>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9842

እጃቸው በንጹሀን ደም የጨቀየ " የካቢኔ አባላት" (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ብስራት አቢ (ፎቶ) አብሮ አደግ ጓደኛዬ ነው። ከሰፈር ልጅነቱ ባለፈ አንድ ክላስም ተምረናል። ይህም ይበልጥ ለመቀራረባችን አስተዋፅኦ አድርጓል ብዬ አስባለሁ። እኔ ወደ ፖለቲካ ከገባሁ በኋላ ደሴ ውስጥ ደፍሮ በተቃዋሚ አባልነት ሊንቀሳቀስ የሚችል ሌላ ሰው ባስብ አልመጣልህ አለኝኝኝ; ከብስራት በስተቀር።
ብስራት ደፋር ነው። በእኛ የጉርምስና ዘመን ደሴ ውስጥ ሰፈር ለይቶ በቡድን መደባደብ ፋሽን ነበር። ያኔ የአራዳ; የሮቢት; የአገር ግዛት; የሰኞ ገበያ. .. ልጅ መባልና በቡድን ተደባዳቢነት መታወቅ ያኮራ ነበር። በዚህ ከሚታወቁና ሥመ-ጥር የአራዳ ልጆች አንዱ ብስራት አቢ ነበር። ብስራት በጣም ትዕግስተኛና በፀብ ለመጣበት ግን ግንባሩን የማያጥፍ ሞገደኛ ነበር። ብስራት በአካልም ጠንካራና ከሰነዘረ አንድ ምቱ በቂ ሊሆን ይችላል።
ብስራት ወደ ተቃውም ፖለቲካ ከገባ በኋላ ኃላፊነት የሚሰማውና በጣም ታጋሽ ሆነ። ይሁንና የሥርዓቱ ታጣቂዎችና የፀጥታ ኃይሎች ብስራትን እዚያው ደሴ ውስጥ በተደጋጋሚ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው እየቀጠቀጡና እየሰባበሩ ጥለውታል። እሱ ግን “ከእንግዲህ አይነሳም” ሲባል ደሴ – አራዳ መንገድ ላይ ሲንጎማለል ይታያል።
የ1997 ምርጫን ተከትሎ በብስራትና ምንም በማያውቁ የሰፈር ጓደኞቻችን ላይ በማዕከላዊ የተፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ነበር። የሚገርመው ግን ከዚያ ሁሉ ድብደባና ስቃይ በኋላ ሲለቀቅ ቆሞ መንቀሳቀስ ችሎ ነበር። ከዚያም ባለፈ በቀድሞው አንድነትና በኋላም በሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባልና ጠንካራ አደራጅ ነበር።
ባለፈው ዓመት ለማደራጀት ሥራ ወደ ደሴ እንደሄደ በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ ማዕከላዊ መግባቱን ሰማሁና ልጠይቀው ሄድኩ። ሳስጠራው እግሩን ብቻ ሳይሆን ሰውነቱን ጭምር ነበር እየጎተተ የመጣው። “ብስሬ; ደበደቡህ አይደል?” ስለው በሚገርም ፈገግታ ታጅቦ “ተዋቸው እነዚህን. ..” አለኝና ፊቱ በአንዴ በቁጭት ክስል ሲል ታየኝ።
በኋላም ቂሊንጦ ከገባ በኋላ ስጠይቀው የተፈፀመበትን አረመኔያዊ ድርጊትና ስቃይ “ተወው ዛሬ አላወራውም” ነበር የሚለኝ። አሁን ከእስር እንደተፈታ ሳላገኘው በቀጥታ ወደ ደሴ ነበር የሄደው። ብስራት ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነው። ቤተሰቡ ጋር ቆይቶ ሲመለስ ነበር ደውሎልኝ ወደ ቢሮዬ የመጣው።
ወደ ቢሮዬ ሲገባ በደስታ ስሜት ሞቅ አድርጌ ልጨብጠውና ላቅፈው እንደምችል ገብቶታል። እናም እኔ ወደሱ ስሮጥ እሱ አፈገፈገ; እጆቹንም ወደኋላ ወስዶ በጀርባው ሸሸጋቸው። ግራ መጋባቴን ሲያይ ፈገግ ብሎ “እጄኮ መጨበጥ ስለማይችል ነው; ጣቶቼን ሳይቀር አድቅቀዋቸዋል” አለኝ። “እሽ አልጨብጥህም” ብዬ አቅፌ ልስመው ስል “እሱንም አልችልም; ትከሻዬንምኮ ገንጥለውታል” አለኝ።
ልቤ ተሰብሮ ወደ ወንበሬ ተመለስኩና ትኩር ብዬ አየሁት። አቅሮ ያወራኝ ጀመር። ጣቶቹን እንዴት እንዳደቀቋቸው; ጥፍሮቹን በጉጠት እንደነቀሏቸው; እጆቹን ወደኋላ አጥፈው በመሳብ ትከሻውን እንደገነጠሉትና ጭንቅላቱን በጣም ስለደበደቡት ሚዛኑን ጠብቆ መራመድ እንደማይችልና ለመናገርም ምላሱን እንደሚይዘው በትካዜ አጫወተኝ። እኔም በሀዘንና በሚደነዝዝ ስሜት ተውጨ ሰማሁት; ያን ጠንካራና ልበ ሙሉ የልጅነት ጓደኛዬን እያሰብኩ።
ሀገራቸውን በመውደዳቸውና ለሥርዓቱ ሥጋት ናቸው ተብለው ቀመጠርጠራቸው በተመሳሳይና ከዚህም በባሰ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው።  “ግን ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው?” ጥያቄውን የሰነዘርኩት ወደራሴ ነው። እንደነገሩማ የህግ ባለሙያ ነኝ።  እንዳውምኮ ለመጀመሪያ ዲግሪዬ የሠራሁት የመመረቂያ ጽሁፍ “who shall bear the cost of illegal arrest!” የሚል ነበር። ግን ምን ያደርጋል? ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምንኖረው።
ብስራት ህክምና ይፈልጋል። ግን ደግሞ የህክምና ወጭውን ለመሸፈን አቅሙ አይፈቅድም። ችግሩን ለማንም እንደማያወራ አውቃለሁ። ለእኔም የነገረኝ ስለተጫንኩት ነው። ያለበትን ሁኔታ ሳውቅ ግን ወደ ውስጤ አነባሁ; አይ ኢትዮጵያ – አገር የማፍቀር ዕዳ!
TeamLemaና ዶ/ር አብይ በተለይ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን ልባችንን ማሸነፋቸው እሙን ነው። ዶ/ር አብይ 27 ዓመት ሙሉ የተነዛውን የጥላቻና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ከህዝቡ/ከትውልዱ ልብ ውስጥ ለመፋቅ እየባዘነ ነው። የሰውየውን ቅንነትና ተምሳሌታዊ የለውጥ ተነሳሽነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከራስ ህሊና ጋር ያጣላል።
ግን ይህ ተነሳሽነት የእሱ የግሉ ወይስ የሚመራው ፓርቲና በዙሪያው ያሰለፋቸው የካቢኔ አባላትም ጭምር ነው? ለመሆኑ ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ባለፈ የግልፅነት; የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት መርሆችን መሠረት ያደረገ የፍትህ ሥርዓት የማስፈን ዓላማ ይኖረው ይሆን? ቢኖረውስ በዙሪያው ያሰለፋቸው ሰዎች ዓላማው እንዲሳካ የሚፈልጉና የሚረዱት ናቸው?
ዶ/ር አብይ ባዋቀረው ካቢኔ ውስጥ ካካተታቸው ሰዎች መካከል እስካሁን ድረስ በዜጎች ላይ ለተፈፀሙ ግድያዎች; እስራቶች; እንግልቶችና ስቃዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ የሚሆኑ አሉ። ታዲያ እነዚህ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት ያለበት የፍትህ ሥርዓት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ በራሳቸው ላይ “ቢላዋ ይስላሉ” ተብሎ ይጠበቃል? እንዳውም በተቃራኒው እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት እውን እንዳይሆንና የዶ/ር አብይ ዓላማ እንዳይሳካ እንቅፋት አይሆኑም?
ዶ/ር አብይ እንዴትና ምን አስቦ ይሆን! መቼም ያ ሁሉ ግፍና በደል ተፈፅሞ ቢያንስ አጥፊዎቹ ሳይታወቁ ጉዳዩ እንደዋዛ ተሸፋፍኖ ይቀራል ማለት ዘበት ነው። የዶ/ር አብይ መንግሥትም ቢሆን ይህን ከባድ ቁስል ረግጦ ለማለፍ እንደማይደፍር ይገመታል። በዚህ ሁኔታ አሁን በካቢኔው ውስጥ የሚደረድራቸውና በድርጊቱ ውስጥ ተዋናይ የነበሩ ሰዎች ጉዳይ ለወደፊቱ አያስቸግረውም ይሆን? ወይስ ተመልሶ እኛኑ አፋችሁን ዝጉ ነው የሚለን?
Filed in: Amharic