>
5:28 pm - Saturday October 10, 7395

ወያኔ ሊወስደው የተዘጋጀው እርኩሳዊው የመጨረሻ እርምጃ! ማስጠንቀቂያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ወያኔ ከገጠመው ወቅታዊ የውድቀት አደጋ ወጥቶ ህልውናውን ለማስቀጠል ወይም “ከ60 እስከ 100 ዓመት እገዛለሁ!” ብሎ ያስቀመጠውን የአገዛዝ ዘመን እውን አድርጎ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር ከሀገር ውጭ በግልና በቡድን ያሉ ተቃዋሚዎችን በሙሉ የማይሆን የማይፈጸም ተስፋ በመስጠት አባብሎ ወደ ሀገር ቤት በማስገባት ሀገር ውስጥ ካለው ተቃዋሚ ጋር ሰልቅጦ በመብላት ተቃውሞን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማዳፈንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰጥ ለበት ብሎ እንዲገዛለት ለማድረግ በከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጥረቱም እስከአሁን ጥቂቶችን ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረግ ችሏል፡፡ በርካቶች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሻንጣቸውን በመቀርቀብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዳያስፖራው (በግዩራኑ) ያለው ተቃዋሚ ሥጋት ሳያድርበት ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ በማድረጉ ረገድም ምዕራባውያኑ ወያኔን በማገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡
ወያኔ የማያደርገውን ተስፋ በመስጠት ተቃዋሚዎችን አባብሎ ካስገባ በኋላ ፈጅቶ በማጥፋት ያለ ተቃውሞ የመግዛት ሐሳብና አቅድ እንዳለው እንዴት ልትረዳ ቻልክ? ካላቹህ ሁለት ነጥቦችን በመጥቀስ ለማስረዳት ልሞክር፦
1ኛ. ባለፈው ሳምንት ዐቢይ የአገዛዙን ሹማምንቶች ሰብስቦ ትምህርት አይሉት መመሪያ ያልለየለትን ልፈፋ ባደረገበት ጊዜ የተናገረውን ነገር ነው፡፡ ዐቢይ በዚህ ዕለት ሲናገር በዳያስፖራው (በግዩራኑ) ያለውን ተቃውሞ ማስወገድ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን፣ ይሄንን ለማድረግም ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ተስፋ ስለሌለው በዳያስፖራው (በግዩራኑ) ያለውን ተቃውሞ እያቀጣጠለና እየመራ ያለውን 30 ሽህ የሚሆን ዕድሜያቸው 60 እና 70 ዓመት የሆናቸውን የደርግ አገዛዝ ባለሥልጣናትንና ተዋንያንን በይቅርታና በምሕረት ወደ ሀገራቸው መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ መናገሩ ሲሆን፡፡
2ኛ. እስከ አሁን ከባዶ ልፈፋ በስተቀር የፖሊሲ (የመመሪያ) ለውጥ በማድረግ ፣ ፀረ ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብቶች የሆኑትንና የራሱን ሕገመንግሥት የሚፃረሩትን አሳሪ ገዳቢና አፋኝ አዋጆቹን ወይም ድንጋጌዎቹን በመሻር ፣ የገዛ ሕጉ ሕገወጥ ያደረጋቸውን የፓርቲ (የቡድን) የንግድ ተቋማትንና የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶቹን በመዝጋት ፣ የሕግ የበላይነትን ተጠያቂነትንና ዕኩልነትን በማስፈን እንደተናገሩት ለለውጥ የቆረጡ መሆናቸውን ሳያሳዩ ሳያረጋግጡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ እንዲያውም ከቀደመውም የባሱ ነገሮች እየተፈጸሙ መሆናቸው ነው፡፡
እነኝህ ሁለት ነጥቦች የሚጠቁሙት ሃቅ ወያኔ/ዐቢይ እየተናገረ እንዳለው መንግሥቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ 30ሽህ ይሆናል ያሉትንና የዳያስፖራውን (የግዩራኑን) ተቃውሞ ይመራል ያስተባብራል ያሉትን 30 ሽህ ዜጋ ወደ ሀገር መግባት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የታሰበውና የተፈለገው የተቃውሞን እንቅስቃሴ ለማዳፈን ለማስወገድ ከመፈለግ ከማሰብ አንጻር ነው እንጅ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጀው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብት ለማክበር ከመፈለግ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ካለው ቅንና ጽኑ ፍላጎት አንጻር አለመሆኑ ነው አደጋው፡፡ መሬት ላይ በግልጽ የሚታዩ ነገሮች የሚያረጋግጡት ይሄንን ሃቅ ነው፡፡
አገዛዙ የፖሊሲ (የመመሪያ) ለውጥ ሳያደርግ፣ አፋኝ ገዳቢ አዋጆችን ሳይሽር፣ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶቹን ሳይዘጋ፣ የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን ሳያሰፍን ሌላም ወሳኝ ወሳኝ እርምጃዎችን ሳይወስድ ወይም መውሰድ ሳይፈልግ ባዶ የቃል ተስፋ ብቻ በመስጠት “ወደ ሀገራቹህ ግቡ!” እያለ እየወተወተ ያለበት ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ ዓላማው እንደምንም ብሎ ተቃውሞን ማዳፈን እንጅ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት ስላልሆነ ነው “ወደሀገራቹህ ግቡ!” ከማለቱ በፊት የሚጠበቁና መሆን የነበረባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ያላስቀደመው፡፡ ወያኔ ከፈረሱ ጋሪውን ያስቀደመበት ምክንያት ዓላማው ክፉ ስለሆነ ነው፡፡
ወያኔ እንደሚለው ለለውጥ የቆረጠና ለለውጥ ጽኑ ፍላጎት ስላለው ቢሆን ኖሮ ሁሉንም ግቡ እያለ ያለው ግቡ ከማለቱ በፊት ከላይ የጠቀስኳቸውን አራት እርምጃዎችን ወስዶ ለለውጥ ቁርጠኛ መሆኑን በተግባር ካሳየ በኋላ ነበር “ኑ ግቡ!” ሊል ይችል የነበረው፡፡ እነኝህን ወሳኝ እርምጃዎችን ሳይወስድ በባዶ ቃል ብቻ ደልሎ ለማስገባት ጥረት ማድረጉ የሚያረጋግጠው ለውጥ የተባለው ሐሰትና ማጭበርበሪያ ማታለያ መሆኑን ነው፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ የገቡትና ለመግባት የተዘጋጁት ሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖች ግን ነባራዊ ሁኔታውን በአግባቡ ማጤን አልቻሉም፡፡ መሬት ላይ ካለው ሃቅ ይልቅ ቅዠታቸውን አምነዋል፡፡ ጅልነታቸውን የምትረዱት ወያኔ ወደር የማይገኝለት እፍረተቢስና ከሀዲ መሆኑን ክህደት በመፈጸምና ቃል በማጠፍ በተደጋጋሚ ያስመሰከረ፣ ያሳየ፣ ያረጋገጠ ነውረኛ የጥፋት ኃይል መሆኑ እየታወቀ ለማታለያ ካደረገው የእስረኛ መፍታት በስተቀር ሌላ ያደረገው አንድም ተጨባጭ ለውጥ ሳይኖር ሳያሳይ ማለትም የፖሊሲ (የመመሪያ) ለውጥ በማድረግ ፣ ፀረ ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሆኑትንና የራሱን ሕገመንግሥት የሚፃረሩ አሳሪ ገዳቢና አፋኝ ድንጋጌዎችን በመሻር ፣ ሕገወጥ የንግድ ተቋማቱን በመዝጋትና በሕገወጥ መንገድ ለዘመናት ያካበቱትን ንብረት ለመንግሥት ገቢ በማድረግ፣ የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ለለውጥ የቆረጠ መሆኑን ሳያሳይ ሳያረጋግጥ በባዶ ቃላት ብቻ ተደልለው መግባታቸውና ለመግባትም ጓዝ እየሸከፉ መሆናቸውን ስታዩ ነው ሰዎቹ ምን ያህል የዋሃንና የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ብስለትና ብቃት አልባ መሆናቸውን የምትረዱት፡፡
የወያኔ ሐሳብ ተጨባጭ ለውጥ ቢሆን ኖሮ ዳያስፖራውን (ግዩራኑን) “ኑ ግቡ!” እያለ ማባበልና መደለል ፈጽሞ አይጠበቅበትም ነበር፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ወሳኝ እርምጃዎች በመውሰድ ብቻ ተቃውሞን በአንድ ቀን ውስጥ ከሀገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራው (ግዩራኑ) ድረስ እንዲቆም ማድረግ ይችል ነበረ፡፡ ወያኔ ይሄንን ቢያደርግ ሕዝቡ ሌላ የሚቃወምበት ምክንያት አይኖርምና፡፡ ወያኔ ግን ይሄንን ከማድረግ ይልቅ ተቃዋሚን አባብሎ ማስገባት ላይ ያተኮረው ሌላ ምንም ሳይሆን ሰይጣናዊ ዓላማ ሸፍጥና ሴራ ስለሸመቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ግፈኛው መንግሥቱ ኃይለማርያም ከጭፍሮቹ ጋር ወደ ሀገርቤት እንዲገባ አይደለም፡፡ ውጭ ያሉት ያረጁ የደርግ ባለሥልጣናትና ጭፍሮች እንደ ደርግነታቸው ሀገር ውስጥ ቢገቡ የሚፈይዱት፣ ባይገቡ ደግሞ የሚያጎሉት ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እንዲያውም ደርጎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የሥራቸውን እንዲያገኙ ነው፡፡
ደርግ ሀገሪቱ በመቶዎች ዓመታት እንኳ ፈጽሞ ልትተካቸው የማትችላቸውን እንደ ጠ/ሚ አክሊሉ ኃብተ ወልድ ያሉ አንጋፋ ቁልፍ የሀገር ባለውለታና ዓይን ዲፕሎማቶችን (መልእኮችን) ፣ ምሁራንን ፣ ሊቃውንትን፣ ወጣቱን፣ ወንድ ወንዱን ሁሉ ምጥጥ አድርጎ ፈጅቶ ሀገሪቱን እንደ አሮጌ ጎታ የአይጥ (የወያኔ) መቀለጃ መጫወቻ መፈንጫ ያደረጋት ደርግ ነው፡፡ ደርግ ይሄንን ግፍ የፈጸመው ይሄንን ማድረጉ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ስለሆነና ስላመነበት አይደለም ለሥልጣን ሲል እንጅ፡፡
ዘወትር የሚገርመኝ ደርግ ለሥልጣን ብሎ ይሄንን ግፍና የደንቆሮ ተግባር በመፈጸም ሀገሪቱንና ሕዝቧን ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የጎዳ፣ የሀገሪቱን ዓይን ድርግም አድርጎ ያጠፋ፣ እግር እጇን እንክት አድርጎ የሠበረ ሆኖ እያለ እንደ ሀገር ወዳድ መቆጠሩ ነው፡፡ ለሀገር የሚያስብና የሚቆረቆር በምንም ተአምር ቢሆን ደርግ ያደረገውን ፈጽሞ አያደርግም፡፡ ደርግን የተካው ወያኔ ባይሆንና ፍትሐዊና ሕዝባዊ ሥርዓት ቢተካው ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደርጎችን ለፍርድ አቅርቦ የሚገባቸውን ተስተካካይ ቅጣት ከማስቀጣት የሚቀድም አንድም ተግባር ባልነበረው ነበር፡፡
ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለደርጎች ያለውን አመለካከት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በመሆኑም ደርጎችን በይቅርታ በምሕረት ለማስገባት ጥረት የጀመረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ከመፈለግ አይደለም፡፡ ሲጀመር ወያኔ የዳያስፖራውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ከደርጎች ጋር ማገናኘቱ ስም ለማጥፋትና ለሸፍጥ ነው እንጅ የዳያስፖራው ተቃውሞ ዐቢይ እንዳለው ከደርግ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስላለ አይደለም፡፡ የደርግ የነበሩ ሰዎች በዳያስፖራው ሕዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ ፈጽሞ የሉም ባይባልም ተሳትፏቸው አናሳ ነው፡፡
ወያኔ/ዐቢይ ደርጎችን “ያለምንም ተጠያቂነት ሀገራቹህ ገብታቹህ መኖር ትችላላቹህ!” እያለ ያለበት ሌላኛው ምክንያት “ለደርጎች ሙሉ ምሕረትና ይቅርታ ተደርጓልና ለየወያኔ/ኢሕአዴግ ሙሰኛና ግፈኛ ባለሥልጣናትም በሰሩት ግፍ ወንጀልና የሀገር ክህደትም አይጠየቁም!” ለማለትና እነሱን ከተጠያቂነት ነጻ ለማውጫነት ዘዴ በማሰብ ነው፡፡
ወያኔ “በሙሰኞች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው!” ለማለት አስሯቸው የነባሩትን የግሙሩክና የመንገድ ሥራ ባለሥልጣናቱን ትናንትና መፍታቱን ሰምታቹሀል፡፡ የአቶ መላኩ ፈንታ እስር አስቀድሞም ቢሆን ፈጽሞ ከሙስና ጋር የማይገናኝና የአማሮችን ከጉራፈርዳ በግፍ መፈናቀል በብአዴን ስብሰባ ላይ ተቃውሞ በመናገሩ በዚህ ቂም መታሠሩን በወቅቱ ተናግሬ ነበረ፡፡ በመሆኑም የሱ መፈታት አግባብና ትክክልም ነው፡፡ ሌሎቹ በሙስና ታስረው የነበሩ የወያኔ ባለሥልጣናት መፈታት ግን በምን አግባብ እንደሆነ ግልጽ አይደለም ፈጽሞም ተቀባይነት የለውም፡፡
ወያኔ ለደርጎችም ምሕረት በማድረግ ወንጀለኛ ሙሰኛና ግፈኛ ባለሥልጣናቱን ከተጠያቂነት ነጻ ማድረጉ ካልተሳካ ነው ሁሉንም አባብሎ ያስገባቸውን ተቃዋሚ አጥፍቶ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚሞክረው፡፡ በመሆኑም ወያኔ ደርጎችን እንደ ጆከር የመጫወቻ ካርድ  ሊጠቀምባቸው ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይፈልግም!!! የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት የደርግም የወያኔም ግፈኛ ባለሥልጣናት ለፍርድ ቀርበው ተስተካካይ ቅጣታቸውን አግኝተው ፍትሕ እንዲፈጸም፣ የፍትሕ ልዕልና እንዲረጋገጥ ብቻና ብቻ ነው እንጅ አረመኔያውያን ግፈኞች በላዩ ላይ ተቋምረው ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁበትና የተፈጸመበት ግፍና ክህደት ተዳፍኖ ፍትሕ ሳይፈጸም እንዲቀር አይደለም!!! በፍጹም!!!…
በነገራችን ላይ “”የወያኔ የመጨረሻ እርምጃ ሁሉንም “ግቡ!” ብሎ አስገብቶ ፈጅቶ በማጥፋት የአገዛዝ ዕድሜውን ያለ ችግር ለማራዘም ነው!”” ብየ ስል “በፍጹም ወያኔ ይሄንን ማድረግ ቢፈልግም እንኳ ሊያደርግ አይችልም! ምክንያቱም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይሄንን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም!” ምንንትስ ቅብርጥስ የምትል ብትኖር “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ!” የምትለው አካል ሕዝቧን አጥግባ መግባ ከማኖርም በላይ የዘመነ ሕይዎት እንዲመራ ስታደርግ የነበረችውን የተረጋጋች ሀገር በጠሉትና ሊበቀሉት በሚፈልጉት አንድ ግለሰብ በጋዳፊ ምክንያት ዶግአመድ አድርገው ወደ የምድር ሲኦልነት የቀየረ ግፈኛ ማኅበረሰብ እንደሆነ ልብ በል፡፡ ምዕራባውያኑ ለጥቅማቸው ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ፣ የፍትሕና የሰብአዊ መብት ጉዳይም ጨርሶ የማያሳስባቸው አውሬዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
የሀገራችንንም ፖለቲካ እንዲህ እንዳይሆን አድርገው ያበለሻሹትና ያወሳሰቡት፣ የሀገርና የሕዝብ ጠላት የሆኑትን ወያኔንና ሸአቢያን የመሰሉ ጠላት ለራሳቸው ጥቅም ፈጥረው እላያችን ላይ የሚያፈነጩብንና እጣፋንታችንን የሲኦል ደጅ ላይ እንዲወድቅ ያደረጉት እነሱ መሆናቸውን ቢያንስ በዚህ ዘመን የማያውቅ ፊደል የቆጠረ ዜጋ ያለ አይመስለኝም፡፡ አሁን ምን እያልኩ እንዳለሁ ይገባቹሀል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ጠላት ከደገሰልን መዓት ሀገራችንንና ሕዝብችንን ይታደግልን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
Filed in: Amharic