>
5:13 pm - Wednesday April 18, 5207

የአማራ ህዝብ መድህን ዴሞክራሲ ወይስ ብሔርተኝነት? (መሀመድ እድሪስ)

                                                                          እንደ መንደርደሪያ…
ብሔርተኝነት (Nationalism) ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዋናነት የትውልድ ቦታን ጠቋሚ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ቃል ቢሆንም እስከ 18ኛው ክፍለዘመን ድረስ ግን ፖለቲካዊ ትርጉም የሚሰጠውና ለፖለቲካ ዓላማ ጥቅም ላይ የሚውል አልነበረም፡፡ በ19ኛው ክፍለዘመን ግን ብሔርተኝነት የፖለቲካ እና የታሪክ ሂደቶችን ቅርፅ ያስያዘ የክፍለ ዘመኑ ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ መሆን በመቻሉ አብዮቶችን አስነሳ፡፡ አገራትን አፍርሶ ትናንሽ አገራትን ፈጠረ፡፡ በትናንሽ አገራት ውስጥም የብሔር አጥሮችን ተሻግሮ አገራዊ አንድነት ማምጣት ትልቁ የፖለቲካ ፈተና ሆኖ ብቅ አለ፡፡
ምንም እንኳን ብሔርተኝነት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ የፖለቲካ አጀንዳ ቢሆንም በብሄርተኝነት ምንነት እና በብሔርተኛ እንቅስቃሴ መመዘኛ መስፈርቶች ላይ ግን የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ብሄርተኝነትን የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ከፍልስፍናቸው ጋር በሚጣጣም መልኩ መስመር ሊያስይዙት የሚደክሙለት ድፍድፍ ጽንሰ ሀሳብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
‹‹ብሔር ምንድን ነው?›› የሚለውን ጥያቄ ከደም እና እና አጥንት ቆጠራ ጋር የሚያስተሳስሩት ‹‹primordialists›› ሐሳባቸውን በፍጹም እርግጠኝነት የሚሞግቱ ሲሆን የብሔር ፖለቲካ በግጭት እና ጦርነት እንዲታጀብም ዋነኛ መንስኤ ሆነዋል፡፡ ከኢንዱስትሪው አብዮት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የህዝቦች አዲስ አሰፋፈር እና ማህበረሰባዊ ስብጥር ተከትለው ካቆጠቆጡ አተያዮች መካከል የሆኑት ‹‹situationalism›› እና ‹‹constructivism›› በበኩላቸው ብሔር በህዝቦች አኗኗር እና አሰፋፈር ከሚፈጠር መስተጋብር የሚገነባ ህዝባዊ ስሪት መሆኑን የሚሞግቱ ሲሆን ‹‹ብሄርን የፈጠረው ማህበረሰባዊ ስብጥር በመሆኑ በደም ትስስር የሚገነባና ከብሔር የሚፈልቅ የብሄርተኝነት ፖለቲካ የለም›› የሚል አቋም አላቸው፡፡
በሌላ በኩል ግን የእነ Benedict Anderson ‹‹ብሔር (ኔሽን) ምናባዊ ማህበረሰብ፣ እንዲሁም በቦታ እና በጊዜ የማይገደብ ሥነ-ልቦናዊ አጀንዳ ነው›› የሚለው እሳቤ በብሄርተኝነት ላይ ትልቅ የአስተሳሰብ አብዮት አምጥቶ እንደ ሊበራሊዝም ያሉ ርዕዮተ ዓለሞች መንገዳቸውን በዚህ መስመር ላይ እንዲገነቡ አብቅቷል፡፡ በተቃራኒ አቅጣጫ የተሰለፈው ማርክሲዝም ደግሞ ብሄርተኝነትን ‹‹አንድ መደብ ራሱን ከሌላው የበላይ ለማድረግ የሚጠቀምበት የፖለቲካ አጀንዳ›› አድርጎ ያቀረበው ሲሆን ብሄርተኝነት በድህረ ኮሚውኒዝም ዘመን ሳይቀር ከኮሚውኒዝም በወጡ አገራትና በሶስተኛው ዓለም በሚገኙ አገራት ዘንድ ለተፈጠሩ ትላልቅ የፖለቲካ ውጥንቅጦች ዋነኛ መነሾ እንዲሆንም አድርጎታል፡፡
የብሄርተኝነትን ፈተና ለመከላከል አገራት በየዘመኑ የተለያዩ መንገዶችን ተከትለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋነኛው ደግሞ ‹‹አሲሚሌሽን››  ሲሆን የፈጠረው ተጽእኖም የብሔር ፖለቲካን ዘመን ተሻጋሪ የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎታል፡፡ የገዢውን መደብ ባህልና ማንነት በሌሎች ውስጥ በማስረፅ ውሁድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከተከተሉት ከአሲሚሌሽን በተጨማሪ የ‹‹ኢንቴግሬሽን›› እና ‹‹ብዝኀነት›› ፖለቲካን ለመከተል የመረጡ አገራት የበርካታ ብሔሮችን ማንነት አመቻምቸው ከፊሎቹ ‹‹የተሳካ›› የአገረ መንግስት ምስረታ ሂደት አድርገዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ የተከተሉት ‹‹አሲሚሌሽን›› የፖለቲካ ማህበረሰብን ከመገንባት ባለፈ አንድ አይነት ባህልን ብቻ መርጦ በማንገስ የተቃኘ የማንነት ነጠቃ ዘመቻ ስለነበር ለቀጣዩ ትውልድ የማንነት ፖለቲካ ቁርሾ ጥለው እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል፡፡
በእነዚህ አገራት የነበረው የአሲሚሌሽን ሂደት መንግስታዊ ባህልን ለማስረፅ ከተከተላቸው ስትራቴጂዎች መካከል አገራዊ ብሔርተኝነትን ማስተማር፣ የህዝቦችን የሰፈራ ፕሮጀክቶች በስፋት ማካሄድ እና የተመረጠውን ባህል እና ማንነት ኦፊሴላዊ እንዲሆን በማድረግ የአገሪቱ ገዢ ባህል እንዲሆን ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ይኸው ሂደት ግን የአገረ መንግስት ምስረታውን አስፈላጊነት የሚያምነው ገዢ ባሕል ሌሎች ማንነቶችን መጨፍለቁን ከምንም እንዳይቆጥረው ያደረገ ሲሆን ‹‹የማንነት ነጠቃ ተካሄደብኝ›› የሚለው አካል ጩኸትም ለአገረ ብሔር ምስረታ እንደእንቅፋት ተቆጥሮ እንዲወገዝ አድርጎታል፡፡ በተለይም በአገራዊ ብሔርተኝነቱ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሆኑት አካላት ባሕል እና ገዢ እንዲሆን የተመረጠው አካል ባህል ተገጣጥመው በተገኙባቸው አጋጣሚዎች አገራዊ ብሄርተኝነቱ ያለምንም የማንነት ፖለቲካ ሽፋን እንዲቀርብ ተመቻችቶለታል፡፡ በተቃራኒው የማንነት ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ግን ጉዳያቸው ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከመቅረብ ይልቅ በድፍኑ ‹‹የአገራዊ ብሔርተኝነት ተቀናቃኝ›› እንደሆኑ ተደርገው በመሳላቸው የብሔራዊ ቁርሾ ሰለባ ለመሆን ተዳርገዋል፡፡
ይህ ብሄራዊ ቁርሾ በአገራችን አብዛኛዎቹን ብሄሮች የነካ ሲሆን ‹‹ከሞላ ጎደል ለመሰል ተግዳሮት ተጋላጭ ያልሆነው የአማራ ህዝብ ነበር›› ማለትም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ የተለየ ተጠቃሚ ነበር ማለት ባይቻልም ባህሉ እና ማንነቱ ግን ‹‹ብሔራዊ ባህል›› እና ‹‹ብሔራዊ ማንነት›› ተደርጎ በመወሰዱ እንደተለየ ብሔር ራሱን የሚያስብበት አስፈልጎት እንዳልገጠመው ግልጽ ነው፡፡
የአማራ በብሔር መደራጀት የማንነት ጥያቄ ነውን?
በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የተካሄዱ ጥናቶች በአመዛኙ የአብዮቱ መንስኤ የመደብ ግጭት እንደነበር ይደመድማሉ፡፡ ከኤርትራ እስከ ኦጋዴን፣ ከባሌ እስከ ራያ፣ ከሐረር እስከ አዲስ አበባ የነበሩ አመጾችን እና አብዮታዊ ንቅናቄዎችን ከመደብ እይታ ውጭ ሊመለከቷቸው ባለመቻላቸው የአብዮቱ ዋና መንስኤ የሆነውን ለዘመናት የዘለቀ ‹‹ማንነትን እውቅና የማሰጠት›› እና ‹‹የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት›› ትግል ችላ በማለት በጥናቶቻቸው ውስጥ ከተቀጥላነት ያለፈ ቦታ እንዳይሰጡት አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ግን ውሎ ሲያድር አብዮቱንም ጎዶሎ፣ ጥናቶቹንም ያልተሟሉ አድርጎ አስቀርቷቸዋል፡፡ የዚህ ዋናው መነሻ ደግሞ የኢትዮጵያን ማህበራዊ ስሪት የተረዱበት፣ አልያም ‹‹የምናስበውን ትርክት ያስቀጥልልናል›› ብለው ለመረዳት የመረጡበት መንገድ ነው፡፡
እንደ ፊውዳሊዝም እና የመደብ ትግል የመሳሰሉ የማህበረሰብ ስሪቶችን ለማውራት ይቅርና በአገራችን ይህ ነው የሚባል የመሬት ስሪት ባልነበረበት ሁኔታ አጥኒዎቹ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነበሩትን እንደ ርስት እና ጉልት የመሳሰሉ የመሬት ስሪት እና ማህበራዊ መዋቅሮችን ብቻ መነሻ በማድረግ የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ህዝቦችን ሁኔታ በአንድ ቋት ከትተው ለመተንተን ያደረጉት ጥረት ለስህተት ዳርጓቸዋል፡፡ ጥናቶቻቸው ከወረቀት ስራነት አልፈው የህዝቦችን አብሮነት ለማምጣት እና የፖሊሲ አማራጭ ለመሆን የተሳናቸውም በዚሁ በተከተሉት ‹‹ሁሉንም በአንድ ጠቅልሎ የመተንተን›› ስሁት ስልት ምክንያት ነበር፡፡
እውነታው ግን የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ የአገራችን አካባቢዎች የነበሩ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ትግሎች በራሳቸው ማዕቀፍ እንዲያዙ እና እንዲጠኑ ግድ የሚያደርጉ ልዩ ባህሪያት ነበሯቸው፡፡ በዚህ ባህሪያቸው ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ መፍትሄም የሚሹ ነበሩ፡፡
በአፄ ምኒልክ የአገር ምስረታና መስፋፋት ዘመቻ ወቅት፣ በኋላ ላይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት (በተለይም ንጉሱ ከእንግሊዝ አገር ከስደት ከተመለሱ በኋላ) የተከተሏቸው ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የማንነት ፖለቲካ ትግሎችን ቅኝት የወሰኑ ነበሩ፡፡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ማንነትን መሰረት ያደረገ የመሬት ነጠቃ እና እደላ ዋና መገለጫ ያልነበረ በመሆኑ ከመሬት ጋር ተያያዥ የነበሩ አመጾች እና ትግሎችን የ‹‹ስልተ ምርት ግንኙነት›› ሊገልፃቸው ይችል ይሆናል፡፡ በተቃራኒው በደቡቡና ደቡብ ምስራቁ ክፍል መሬትን ተንተርሶ የተነሱ ጥያቄዎችን ከስልተ ምርትነት እና ከመደብ ጥያቄነት ይልቅ ወደማንነት ጥያቄ ከፍ የማድረግ አቅም ነበራቸው፡፡ አድርጓቸዋልም፡፡
እዚህ ላይ በ1969 የወጣውን የመንግስት ሪፖርት እንደማሳያ መውሰድ እንችላለን፡፡ በሐረርጌ መታረስ ከሚችለው መሬት 79 በመቶው፣ ከሲዳሞ 75 በመቶው፣ እንዲሁም የቆላማው የአገሪቱ ክፍል ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የመንግስት መሬት እንዲሆኑ ተወስኖ ነበር፡፡ መንግስት እኒህን መሬቶች ከባለመሬቱ ውጭ ለሆኑ አካላት የማደል ስልጣኑን በመጠቀም ለቤተ ክርስትያን፣ ለአዳዲስ ባለይዞታዎች (ወታደሮች፣ የመንግስት ባለሟሎችና አገልጋዮች፣ ሰፋሪዎች) እና ሲሶውን ደግሞ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ ለሚታመኑ የአካባቢው ባላባቶች አድሎታል፡፡ ይህ እርምጃ መሬትን ከ‹‹ስልተ ምርትነቱ›› አውጥቶ ከባለቤቱ ተነጥቆ በመሰጠቱ ብቻ ለባለመሬቱ በደሉን የማንነት በደል አድርጎታል፡፡ የዛሬውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅርፅ እያስያዙ የመጡት ከእነዚህ እርምጃዎች የተወለዱ ብሔር ተኮር እና ሌሎች ማንነት ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
ከዚህና ፅሁፉን ለመመጠን በጥልቀት በማንገባባቸው እውነታዎች አንፃር ስናየው የአማራ ህዝብ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ትግል ሊያደርግበት የሚችልበት ታሪካዊ መሰረት የሳሳ ሆኖ ይታያል፡፡ይህ ማለት ግን የአማራ ህዝብ ለቡድን መብቱ በጋራ የሚታገልለት አላማ አይኖረውም ማለትን አያሲዝም፡፡ ማንነት ትግል ሌላ ለቡድን መብት መታገል ሌላ ነውና፡፡  ‹‹የአማራ ህዝብን ይወክላሉ›› የሚባሉ ባህላዊ እሴቶች ብሔራዊ እውቅና አግኝተው መቆየታቸው፣ የአማራ ህዝብ አሰፋፈርም የራስን እድል ለመወሰን ላለመ አንድ ወጥ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ የማይጋብዝ መሆኑ ከግንዛቤ ሲገባ ደግሞ በተጠቂነት ስሜት የተጀመረው የአማራ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ጠንካራ የማንነት መሰረት እንደሌለው እንረዳለን፡፡ ከላይ በመንደርደሪያነት የተነሱ ንድፈ ሐሳባዊ ሚዛኖች ውስጥ ብንከተውም የአማራ ብሔርተኝነት አዲስ ውቅር ብሔርተኝነት የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡
እንደአብነት ብንወስደው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ራሱን በዘር ግንድ የሚቆጥርበት የደም ትስስር እና ሌሎች ብሄሮችን ኦሮሞነት አላብሶ የሚቀበልበት የሞጋሳ ስርዓት ያለው ሲሆን ይህንንም ለብሔርተኝነቱ ስር መሰረት አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ተቀራራቢ ባህል እና ውስን ሆኖ ሊገለፅ የሚችል የህዝብ አሰፋፈር ሁኔታም ብሔርተኝነቱ ለሚያቀነቅነው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንደመነሻ ሆኖ ጠቅሞታል፡፡ ኦህዴድ በሚያቀነቅነው የኦሮሞ ብሔርተኝነት እና ኦነግን የመሳሰሉ ብሔርተኞች በሚያነሱት አጀንዳ መካከልም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የህዝቡ አሰፋፈር እና ያንን ተከትሎ የሚያዘው ፖለቲካዊ አቋም ትልቅ የልዩነት አጀንዳ ነበር፡፡ ይህም ከመሆኑ ጋር የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከክልሉ ውጭ ያሉ ተወላጆች የሰፈሩበት ሁኔታ በአመዛኙ በአንድ አካባቢነት የሚታወቅ እና አስተዳደራዊ መዋቅር ለመዘርጋት የሚያመች በመሆኑ የቦታ ልዩነቱ የፈጠረው እክል እንዳይጎላ አድርጎታል፡፡
በተቃራኒው የአማራ ብሔርተኝነት ይህንን ተሞክሮ ሊከተል የሚያስችለው የዘር፣ የባህል እና የአሰፋፈር ሁኔታ ያለው አይመስልም፡፡ ሌላው ቢቀር አማራነትን የሚገልፅበትን ማእቀፍ ብሔር ተኮር ከማድረግ ይልቅ ትግል ተኮር እንዲሆን ወደማድረግ ማዘንበሉ ይሄ ነው የሚባል መገለጫ እንዳይዝ አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ እነ አቶ አዲሱ ለገሰን እና አቶ በረከት ስምኦንን የመሳሰሉ ታጋዮቹን በአማራ ማልያ ብአዴን ውስጥ ሲያሰልፋቸው አማራ የሚያስብላቸውን ማንነት እውቅና በመቸር ነው፡፡ በተቃራኒው የአማራ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ እንደ ወሎ ያሉ የራሳቸው ማንነት ያላቸውን ህዝቦች ማቀፍ የሚችልበት ውቅር ባለማበጀቱ ‹‹ከገዢው መንግስት ጋር ያብራሉ›› ብሎ የሚያስባቸውን ሹማምንት የአማራ ማንነት ሲነፍግ ይታያል፡፡
ከዚህም ባለፈ ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሔር ተኮር ትግል ያደርጉ የነበሩ ኃይሎችን እንዲፈጠሩ ባደረጋቸው ታሪክ እና የአገረ ብሔር ምስረታ ሂደት ላይ ያለውን የታሪክ ግንዛቤ ለመከለስ ፍቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ ‹‹ትግላችን ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ነው›› ብሎ መነሳትን መርህ አልባነት ያደርገዋል፡፡
ብሔርተኛ እቅስቃሴው አማራን ይታደገዋልን?
በ2007 የህዝብ እና ቤት ቆጠራ አኀዝ መሰረት 4,125,185 (4 ነጥብ 1 ሚሊየን) የአማራ ተወላጆች ከአማራ ክልል ውጭ ይኖራሉ፡፡ ይህ አኀዝ ክልል ተብለው ከተዋቀሩ እንደ አፋር፣ ጋንቤላ፣ ቤኒሻንጉል እና ሐረሪ ክልሎች ጥቅል ቁጥር የሚበልጥ ነው፡፡ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ተበትነው ከሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች አንፃር ካየነው ደግሞ ከነጭራሹም የሚስተካከለው የለም፡፡ ይህ እውነታ የራሱ የሆነ ታሪካዊ መሰረት ያለው እንጂ የክልሉ ህዝብ ብዛት ከሌሎች በመብለጡ ከሚፈጠር የአሰፋፈር ልዩነት የመነጨ አይደለም፡፡
የአማራ ህዝብ በሌሎች ክልሎች ውስጥ ከየዘመናቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በሚቀያየር የተስፋፊነት፣ የሰፈራ፣ የስደት እና የስራ አጋጣሚዎች በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ተበትኖ በመኖር ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ችሏል፡፡ እንደፖለቲካው ሁኔታም የእነዚህ ዜጎች ሁኔታ ይለያያል፡፡ ከደርግ መንግስት በፊት በነበሩት ጊዜያት በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የተስፋፉት እና የሰፈሩት ማንነታቸው የተከበረ፣ ርስታቸው የማይደፈር በሚባል ደረጃ ጥብቅ ይዞታ ነበራቸው፡፡ የደርግ መንግስት የመሬት ስሪት የይዞታ ለውጥ ከመፍጠሩ በስተቀር ወደፊት ያመጣው ‹‹አንድ ኢትዮጵያ ወይም ሞት!›› መፈክር በኢትዮጵያዊነት ውስጥ በሚገለፀው የአማራ የራስ ማንነት መገለጫዎች ላይ የደቀነው አደጋ አልነበረም፡፡
የአማራ ብሔርተኝነት አሁን ላይ ማቆጥቆጥ ሲጀምር ዋነኛ ምክንያቱ እና ዓላማው ‹‹አማራው ህዝብ (በተለይ ደግሞ በሌሎች ክልሎች ተበትኖ የሚኖረው) ሆን ተብሎ የታቀደ የጥቃት ሰለባ እየሆነ በመምጣቱ ራሱን መከላከል አለበት›› የሚል መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ ይህ በበኩሉ ጥቃቱን በብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ለመከላከል ከተፈለገ ተበትኖ በሚኖረው የአማራ ተወላጅ ውስጥ አዲስ ማንነትን ማብቀል እና ለዚህ ማንነት እንዲታገል ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ ተበትነው የሚኖሩ አማራዎች ብዛት እና በቆይታ የተላበሱት ሥነ-ልቦና ግን ለዚህ የሚመች ሆኖ አናገኘውም፡፡
በአሰፋፈርም ካየነው ከአዲስ አበባ በስተቀር በሌሎች አካባቢዎች አማራው ከአካባቢው ነዋሪ ቁጥር አንፃር በጣም አናሳ ነው፡፡ በአካባቢው የሰፈሩበትን ታሪካዊ ሁኔታ እና አሁን ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ያላቸውን ማህበረ ፖለቲካዊ መስተጋብር ከግንዛቤ አስገብተን ካየነው ‹‹በአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቅቻለሁ›› የሚል ዓይነት ሥነ-ልቦና እና የመከላከል እርምጃ ሁኔታውን ይበልጥ የከፋ ሊዲርገው ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ እንደመፍትሄ የሚጠቆመው ነዋሪውን በሌሎች ምቹ በሚባሉ ክልሎች መልሶ የማስፈሩ ሐሳብም ቢሆን ችግሩን ቢያወሳስበው እንጂ አያቀለውም፡፡ ለአዲስ ሰፈራ የሚታጩ ክልሎች ራሳቸውን ዝግ በማድረግ እና የ‹‹ተወረርን›› ሥነ-ልቦና በማሳደር አዲስ ዓይነት የብሄር ፖለቲካ አሰላለፍ ሊፈጥሩም ይችላሉ፡፡ ይህም በተራው የአማራውን ተጠቃሚነት እየቀነሰው የሌሎች ብሔርተኛ እቅስቃሴዎችን ህብረት የሚያጠናክርበት አየር ይፈጥራል፡፡ በምርጫ 97 ቅንጅት ሐረርጌን በመሳሰሉ አካባቢዎች በእጩነት ያቀረባቸው ግለሰቦች በቀድሞው ስርዓት የመሬት ባለቤቶች፣ አልያም የእነርሱ ወራሾች መሆናቸውን በማየት ብቻ ያለምንም የፖሊሲ ፍተሻ ለፓርቲው አሉታዊ ምልከታ ተፈጥሮ የነበረ መሆኑ ለዚህ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡
በጥቅሉ የቸማራ ብሄርተኝነት በአካባቢው ማህበረሰብ ‹‹ተጠቃ›› እና ‹‹ተፈናቀለ›› የሚል ዓይነት ትርክት መከተሉ አዋጭ አካሄድ ሆኖ አይታይም፡፡ በተለይም ከመፈናቀል ጋር ተያይዞ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን የሚሰጣቸው አጋጣሚዎች በትክክል ማንነት ላይ ያነጣጠሩ መሆን አለመሆናቸው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች የፈጠሯቸው መሆን አለመሆናቸው በወጉ ባልተጠናበት ሁኔታ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ የማንነት ፖለቲካ የቆመለትን ህዝብ ከመታደግ ይልቅ የልሂቃኑ እና የፖለቲከኞች ገበያ ከመሆን ላያልፍ ይችላል፡፡
አማራን ማን ይታደገው?
የአማራ ብሔርተኝነት ላይ የሚነሱ ክርክሮች ‹‹የህዝቡን ጥቅም ያስከብራል ወይስ አያስከብርም?›› ከሚለው ይልቅ የተሳሳተ ጥያቄ አንስቶ የተሳሳተ መልስ የመቀበል አካሄድ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅም የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ማንሰራራት ኢትዮጵያዊነት ላይ የተደቀነ አደጋ እንደሆነ መቁጠርን መርጠዋል፡፡ ይህ ጭቅጭቅ ወደፖለቲካዊ መሰነጣጠቅ እንደሚገፋ የሰጉ አካላት መንስኤው ላይ ከማተኮር ይልቅ የአማራ ብሔርተኝነት ቢበዛ መብት ተደርጎ የሚታይበትን ድንበር አልፎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታላቁ ፈተና እንዲመስል አድርገው መሳላቸው ተገቢ ሆኖ አይታየኝም፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የብሔርተኝነቱ መጠናከር በተለምዶ ‹‹የአንድነት ኃይል›› የሚባለው ክፍል መሰረት የሆኑ አካባቢዎችን የመንጠቅ አደጋ ተደርጎ ስለሚወሰድ አጀንዳውን ወደፓርቲ ፖለቲካነት ኣሳድጎት ጉዳዩን የፓርቲዎች የኮንስቲቱዌንሲ ሽሚያ ያስመሰለበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ አካሄድ መሰረታዊ ስህተቶች ይስተዋሉበታል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊነትን በአማራ ህልውና ላይ አንጠልጥሎ የማሰቡ ስህተት ነው፡፡ ‹‹የአማራ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነትን ያከሽፋል›› ብሎ ማመን አስቀድሞ ስለኢትዮጵያዊነት ከተያዘ የተዛባ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ የአማራ ብሔርተኝነትን በኢትዮጵያዊነት ላይ የተሳበ የመጨረሻ ቃታ አድርጎ የማሰቡን ስሁት የኢትዮጵያዊነት ግንዛቤ እኔ በግሌ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብዬ አልወስድም፡፡
ከፖለቲካ ትግል ጋር በተያያዘም ፓርቲዎቹ ለትውልድ ሽግግር እውቅና የሰጠ ተራማጅ የፖለቲካ ፕሮግራም የመቅረፅ አቅማቸው መዳከሙን እና አንድ አካባቢን ብቻ እንደርስት የመቁጠር ድክመታቸውን በአማራው ብሄርተኝነት ላይ በማሳበብ ፖለቲካዊ ገበናቸውን ለመሸፈን እየጣሩ ያሉ ይመስላል፡፡ ብሔራዊ ፓርቲ ተብለው ተደራጅተው ሳለ መራጫቸውን ከአንድ አካባቢ ብቻ እደሚያገኙ ማሰብ ጉዳዩን የፓርቲዎቹ እንጂ ብሔርተኛ እቅስቀሴው ፈተና አያደርገውም፡፡ስለብሔርተኛ እንቅስቃሴውም ሲታሰብ በትክክል መልስ የሚፈልግ የነበረው ጥያቄ  ‹‹ልክ እንደ ሌሎቹ ህዝቦች ሁሉ አማራን ሊታደግ የሚችል አማራጭ አለን ወይ?›› የሚለው ነው፡፡
ይህም ሆኖ የአማራ ብሐየርተኝነት እንቅስቃሴ በተነጻጸሪነት አንድ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ማስረፁን መካድ አይቻልም፡፡  የኸውም የፖለቲካ ተዋንያን ‹‹የቡድን መብት›› ሲባል ታሳቢ ያደርጓቸው ከነበሩ ህዝቦች ተርታ የአማራን ህዝብም እንደብሔር ባይሆንም እንኳን ታሳቢ ማድረግ መጀመራቸው አይቀርም፡፡
ከላይ በስሱ ለማንሳት እንደተሞከረው ሌሎች የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች ታሪካዊ መነሻዎች አሏቸው፡፡ የእውቅና እና ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች የፖለቲካ ጥያቄ ከመሆናቸው በፊት የማንነት ጥያቄዎች እንዲሆኑ ስቻሏቸው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ልዩነቶች አስተናግደዋል፡፡ሆኖም ግን እነዚህ የማንነት ጥያቄዎች በጊዜ ሂደት ጡዘታቸው እየረገበ፣ የማታገል አቅማቸውም እየጠፋ መሄዱ አይቀርም – እየሄደም ነው፡፡ ሁሉም ህዝቦች በማንነታቸው የማይደራደሩበት ምህዳር ከተፈጠረ የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነት የመገንባቱ እና የማንም ብሔር ተኮር የበላይነትና የበታችነት ጉድኝት የማይስተዋልበት በዜግነት ላይ የተመሰረተ ማንነት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ በማንነት ፖለቲካ ከተጓዝንበት ረዥም የፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ አንፃር ስናየው ይህ ሽግግር አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ መምጣቱ አይቀርም፡፡
የአገሪቱ ማህበራዊ መዋቅር ሽግግር እያካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዳግም ወደብሔርተኝነት የሚመሽገው የአማራ ብሔርተኝነት በእርግጥም ግቡ የአማራው ህዝብ ተጠቃሚነት ከሆነ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ከሚደረግ አገራዊ ትግል የተሻለ አጭር መንገድ አይኖረውም፡፡ ቀደም ሲል ‹‹የፍትህ አቀንቃኝ›› እና ‹‹የዴሞክራሲ ፋኖ›› አድርገው ራሳቸውን ሲቆጥሩት የቆዩት ልሂቃን በዚህ አጋጣሚ ፖለቲካዊ ፋውል ሰርተው ከፎረሹ የአማራ ብሔርተኝነት በራሱ የሚያመጣው ትልቅ ለውጥ ባይኖርም ብሔርተኝነቱ ራሱን ቅርፅ ለማስያዝ በሚያደርገው የባህል መረጣ፣ አካባቢያዊ ክለላ እና በተለይ በእምነት ነክ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ መሳሳብ እንዲፈጠር፣ አማራውንም ዘግይቶ በተቀላቀለበት የብሔር ጨዋታ ተመጣጣኝ ያልሆነ ተፎካካሪ እንዲሆን ግብዣ እያቀረቡ እንደሆነ ሊያውቁ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በበኩሌ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የሚካሄደውን አገራዊ ትግል በኢትዮጵያዊነት እየጋረዱ የማቅረቡን ትርክት በማስቀረት ‹‹ድህረ የማንነት ፖለቲካ›› ለሚጠይቀው በዜግነት ላይ ለሚመሰረት ዴሞክራሲያዊ የዜጎች መብት አጥር ዘለል ትግል ማድረግ አማራውን ይታደገዋል፤ ሌላውን ህዝባችንንም እንደሚታደገው ሁሉ፡፡ ለዛሬ ይብቃኝ፡፡
Filed in: Amharic