
ድርድር የሃይል ሚዛንን ተንተርሶ የሚካሄድ በማቀበልና በመቀበል ላይ የተመሰረተ የችግር መፍቻ ዘዴ ነው። የሃይል ሚዛን ተመጣጣኝ ሲሆን ሀሉም አሸናፊ ሁሉም ተሸናፊ የሚሆንበት ድርድር ማካሄድ ይቻላል። አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶች ራሳቸውን ከኢህአዴግ ጋር አነጻጽረው ጉልበታቸውን ደካማ አድርገው ስለሚቆጥሩት ይመስለኛል፣ ብዙ ጊዜ ብዙ ሰጥተው ትንሽ ለመቀበል ሲጣደፉ አያለሁ። በራስ የመተማመን ችግር ካልሆነ በስተቀር የተቃዋሚዎች ሃይል ከኢህአዴግ ሃይል ቢበልጥ እንጅ አያንስም። ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር በእኩል እንዲደራደሩ የሚያደርጋቸው እኩል ወይም የበለጠ ሃይል እንዳላቸው የሚያምኑ አይመስለኝም። ቢያምኑም ባያምኑም ኢህአዴግ ያለባህሪው “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ቃል እንዲገባ ያስገደደው፣ ተቃዋሚዎች በደንብ ሊረዱት ያልቻሉት ስውሩ ሃይል ነው። ስውሩ ሃይል ስውር ስለሆነ አይታይም፣ ስለማይታይም የሌለ ይመስላል። የለም ብለህ ስትለው አንድ ቀን ገንፍሎ ይወጣና መኖሩን ብቻ ሳይሆን፣ ሃይሉን የሚያቆመው ሌላ ሃይል እንደሌለ እንድትረዳ ያደርግሃል። ይህ ሃይል የት የሚገኘው? ህዝብ መሃል ነው። የህዝብ ሃይል ነው። በህዝብ ሃይል ከተለካ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን በብዙ መጠን ይበልጡታል። የሃይል አጠቃቀሙን ያውቁበታል አያውቁበትም ሌላ ነገር ነው። ብቻ ማንኛውም እውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅት ህዝብ የሚባል ሃይል እንዳለው በማመን፣ ከኢህአዴግ ጋር በእኩል መደራደር እንደሚችል በቅድሚያ ራሱን ማሳመን አለበት፤ ራሱን ካሳመነ በሁዋላ ደጋፊውም የድርድሩን አላማ በደንብ እንዲረዳ በማድረግ ከአላማው ጎን እንዲሰለፍ ማድረግ አለበት። እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚመጣው 51 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ ተስማምቶ የሚገዛበት ህግ ሲረቀቅና በዚያ ህግ መሰረት ስንተዳደር ብቻ ነው። ህጉ ሲረቀቅ የመንግስት ተቋማትም በዚያው መልኩ እንደገና ስለሚዋቀሩ ብዙ ጥያቄዎች መፍትሄ ያገኛሉ። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ እውነተኛ ለውጥ ሲያመጣ አይታየኝም። ከልቡ ለውጥ የሚፈልግ መንግስት ደግሞ በህጎች ላይ የሚደረግን ድርድር አይፈራም፤ አንድ ነገር ከጀርባው ካላስቀመጠ በስተቀር “ ህገ መንግስቱን ተቀበል” የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ወደ ድርድር አይገባም።
አህመድ ሺዴ የተናገረው የራሱን ይሁን የአዲሱን መንግስት አቋም አላውቅም፤ ዶ/ር አብይ ግን አንድም ቦታ ላይ “ህገመንግስቱን” ከተቀበሉት ጋር ብቻ ድርድር እናደርጋለን ወይም የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ህገመንግስቱን መቀበል ነው ሲል አልሰማሁትም። አህመድ ሺዴ ከማን ወገን ነው? ከማን ወገን እንደሆነ እገምታለሁ።