየር (Constructive engagement) በሚል ወዳጅነት ሽር ጉድ ማለቱን ተያያዘው፡፡ የአገዛዝ ወፍጮ ድምፅ ከሩቅ ድረስ ቢሰማም ቋቱ ላይ ግን ጠብ የሚል ጠፋ፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊቢራል ዲሞክራሲን ይወልድ ዘንድ ማርያም ማርያም ብንልም የተፈጥሮ ህገ አሸናፈ፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እየደጋገመ እራሱን ወለደ፡፡
በሁሉም ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊብራል ዲሞክራሲን ይወልዳል በሚል ተስፋ ብዙዎች በአዋላጅነት የተሰበሰቡበትን ታሪካዊ ወቅት 1997ን ዛሬ እንደታሪክ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ በቦታው ባትኖሩም እንኳን በያላችሁበት ማሪያም ማርያም ስትሉ ነበርና፡፡ የዴሞክራሲ የመወለድ ጭንቅ አገራችን ሰቅዞ ቢያሰቃያትም ሕይወቷን አልጠየቀም፡፡ የዲሞክራሲ ሺል ግን በትክክለኛ መንገድ ከእውነተኛ እና ትክክለኛ ዘር አልተገኘምና ብርሀን ሳያይ ተጨናገፈ ፡፡ ሳይወለድ ቀረ፡፡
ዲሞክራሲን የተራቡ ኢትዮጵያውያን ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ ውጪ ሀገር ልደቱን ሊያከብሩና ሊዘክሩት የነበረው የዲሞክራሲ ንጋት ለዘመናት በዘለቀው የአገዛዝ ባሩድ ጽልመት ለብሶ ዜጎች የነበራቸው የተስፋ ሙላት ወደ ጥልቅ ብሶትና የተስፋ እጦት ተቀየረ ፡፡ አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ማጎሪያ ካንፖች ተጓዙ፤ የህይወትን እሸት ለመቃም የተዘጋጁ ወጣቶች በአገዛዙ አፈር በሉ ፡፡ የህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የመሆን ትግል በአገዛዙ ፈርጣማ ጡጫ ድባቅ ተመታ ፡፡ ህዝብ አምጦ የወለደው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋነኛ የአገዛዙ ሰለባ ሆነ ፡፡
የአገዛዙ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ባቡር የማስመሰያ ጭንብሉን አውልቆ በአፈና ሀዲዱ ላይ መትመም ቀጠለ፡፡ የኋልዮሽ ተምዘገዘገ፡፡ በዚህ የኋልዮሽ ጉዛ ፍርኃትን ሰብረው እና ሞትን ንቀው የሚውተረተሩ ኢትዮጲያውያንን ማደን፣ ታፔላ እየለጠፉ መቀመቅ ማውረድ የሚመጻደቅበት የጀግና ውሎ አደረገው ፡፡ በጨለመበት ሰአት ከአለም እንደሚሰወር መናኝ ለአመታት ከህዝብ፣ ከወገን እና ከሚያባቡ ልጆቻችን ተለይተን አመታትን ተጋፈጥን ፡፡ እድሜ ይፍታህ ተባልን፡፡ እድሜን የሚሰጥ ፈጣሪ እንጂ ሰው አይደለም፡፡ ውሳኔው አልሰመረም፡፡ የትግሉ መርዘም እና ማጠር በህዝብ የትግል ጽናት እንጂ በገዥዎች እብሪት አይወሰንም በመጨረሻም ለዛሬ ቀን በቃን፡፡
ዛሬ ጭላጭል ይታያል፡፡ አገዛዙ የመጣበት መንገድ የትም እንደማያደርሰው የተረዳ ይመስለኛል፡፡ ለጋ ወጣቶችን ለህዝባዊ ልእልና ሲሉ ያላቸውን የመጨረሻ መስዋእትነት ህይወታቸውን በክብር ገብረዋል፡፡ ችግሩ አገዛዙ ትግሉ ጋብ ሲል ወደ ጥንካሬው የተመለሰ ህዝቡም ያከበረውና የደገፈው ይመስለዋል ፡ ይህን አይነት ግንዛቤ አሁንም ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ስህተት ይሰራሉ ፡፡ አሁን አገዛዙ ለህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ሊገዛ ግድ ይለዋል ፡፡
መፍትሄዎችን ሁሉ ከአገዛዙ እንስራ እንዲንቆረቆሩልን መጠበቅ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር መፍትሄን ከአንድ ሰው መጠበቅም አይገባም፡፡ ሁሉም የራሱን ጽዋ ሊያነሳ ይገባዋል፡፡ ተቀዋሚዎች እያለፈ ያለውን ዘመን ሳያልፍብን ልንሰራ ይገባል፡፡ ከዘመነ-መሳፍንትም ሆነ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚጨለፈውን ያለመቻቻልና የመለያየት ፖለቲካ ልንቀብረው ይኸው ዘመን ግድ ይለናል ፡፡ እልህ መጋባት ያለብን ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ እንጂ ለመጠፋፋት መሆን አይገባውም ፡፡
በሀገራችን ተጀምሮ የሚቋጭ ለውጥ ማምጣት አልቻልንም፡፡ ነገራችን ሁሉ ድንገቴ ( ) ታስቦ፣ ታልሞ የማይሰራና የማይዘልቅ ሆኗል፡፡ ዋነኛ ምክንያቱ ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ባለመሆኑ፣ ህዝብ ያላመነበት እንቅስቃሴ ደግሞ ለውጤት አይበቃም ፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ የኢትዮጵያ ገዢዎች ጠንካራ መንግስት ሊፈጥሩ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ የህዝብ መንግስታት ስላልሆኑ፡፡ ጠንካራ መንግስት የሚባለው በመሳሪያ ክምችት፣ በሰራዊት ብዛትና በታንክ ጋጋታ አይደለም፡፡ የህዝብን ይሁንታ ያገኘና ስር በሰደደ ፍትሀዊ ተቋማት መሰረት ላይ የተገነባ መሆን አለበት፡፡ የአፄ ኃይለስላሴ ዘውዳዊ ስርዓት በ6 ወራት ትቢያ ሲሆን ታይቷል፡፡ በአፍሪካ እንኳን ገዝፎ ይታይ የነበረው የደርግ ሰራዊት በአይናችን ስር የዶግ አመድ ሲሆን አይተናል ፡፡ ጥንካሬውን በተተበተበ የጎሳ መረብ ላይ የመሰረተው የዚህ ዘመን አገዛዝም ቢሆን በህዝብ ሰላማዊ የአመጽ ትግል አጽሙ ሲቀር ሁሉም ታዝቧል፡፡ ይኸኛውን ልዩ የሚያደርገው የሀገራችን መሰረትም ማናጋቱ ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የተረጋጋና የሰመረ ዘመን ይነጋ ዘንድ ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆን ይገባዋል፡፡
የአገዛዞች የአፈና ናዳ ቢበዛም በባህላችን እና ታሪካችን ያሉን የውል ተዘክሮዎቻችንና መስተጋብሮቻችን ስር የሰደዱ በመሆናቸው የናዳውን ውርጅብኝ ተቋቁመን ለማለፍ ትልቅ ሀይል ሆነውናል፡፡ እስከ አሁን ያለው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ትርጉም ያለመስጠት ወይንም የማበሻቀጥ ሂደት የትም አያደርስም፡፡ ተግዳሮቶቻችንን ተቋቁመን ተስፋዎቻችንን ለመጨበጥ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መሰማማት ይገባናል፡፡ በታሪካችን ሳንግባባ ሁላችን የምንወዳት ሀገር መገንባት አንችልም፡፡ አንዳችን የምንሰራውን ሌሎቻችን እያፈረስን እንቀጥላለን፡፡ ምክንያቱም የታሪክ ትንታኔዎቻችን ይለያያሉና፡፡ የታሪክ ህፀፅ የሌለበት ሀገርም ሆነ ሕዝብ የለም ልዩነቱ ከታሪክ ተምሮ መጭውን ዘመን በአስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባቱ ነው፡፡
ዛሬ የሀገር አንድነትን ውቅረ መንግስት ለመፍጠር ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉትን የአፄ ቴዎድሮስ 150 የሕልፈተ-ዓመት ስንዘክር ኢትዮጵያውን ጎሳቸውን እንደዮኒቨርስ ማየት በጀመሩበት ወቅት ነው፡፡
ዛሬ ጎሳን መሰረት ባደረገው የአገዛዙ ስሌት ሀገር ምድሩ ተናግቷል፡፡ ስነ ልቦናችን ተዛብቷል፡፡ አንዱ የእኔ ብሔር ሰው የሚለው ስልጣን ሲይዝ ሲደሰት ሌላው ስለነገው እርግጠኛ መሆን ይሳነዋል፡፡ የሰውን ልጆች ሁሉ ክብር የሚቀበል ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይገባናል፡፡ ሁሉም የሚደመጥበትና ሀገሬ ብሎ የሚኮራበትን ማዕቀፍ መዘርጋት ለነገ የሚያድር ስራ አይደለም፡፡ በጋራ ርዕዮት ላይ የጋራ ሀገር ለመገንባት መቀራረብ መወያየትና መግባባት ተቀዳሚው አጀንዳችን ሊሆን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የሚመክሩበት ጉባኤ መጠራት ይገባዋል፡፡ ለውጥ በተለይም መልካም ለውጥ በኢትዮጵያ ከኤሊም በላይ ያዘግማል፡፡ አሁን እንደቀድሞው እንቀጥል ዘንድ ዘመኑ አይደለም፡፡ የአጣዳፊ ለውጥ ዘመን ነው፡፡ አገዛዙ ሳይውል ሳያድር መድረኩን ሊያዘጋጅ ከሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ደግሞ ዘመኑን ለሚመጥን የፖለቲካ ለውጥ ሊዘጋጁ ይገባል፡፡
ሂሳብ የማወራረድ ባህልና ፍላጎት ዝቅ ብሎ ሊቀበር ይገባዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የፓለቲካ ችግሮቻችን የሚፈቱት በፓለቲካ እንጂ በህግ አይደለም፡፡ በእርግጥ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሕግ የበላይነት እንደንጣፍ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ነገር ግን ሁሉን ነገር በህግ ቋጥረን ልናልፍ አንችልም፡፡ በይቅርባይነት አንዳችን ለሌለው የእዳ ስረዛ ልናደርግ ይገባል፡፡ “እርቅ ደም ያድርቅ” እንደሚባለው ለብሄራዊ እርቅ እና ወንድማማችነት ልባችንን አጥበንና ታጥለን መገኘት አለብን፡፡
ይህ የእርቅ መንገድ ህዝባዊ ልዕልና የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ትኖረን ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን የእርቅና የወንድማማችነት መንገድ በከፋ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ሀገሮች ሲጠቀሙበት አይተናል፡፡ ጊዜው አንዳችን በሌለው ውስጥ ያለውን በጎ አስተዋፅዖ ለማስተዋል ለራሳችን እድል የምንሰጥበት ነው፡፡ ጊዜው የዴሞክራሲ ለውጥ ያመጡ ዘንድ ጥቂት ግለሰቦችን የምንጠብቅበት ሳይሆን ሁላችንም ሌላውን ሳንጠብቅ ሃላፊነታችንን የምንወጣበት ነው፡፡ ጊዜው በቲኒኒሽ ድሎች የምንኮፈስበት ሳይሆን የሁላችንም የዘመናት ናፍቆት የሆነውን የዴሞክራሲ ንጋት እውን ለማድረግ ያለንን ሁሉ የምንሰጥበት ነው፡፡ ቀይ ባህር አጠገብ ቆመናል፡፡ የአገዛዝን ባህር ከፍለን ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገስገስ ወይንም በቀጫጭን የልዩነት ድሮች ተተብትበን ባህሩ ውስጥ መስመጥ፡፡ እኔ የአገዛዝን ባህር በእርቅ፣ በፍቅርና በወንድማማችነት በትር ከፍዬ ሊሻገር ቆርጫለሁ፡፡ ነገር ግን ብቻዬን መሻገር አልችልም፡፡ ብቻዬንም መሻገር አልፈልግም፡፡ ወደ ተስፋችን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመሻገር የፀና የሰላማዊ ትግል መስመር ላይ አብረን ተስፋችን ሳንጨብጥ ወደኋላ ሳናይ ለመጓዝ አሁን እንቀሳቀስ፡፡ ዴሞክራሲን የማዋለጃው መንገድም ይኸው ነው፡፡
ፍትህ እንደ ቀትር ፀሐይ ፍቅር እንደ ሃይለኛ ጅረት ወንድማማችነትም እንደጉንጉን አበባ በኢትዮጵያ ላይ ይንገስ!
(ፍራንክፈርት፤ ግንቦት 2010 ዓ.ም)