>

ESFNA እና የዶ/ር አብይ ጥያቄ! (ያሬድ ሀ/ማርያም)

ESFNA ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት እጁ ላይ ወድቋል። ይህን እድል በጥንቃቄ መጠቀም ትልቅ የአመራር ብስለት ይጠይቃል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ጉዳዩ ብዙዎችንም እያነታረከ ነው። ብዙዎች እንዳሉት ይህ ሁኔታ የESFNA አመራሮችን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከታቸው ግልጽ ነው።
እንደ እኔ እምነት ይህ የእስፓርት ቀን በያመቱ የሚመጣና የሚያመልጥም እድል ስላልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ባሉት እጅግ አንገብጋቢና ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ላይ ቢያጠፉ ደስ ባለኝ ነበር። ይሁንና ከአገር ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱት ቀጣይ ለውጦችም ሆነ እንቅስቃሴዎች ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን እና ሊያበረክት የሚችለውንም አስተዋጽዎ ከግምት በማስገባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላችሁበት ድረስ መጥቼ ላናግራችሁ ሲሉ አሻፈረኝ ማለት አግባብ አይመስለኝም። የወያኔ ጀሌዎች በየአገሩ ባሉ ኤምባሲዎች ውስጥ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሥርዓቱን ደጋፊዎች ብቻ እየሰበሰቡ ሲያወያዩና ሲዶልቱ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ልገለል አይገባም እያለ አጥር ደርምሶ ለመግባት ሲታገል የኖረ የዲያስፖራ አባል ዛሬ ጠቅላዩ አንተው ያለህበት ድረስ ልመጣ ነው፤ ሲሉት አሻፈረኝ ብሎ በሩን በተራው ከዘጋ ግራ መጋባት አለ ማለት ነው።
እኚ ሰው የሚመጡት አቢዮታዊ ዲሞክራሲን ሊያጠምቁ ወይም የምርጫ ዘመቻ ሊያካሂዱ አይደለም። ባለፉት 27 አመታት በማህበረሰባችን ውስጥ የተፈጠረውን መሻከር እና ጥላቻ ለማርገብ እና በቀጣይ ሊሚካሄዱት ብሄራዊ እርቅና መግባባት ድልድዩን ለመዘርጋት ይመስለኛል። ይህን የእርቅና የፍቅር ጥሪ ተቀብሎ በአግባቡ ማስተናገድ ልቆና በልጦ መገኘት እንጂ ሽንፈት አይደለም።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ዲያስፖራዊ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ ከፍተኛና ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ሥርዓቱ እየተረዳ መምጣቱን ስለሚያሳይ የስፖርት ፌዴሬሽኑ ይህን ድልድይ በመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር ተቀራርበው እንዲወያዩ እግረመንገዱን ሁኔታዎችን ቢያመቻች ትልቅ አገራዊ ውለታ ተደርጎ ይቆጠርለታል።
እርቅን እየገፉ ሰለ ብሄራዊ እርቅ ማውራት፣ ፍቅርን እየገፉ ሰለ አገር አንድነትና ይቅር መባባል መስበክ አይቻልም። ባለፉት 27 አመታት ሥርዓቱ በፈጸማቸው ግፎችና የመብት እረገጣዎች ዙሪያ ለመነጋገር፣ እውነቱ እንዲታወቅ፣ ግፏን እንዲካሱና ፍትህ እንዲሰፍን እንዲሁም ብሄራዊ እርቅ የሚካሄድበት ሁሉ አቀፍ የውይይትና ምክክር መድረክ እንዲዘጋጅም በቅድሚያ በዳይና ተበዳይ ፊት ለፊት ተገናኝተውና በቅን ልቦና ላይ ተመስርተው ሊወያዩና ሊነጋገሩ ይገባል። ይህን ለማድረግ ሥርዓቱ ከእብሪት ወጥቶና ድፍረቱን አግኝቶ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሲሄድ ሌላው የለውጥ ኃይለ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ የሚያፈገፍግ ከሆነ የእዚች አገር መከራ ይራዘማል እንጂ አይቋጭም።
ESFNA ባጋጣሚ እጁ የገባውን ይህን ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ቢወጣ ምኞቴ ነው።
2)
Filed in: Amharic