>

የአማራ ብሄርተኝነት 2.0 (ሚኪ አምሃራ)

ስለ አማራ ብሄርተኝነት፤ ስለ አመጣጡ፤ ስለ ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆን እና ስለጤነኝነቱ ብዙ ተወርቷል፡፡ የመጀመሪያዉ ምእራፍ ከዚህ አድርሶናል፡፡ የቀረ ካለ በሂደት እየተብላላ እየተሞረደ የሚያድግ ነዉ የሚሆነዉ፡፡ ቀጣዩ ምንድን ነዉ እንዴት ነዉ ከቲዎሪ ወቶ ወደ አደረጃጀት የሚገባዉ የሚለዉ እና ብሄርተኝነቱ ወደ ሁለተኛዉ ምእራፍ እንዴት ይሸጋገር የሚሉት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል [“A transition to a more advanced and superior version of the Amhara nationalism (2.0)]”፡፡ እናም ቀጣይ አቅጣጫወችና እስካሁን በስፋት ያልተሰራባቸዉን አካባቢ ለመዳሰስ እሞክራለዉ፡፡
አዲስ አበባ የብሄርተኝነቱ ማእከል
የአማራ ብሄተኝነት ባብዛኛዉ ደንበር አካባቢ ባለዉ ማህበረስብ ጎልቶ ይታያል፡፡ ምናልባትም ከሌሎች ህዝቦች አካባቢ በሚገናኝበት ሁኔታ የሚያጋጥመዉ ዘርን ተኮር ያደረጉ ሁኔታወች፤ የመሬት መቀማት፤ በቋንቋዉና በባህሉ መጠቀመን የሚከለክልና በጎረቤት ህዝቦች ቋንቋ እና ባህል ተገዠ እንዲሆን መደረጉ የሚያድነዉ አማራነቱን ማእከል አድርጎ መታገለል ነዉ ብሎ ሰለደመደመ ይሆናል፡፡ ለአማራ ብሄርተኝነት መፏፏም እና ማደግ ትልቁ ቦታ መሆን ያለበት አዲስ አበባ ነዉ፡፡ አዲስ አበባ 2/3ኛዉ አማራ ነዉ፡፡ ከ7 ሚሊየን ህዝብ በላይ ያለዉ ከተማ እስከ 4 ሚሊየኑ አማራ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ የአዲስ አበባ አማራ የተሻለ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና፤ የትምህርት እድል እና በኢኮኖሚም ያልተጎዳ ነዉ፡፡ ይህ ከተማ የአማራን ባለሃብቶች አቅፎ የያዘ ነዉ፡፡ ‘አማራ ክልል ላይ’ ቅሪት ከያዘ በኋላ በሰፊዉ ኢንቨስት የሚያደርገዉ አዲስ አባባ ላይ ነዉ፡፡ አብዛኛዉ የአማራ ሙሁራንም እዚሁ ከተማ ዉስጥ ተሸጉጠዉ ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት የአማራ ህዝብ ሀብት እዛ ዉስጥ አለ ማለት ነዉ፡፡ታሪካችንም እዛዉ ነዉ፡፡ የአለም ዲፕሎማቶችንና የአፍረካ ህብረትን አቅፎ የያዘ ከተማ ነዉ፡፡ የአማራን ድምጽ ጎንደር ላይ ወይም ራያ ላይ ሁነን በምንም ያህል ጩኸት ብንጮኸዉ አዲስ አባባ ላለዉ መንግስትና የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ እጅግ በለሰለሰች እና በማትሰማ ድምጽ ነዉ የምትደረሰዉ፡፡ ላይደርስም ይችላል፡፡ አዲስ አበባ እንደ መገናኛ በመሆን የአማራ ‘ክልል’ ህዝብን በሌሎች ክልሎች ዉስጥ ከሚገኙት የአማራ ማህበረሰብ ጋር ያስተሳስራል፡፡አዲስ አበባ ኔትወርክ መፍጠሪያ ማእከል መሆን አለበት፡፡ ቤንሻንጉል ላይ ወይም ወልቃይት ላይ ተገደለ ወይም የታሰረ አማራ የአፍሪካን ህብረት ስብሰባ ማስቆም መቻል አለበት፡፡ ወለጋ ወይም ቀብሪዳህር የሚኖር አማራ ላይ የደረሰች አንዳች ችግር የአዲ አበባ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማስቆም መቻል አለበት፡፡ ወለጋ ላይ ለደረሰ ችግር ጎንደር ላይ ብናምጽ መንግስትን ስጋት ዉስጥ ጥሎት መልስ የሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሁሉም ነገር ወደ አዲስ አበባ አምርቶ ከዛም ከአዲስ አበባ ነዉ ወደሌሎች አካባቢ መሰራጨት ያለበት፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት መቆጣጠሪያ ጣቢያዉና ቆጣሪዉ አዲስ አበባ መሃል ፒያሳ መሆን አለበት፡፡
አዲስ አበባ ላይ መንግስት በስፋት ገንዝብ ኢንቨስት በማድረግ ከ 20 በላይ ሬድዮ እና የቴሌቪዥን ቻናሎች እንዲሁም የቀልድ የሚመስሉ ብዙ ተከታይ ያላቸዉ የማህበራዊ ገጾች በመክፈት አዲስ አበባ ሰዉ እንጅ ዘር የለዉም በማለት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛ የሚዋልበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ፡፡ ይህ ታቅዶ የተቀረጸዉ 2/3ኛዉ አማራ የሆነበት ከተማን ሰጥ ለበጥ አድርጎ ለመግዛት፤ ስለወገኑ ስሜት እንዳይኖረዉ የማድረግና ከሌላዉ አማራ የመነጠል ስራ ነዉ እየተሰራ ያለዉ፡፡ ብሄርተኝነታችን በፍጥነት ለዉጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ፤ መንግስትን ለማንኮታኮት ከተፈለገ ይህን የፕሮፖጋንዳ መርፌ ተደራጅተን ልናስቆመዉ ይገባል፡፡ አማራ ክልል ላይ ዘርን መሰረት በማድረግ የተሰሩ ብዙ ግፎችን አዉጥተን ለህዝቡ ለራሱ ስላሳየነዉ በምንፈልገዉ መስመር እየሄደ ነዉ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ዘርን መሰረት ያደረጉ እጅግ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል ኮንዶሚኒየም ከማደል ጀምሮ፤ ከትዉልድ ቀየ እስከማፈናቀልና ከስራ እስከማባረር በአማራ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ይህን መረጃ አቀናጅተን እና አደራጅተን መልስን ለህዝቡ መመገብ ያስፈልጋል፡፡
የአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች አካባቢ ያሉ አማራወችን ከ mainland አማራ ጋር ማቆራኘት
በአሁኑ ሰአት አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገዉ ሌላ የትም ወቶ የማያዉቅ ቢያነስ ከ 2ሚሊየን በላይ አማራ አለ፡፡ ይህ ትዉልድ ከሌላዉ የአማራ አካባቢ ይልቅ ዱባይን ወይም ታይላንድን በተሻለ ሊያዉቅ ይችላል፡፡ ኦሮሚያ ተወልዶ ያደገ በሚሊየን የሚቆጠር አማራ አለ፡፡ እናት አባቱ አማራ ነን ሲሉት ካልሆነ በቀር አማራነት ምን እደሆን መነሻዉ የት እንደሆን ማያዉቅ አማራ ብዙ ነዉ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት አንዱ አላማዉ ይህን በተለያየ ቦታ ያለ አማራ በብሄርተኝነት ማእቀፍ ዉስጥ ገብቶ የማንነት፤ የቋንቋ፤ የባህል፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንዲያረጋግጥ እና በሌላዉ አካባቢም ያለዉ ወገኑን እንደራሱ ባመየት ለወገኑ ተጠቃሚነት አንዲሰራ ማድረግ ነዉ፡፡ ስለዚህም ይህን ሶስት ቦታ ላይ ያለ አማራን በብሄርተንነት ሰንሰለት ማያያዝ አስፈላጊ ነዉ፡፡ አማራ ክልል ዉስጥ ያለን አማራ ከማደራጀት ከክልሉ ዉጪ ያለዉን አማራ ማደራጀት እጅግ ወሳኝነት አለዉ ቅድሚያም ሊሰጠዉ ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ዉስጥ እና ሌሎች ክልሎች ያሉ አማራወች በመሰባስብ በተለያዩ የአማራ ህዝብ የሚኖርባቸዉ አካባቢዎች ትምህርት ቤት የመገንባት፤ ሆስፒታል የመገንባት፤ አካባቢችን የመጎብኘት ስራ በመስራት የብሄርተኝነቱን ገመድ ማያያዝ ይቻላል፡፡ ጅጅጋ ያለ አማራ ሰቆጣ ዉስጥ ያለ አንድ ትምህርት ቤት ቢቀይር፤ የአዲስ አበባ ያለ አማራ ተደራጅቶ በለሳ ዉስጥ አንድ ጤና ጣቢያ በስማቸዉ ቢከፍቱ ህዝቡን ያስተሳስራል ማለት ነዉ፡፡ ጎንደር ወይም ጎጃም ያለ አማራም ሰብሰብ ብሎ በተመሳሳይ መልኩ ከፋ አካባቢ በብዛት አማራ ያለበት አካባቢ የሆነ ነገር ሄዶ ሊሰራ ይችላል፡፡ ይህ መገናኘትና መነጋገር ነዉ ሊያስተሳስረን የሚችለዉ፡፡ በአራቱም አቅጣጫ በዚህ መንገድ ካስተሳሰርነዉ አንድ ቦታ ላይ የምትደርስ ጥፋት ሙሉ የኢትዮጵያን እስትንፋስ ማስቆም ሁሉ እንችላለን ማለት ነዉ፡፡ የሚመሰረተዉ ፓርቲ የአማራ ማህበረሰብ በርከት ብሎ በሚኖርበት አካባቢ ቢሮ የመክፈት እና አባላትን የማፍራት ሂደት ማመቻቸት አለበት፡፡ የሙያ ማህበራት እና የሲቪክ ድርጅቶችም እንዲሁ አሁን የአማራ ክልል ከተባለዉ ዉጪ የሚገኘዉን አማራ ተደራሽ የማድረግ ስራ መስራት ይሀን ትስስር ይበልጥ ድርጅታዊ ይዘት እንዲኖረዉ ያደርጋል፡፡
የአማራ እሴቶችን መመለስ
በባለፉት 27 አመታት ትልቅ ስራ የተሰራብን እሴቶቻችን በማጥፋት ትዉልዱ ቀዉስ ዉስጥ እዲገባ መደረጉ ነዉ(value crisis):: ለምሳሌ የአማራ ህዝብ የሚታወቅበትን የሽምግልና ባህል ሙሉ ለሙሉ እንዲፈርስ ሁኗል፡፡ ይህም ሽማግሌዎችን፤ የሃይማኖት አባቶችንና አስተማሪዎችን በገንዘብ እና በጊዚያዊ ጥቅም በመደለል እንዲያም ሲል በማስፈራራት የተለመደዉን የሽምግልና ባህላችን እንዳይሰራ አድርጓል፡፡ድሮ በአካባቢዉ ሰዉ ሲጣላ በፍጥነት የሚያስቆሙ፤ ወጣቱን የሚመክሩ፤ መንግስት ያልሆነ ነገር ሲያደርግ የሚያስቆሙ እና ጫና የሚያሳድሩ ሽማግሊወች ነበሩ፡፡ የሽምግልና እሴታችን ባይፈራርስ ኖሮ መንግስት ወታደሩን በፈለገዉ ሰአት ልኮ 120 ሰዉ በአንድ ከተማ ሊገደል አይችልም ነበር፤ አብሮ የኖረ ማህበረሰብ ቅማንት አማራ ተባብሎ ሰዉ አይሞትበትም ነበር፤ የመንግስት አመራር ለህዝብ ትምህርት ቤት ማሰሪያን፤ ሆስፒታል ማሰሪያን የተመደበ ገንዝብ ለራሱ ህንጻ አይሰራበትም ነበር፡፡ ዛሬ አስተማሪ ክፍል ገብቶ እያስተማረ ተማሪ ጫቱን ይዞ የሚቀመጠበት ወቅት ከትቂት አመታት በፊት ዉግዝና ነዉር የነበረ ባህሪ ነዉ፡፡ የአስተማሪ አፍንጫ በድብድብ የሚሰበር ተማሪ ነዉ ያለዉ፡፡ ይሄም በፖሊሲ ደረጃ ተይዞ ከአስተማሪዉ ይልቅ ለተማሪዉ ነጻነት ተሰጦት፤ አስተማሪዉ ማስተማሩ ላይ ሳይሆን 1-5 እያለ እተነታረከ እንዲዉል በማድረግ የተፈጸመ የትዉልድ ገደላ ነዉ፡፡ ይህ የአማራ እሴት አይደለም፡፡ ሽማግሌ፤ ትልቅ ሰዉ፤ የሃይማኖት አባት በገንዘብ ተታሎ የራሱን ማህበረሰብ የሚሸጥ እሴት የለንም፡፡እንደ አማራ ህዝብ ትምህርት ወዳድነት ተማሪ አስተማሪን ከክፍል የሚያባርር እሴት የለንም፡፡ ስለዚህም የማህበረሰባችን ስነልቦናዊና የሞራል ልእልና የምንመልስ ከሆነ የነበሩንን እሴቶች መመለስ ግድ ይለናል፡፡ ይህ የብሄርተኝነት አንዱ አካል ነዉ፡፡የአርማጭሆ ደም አድርቅ፤ የደባርቁ 7 ከዘራ፤ የወሎዉ ቅሬ እና የመሳሰሉት የሽምግልና ባህላችን ሊመለሱ ይገባል፡፡ በ values and principles ያልታነጸ ትዉልድ ስለ ብሄርተኝነት ወይም ሰለወጣበት ማህበረሰብ ሰፋ አድርጎ የማሰብ ፍላጎቱም ብቃቱም አይኖረዉም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ
እያደገ የመጣዉ የአማራ ብሄርተኝነት ወደ ግቡ ለማድረስ ከተፈለገ እያንዳንዱ ሰዉ በተደራጀ መልኩ ለማህበረሰቡ አስተዋጽዎ ማድረግ መጀመር ይኖርበታል፡፡ የብሄርተኝነት ዋና አላመዉም ተደራጅቶ ወደ ዉስጥ መመልከት ነዉ፡፡ ስለዚህም አሁን ያለዉን ኢነርጅ ወደ ስራ ለመቀየር በረድፍ በረድፉ መደራጀት አስፈላጊ ነዉ፡፡ አንደኛዉ የፖለቲካዊ አደረጃጀት ነዉ፡፡ ይህም ፓርቲ በመመስረት ወጣቱ፤ ሙሁሩ፤ ገበሬዉ ተስማምቶ በሚወጣዉ የአማራን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል የፖለቲካ አይዲዮሎጅ  እና ፖሊሲ በመንደፍ አስዋጽዎ ማድርግና መታገል ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ አሁን  የተጀመረዉ ፓርቲ የመመስረት እንቅስቃሴ ብዙ ሸክሞችን ያቃልላል፡፡ አዲሱ ፓርቲ በተለይም እስካሁን ድረስ በቴክኖሎጅዉ ምክንያት ልንደርስበት ያልቻልነዉን የገጠሩን ህዝብ በማደራጀት እና በማስተማር ትልቅ አስተዋጽዎ ኖረዋል፡፡
የፕሮፌሽናልና ሲቪክ ማህበራት አደረጃጀት
የአማራን ብሄተኝነት ይዟቸዉ የተነሳዉን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የማንነት እና የመሳሰሉት ጥያቄወች በፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይፈታም፡፡ ሁሉን ነገር ለፖለቲካ ፓርቲ መተዉ ፓርቲዉን ከሚችለዉ በላይ በመጫን እንዲከስም ለያደርግ ይችላል፡፡ በባለፉት ሶስት አመታት አግር ኳሳችን ላይ የብሄርተኝነቱን መልህቅ ጥለንበት እጅግ ከብዶት እና መሸከም እስኪያቅተዉ በመጫናችን ክለቦቻችን እንዲንገዳገዱብን አድርገናቸዋል፡፡ይህ በፖለቲካ ድርጅቱ ላይ መደገም የለበትም፡፡ ስለዚህም ብዙ የአማራ ባለሙያወች ማህበር በማቋቋም የአማራን ህዝብ ችግሮች በተደራጀ መልኩና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ አየሞገቱ እንዲፈቱ ማድረግ ነዉ፡፡ የአማራ ኢኮኖሚ ማህበር፤ የአማራ የህግ ማህበር፤ የአማራ ሴቶች ማህበር፤ የአማራ ተማሪዎች ማህበር፤ የአማራ ኢንጅነሮች ማህበር እና የመሳሰሉት፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የበጎ ፈቃደኞች ማህበር በማቋቋም ብሀብረተሰባችን ላይ ችግሮች እንዳይደርስ ቀድሞ በመስራት፤ ችግር ከደረሰም የሙያ ማህበራት በአንድነት መበመንቀሳቀስ ጫና የማድረግ እና ለተጎጅዉ አካል ድጋፍ በመስጠት ከፍተና ስራ መስራት ይቻላል፡፡ እኒህን ማህበራት በዋነኛነት በየየኑቨርስቲዉ ያሉ የአማራ ሙሁራንና ተማሪዎች በመመስረት አመታዎ ኮንፈርንስ በአማራ ከተሞች ላይ በማዘጋጀት፤ ለተማሪዎች ስኮላርሽፕ በመስጠት እና በመሳሰሉ ስራወች በመካፈል አማራን የመታደግ ስራ መስራት ይቻላል፡፡ አመታዊ ሪፖርቶችን የማዉጣት፤ መጽሃፍ የማሳተም እና ምርምሮችን የመስራት ስራም ይሰራል፡፡ብሄርተኝነት መንፈስ አይደለም አደረጃጀት ነዉ፡፡ በዚህ መንገድ መደራጀት ጊዜ የማይሰጠዉ ጉዳይ ነዉ፡፡
ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ጋር የሚኖረዉ ግንኙነት
የአማራ ብሄተኝነት የሌሎችን ህዝቦች ጥቅም እና ፍላጎት ያከብራል፡፡ በሚቀጥሉት ጊዚያቶች የአማራ የነበሩ መሬቶች ለምሳሌ አንደ ወልቃይት፤መተከል፤ራያ በሚመለሱበት ጊዜ በዉስጡ ያሉ የሌሎች ብሄሮች በቋንቋቸዉ የመማር፤ የመዳኘትና የመናገር ሙሉ መብት ይከበርላቸዋል፡፡ ከአማራ ህዝብ እኩል መብት በማንኛዉም መንገድ የኖራቸዋል፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎ እና ዉክልና ይረጋገጥላቸዋል፡፡ቋንቋቸዉ ባህላቸዉ እንዲያድግ በአማራ ላይ የደረሰዉ ግፍ እና በደል በማኝኛዉም ህዝብ ላይ እንዳይደረስ የአማራ ብሄርተኝነት በዋነኛት ዘብ የሚቆምለት ነገር ቢኖር ይህ ነዉ፡፡ ማንነትን መሰረት ያደረጉ በደሎች ምን ያህል የማህበረሰብ ቀዉስ እንደሚያመጣ ከአማራ ህዝብ በላይ ማንም አያዉቀዉም፡፡ ይህ አይደለም በሌላዉ ኢትዮጵያዊ ላይ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያሉ የተለያዩ ብሄሮች እንዲህ አይነት ነገር እንዳይደርስባቸዉ ይታገላል፡፡ የብሄርተኝነታችን ዋናዉ ማእከል ይህ ነዉ፡፡ አሁን ወደመደራጀት ስንገባ የህን ለህዝባችን የምናስተመር ይሆናል፡፡ ከዚህም ዉጭ በክልሉ ዉስጥ ያለዉን የቋንቋ፤ የሃይማኖት የብሄር diversity በማሳደግ የአማራ ህዝብ ትልቁ ህብቱ እንዲያደርገዉ እና እንዲንከባከበዉ ብሄርተኝነታችን አበክሮ ይሰራል፡፡
ሚዲያ
ሚዲያ የማህበረሰብን ችግር ነቅሶ በማዉጣት፤ በማስተማር እና የፖለቲካ ትርክትን አቅጣጫ በማስያዝ ከፍተኛ ሚና አለዉ፡፡ ስለዚህም ሚዲያ አገር ዉስጥ አስፈላጊ ነዉ፡፡ ቢቻል ሬድዮ እና ቴሌቪዥን የሚከፈትበትን ሁኔታ መፍጠር አለያ ግን መጽሄቶች፤ ጋዜጦችና ድህረገጽን ማእከል ያደረጉ ሚዲያወች ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ አዲስ ስታንዳርድን ብናየዉ በኦሮሞ ፖለቲካ ላይ ይህ ነዉ የማይባል ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡ ታማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን የአለም አቀፍ አዉታሮች ሁሉ ሲጠቀሙት አይተናል፡፡ እንደዚህ አይነት ታማኝ የሆነ ሚዲያ ለአማራ ህዝብ በጣም ወሳኝ ነዉ፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ዘርፍ በሰፊዉ ልምድ ያላቸዉ ሰወችና እና ታማኝ የሆኑ እንደ እነ  እስክንድር ነጋ አይነቱ የአማራ ሚዲያን ወይም አማራ ላይ ያተኮረ ሚዲያ በመክፈት የህዝባችን መወያያ መድረክ ፤ ብሄርተንነታችን የምናሳልጥበት እና ችግሮቻችን ወደ ዉጪ የምናወጣበት መንገድ እንዲሆን ማድረግ ነዉ፡፡ዲስፖራዉም የአማራ ሚዲያ መክፈት ከቻለ ባለዉ ነጻነት ተጠቅሞ ብዙ ነገር ማበርከት ይችላል፡፡ነገር ግን ከዲያስፖራዉ መጠበቅ አሁን አያዋጣም ሁሉም ነገር ባገር ቤት መሞከር እና ወደ መሬት መዉረድ አለበት፡፡ መስዋትነት ቢኖረዉም እስካሁን ከተከፈለዉ አይበልጥብንም፡፡
Filed in: Amharic