ጠቅላይ ሚንስትሩ በብዙኀኑ ኢትዮጵያውያውያን እና የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚያሳስባቸው የውጭ ኃይሎች ከፍተኛ የሚባል ቅቡልነት ማግኘታቸው እየታየ ነው። የዶክተሩ የቅቡልነት ምንጭ ግን ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ከወቅቱ ወጀብ ሰከን ባለ መልኩ ሊፈተሽ የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ‹‹ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በተስፋ እንዲታዩ ያደረጋቸው ይዘውት የቀረቡት አማራጭ ፍኖተ ካርታ ስላለ ወይስ ከእርሳቸው የቀደመው ተስፋ አስቆራጭ ሂደት እርሳቸውን በተስፋነት እንዲታዩ አድርጎ ይሆን?›› የሚለውም ትኩረት ይሻል። ምክንያቱም ቀጣይነቱን እና በማስከተል ሊኖሩ የሚችሉ ፖለቲካዊ ሂደቶችን የመወሰን አቅሙ ብርቱ ነውና።
በዚህ ጽሑፍ በአገራችን ስለነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ አልያም አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ወደሥልጣን እንዲመጡ ጥርጊያውን ስላመቻቸው ሕዝባዊ ትግል ለመዳሰስ አልተነሳሁም። በጠቅላይ ሚንስትሩ የሹመት ንግግር ላይም አስተያየት የመስጠት ሐሳብ የለኝም። ይልቁንም አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር በተስፋ እንዲጠበቁ ያደረጓቸውን እና መዋቅራዊ መልክ ያላቸውን የትግል ውጤት የሆኑ ጉዳዮች ዋና ትኩረቴ አደርጋለሁ።
የቅቡልነት ምንጭ በጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት
የኢሕአዴግ የሥልጣን ምንጭ ነፃና ፍትሐዊ የፉክክር ፖለቲካ ባለበት የሚደረግ ምርጫ አለመሆኑ ለውይይት የሚቀርብ አይደለም። እርግጥ ነው እንደብዙዎቹ ጠቅላይ አውራ ፓርቲ (Authoriterian Dominant Party) ወቅቱን የጠበቁ ምርጫዎች እየተካሄዱ ሥልጣን በምርጫ አሸናፊነት ስም ስለሚያዝ ኢትዮጵያ የምርጫ ዴሞክራሲ (Electoral Demoracy) ያለባት አገር ለመባል እንደምትበቃ የሚከራከሩ ይኖራሉ። በተቃራኒው ይህን ለማስተባበል መከራከሪያ ማቅረቡ አስቸጋሪ አይደለም። ሆኖም ግን ‹‹ግንባሩ ሥልጣን የሚይዘው በፍትሐዊ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ በማግኘት አይደለም›› ማለት ‹‹ሥልጣን ከጨበጠ ጀምሮ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የተጠቀመው አማራጭ ኃይል ብቻ ነው›› ማለት ከመርሆች የሚጋጭ፣ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ የማይገጥም፣ እንዲሁም በተለያዩ አገራት ባሉ ተሞክሮዎች የታየን እውነታ የሚደፈጥጥ ነው።
ከመርህ አኳያ አንድ መንግሥት ከምርጫ ባለፈ ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚያገኝባቸው በርካታ መንገዶች አሉት። በአገር አሥተዳደር እሳቤ እና ፍልስፍና ከግሪኩ አሪስቶትል እስከ ሮማው አውጉስቲን፣ ከሆብስ እስከ ማርሲለስ፣ ከማካቬሊ እስከ ዢን ዣክሩሶ ያሉት ፈላስፋዎች ኃይልን የአንድ መንግሥት የሥልጣን ምንጭም፣ በሥልጣን ላይ መዘውተሪያ መሣሪያም አድርገው ይወስዱታል።
በእነዚሁ አሳቢዎች እይታ ውስጥ ግን ኃይል ብቻውን የሕዝብ ይሁንታ ያለማስገኘቱ እውነታ እና መንግሥትም ያለይሁንታ መቆየት ስለማይችል በተለዋጭ ቅቡልነት የሚያገኝባቸው መንገዶች ልዩ ትኩረት ተችሯቸዋል። ሁሉም ፍልስፍናዎች ካላቸው ሰፊ ልዩነት ጋር ‹‹መንግሥት በሥልጣን ላይ መሰንበት የሚችለው በእርሱ ላይ ተስፋ የሚጥልበትና ይሁንታውን የሚቸረው ሕዝብ እንዲኖር በሚከተላቸው ፖለቲካዊ ሥልቶችም ጭምር እንጂ በኃይል ብቻና ብቻ አይደለም›› የሚለውን አስተሳሰብ ይጋራሉ።
ፓሮኪያል ሊባል በሚችል የፖለቲካ ባሕል ውስጥ በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥም ቢሆን ሕዝብ ለመንግሥቱ ይሁንታ የሚቸርባቸው መንገዶች አሉ። በተለይ ከተሟላ ዴሞክራሲያዊ አሥተዳደር በመለስ ካሉ ሥርዓቶች መካከል ‹‹ጠቅላይ አውራ ፓርቲ›› በመባል የሚታወቀው ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረግ ሽግግር አንፃራዊ አመቺነት ያለው ብቻ ሳይሆን ሕዝብ በሥርዓቱ ላይ ተስፋ ሊጥልበት የሚያስችለው ቅቡልነትን አጣምሮ መያዝ የሚያስችለው ተቋማዊ ባሕሪ አለው። እንደ አብነት እንደ ሜክሲኮ፣ ማሌዥያ እና ኬንያን የመሳሰሉ አውራ ጠቅላይ ፓርቲ ሥር የነበሩ አገራት ወደ ዴሞክራሲ ያደረጉት ሽግግር ኃይል መር የነበረው የቀድሞው መንገድ ተስፋ ሲያስቆርጥ በተከተሉት ከፓርቲዎቹ በሚመነጭ የሕዝብን ቅቡልነት የሚያስገኝ የጥገና የለውጥ ሂደት ነው።
በአገራችንም ተሞክሮ ሥልጣንን ከአምላክ የሚሰጥ መለኮታዊ በረከት አድርገው ሲገዙ የኖሩ ነገሥታት ምድራዊ የቅቡልነት (ሌጂቲሜሲ) ማግኛ መንገዶችን መከተል ግድ ይላቸው ነበር። ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ሳይቀር በአንዳርጋቸው አሰግድ የመኢሶን ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ የተቀመጠውን አገላለፅ ብዋስ ከነበሩት የመጨቆኛ መሣሪያዎች እና አዋጆች በተጨማሪ ከሕዝቡ ብዙኀኑ ፈቅዶ እንዲገዛለት ለማድረግ ‹‹አብዮታዊ ቅቡልነት›› የሚያስገኝለትን ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረበት።
‹‹መንግሥት ያለ ሕዝባዊ ቅቡልነት መቆየት አይችልም›› ስንል የሚሻሻለውና የሚቀየረውም በአንድ አካባቢ በሚነሣ ብርቱ ተገዳዳሪ ኃይል ሳይሆን ቅቡልነቱ የልዩነት ገደብ ከሌለው የብዙኀን ባሕል (Public culture) በሚመነጭ የቅቡልነት መነፈግ እንደሆነ የAlexis de Tocqueville የአብዮት ጥናት ንድፈ ሐሳብ ያትታል። ለዚህም ሲባል ፍጹም አምባገነን መንግሥታትም ይሁኑ ጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት መንገዱ ቢለያይም የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ይሠራሉ። መሠረታዊው ጉዳይ መንግሥታት የሕዝብን ይሁንታ ሲያጡ ሥልጣናቸውን አስመልክቶ የሚወስኑት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። አብዮት ወንበራቸው ላይ መሞት ለሚመርጡ አምባገነን መንግሥታት ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ሲያገለግል የጥገና ለውጥ ደግሞ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሕዝብን ይሁንታ የማስቀጠልን እድል ለመጠቀም የወሰኑ መንግሥታት መውጫ ቀዳዳ ነው። ኢሕአዴግም ዛሬ የደረሰበት ተስፋ መቁረጥ ዶክተር አብይን ተስፋ እንዲያደርግ ሳይገፋው በፊት የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት የተጓዘው ረዥም ርቀት ዛሬ ላይ ወዳለበት የቅቡልነት መንጠፍ በድንገት እንዳልመጣ የሚነግረን ነገር አለው።
የኢሕአዴግ ተስፋ መቁረጥ የጠቅላይ ሚንስትሩ የቅቡልነት ምንጭ
የኢሕአዴግ መንግሥት በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም፣ በየወቅቱ በሚፈጥራቸው ዲስኮርሶች እና ልማትና አሥተዳደር ተኮር አገራዊ ቅኝቶች ከኃይል በመለስ ሕዝብ ተስፋ እንዲያደርገው የሚያስችሉ ካርዶች ነበሩት። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አሰላሳይነት እየተተነተነ በተለይም ከፍተኛ እና መካከለኛውን አመራር በአንድ እዝ ስር ለመጠርነፍ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
ርዕዮተ ዓለሙ በግልፅ የቀረበ እና ሁሉም በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው ትርጓሜ እንደሌለው ምሁራን እና ፖለቲከኞች ሲናገሩ ይደመጣል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን ኢሕአዴግ ለራሱ በራሱ የቀረጸው በዓለማችን የሌለ አዲስ ርዕዮት ሳይሆን ካሉት ውስጥ መርጦና አሻሽሎ የተጠቀመው ነባር ርዕዮተ ዓለም ነው። የኢሕአዴግ አመራርም የሥርዓቱ ተጠቃሚ ከመሆኑ ጋር ይህንን ርዕዮተ ዓለም አምኖበት ሲቀበለው እና ሲሰብከው ኖሯል፡፡ ይህም ሥልጣን ላይ የመቆየቱ ሂደት በተወሰነ መልኩ ይሁንታ ላይ እንዲመሠረት የራሱን ሚናውን ተጫውቷል።
‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት›› የኢሕአዴግ መንግሥት በርትቶ የሠራበትና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ የሕዝብ ይሁንታን በማስገኘቱ ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሁነኛ ውጥን ነበር። የማንነት ጥያቄ፣ በተለይም የብሄር እና የሃይማኖት መብት ጥያቄ የ1966 አብዮት ዋና ገፊ ምክንያቶች እና አንኳር ጥያቄዎች እንደመሆናቸው መጠን ይህ አጀንዳ ለኢሕአዴግ ካርድ ብቻ ነበር ማለትም እውነታውን ማድበስበስ ይሆናል። እጅግ በተገደበ ማዕቀፍ እና የሥልጣን እድሜን ማራዘም በሚያስችል መልኩ ተቀምሮ ጥቅም ላይ የዋለው ይህ አጀንዳ ኢሕአዴግን መዋቅሩ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በተስፋ እንዲጠብቀው ማድረግ ያስቻለ ነው።
ለብሔር ጥያቄዎች ተቋማዊ በሆነ መልኩ መልስ ለመስጠት የተደረጉ ሙከራዎች ሙሉ ቁመና ኖሯቸው ወደተግባር እንዳይወርዱ ሆን ተብለው እንዲውሸለሸሉ የተደረጉ እና በራሳቸው ለመቆም ሲሞክሩ አንገት ቀና በማያስደርግ ርቀት ጣሪያ የተበጀላቸው ቢሆንም በተለይ በክልሎች ሕዝቡ ‹‹ከኢሕአዴግ ውጭ የተሻለ አማራጭ ይኖራል›› ብሎ እንዳያስብ እስከማድረግ የደረሰ ብርቱ የቅቡልነት ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። ይህንን ሥልት የመረጠው ድርጅቱ ግን ሕዝቡን የቱ ጋር እንዳገኘው እንጂ የት ድረስ ይዞት ሊጓዝ እንደሚችል አስቀድሞ መተንበይ ባለመቻሉ ከዚህ በላይ ሊያስጉዘው እንዳልቻለ ከረፈደም ቢሆን በሚገባ ተረድቶታል። የብሔር ፖለቲካ ጅረት በስተመጨረሻ የሚደላደልበት የአካታች ፖለቲካና ፍትሐዊ አሥተዳደር ግድብ ካልተሠራለት መድረሻው ላይ የሚያስከትለውን አደጋ፣ እንዲሁም በመንገድ ላይ ከመስመር እየተገነጠሉ አቅጣጫ ስተው የሚፈሱ ብሄር ተኮር የፖለቲካ አክራሪነቶች የሚያመጡትን መዘዝ መተንበይ አልቻለም።
የብሔር ፖለቲካ ከማንነት ንቃት እና ማስከበር አልፎ ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አጀንዳው ሲያደርግ ያንን የሚያስተናግድ ተስተካካይ የፖለቲካ ማሻሻያ ይፈልጋል። ብሔርን መሠረት ያደረገው የፖለቲካ ሥርዓት ከትሩፋቶቹ ባሻገር ተቀናቃኝ ኃይሎችን ለማዳከም የረዳ ቢመስልም የሁሉም ብሔሮች አጀንዳ ፍትሐዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መሆን ሲጀምር ግን የፖለቲካ ጨዋታው በጠቅላዩ አውራ ፓርቲ እና በብዙኀኑ ሕዝብ መካከል እንዲሆን ማድረጉ አልቀረም። ኢሕአዴግ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያስገኝልኛል ብሎ ተስፋ የጣለበት የብሔር ፖለቲካ ተስፋ ማስቆረጥ የጀመረውም በዚሁ ምክንያት ነበር።
እዚህ ጋር በግሌ የማላምንበትን አንድ ሐሳብ አንስቼ ልለፍ። የብሔር ፖለቲካ ለኢሕአዴግ የሥልጣን ምንጭ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን ሆን ተብሎ የተሰራ ቀመር እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበው መላምት የማንነት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የሚያስፈልጋቸውን ፖለቲካዊ መፍትሄ እውቅና የነፈገ፣ አስረጅ ሲቀርብለት የማይታይ፣ ለኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግሥት አስተዳደር ተሞክሮ የማይመጥን እና የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት ሚስጥርን የዘነጋ መሠረት የሌለው መላምት ሆኖ ይታየኛል። ስለዚህ የብሔር ብሔረሰብ መብትን ኢሕአዴግ ለሥልጣን ቆይታው በአንድ በኩል የጋራ ፍላጎት ኖሮት በአንድነት የሚቆም ሕዝብ እንዳይፈጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦችን የተገደቡ የተናጠል ፍላጎቶች በመሙላት ያልተማከለ የሕዝብ ይሁንታን የማግኛ መንገድ አድርጎ መጠቀሙን ካሰመርን ለእውነታው በቂ ነው።
የብሔር ካርዱ ሙሉ ለሙሉ ባይከሽፍ እንኳን ሩቅ እንደማያስጉዝ በመታመኑ ደጋፊ በማበጀት ማስቀጠሉን በመሻት የልማታዊ መንግሥት እሳቤ የፖለቲካውን ገበያ በበላይነት እንዲቆጣጠር ተደርጓል። ይህም ቢሆን ግን የሚሸከም የፖለቲካ እና የቢሮክራሲ መዋቅር ይፈልጋልና ከኢሕአዴግ በነበረበው ዘይቤ ብቻ የመጓዝ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።
በልማታዊ መንግሥት ስኬታማ ተሞክሮ የነበራቸው የእስያ አገራት ጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ማለፋቸው ሁሉም ጠቅላይ አውራ ፓርቲ ያንን ማሳካት ይችላል ማለት አይደለም። የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ከሚቆምባቸው አራት ዋና ዋና ማዕዘናት ውስጥ ከፊሎቹ ቀድሞውንም በኢትዮጵያ ያልነበሩና አሉ የሚባሉትም በሂደት እየተሸረሸሩ የመጡ ነበሩ። ሞዴሉ ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ መንግሥት እና መሪ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን የሚቀርፅና የሚከታተል በክህሎት የሚመራ ገለልተኛ ቢሮክራሲ፣ ከመንግሥት ጋር በመተባበር መንፈስ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ፍቃደኝነቱም አቅሙም ያላቸው ባለሐብቶች፣ እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ ሕዝቡን በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያሰባስብ የሚችል ብሄራዊ የአገር ፍቅር ስሜት በመሠረታዊነት ያስፈልጋሉ።
ልማታዊው መንግሥት የሕዝብን ቅቡልነት ያስገኛል ተብሎ ሲታሰብ በወቅቱ በዋናነት ገለልተኛ ቢሮክራሲ አለመኖሩ ትልቁ ፈተናው ነበር። በኢትዮጵያ ሚሌኒየም አጋጣሚ ጀምሮ በኅዳሴው ግድብ የቀጠሉት የብሔራዊ ስሜት ማጎልበት ሙከራዎች፣ እንዲሁም የጠንካራ መሪ ጉዳይ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ሊገኙ አልቻሉም። የፖለቲካ ሥርዓቱ ሞዴሉን ለማስተግበር የሚያስችለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ሙስናን የመከላከል አቅም ማጣቱ ጅምር ፕሮጀክቶች ናሙና ለመሆን እንኳን ሳይበቁ በቆሙበት እየቀሩ ሞዴሉ የታለመለትን ግብ ሳይመታ ቀረ።
ኢሕአዴግ እንደማንኛውም ጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦ እንኳን የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማምጣት ቢሳካለት ቅቡልነቱን ማስቀጠል የሚችልበት እድሉ ነበር። ግና እያደገ ከመጣው የሕዝብ ፍላጎት አንፃር ተስተካካይ በሆነ መልኩ ማደግ የተሳነው ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ፍጹም ኢ-ፍትሐዊነት የተሞላበት የሐብት ክፍፍል ኅብረተሰቡን በድህነት ውስጥ እንዲቆይ ሲያደርጉት በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች መክሸፍ የልማታዊ መንግሥት እሳቤ ሥጋ ለብሶ መቆም ያልቻለ ምኞት ብቻ ሆኖ እየቀረ ለመሆኑ ጠንካራ ማሳያዎች ሆኑ። በዚህም የሕዝብን ይሁንታ የሚያስገኙ ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ የማይቻልበት ‹‹መንግሥታዊ ተስፋ መቁረጥ›› ውስጥ መገባቱ ለቀጣዩ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ በር የከፈተ ነበር። ይህ ሁሉ ሲደማመር ኢሕአዴግን ተስፋ የቆረጠ ድርጅት አደረገው።
ይህ መንግሥታዊ ተስፋ መቁረጥ የማይነካውን መንካት እና የማይሞከረውን የመሞከር ግብታዊ አካሄድን መውለዱ የሚጠበቅ ነበርና ችግሮች እዚያም እዚህም መከሰት ጀመሩ። ሃይማኖት እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የመብት ጥያቄዎች አራት አሥርት ዓመታት የከሰሙ መስለው ከነበሩበት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። አስቀድሞ በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ለመጋረድ ቢሞከርም ተግባራዊ መገለጫ ስላተበጀለት የ‹‹ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን›› የቃላት ውዳሴ በኢትዮጵያ ‹‹የከፍታ ዘመን›› የቃላት ተውሶ ቢተካም ‹‹አሮጌ ወይን በአዲስ አቁማዳ›› ከመሆን ማለፍ ባለመቻሉ ከትሳፎ መቅረቱ ግድ ሆነ። ታዲያ የኢሕአዴግ ተስፋ ማን ይሆን?
ተስፋ ለቆረጠው የተቃዋሚ ፖለቲካ ተስፋ የሆነው ጠቅላይ ሚንስትር
ከገዢው ፓርቲ በተቃራኒ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የተሻለ ቅቡልነት ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ያደረጉት ጥረት ኢሕአዴግ ባጠበበው የፖለቲካ ምኅዳር እና በፓርቲዎቹ የውስጥ ድክመት ምክንያት ለራሳቸውም ለሕዝቡም ተስፋ መሆን እየቻሉ አይደለም። በሦስት እርከን እንኳን ከፍለን ብንመለከተው ከ1983 እስከ ምርጫ 1997 ያለው ሂደት አዝጋሚ፣ ነገር ግን ተስፋው ያልተሟጠጠ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲካ ነበር ማለት እንችላለን። ፓርቲዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በራሳቸው መንገድ ሕዝብን የሚደርሱ እና ስለሕዝብ የሚቆሙባቸው እድሎች ነበሩ። ከምርጫ 97 በኋላና በተለይም ሕዝባዊ አመጽ በስፋት መቀስቀስ እስከጀመረበት 2004 እና 2007 ድረስ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸው የቀነሰበት፣ ነገር ግን ሕልውናቸው ሙሉ ለሙሉ ያላከተመበት ሁኔታ ነበር። ፓርቲዎቹ ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚፎካከሩበት እድልም አቅምም ባልነበረባቸው በእነዚህ ዓመታት ሕዝብ ከተቃውሞ በዘለለ ድምጹን ሊያሰማበት የሚችለው አቅም በሌለው ሁኔታ የሕዝብን አጀንዳ ህጋዊ ሽፋን በመስጠት ለማጉላት የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ ቆይተዋል። እነሱም እንደ ፓርቲ የመቀጠላቸውን አስፈላጊነት የሚያምኑበት ዋነኛ ምክንያት ይኸው ሆኖ ዘልቋል።
በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ እና በሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው አለመረጋጋት ግን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና ምንም ያደረገ እና ገዢውን ፓርቲ ሳይቀር ከፓርቲነት ወደ ንቅናቄነት ዝቅ ያደረገ አጋጣሚ ሆኗል። ፓርቲው በሁሉም እንቅስቃሴዎቹ ያልተደራጀ፣ ያልተጠና፣ ተቀባይነት ማግኘት የማያስችል አካሄድ እና ግብረ መልስ በመስጠቱ የአገሪቱ የፖለቲካ ውጥረት መብት በሚጠይቅ ሕዝብ እና በገዢ ፓርቲ መካከል መምሰሉ ቀርቶ በሁለት ትላልቅ ንቅናቄዎች መካከል የሚደረግ ያልደራጀ ፉክክር እስከመምሰል ደርሷል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ከፍ ብሎ የሚያስብ፣ ለሕዝብ ተስፋ መስጠት የሚችል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም። ለ27 አመታት የዘለቀው የፓርቲ ፖለቲካ ለውጥን ከገዢው ፓርቲ ውጭ ሊያመጣ የሚችልበት ሞዴልም ፍንጭም ማሳየት ባለመቻሉ ለውጥ ፈላጊዎች ከኢሕአዴግ ሰፈር የሚመጣን ተስፋ ከመጠባበቅ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም። ኢሕአዴግ በራሱም በሕዝቡም ተስፋ ሲቆርጥ ሕዝቡም በኢሕአዴግ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በራሳቸው፣ ሕዝቡም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስፋ ቆርጠዋል።
በዚህ ተስፋ መቁረጥ መካከል ነው እንግዲህ ዶክተር አብይ ወደጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቅ ያሉት። ኢሕአዴግም ከመዋቅሩ በላይ በዶክተሩ ተስፋ አድርጓል። ሕዝቡም በኢሕአዴግ ሳይሆን በዶክተሩ ተስፋ አድርጓል። ተቃዋሚውም በራሱ አቅም ወይም በኢሕአዴግ ለውጥ የማምጣት የፓርቲ ፈቃደኝነት ሳይሆን በዶክተር አብይ ተስፋ አድርጓል። እነዚህ ተደራራቢ ተስፋ መቁረጦች አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የመጪው ጊዜ ተስፋ ተደርገው እንዲሳሉ ያደረገ ዋነኛ የቅቡልነት ምንጭ ሆኗል።
በራሱ ሰፊ ርዕስ የሚፈልግ በመሆኑ በዝርዝር ባልገባበትም የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም ምዕራባውያን በቀደመው የሕወሓት የበላይነት በሚመራው የኢሕአዴግ አሠራር ተስፋ ቆርጠዋል። በቀጠናው ላይ ሁሌም መረጋጋት እንዲኖር መፈለጋቸው እና የኢትዮጵያ ቀውስ ከቀጠናው አልፎ እነሱንም እንደሚነካ ማወቃቸው አገሪቷ ዳግም ወደተረጋጋ ሁኔታ መመለሷን አጥብቀው እንዲፈልጉት አድርጓቸዋል፡፡ አምባገነን መንግሥታት የውስጥ ጉዳያቸውን መቆጣጠር እስከቻሉና የእነርሱን ጥቅም እስካስከበሩላቸው ድረስ ምዕራባውያን ለዴሞክራሲ ማስፈን ብለው የሚከፍሉት ዋጋ እንደሌለ መካከለኛው ምሥራቅ ሕያው ምስክር ነው። የአሜሪካ የጸረ ሽብር ዘመቻ ትርክት እየደበዘዘ መጥቶ በኃያላን አገራቱ ፉክክር የአሜሪካንን አሸናፊነት ማሳየት ዋናው ግብ ወደመሆን መሸጋገሩ ከፈረንጆቹ ጥር ወር ጀምሮ መታወጁ ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር ዘመቻው አጋር በመሆን ያላትን ትኩረት ቢቀንሰውም አገራቱ በቀጠናው ላይ ላላቸው ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም አሁንም ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና አላትና ዋና አጀንዳቸው ነች። ኢሕአዴግ ግን አጋራቸው የሆነችውን ኢትዮጵያን የማረጋጋት የውስጥ አቅሙን እንዳጣ ተረድተዋል። ዶክተር አብይን ወደ ሥልጣን እንዲመጡና ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኙ የረዳቸው ሶስተኛ ተስፋ መቁረጥ የምእራባውያን አድርገን ልንወስድ እንችላለን።
ተስፋ ሲወለድ ተንከባካቢ ተስፈኞች ይፈልጋል
ዶክተር አብይ አሕመድ የተመሳሳይ ሥርዓት እና የተመሳሳይ መንግሥት ተተኪ ጠቅላይ ሚንስትር እንጂ አዲስ ሥርዓት እና መንግሥት ይዘው ባለመምጣታቸው ሹመታቸውም ሆነ በቀጣይ ከርሳቸው የሚጠበቁ የለውጥ ሂደቶች ሊመዘኑ የሚገባው በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑን ማስታወስ ይሻል። ምክንያቱም የፍላጎት መቃወስ (Expectation Crisis) ትልቁ ቀጣይ ፈተና ስለሚሆን የሚጠበቀውን ብቻ በመጠበቅ መርህ ላይ መጓዝ ወሳኝ ነውና።
ሕዝባዊ ትግሉ በዋናነት ሁለት የተለያዩ ግን ደግሞ ተያያዥ ውጤቶች እንዲመጡ በማድረግ ድል አድርጓል። በቅድሚያ ከዚህ ቀደም የኢሕአዴግ ሕልውና ማለት የህወሓት ህልውና እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታይ ኢሕአዴጎች ህወሓትን መስማት እና መንከባከብን የሕልውና ጉዳያቸው አድርገው ይይዙት ነበር። አሁን ግን የህወሓት ሕልውና መቀጠል የሚችለው በኢሕአዴግ ሕልውና ውስጥ ብቻ በመሆኑ ኢሕአዴግን ሕያው ድርጅት እንዲሆን ማድረግ ህወሓት ለሕልውናው ሲል የሚሠራው ተቀዳሚ ኃላፊነቱ ያደርጋል።
በሁለተኛ ደረጃ የኢሕአዴግ ሕልውና የሕዝብን እና የአገርን ሕልውና የሚወስንበት ሁኔታ ተቀልብሶ ኢሕአዴግ ሕልውናው በሕዝብ እጅ እንዲሆን አድርጎታል። የመንግሥት የላይኛው የሥልጣን እርከን እታች ባለው ኅብረተሰብ ድጋፍ እና ተቃውሞ የሚወሰንበት አዲስ የፖለቲካ ንፋስ እየነፈሰ ነው። ይህን ስኬት የህግ፣ የመዋቅር እና የአሠራር ሂደት ውስጥ በመክተት እንዳይቀለበስ ማድረግ ‹‹ተስፋ መቁረጥ ዶክተር አብይን ተስፋ እንዲያደርጉ ያደረጋቸው ሁሉ›› ኃላፊነት ነው። በሌላ አገላለጽ ዶክተሩ የሥር ነቀል ለውጥ መሸጋገሪያ እንዲሆኑ ትእግስት እና ትብብር ይሻሉ። ጠቅላይ አውራ የፓርቲ ሥርዓት ጥገናዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ የሚፈልገውን ትንፋሽ እንዲወስድ እድል ሊሰጠው ይገባል።
በአንድ ሥርዓት ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በአብዮት ብቻ ሳይሆን በስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ ተፅእኖ ማሳደር የሚችለው የኃይል ክፍል ከነበረበት ቦታ የተሻለ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት ወደሚችልበት ቦታ መዛወር ሲችልም ሊሆን ይችላል። ሥልጣን ከግለሰብ እና ቡድን ወደ ሕዝብ እና የሕዝብ ተወካዮች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ከፖለቲካ ምርኮ ነጻ ወጥቶ በሦስቱ የሕግ አካላት የበላይነት መርህ በሚኖር አሠራር መተካት ሲቻልም ለውጡ ሥር ነቀል ለመባል ይበቃል። ፍትሐዊ ምርጫ የማያደርግ ጠቅላይ አውራ ፓርቲ የራሱንም ሕልውና በምርጫ ለማረጋገጥ ወስኖ ወደ ምርጫ ከገባም አብዮት ሊያስገኘው ከሚችለው ውጤት በላይ ትርፍ ሊኖረው ይችላል። በተለይ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ የሚያደርገው ሽግግር ውጤታማ የሚሆነው የራሱን ሕልውና ማስከበር በሚችልበት ሂደት ውስጥ እንዲያልፍ ቀዳዳ ሲያገኝ በመሆኑ ተስፋ መቁረጡ ተስፋ ያስገኘላቸው ባለድርሻዎች በሙሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚያጋጥማቸውን የፍላጎት መቃወስ (Expectation Crisis) ሊሸከሙላቸው ይገባል።
ተስፋ የቆረጠው ኢሕአዴግ ዶክተሩ ሕዝቡን እንደ ቀድሞ ትኙ እንዲያደርጉለት፣ አልያም ስታተስኮውን ብቻ እንዲያስጠብቁለት ከማሰብ በአገሪቱ ሕልውና ውስጥ እውን የሚሆን ሥርዓታዊ ሕልውናውን እንዲያረጋግጡለት ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኢትዮጵያ ትንሳዔ የራሱን አሻራ የሚያሳርፍበት እድል አለ። ተቃዋሚዎች የ27 ዓመት ተሞክሯቸው የፈጠረውን ተስፋ መቁረጥ በተለምዶ በሚነገረው የ100 ቀናት የሥልጣን ቆይታ ቆጠራ ለማካካስ ከመሞከር ቢቆጠቡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲመጣና እነሱም የዚያ ሥርዓት ትርጉም ያላቸው ተዋንያን እንዲሆኑ መንገዱን መጥረግ ይችላሉ። ከዴሞክራሲ ግንባታ በላይ በዴሞክራሲ መደላደል (Democratic Consolidation) ላይ የተሻለ ሚና ስለሚጫወቱ ለዚያ በሚመጥን መልኩ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ቀጣይ ሚናቸውን ማሳደግ ይችላሉ።
ከሕዝባዊ ትግሉ በስተጀርባ ያሉ አካላት በበኩላቸው ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ትምህርት በመውሰድ የለውጥ ሂደቱን ፍሬ እንዲያፈራ የማገዝ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት አካሂደው በወታደራዊ መንግሥት አብዮታቸውን ተቀምተዋል። በትጥቅ ትግል ለ17 ዓመታት የቆመችው አገራቸው በጠቅላይ አውራ ፓርቲ ሥርዓት መዳፍ ሥር ወድቃ መቆየቷ ውጤቱ ምን እንደሆነ አይተዋል። ባልተደራጀ እና የአንድን ሕዝብ ፍላጎት ብቻ ባማከለ ትግል አገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ትምህርት ቀስመው መንገዳቸውን በማስተካከል ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ከእነዚህ ሂደቶች የሚወሰደው ዋናው ትምህርት ደግሞ የለውጥ ሂደት ለየትኛውም አካል በአደራነት ተላልፎ የማይሰጥ የራሱ የሕዝቡ ኃላፊነት መሆኑ ነው። ሕዝብ የለውጥ ሂደቱ ዘብ ሊሆን ይገባዋል። ዘብ ሲሆን ግን ያለጊዜው የሚረግፍ ፍሬ ሆኖ ከመንገድ እንዳይቀር እና በተሳሳተ መስመር ተጉዞ ከሚታሰበው ተቃራኒ ውጤት እንዳያመጣ ብልህነት እና ታጋሽነት በተሞላበት መልኩ የተጠና ጉዞ በማድረግ ነው። ሕዝቡ ሁሌም ከአገሩ እና ከጥቅሙ ጎን እንደሆነ ሁሉ ነገም አገሩን እና ጥቅሙን እያሠላ መጓዙን ከቀጠለ ድል የሕዝብ ከመሆን ውጭ አማራጭ አይኖራትም።