>

በወርሃ ግንቦት የመለስ/ኢህአዴግ ራዕይ ሲዘከር… (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ወሩ ግንቦት ነው፡፡ አስከፊው የደርግ አገዛዝ የተገረሰሰበት ወቅት፡፡ ግንቦት በደርግ ግብኣተ መሬት ላይ የኢህአዴግ አፋኝና ከፋፋይ የአገዛዝ ሥርዓት የተንሰራፋበት ታሪካዊ ወር ነው፡፡ ዘንድሮ የግንቦት 20 በዓል ሲከበር መድረኩን መለስ አይንጎማለሉበትም፡፡ ይልቁንም ከግንቦት ጋር ራዕያቸው ሊዘከር ይችላል፡፡ ግን የትኛው ራዕያቸው?
በእኔ እይታ፡- አቶ አቶ መለስ ያኔ በለጋ ዕድሜያቸው ከሌሎች የትግል ጓደኞቻቸው ጋር ነፍጥ አንስተው ጫካ ሲገቡ ምን ዓይነት ኢትዮጵያንና ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ነበር ለማየት የሚፈልጉት? የሚል ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊና ተገቢም ይሆናል፡፡
ወደኋላ መለስ ብሎ የህወሓትን ዓላማና ግብ ለፈተሸ አቶ መለስና ድርጅታቸው መላው ኢትዮጵያን የሚወክል የፖለቲካ አጀንዳና ራዕይ እንዳልነበራቸው መረዳት አይሳነውም፡፡ በወቅቱ የነበራቸውን ራዕይ የትግራይ ህዝብ ሊጋራው ስላልቻለና በታጋዩም ውስጥ ጥያቄ ስላስነሳ ብዙ ርቀት ሳይሄድ ቢሰረዝም የአቶ መለስና ድርጅታቸው ዓላማና ግብ “ነፃ የትግራይ ሪፐብሊክን ማቋቋም” የሚል እንደነበር አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ መላው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር በተቃረበበት በ1980ዎቹ መጀመሪያ የሲ.አይ.ኤ ባለሟል ከሆነው ፖል ሄንዝ ጋር ባደረጉት ምስጢራዊ ውይይት “ትግራይ የባህር በር እንዲኖራት እንፈልጋለን” በማለት ያ ጠባብና ድብቅ አጀንዳቸው በውስጣቸው መኖሩን አረጋግጠው ነበር፡፡
አቶ መለስና ድርጅታቸው “የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚመለሰውም ኤርትራ ነፃ ስትወጣ ነው” በሚል ሽንጣቸውን ገትረው የተከራከሩ ናቸው፡፡ ከዚህም አልፈው የትግራይ ወጣቶች ከሻዕቢያ ጎን ተሰልፈው የአንድነት ኃይሎችን እንዲወጉና በማይመለከታቸው ጦርነት ውስጥ እንዲማገዱ አድርገዋል፡፡
የኤርትራ የነፃነት ታጋዮች በወቅቱ ከነበረው የደርግ መንግሥት ጋር የመደራደር ፍላጎት ባሳዩበት ወቅትም እነመለስ “የኤርትራን ህዝብ ትግል ለማን ትታችሁ” በሚል ዳጎስ ያለ መጽሐፍ እስከመጻፍ ደርሰዋል፡፡ ጦርነቱ በፀረ-አንድነት ኃይሎች ከተጠናቀቀ በኋላም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ሉኣላዊት አገር እንዲትሆን  ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥረታቸው አፍርቶም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን አጥታለች፡፡
በ1990-91 በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ሳቢያ በብዙ አሥር ሺህ የሚገመቱ ወጣቶች እንደቅጠል ከረገፉና ግዙፍ የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት ከወደመ በኋላም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጥ የምትችልበትን መልካም አጋጣሚ እንደዋዛ አምክነዋል፡፡ በወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ የወጣውን የባህር በር ጥያቄ ለማዳፈን “አፋሮች ከፈለጉ ግመሎቻቸውን ውሀ ያጠጡበት” በማለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የህዝብ ፍላጎት ላይ ተሳልቀዋል፡፡
በወቅቱ የሌሎች አገሮች የፖለቲካ ታዛቢዎችና ተንታኞች ሳይቀር ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን የምታረጋግጥበት መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረላት ይገልፁ ነበር፡፡ አቶ መለስ ግን የባህር በር ማስመለስ ይቅርና ሠራዊቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የተቆጣጠራቸውን የኤርትራ መሬቶች ለቅቆ እንዲወጣ ነበር ትዕዛዝ የሰጡት፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት ድንበራችንን አልፈን የኤርትራን ሉኣላዊ ግዛት መድፈር ዓለማቀፍ መርህን በመጣስ ሊያስጠይቀን ይችላል የሚል ነበር፡፡
በአንፃሩ በሶማሊያ እስላማዊ ም/ቤቶችንና አልሸባብን ለመዋጋት ድንበር ጥሰው ሲገቡ ግን ወደ ኤርትራ ዘልቀው እንዳይገቡ የከለከላቸው መርህ መኖሩንም ያስታወሱ አይመስልም፡፡ ለነገሩ አቶ መለስ ከሁኔታዎች ጋር የሚገለባበጡ እንጅ ለመርህ የሚገዙ አለመሆናቸውን በርካታ አስረጅዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች አቶ መለስ ተቃዋሚዎቻቸውን አፍ ለማስያዝ የሚያቀርቡት መከራከሪያ “እኛ ከህዝቡ እንጅ ከመሬቱ ጉዳይ የለንም” የሚል ይዘት ነበረው፡፡ ነገር ግን አሁን ኤርትራ በተባለው ክልል የሚኖሩ አፋሮች “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” የሚለውን መርህ በመጠቀም ኢትዮጵያዊነታቸውን ለማረጋገጥ ለተባበሩት መንግሥታት የተማፅኖ ደብዳቤ ቢያቀርቡም አቶ መለስ “ጉዳያችን ከህዝብ ነው” የሚለውን ድርጅታዊ መርህ በተግባር ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ከሻዕቢያ ጋር የነበራቸው ፍቅር ሳይቀዘቅዝ በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ወታደራዊ ግንባር ፈጥረው ደቁሰውታል፡፡
አቶ መለስና ድርጅታቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ከአንድ መቶ ዓመት የዘለለ እንዳልሆነ ሲሞግቱና ኢትዮጵያ የ3ሺህ ዘመን የታሪክ ባለቤት ስለመሆኗ የጻፉ ምሁራንንም “ከፊውዳል ህብረተሰብ አዝማሪዎች” የማይለዩ በማለት ሲያናንቁ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
እንዳሰቡት ባይሳካም ከዓለም ገናና ሥልጣኔዎች አንዱን የሚወክልና አንፀባራቂ የሆነውን የኢትዮጵያን ታሪክ በማናናቅ ወደ ተራ ተረትነት ዝቅ ሊያደርጉት ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ የታሪክ ግንዛቤና ትንተና ብዙ ርቀት እንደማያስኬዳቸው ተገንዝበው በስተመጨረሻ እያቃራቸውም ቢሆን ነባሩን ታሪካዊ ግንዛቤ ለመቀበል ሳይገደዱ አልቀሩም፡፡
መለስና ድርጅታቸው የኢትዮጵያን ባንዲራም ከተራ “ጨርቅ” ያለፈ ትርጉምና ዋጋ እንደሌለው ሲገልፁና ሲያጣጥሉ እንደነበር ሌላው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅርና ክብር በቀላሉ ሊፋቅ/ሊሰረዝ ስላልቻለ ዛሬ የሰንደቅ ዓላማ ህግ ወጥቶ በየዓመቱ የባንዲራ ቀን ማክበር ተጀምሯል፡፡ አቶ መለስ ሲሞቱም በዚያች “ተራ ጨርቅ” ብለው ባጣጣሏት አራንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ባንዲራ ተጠቅልለው ሲቀበሩ በትዝብት ተመልክተናል፡፡
አቶ መለስና ድርጅታቸው ኢትዮጵያ “የብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች” እስር ቤት ናት የሚል ገዥ አስተሳሰብ በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የነበረውን ነባር አስተሳሰብ ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በርግጥ በየዓመቱ “የብሔረሰቦች ቀን” መከበሩ የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ረገድ የራሱ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን በነአቶ መለስ እምነት/እይታ የኢትዮጵያ አንድነት እነሱ ቅድሚያ ከሚሰጡት “የብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ጥያቄ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ጉዳይ (secondary issue) ነው፡፡ አቶ መለስና ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢነት ቢኖራቸው ኖሮ ከዚህ በተሻለ መንገድ “የአንድነት ቀን” በሚል የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እንዲሰባሰቡና ይበልጥ እንዲቀራረቡ ብሎም አንድነታችን ይበልጥ እንዲጠናከር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡
አቶ መለስ “የአየር ንብረት ለውጥን” የመሳሰሉ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በመጠቀም የአፍሪካና ሌሎች ታዳጊ አገሮች ተሟጋች ተደርገው ቢሳሉም በዓለማቀፍ መድረኮች ለመሳተፍ መሠረት ለሆነቻቸው ኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ግን ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ነው፡፡
እርግጥ አቶ መለስ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዳይነሳ ሽንጣቸውን ገትረው መከራከራቸው አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ “የኢትዮጵያ-ብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች”፣ “አገሪቱ” ከሚሉ አገላለፆች በቀላሉ መላቀቅ አልቻሉም፡፡ “የኢትዮጵያ ህዝብ”፣ “እኛ ኢትዮጵያውያን”፣ “ሀገሬ/ሀገራችን ኢትዮጵያ” የሚሉ አገላለፆችን ለመጠቀም እጅግ ሲከብዳቸው ታዝበናል፡፡
አቶ መለስና ድርጅታቸው ሌላው ቀርቶ የመላው ጥቁር ህዝብ መኩሪያ ለሆነው የአድዋ ድል እንኳ ተገቢውን ዋጋና ክብር ለመስጠት ሲቸገሩ አስተውለናል፡፡ የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የውስጥ ግጭቶቻቸውን ወደጎን በመተው ዳር እስከዳር ተጠራርተው በነቂስ የተሳተፉበትና ለመላው ጥቁር ህዝብ አርኣያና የነፃነት ፋና ወጊ መሆን የቻሉበት ከመሆኑም በላይ አንድነታቸውን ያረጋገጡበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአድዋ ድል በሁሉም ኢትዮጵያዊ መስዋዕትነት የተገኘና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ በመሆኑ በደማቅ ሁኔታ ልናከብረው ይገባ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አቶ መለስም ከህዝብ ጋር መገናኘት የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችል/ይገባ ነበር፡፡
ሆኖም ግን የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የአድዋ ድል የተመዘገበበትና ሌሎች በአገር ደረጃ ትርጉም ያላቸው ሁነቶች የተከናወኑባቸው ታሪካዊ ቀናት “ግንቦት 20”፣ “የብሔረሰቦች ቀን”ና ሌሎችም በሚከበሩበት መንፈስ ሲከበሩና ሲዘከሩ መሪዎቻችንም ሌላው ቢቀር ለህዝቡ ተገቢውን መልዕክት ሲያስተላልፉ ማየት አልቻልንም፡፡ ከዚህ ተነስተን እነዚህ ሰዎች መላው ጥቁር ህዝብ በሚኮራበት ታሪካችን የማይኮሩትና የህዝቡን ስሜት የማይጋሩት ለምንድ ነው? ይህን ስሜት ይዘውስ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ሊኖራቸው ይችላል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንገደዳለን፡፡
ምናልባት አንዳንድ ወገኖች የመለስን ራዕይ “የኢትዮጵያ ህዳሴ” ከሚለው “መሪ” ቃላቸው ጋር አያይዘው ሊያዩት ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ “የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚሉት ነገር ስለኢትዮጵያ ታሪክ ካላቸው ግንዛቤና ትንታኔ ጋር የሚጣረስና (self-contradictory) ተያያዥ ጥያቄዎችን የሚጋብዝ ነው፡፡ እነ አቶ መለስ ህዳሴ (Rennaisance) የሚሉት ለየትኛዋ ኢትዮጵያ ነው፤ የጥንታዊ ሥልጣኔና ገናና ታሪክ ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ወይስ እነሱ የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት ለሚሏት አገር? ትክክለኛና ግልፅ ታሪካዊ ግንዛቤ፣ እንዲሁም እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ሳይኖር አገራዊ ራዕይ መቅረፅ ይቻላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ነው፡፡
የአቶ መለስ አምላኪዎች እንደ መጨረሻ ካርድ ሊመዝዙት የሚችሉት እሳቸው ያስጀመሩትን ታላቁን “የህዳሴ ግድብ” መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የ“ህዳሴው ግድብ” ግንባታ በአቶ መለስ ቢጀመርም መቼና በማን ታቀደ? ከግድቡ ግንባታ ጀርባ ያለው ድብቅ ፍላጎትና ዓላማስ (hidden motive and objective) ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ወደጎን ብንተዋቸው እንኳ ከዚህ ይልቅ ቅድሚያ የምንሰጣቸው አንገብጋቢ ፕሮጀክቶች ወይም ብሔራዊ ጉዳዮች አልነበሩንም ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡
ይህን ጥያቄ የምናነሳው የግድቡ ግንባታ የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ሊፈጥር የሚችለውን ብሔራዊ ኩራት በመዘንጋት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በትክክል ከታሰበ “የባህር በር” ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ በትህትና ሊቀርብ ይቻላል፡፡ ምናልባት ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ከፀጥታ ሥጋት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታም ቢሆን በተለይ ግብፅ  ከምታራምደው አቋም አንፃር ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም አንፃር የባህር በር ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ ሁሉም ወገን የሚረዳው ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የባህር በር ብሔራዊ ደህንነታችንን ከማረጋገጥ፣ ዓለማቀፍ ግንኙነታችንን  ከማጠናከርና የተፅዕኖ ክልላችንን ከማስፋት አንፃር ያለው ስትራቴጂያዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
የባህር በር ባለቤትነታችንን ለማረጋገጥ እውነተኛ ብሔራዊ ስሜት ሰንቆ ታሪካዊ፣ መልካዓ-ምድራዊና ህጋዊ መብቶቻችንን መሠረት በማድረግ ከመከራከርና ከመደራደር ባለፈ 80 ቢሊዮን ብር እንዲናወጣ ግድ አይለንም፡፡ የባህር በር ባለቤትነታችንን የማረጋገጥ ጉዳይ ካለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ጠቅላላ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ አንፃር መሪዎቻችን ይህ ጥያቄ እንዳይነሳና ተዳፍኖ እንዲቀር የሚያደርጉት ጥረትና የሚከተሉት ስልት ለጥርጣሬ በር የሚከፍት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጀርባ ያለው ድብቅ ፍላጎትና ዓላማ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ግድ የሚሆነው፡፡
መለስና ድርጅታቸው የደሞክራሲ ወዳጆች እንዳልሆኑም በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ “የዴሞክራሲ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፣ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችላለች” በማለት ሲያስፈራሩን የነበሩት አቶ መለስና ድርጅታቸው የ97 ምርጫ የፈጠረው የለውጥ ማዕበል በታኣምር ሲተፋቸው ወደሌላ አቅጣጫ እጥፍ ብለው ማስፈራሪያውን “የልማት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው” በሚል ዜማ ቀይረውታል፡፡ ከዚህም አልፈው “የዳቦ ጥያቄው ያልተመለሰ ህዝብ ዴሞክራሲ ምኑ ነው” በሚል የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ሊሸብቡን እየሞከሩ ነው፡፡ የዚህ ምስጢሩ ሌላ ሳይሆን የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን ማፈንና በሥልጣን ላይ መቆየት ስለሚያስችላቸው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
የአቶ መለስና ድርጅታቸው ራዕይ በኢትዮጵያ ምድር ጠንካራ ተቀናቃኝ የሌለው የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ማስፈን ነው፡፡ ይህን ዓላማና ግብ ለማሳካትም የፀጥታ ኃይሎችን ከማጠናከርና መዋቅራቸውን ከማስፋት ባለፈ አፋኝ የሕግ ማዕቀፎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በዚህ መንገድ “ልማታዊ” መንግሥታችን የህዝቡን ሰብኣዊና ዴሚክራሲያዊ መብቶች፣ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የሆነውን የለውጥ ጥያቄ እየደፈጠጠ በ“ፈጣን ዕድገት” እየጋለበ ነው፡፡
አቶ መለስና ድርጅታቸው ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ? የሚለው ጥያቄም እንደዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የአቶ መለስና ድርጅታቸው ፍላጎት “አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በተናጠል ብቻውን ሆኖ ስለአንድ ጥያቄ ሲያስብ … ዞሮ ዞሮ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቋም ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ” እንዲፈጠር ነው፡፡ በእሳቸው እምነት “አብየታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በሁሉም አቅጣጫ ሰርፆ በመግባቱ የተነሳ ሰው በየግሉ ሲያስብ ከሱ ውጭ ማሰብ የማይችልበት ደረጃ ላይ” ይደርሳል፡፡
ነገር ግን ይሄ ባንድ ወቅት “ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን” ከሚለው ግብዝ አስተሳሰብ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ ረቂቅ የሆነውን የሰውን ልጅ አስተሳሰብ መግራት ባይቻልም ማሰቡ በራሱ አደገኛ ነው፡፡ የአቶ መለስና ድርጅታቸው ራዕይ እንቅስቃሴና ድርጊቶቹ ብቻ ሳይሆኑ አስተሳሰቡም ሳይቀር በእነሱ ፍልስፍና የተቃኘ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ መፍጠር ነው፡፡
ከዚህ በተለዬ መንግድ የሚያስብ ሁሉ “ፀረ- ሕዝብ”፣ “ፀረ-ሰላም”፣ “ፀረ-ልማት”፣ “ፀረ-ሕገመንግሥት”፣ “ብርተኛ” ወዘተ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ አቶ መለስ በቀጥታ ለህዝብ በሚሰራጭ የፓርላማ መድረክ የም/ቤቱን ክብር በማይመጥንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው ቋንቋ ተቃዋሚዎቻቸውን ሲዘልፉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወገናዊነት በጎደለው መንፈስ ተቃዋሚዎችቸውን ሲሳደቡና ሲያንቋሽሹ የሰማና ያዬ የጥላቻ ስሜታቸውን መቆጣጠርና መደበቅ ያቅታቸው እንደነበር መታዘብ ይችላል፡፡
*            *           *
እስቲ አሁን ያን የጥላቻ ስሜት; ያን ዘለፋ; ያን እብሪት; ያን ክፋት; ያን መሰሪነት … ማስታወስ ምን ይባላል? እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ሰው ሞተ ተብሎ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር የሀዘን ከል እንዲለብስ የተደረገውስ ለምን ነበር?
ጎበዝ ዘመነ-ወያኔን እንዘክረው ከተባለማ ስንት የሚሻክርና የሚጎመዝዝ ትውስታ አለኮ! ደግነቱ ዶ/ር አብይ ክሶናል።
አላህ ከዚህም የተሻለ ያሳየን!!!
Filed in: Amharic