>

የዴሞክራሲ ፍኖተ ካርታ አስፈላጊነት 

ሰማህኝ ጋሹ
አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ዶ/ር አብይ በቸርነቱ በየቀኑ በሚለቅልን ዜናዎች ላይ በመመስረት ያልተቆጠበ ድጋፍ በሚሰጥና ጉዳዩን በጥርጣሬ በሚያይ መካከል ያለ ፍትጊያ ነው። አብይ እያደረጋቸው ያሉት ነገሮች አይጠቅሙም ብሎ የሚከራከር ሰው ያለ አይመስለኝም። ትልቁ ችግር በወያኔ 27 አመታት የተደቆሰች አገር ከግጭትና ጭቆና ተላቃ ወደ ዴሞክራሴያዊ ስርአት ግንባታ እንዴት ልታመራ ትችላለች የሚለው ግልፅ የሆነ ፍኖተ ካርታ ስላልተቀመጠለት ነው። በተለይ በአገዛዙ በኩል በትክክልም እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነቱ ካለው ግልፅ የዴሞክሲ ፍኖተ ካርታ (road map to democracy) ማቅረብ አለበት። እስከ አሁን ከዶ/ር አብይ የሰማናቸው ጥቅል የሆኑና መቼ እና እንዴት እንደሚፈፀሙ ዝርዝር ፖሊሲ ያልተቀመጠላቸው ጉዳዮች ናቸው። እንዲህ ግልፅነት በጐደለው ንግግር ላይ ተመስርተን በየቀኑ እየተለካች በምትለቀቀልን የፕሮፓጋንዳ ሙዳ ሀሴትን የምናደርግ ከሆነ አገዛዙ እንደ እስስት እራሱን እየቀየረ መሆኑን ለመረዳት ይሳነናል።
ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሂደት ምን መምሰል አለበት ለሚለዉ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በበርማ/ምይንማር እየተደረገ ያለዉ የዴሞክራሲ ለዉጥ ሂደት ነዉ። ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆየዉ ወታደራዊ መንግስት ከፍተኛ የሆነ አፈና ሲፈፅም ከቆየ በሁዋላ ህዝቡ ባዳረገዉ ትግል የፖለቲካ ለዉጥ ማድረግ እንዳለበት  ተገደደ። ለዉጥ ለማምጣት አገዛዙ ቅድሚያ ያደረገዉ የዴሞክራሲ ፍኖተ ካርታ ማቅረብ ነበር። በዚህ ፍኖተ ካርታ አዲስ ህገ መንግስት ስለ ማፅደቅ፥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስለሚደረግበት ሁኔታና ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ያካተተ የለዉጥ ሁኔታ እንደሚያደርግ ቃል በመግባት የለዉጥ ሂደቱን ጀመረ። አለም አቀፍ ማህበረሰቡና የተቃዋሚ ሃይሎች ግልፅ አጀንዳ የቀረበ በመሆኑ ለለዉጡ ሂደት አብረዉ ለመስራት ተስማሙ። በዚህም የተነሳ ላለፉት 7 አመታት በአገሪቱ የትካሄዱት የፖለቲካ ለዉጦች ከፈተኛ ለዉጥ አሳይተዋል።
ለኢትዮጵያም የተሻለዉ ልምድ ይሄ ይመስለኛል። እዉነት አለቃ አብይ የለዉጥ ሀዋርያ ከሆነና ለዚህም ለዉጥ ፓርቲው ዝግጁ ከሆነ ወሳኙ ምእራፍ ይህንን የዴሞክራሲ ፍኖተ ካርታ ማቅረብ ነዉ። በዚህ ፍኖተ ካርታ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ስለመጥራት፥ በዘር ላይ የተመሰረተው ስርአት ያመጣዉን ችግር ለማስወገድ የሚያስፈልገዉን ህገ መንግስታዊ ለዉጥ፥ ባለፉት 27 አመታት የተፈፀሙትን ወንጀሎችና ዝርፊያዎች የሚያጣራ ኮሚሽን ስለማቋቋምና ተቋማትን የማጠናከር የመሳሰሉትን እርምጃዎች ሊያካትት ይገባል።
አገሪቱን ካለችበት ቀዉስ ለማዉጣት ይህንን ሂደት ማለፍ ግድ ይላል። ዶ/ር አብይ የሚወስዱዋቸዉ እርምጃዎች ለጊዜዉ ሁኔታዎች ለማረጋጋት የቻሉ ቢሆንም ስር የሰደደዉን የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ግን ጉልበት የላቸዉም። ስለዚህ አገራችን ከግጭት እንድትወጣ ካስፈለገ ትኩረታችን መሆን ያለበት መሰረታዊ ለዉጦች እንዲደረጉ መታገል ነዉ። ግልፅ የሆነ ፍኖተ ካርታ ባልቀረበበት ሁኔታ በየቀኑ ከሚለቀቅልን የፕሮፓጋንዳ ምግብ ላይ ብቻ ተመስርተን አብረን ብንነጉድ ዉጤቱ አስከፊ ይሆናል። ዶ/ር አብይ ለዉጥ ለማድረግ ጊዜ ሊሰጣቸዉ የሚገባዉ ከላይ የገለፅኩትን አይነት ፍኖተ ካርታ ሲያቀርቡልን መሆን ይገባዋል።
Filed in: Amharic