>

ኢጎር ሲኮርስኪ  — የአይቻልምን መንፈስ የሰበረ — የሰማይ በራሪ!! (አሰፋ ሀይሉ)

‹‹ነቲንግ ኢዝ ኢምፖሲብል!›› — ‹‹የማይቻል ነገር የለም!›› — የምትለውን ታላቅ ሐረግ — ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋላት — ሩሲያዊው ቀደምት የኬሚስትሪ ሊቅ — አንቷን ላቮዢዬር ነበር፡፡  በእርግጥም — የማይቻል ነገር የለም — ከባዱን ጦርነት — ከራስ ጋር ጦርነት ገጥሞ — ራስን ማሸነፍን ያህል ታላቅ ጀብዱ ጭምር — እርሱም — ይቻላል፡፡ ‹‹ታላላቅ ነገሥታትን ከሚያሸንፍ ይልቅ፤ ራሱን ማሸነፍ የቻለ ሰው እርሱ ታላቅ ነው!›› ይል እንደነበረው ማለት ነው – ፈረንሣዊው የጦር ጀግና — ታላቁ ናፖሊዮን ቦናፓርት፡፡ አዎ — የ‹‹አይቻልም!››ን መንፈስ ከውስጣቸው ገፍፈው — የ‹‹ይቻላል!››ን መንፈስ መላበስ የቻሉ — ተላብሰውም የማይቻለውን የቻሉ — እነርሱ — እውነትም ራሳቸውን ተዋግተው ያሸነፉ — የራሳቸውን የአይቻልም ጋኔን ተዋግተው ድል የነሱ ጀግናዎች ናቸውና — እውነትም ‹‹ታላቅ!›› እየተባሉ — ታሪካቸውም በሰዎች እየተከረላቸው — ለሁልጊዜም የመንፈስ ስንቅ ሆነውን — ከሞታቸውም በኋላ — ከእኛ ከህያዋን ጋር ለሁልጊዜም ይኖሩ ዘንድ — ዘለዓለማዊ የክብር ሥፍራ ይገባቸዋል፡፡
ራሳቸውን አሸንፈው፣ የማይቻለውን ችለው፣ ይህን የታላቅነትን ክብር ከተቀዳጁ — እና ታሪካቸው በዓለም ሁሉ ሲወሳላቸው ከሚኖሩ — እና ቱሩፋታቸውም ዓለማችንን ሲያዳርስ ከሚኖር — ከጥቂት ታላላቅ የሥኬት ሰዎች መሐከል — አንዱ — ኢጎር ኢቫኖቪች ሲኮርስኪ ነው፡፡ ኢጎር ኢቫኖቪች ሲኮርስኪ — በዛሬዋ ዕለት — በሜይ 25 ቀን 1881 ዓመተ ምህረት — ወደዚህች ምድር ብቅ ያለው — ኢጎር ኢቫኖቪች ሲኮርስኪ — አንዱ ነው፡፡
የዛሬው ባለታሪካችን — ኢጎር ሲኮርስኪ — በቀድሞዋ የሩሲያ ኢምፓየር — በአሁኗ የሀገረ ዩክሬይን ዋና ከተማ በኪዬቭ — ልክ የዛሬ 129 ዓመት — ልክ በዛሬዋ ዕለት — ማለትም በጎርጎሮሣውያን የዘመን አቆጣጠር በሜይ 25 ቀን 1889 ዓመተ ምህረት — በእኛ የዘመን አቆጣጠር አፄ ዮሐንስ በመተማ ደርቡሾች ላይ ዘምተው አንገታቸው ለሠይፍ ተጥፎ ውድ ህይወታቸው በተሰዋበት፣ እና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ሆነው በኢትዮጵያችን በነገሡበት ዓመት — ማለትም በ1881 ዓመተ ምህረት ላይ ነበር — ይህ የሩሲያ ሕልመኛ በራሪ — ‹‹ባህር ውቅያኖሱን – ባሳብ ተሻጋሪ›› — ጨቅላው ኢጎር ሲኮርስኪ — ወደዚህች ዓለም ብቅ ያለው፡፡
ኢጎር ሲኮርስኪ — ስለማንነቱ ሁልጊዜም ሲጠየቅ — እኔ — ልቅም ያልኩ የኪዬቭ ሩሲያዊ ነኝ — ዕምነቴ ደግሞ ምንም የማያወላዳ ‹ኦርቶዶክስ ክርስቲያን› ይል ነበር፡፡ ስለ ሐይማኖት የሚያወሱ ሁለት መጽሐፎችንም በሕይወት እያለ አሳትሟል፡፡ ነገር ግን ኢጎር ሲኮርስኪ ስለማንነቱ — እና ስለሥረ-መሠረቱ እንዲህ ይበል እንጂ — በበቀለባት — እና ከፍተኛውን የቅዱስ ቭላዲሚር የክብር ኒሻን የተሸለመባትን እናት ሀገሩን ሩሲያን ትቶ — ወደአሜሪካ የኮበለለው — ገና የሩሲያ የቦልሸቪክ አብዮተኞች — እነሌኒንና እነ ስታሊን — ዛር ኒኮላስ ዳግማዊን ከነመላ ቤተሰቡ በአሲድ አቃጥለው — የሀገር ማስተዳደር ሥልጣነ-መንግሥቱን በተረከቡ ገና በ2ኛ ዓመቱ ነበር፡፡ እርሱ ማለት — በሩሲያው ንጉሥ — በዛር ኒኮላስ እጅግ የተወደደ ወጣት የአቪዬሽን ኢንጂነር ነበረ፡፡ እና እነዚህን ሶሻሊስቶች ፈጽሞ አልወደዳቸውምና — ሀገሩን ጥሎ — በመጀመሪያ ወደ ፈረንሣይ — ቀጥሎም ወደሃገሩ — በመጨረሻም ወደ አሜሪካ ኮበለለ፡፡ በሀገሩ እያለ ነበር ግን — ኢጎር ሲኮርስኪ — በዓለም የታወቀበትን ታላቁን ግኝቱን እንኪልኝ ሀገሬ ያለው፡፡
ያ የሲኮርስኪ ታላቅ ግኝት — ሌላ ሣይሆን — በአሁን ዘመን — ዓለም ሁሉ የሚጠቀምበት — የዚያን ጊዜ ደግሞ ለዓለሚቱ ብርቅም የማይታሰብ ሕልምም የነበረው — ጥንት ከ400 ዓመታት በፊት በዳ ቪንቺ ንድፉ ተሞክሮ በዚያው ቀቢፅ ሆኖ የቀረው — እና አይቻልም ተብሎ ብዙዎችን ተስፋ ሊያስቆርጥ የደረሰው — በሠማይ በራሪ ሔሊኮፕተርን — ወይም በወቅቱ አጠራር — በሠማይ ሰውን ጭኖ መንሣፈፍ የሚችል — የሰማይ በራሪ ሔሊኮፕተርን — የዚያን ዳቪንቺ የተጠበበበትን የበራሪ ሄርኒቶፕተር – ሮፕተር – ስካይ ሺፕ – የዚያን ግዙፍ በራሪ አካል ዲዛይን ነበር — ይህ ባለ ብሩህ አዕምሮ — ለሀገሩ ለሩሲያም —የፖሊቴክኒክ ሙያን ሀ ብላ ላስቆጠረችው ለትውልድ ሥፍራው ኪዬቭም — እና ለዓለምም አብርክቶ ያለፈው፡፡
ይህ ሰው በአሜሪካ ሲመጣ — የተገፉትን ሰብሳቢዋ አሜሪካ — እጇን ዘርግታ ነበር የተቀበለችው፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህር አደረገችው፡፡ የቴክኒክ አሠልጣኝ አደረገችው፡፡ በመጨረሻም የሚረዱትን ያገሩን ልጆችና የራሷን ካዝና አሰባስባ — ትልቅ የበረራ ቁሳቁስን የሚሠራ — በራሪ ሔሊኮፕተሮችን ዲዛይን የሚነድፍ እና የሚያመርት — ግዙፍ የኤሮኖቲክስ ኮርፖሬሽን እንዲመሠርት አስቻለችው፡፡ እርሱም ውለታውን ፈጽሞ አልረሳም፡፡ በመጀመሪያ ኤስ-3 — ኤስ-4 — ኤስ-5 እያለ በመጨረሻም መላውን ዓለም ጉድ ያሰኘውን — እና ምናልባትም በ2ኛው የዓለም ጦርነት እነ አሜሪካና ሸሪኮቻቸው — ከጀርመን ሠራሽ ዜፒሊን ተዋጊ አውሮፕላኖች ልቀው — ሠማዩን እንዲቆጣጠሩ የረዷቸውን — እነዚያን የሠማይ ንሥር አሞራዎች — ሠርቶ እጃቸው ላይ ቁጭ አደረገላቸው፡፡ እና ደግሞ እነርሱም ፓተንቱን መዘገቡለት — ሐብታም አደረጉት — ክብር፣ ፍቅርና ማዕረግን ሁሉ አዘነቡለት፡፡ እናም በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ በብዛት በፋብሪካ የሚመረቱ ሔሊኮፕተሮች በ2ኛው የዓለም ጦርነት እየፋመ በነበረበት በ1942 እ.ኤ.አ. በምድረ አሜሪካ ተቋቋመ፡፡ እነዚያን መሠረታዊ የሲኮርስኪ ንድፎች የሚጠቀሙ ዘመናዊ ሔሊኮፕተሮችና አውሮፕላኖች — ዛሬም ድረስ — በእርሱ ስም ይጠራሉ፡፡
ይህ ሩሲያዊ ትውልድ ያለው አሜሪካዊ — ይህ አስደናቂ የፈጠራ ሰው — ለዚህ ፈጠራው ያነሣሣው — ገና በልጅነቱ — ለሳይንቲፊክ ቱር — ወይም ለሳይንሳዊ ጥናት በሚደረግ ጉዞ ላይ ለመሳተፍ ወደ ጀርመንና ፈረንሣይ ያቀና የነበረውን ወላጅ አባቱን ተከትሎ በሄደበት ወቅት —  በጀርመንና በፈረንሳይ እንዲሁም በኦስትሪያ ያጋጠመው እና ያየው እና የሰማው አስደናቂ የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ እንደነበር በሶስተኛው መጽሐፉ ውስጥ ገልጾታል ተብሏል፡፡ እና ይህ ከልጅነቱ — እንዴት ወደሰማይ መብረርና ማብረር እንደሚችል ሲያውጠነጥን ያደገ —  ‹‹የሔሊኮፕተር አባት›› በመባል የሚታወቅ ሰው —  ትናንት ድክ ድክ በሚል ጉልበቱ —  ወደሰማይ አርቆ በወረወራት የወረቀት ተንሳፋፊ ወላንዶ ጊዜ ጀምሮ የተጫረ —  ታላቅ የልጅነት አብርሆተ ሕልም ነው ብንለው —  ብዙም ከእውነታው አንርቅም፡፡
አዎ ይህ ሰው — የዓለምን አይቻልም ደምስሶ — በይቻላል መንፈስ — እንደኦርዊል ብራዘሮች — እንደ ሌሎችም የዓለማችን የኤሮኖቲክስ ፈርቀዳጆች — እርሱም በባህር ላይ የሚንሳፈፍን አውሮፕላን፣ ትልቅ ህንፃን መሸከም የሚችል የዕቃ ማጓጓዣ ሔሊኮፕተር፣ በላዩ ላይ ታንክን ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ የጦር መሣሪያዎችን መታጠቅ የሚችል የጦር ሜዳ ሠማይ ንጉሥ የሚሰኝ እና እስካሁንም እየተሻሻለ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን — ተዋጊ ሔሊኮፕተር — እና ብዙ እጅግ ብዙ የበረራ ፈጠራዎችን አበርክቶ — የፈጠራቸውን በራሪ ሔሊኮፕተሮች ደግሞ — በታላቅ ወኔያዊ ድፍረት የመከስከስ አደጋንና ሞትን በተደጋጋሚ ተጋፍጦ ራሱ እያበረረና እየሞከረ — ራሱንም ሀገሩንም የሰውን ልጅም ለታላቅ ሣይንሳዊ እርምጃ ያበቃ፣ ኑሮንና ሕይወትን ያቀለለ፣ የሰው ልጅ እንደምናባዊ መላዕክታት በሰማይ እንዲበር ያስቻለ፣ የእነዳቪንቺን የ16ኛው ክፍለዘመን ያልደረሰበት ንድፈ ጥበብ በ20ኛው ክፍለዘመን እውን ያደረገ አስገራሚ ድንቅ ሰው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በአሜሪካ ብዙ የወታደራዊ ዩኒቨርሲቲዎች በስሙ የተለያዩ ነገሮችንና ሥፍራዎችን የሰየሙለት ሲሆን፣ እና ‹ሆል ኦፍ ፌም› የሚሉት የክበር መዝገብ ስሙን ያሰፈሩት ሲሆን — በቅርቡ ደግሞ — በአሜሪካኖቹ ጠያቂነት — በዩክሬይን ዋና ከተማ የሚገኘው ዋና አደባባይ በኢጎር ሲኮርስኪ ስም፣ የኪዬቭ አውሮፕላን ማረፊያ በእርሱ ስም፣ መንገዱ በእርሱ ስም፣ እና ድሮ ገዝቶት ከሩሲያ ጥዬ አልሄድም ብላ ሁዋላ ልጁን አሜሪካ ልካ እርሷ እዚያው ትኖርበት የነበረውና ባዶውን ያለእድሳት የቀረውን የሲኮርስኪን የድሮ ፎቅ ቤት ደግሞ በማደስ ሙዝየም እንዲሆን ወስነው አድርገውለታል፡፡ እንግዲህ — አይቻልምን የጣሱ ሕልመኞች — ሲሳካላቸው — እንዲህ ስማቸውና ሥራቸው — ድንበርን ተሻግሮ — በሰው ልጅ ትውልድ ሁሉ — ለዝንተዓለም ሲወሳላቸው፣ ሲዘከርላቸው ይኖራል፡፡ እና — በቃ — ነቲንግ ኢዝ — ኢምፖሲብል!! የማይቻል — ምንም ነገር የለም!!
ለማንኛውም በነገው ዕለት የሊቨርፑልንና የሪያል ማድሪድን የሻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የእግር ኳስ ግጥሚያ ለማስተናገድ ሽርጉድ እያለች ላለችው የኢጎር ሲኮቭስኪ ትውልድ ሃገር ኪዬቭ — እና ለሊቨርፑል (እንዲሁም ለማድሪድ! – ምን አደረገኝ እሱስ?) — መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ — በዚህ የታዋቂው አሜሪካዊ ዘፋኝ — የአር ኬሊ — አምናለሁ መብረር እችላለሁ እያለ በሚያዜመው የዘመኔ ድንቅ ዜማ — ኢጎር ሲኮርስኪንና የማይሞት ሕልሙን፣ መንፈሱን፣ ነፍሱን ዘክሬ — በዚሁ አበቃሁ፡፡ መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ በጥበብ፣ በራዕይ፣ በጸጋና በሥኬት ከፍ ብላ ለዘለዓለም ትኑርልን፡፡ አሜን፡፡፡
 “I believe I can fly
I believe I can touch the sky
I think about it every night and day (Night and day)
Spread my wings and fly away
I believe I can soar
I see me running through that open door
I believe I can fly
I believe I can fly
I believe I can fly hoo!”
ምስሉ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
‹‹Igor Sikorsky – The Father of Helicopter – The man who made Lionardo Davinchi’s dream come true – 1889 – 1972››
Filed in: Amharic