>
5:18 pm - Monday June 15, 1592

ረሃብ... ጊዜ ይሰጣል?! (ውብሸት ታዬ)

ሰሞኑን በማሕበራዊ ሚዲያው ከሚቀርቡና ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ የብሔር ማንነትን አማክሎ፤ በዜጎቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ከማፈናቀል አንስቶ የማንኛውንም ሰብአዊ ፍጡር ልብ በሐዘን የሚሰብር የአካል ጉዳትና የሕይወት መጥፋት መከሰት ነው።
  ማዘን፣ መቆጨትና ሁኔታውን ማጋለጥ፤ ከዚያ ባለፈም ተጎጂ ወገኖቻችንን ቢያንስ ካሉበት ነባራዊ ችግር ለመታደግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አክብሮት የሚቸረው ነው። በተለይ ሳይማር ያስተማረ፣ ከጉድለቱ አካፍሎ ለቸገረው የደረሰ፣ ቢርበው እንኳ የሰው እጅ ላለማየት የውስጡን በውስጡ ችሎ ተመስገን ሲል የኖረ ወገናችን እንዲህ በግራ ቀኝ አሳር ሲለበለብ ማየት እውነትም ያሳዝናል፤ ያስቆጫል!
    ችግሩ ግን ስር የሰደደና በዓመታት ሂደት እየተወሳሰበ የመጣ፣ ከጀርባው የእኩይ ተግባሩ ተዋንያን ስውር እጅ ያለበት፤ ለመፍትሔው እየተሄደበት ያለው መንገድ ደግሞ መጠነኛ፣ ቅንጅት የጎደለውና ላለመደገሙ ዋስትና የማይሰጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይህን የምልበትን ምክንያት በጣም በአጭሩ ለማስቀመጥ ልሞክር።
    የጊዜውን ርዝመትና የችግሩን ስር መስደድ የሚያሳየን ወደቅርቡ ስንመጣ ያለፉት 27 ዓመታት፤ ወደሁዋላ ገፋ ስናደርገው ደግሞ የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ተከትሎ የተፈፀመውን በታሪክ የተመዘገበ ማንነትን ያማከለ ሁለንተናዊ ጥቃት እናገኛለን። በእነዚህ ወደ 80 የሚጠጉ ዓመታት ብዙ ግፍ ተፈፅሟል፤ ብዙ ነገር ሆኗል። የሆነውንና የተደረገውን በደልና ግፍ ኢምንት ያህል መፍትሔ አልተወሰደም።
     እንዴት? ለምን? እስከመቼ? ማለት ይገባል። ከዚያ በፊት ግን ለሁነቱ መከሰት የተለያዩ መንስኤዎች ቢኖሩትም ዋንኛው ግን እንደ ቡድን እኩይ ተዋናይ ያልናቸውና የመንግስት አስፈፃሚውን መዋቅር ለግባቸው(ለግፋቸው) መጠቀም የቻሉ አካላት መሆ ናቸውን ልናሰምርበት ይገባል። ይህን የምንለው ለምንድነው?
   ቀደም ሲል የጠቀስነውን የ80 ዓመት ያለፉ ተሞክሮዎቻችን ስንገመግም በገሃድ የምናገኘው ይህንኑ በመሆኑ ነው። ነገሩ ሲብስና ለማስተባበል አስቸጋሪ ሲሆን የቀድሞው ጠ/ሚ/ር አቶ ሃይለ ማርያም አንዴ እንዳደረጉት የተጎጂዎችን ጩኸት ቀምቶ “ይህን ያደረጉት ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያሉ ባለስልጣናት ናቸው” ብሎ ሰለባ(ፈረንጆቹ scape goat ይሉታል) ማፈላለግ ነው።
     በተለይ የቤኒሻንጉሉ ጉዳይ ከዚህ ውጪ ሆኖ አያውቅም። ከ10 ዓመት በፊት በኦሮሞ ተወላጅ ወገኖቻችን ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈፀመውና ፍ/ቤቱ ለመጀመርያ ጊዜ(እኔ እስከማውቀው ድረስ)”የዘር ማጥፋት” ብሎ የበየነው ድርጊት አሁን ከምናየው ስልታዊ አጠቃቅ ጋር ተሰናስሎ ሲታይ የወንጀሉ ሽፋን ተገፎ ይስተዋላል። ይህም ብቻ አይደለም።
    በሰባት ዓመቱ የእስር ቆይታዬ ካገኘሁዋቸው የስርዓቱ የቀድሞ ባለስልጣን አንዱ የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹም ናቸው። አቶ ያረጋልን እኔና ወንድሜ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በጉዳዩ ዙርያ በተለያዩ ጊዜያት በጨዋታ እያዋዛን እንጠይቃቸው ነበር። ምንም እንኳ የሰቆቃውን ተዋናዮች በቀጥታ መግለፅ ባይደፍሩም በሳቸው የስልጣን ዘመን ሳይቀር ያለ’ሳቸው ዕውቅናና ይሁንታ ይደረጉ የነበሩ ‘ጥፋቶች’ እንደነበሩ ማስተባበል አልቻሉም፤ አልፈለጉም!
    ይህን ካልን በሁዋላ ለመፍትሔው እየተሄደበት ያለው መንገድ መጠነኛ፣ ቅንጅት የጎደለውና ላለመደገሙ ዋስትና የማይሰጥ ሆኖ ይታያል ወዳልነው ነጥብ ስንገባ ሶስት መሰረታዊ እጥረቶችና ስህተቶች ይታያሉ።
1- የጉዳቱ መጠነ ሰፊነትና ኢምንት ድጋፍ፦ መፈናቀል ሲከሰት ለዓመታት ያፈሩት ንብረት ለውድመትና ዝርፊያ ተጋልጦ ባለንብረቱ በአንድ ጀንበር ከነቤተሰቡ ሜዳ ላይ ይወድቃል። ማሕበራዊ መሰረት ከሥሩ ይደረመሳል። የተጎጂዎች መጠን በሰፋ ቁጥርም ችግሩ ይገዝፋል። በእንደዚህ ያለው ሁኔታ ውስጥ የህፃናት ሴቶችና አዛውንቶች ችግር በባህሪው ፋታ የማይሰጥ ይሆናል። አሁን ነገሩ የከነከናቸው ወገኖቻችን የሚያደርጉት ድጋፍ የተቀደሰ ቢሆንም ከችግሩ አንፃር የጠብታ ያህል ነው!
2- ከተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ፈጣን ምላሽና እርምጃ(የተጎጂዎቹን ችግር የተረዳና ለዚያ የሚጠቅም)ሊወስድ የሚገባው የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት አሳፋሪ ዳተኝነት፦ በአንዳንድ አከባቢዎች የድጋፍ ማሰባሰብን እስከማስተጓጎል ተደርሷል….
ለአብነት፡-
ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ የወዳጅነት፣ የአጋርነት ጨዋታ ለማካሄድ ሁለት የአማራ እግር ኳስ ክለቦች ጠይቀው ‘ብአዴን’ ፈቃድ ነሳቸው ሲሉ ሰማሁ፤ አልገባኝም። መቼም አይገባኝም! ብአዴን የአማራነት ፖለቲካዊ ማንነት ቢኖረው ኑሮ ይህን ሃሳብ አነሳስቶ የሚያስፈፅመው እራሱ ነበር። ግን አይደለምና ክለቦች ጠይቀው እንኳ ሊፈቅድ አልቻለም አስገራሚ አሳዛዝኝም…..
3- እስከዛሬ ተጣብተውን በቆዩ ያልተላቀቅናቸው የወገንተኝነት ዕሳቤና የተዛባ ፖለቲካዊ አረዳድ ጉዳዩን ከመፍታት ይልቅ ማክረርና ሳያስፈልግ በተቃርኖ ፅንፍ መጓተት፦ በአንዲት አገራችን ጥላ ስር የሆንን፣ ተቆጥረው በማያልቁ የባሕል፣ የታሪክ፣ የማንነትና የምንነት ጥብቅ ገመድ የተሳሰርን መሆናችንን መካድ…
     በዚህች አጭር ዳሰሳ ጥልቅና ዝርዝር ሁኔታዎችን መድረስ አይቻልም። እያዘንን እየተቆጨን አርምመን ከመቀመጥ በሚል ነው። መፈናቀሉ መጎሳቆሉ መራብ መጠማቱ የእኔም ነው ለማለት ነው። በጋራ እንቁም፤ የምንችለውን ያህልና ቶሎ እንድረስላቸው ለማለት ነው። ዕውቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቀዌሳ እንዳለው ‘ረሃብ ስንት ጊዜ ይሰጣል?’ ብለን ፊታችንን እንድናዞርላቸው ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic