>

ግንቦት 20 ለጋሞ ጎፋ ሰው ምኑ ነው?(ጋሞ ጎፋ ኦንላይን)

ሥርዓቱ እና የሥርዓቱ ሰዎች ወታደራዊውን የደርግ መንግስት ከሥልጣን የገረሰሱበትን 27ኛ ዓመት ልደት እያሰቡ ይገኛሉ። ምንምእንኳን ብዙሃኑን የሀገሪቱን ህዝብ ወይም አካባቢ አይወክሉ እንጂ በዚህ ቀን ምክንያት ያለፉትን ሀያ ሰባት ዓመታት የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ የተመረጡ በርካታ የህበረተሰብ ክፍሎች አሉ። ለእነርሱ ይሄ ቀን በርግጥም እንደብሄራዊ በዓል መቆጠሩ ስያንሰው ነው።
ብዙዎች ግንቦት ሃያን በጦርነቱ ድል የተቀናጁት ኢህአዴጋውያን በፌሽታ የሚያከብሯት፤ድል ተነስቶ ሀገር ጥለው የኮበለሉት የደርግ ሰዎች በመጥፎ ትዝታ የሚያስቧት ብቻ እንደሆነች አድርገው ያስባሉ።
ነገር ግን ግንቦት 20 ከደርግ እና ኢህአዴግ ትዝታዎች በላይም ነች።
ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ሀገር ወደመምራት በመምጣቱ የተነሳ የተጠቀመም የተጎዳም አካል አለ።
ስለተጣቃሚዎቹ ተጠቃሚነት የሚነግሩን የሥርዓቱ ሚዲያዎች ተኝተው ስላማያድሩ ድምፃቸው ስለተነፈገባቸው የግንቦት ሃያ ተጎጂዎቹ እናውራ።
ደርግ አከናወናቸው ስለሚባሉ እውነታዎች እንዳይወራ እና ዘላለም መጥፎ ሥራዎቹ ብቻ ሲነገሩ እንዲኖር በሚፈልጉት የኢህአዴግ ሰዎች ዘንድ በርግጥ ይሄ ጥረት የሚያስኮንን ነው። ይሄን በማለታችን ግን ወይ ተናደው የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ቢሉን አልያም ደግሞ ከፍ ካለም ራስ ምታት ቢለቅባቸው ነው።
ደርግ እና ሊቀመንበሩ መንግስቱ ሀ/ማርያም የሚተቹባቸው ደካም ጎኖች አሏቸው። በተፃራሪው ደግሞ በርካታ መልካም ሊባሉ የሚችሉ ጥንካሬዎችም እንደዝያው አሏቸው።
አምባገነንነት ያልደበቀው የማያወላውል የሀገር ፍቅር ስሜት፣ምክንያታዊነት እና ተቆርቋሪነት ከደርግ ውድቀት በኋላ ለዝህ ዘመን ትውልድ እንዳይወሩ ጥረት የተደረገባቸው መገለጫዎቹ ናቸው።
ብዙዎቻችን መገለጫው ነው ብለን እናስብ ከነበረው አጥፊነት ሲመለስ የተረፈውን ጊዜ ትውልዱ አሁንም ድረስ ስያመሰግነው እንዲኖር የተገደደባቸው የሚታዩ ሥራዎችን ሰርቶ አልፏል። የደርግን ከኢህአዴግ ያልተናነሰ የልማታዊነት ባህርይ ለመረዳት የአርባ ምንጭ ከተማን ጉዳይ አንስቶ መነጋገሩ በቂ ነው።
ደርግ ዘውዳዊውን የአጼ ሀይለሥላሴን ዙፋን በመፈንቅለ-ምንግስት ገርስሶ ሥልጣን ሲቆጣጠር አርባ ምንጭ ገና 10 ዓመት በቅጡ ያልሞላት እምቦቅቅላ ነበረች።
በ17 ዓመቱ የደርግ አገዛዝ ዘመን በመላ ሀገሪቱ ፍትሀዊ የሀብት እና ዕድገት ክፍፍል እንዲኖረ በተደረገው ጥረት ከተማዋ ተጠቃሚ መሆን ችላለች። የሚያስፈልጋትንም ሆነ የሚገባትን ሊሰጣት የሞከረ መንግስት ነበር።
ኮለኔል መንግስቱ ሀ/ማርያምም የዛሬው አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ግንባታ የመሰረት ድንጋይን ለማስቀመጥ የተገኙበትን ጨምሮ ከ3 ጊዜ በላይ ወደከተማዋ ተመላልሰዋል። አንድ መሪ ወደአንድ አካባቢ ደጋግሞ ከተገኘ ለዝያ አካባቢ ያቀደው መልካም ነገር አለ ማለት ነው።[ልክ የዛሬዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች ወደሀዋሳ መለስ ቀለስ እንደሚሉት መሆኑ ነው እንግዲህ]
ይህ ለሀገሪቱ ከአዲስ አበባ እና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ቀጥሎ የተሰጠው 3ኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በኮለኔሉ መልካም ፍቃድ የአፍሪካ የውሀ ምርምር ሥራዎች የልዕቀት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ ነበር የተቋቋመው። ለምሥረታው ጀምሮም ለዓመታት ጠንካራ የምርምር ተቋም መሆን ችሏል።
ዩኒቨርሲቲው ከሚገኝበት ሥፍራ ብዙም ሳይርቅ በተመሳሳይ ዓመት ሊባል በሚችል የጊዜ ልዩነት የሀገሪቱ ግዙፍ የኢንዳስትሪ ማዕከል አሁንም በሊቀመንበሩ መልካም ፍቃድ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ።
በወቅቱ ደርግ አርባ ምንጭን የሀገሪቱ አንዷ አካል እንደሆነች ያስመሰከረበትን ኢንዳስትሪ ለመገንባት የፈጀበት ገንዘብ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የነበረ ሲሆን የፋይናንሱም ምንጭ የያኔዋ ወዳጅ ሀገር ሰሜን ጀርመን ነበረች።
እነዚህን ሁለት በቀድሞው መንግስት ለከተማዋ የተበረከቱ ስጦታዎችን አየን እንጂ ህያው ምስክሮቹስ ብዙ ናቸው።
እስኪ አሁን ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያለፉባቸውን መንገዶች በወፍ በረር እንመልከት።
አርባ ምንጭ ዩነቨርሲቲ የአፍሪካ የውሀ ምርምር የልዕቀት ማዕከል የመሆን ህልሙ ቀርቶ በብዙ መንገዶች የድርቀት ማዕከል ሆኗል። ድሮ ድሮ ከቀዳሚዎቹ ተመራጭ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የነበረው ተቋም ዛሬ በአከባቢው ለተከሰቱ ችግሮች እንኳ መፍትሄ መፈለግ አቅቶት በቴክኒክ እና ሞያ ኮሌጆች ተበልጧል። በተጨማሪም በተለያየ ጊዜ እንደሚሰማው የተጧጧፈ የሙስና ሥራዎች የሚሰሩበት፣በውሀ በተከበበችው ከተማ ውሀ በተደጋጋሚ ጠፍቶ ሲትጠማ በምርምር ሥራዎቹ መፍትሀ መሆን ሳይችል ቀርቷል።
ኢንዳስትሪ የተባለውም ከጊዜ ወደጊዜ ተመናምኖ አሁን ላይ በከተማዋ ከፍታ ስፍራ ላይ ሆኖ ለሚመለከት ሰው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ወደመምስል የደረሰ ተቋም ነው። ምንም አይነት ማስፋፍያም ሆነ ጥገና ተደርጎለት የማያውቀው ይህ ተቋም የሥራ ዕድል አግኝተው ይሰሩ የነበሩትን የአካባቢውን ተዎላጆች በሂደት በማባረር ሙሉበሙሉ ማለት በምያስችል ደረጃ ከተማዋን ለቆ ወጥቷል። ይሄንን እንድንል የሚያስገድደንም ከዓመት በፊት ፋብሪካው ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ወደሌላ አካባቢ ተዟዝሮ መገንባቱ ነው።
27 ዓመታትን ተጉዘን ዛሬም ድረስ ያቺ ድፍን ሀገርን በሙዝ እና ዓሳ ምርት የምትመግበው ፣እርሷን እና የተፈጥሮ ሀብቷን ለማየት ብለው ባህር ተሻግረው ከሚከትሙ ጉብኝዎቿ በሚገኝ ገቢ የሀገሪቱ የቱሪዝም የገቢ ምንጭ የሆነችው ከተማ አሉልኝ ብላ የምትኮራባቸው የማዕከላዊ መንግስት ስጦታዎቿ እነዚህ ብቻ ናቸው። ለ27 ዓመታ ኢህአዴግ አፉን ሞልቶ ይሄን ሰራውላት የሚለው ነገር የለውም!
ይሄንን እና መሰል የአርባ ምንጭ አሳዛኝ ገጽታዎችን ለተመለከተ ሰው ደርግ ኖሮ ኢህአዴግ የሚባለው ሥርዓት ባይመጣ ምነው ማለቱ አይቀርም።

Filed in: Amharic