ትልቁ ብሥራት የፖለቲካ እስረኞች ክሶች መቋረጥና መፈታት ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊነት መሰበኩ ነው ፡፡ የመግባባትና የእርቅ ድባብ እንዲወርድ ፍላጎት ማሳየቱ ነው ፡፡ «ተፎካካሪ ፓርቲዎች» ስለ ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅ ማውረጃ ንድፎች ላይ ሃሳብ ለሃሳብ እንዲወያዩ መጀመሩ ነው ፡፡ ባጭሩ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ ሂደት በምር መጀመሩ ፍንጭ መታየቱ ነው ትልቁ የዶክተር ዓቢይ የእስካሁኑ ስኬት ፡፡ በሁሉም ዘንድ ተስፋችን መለምለሙ ብቻ ሳይሆን የእርስ በእርስ መበጣበጥና መመሰቃቀል አፋፍ ላይ የነበረችው አገር ወደ መረጋጋት ፊቷ መመለሱ ነው ትልቁ ነገር ፡፡ ምንም እንኳን ለዶክተር ዓብይና ለቲም ለማ ሁሉም በተራውና ከየአቅጣጫው የፍላጎቱ መመዝገቢያ ሊስት Wish listቢያዥጎደጉዱለትም፣ ዕድልና አዲስ ተስፋ መፈንጠቁን እናቶች ተቀብለው ነው ቱፍ ፣ ቱፍ እያሉ ከፉ አይንካብን ምርቃት የሚቸሩት ፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ሥስቴ የሚል አዲስ ስም አወጡለት እየተባልንም ነው ፡፡
ባንጻሩ ጥርጣሬው ለከት የለውም ፡፡ ዋናው ዶክተር ዓብይን የወያኔ/ ኢሃዴግ ሴራ ተቀባይና ወኪል አድርጎ መመልከቱ ነው አንዱ የጥርጣሬ ስጋት፡፡ በስርአቱ ተኮትኩቶ የተመነደገ የጉዲፈቻ ልጅ እስከማለት ፡፡ እነዚህ ምክንያቶቻቸውን እንደሚደረድሩት ሁሉ የዓብይ ደጋፊዎችም በተራቸው ከሙሴ እስከ ጎርባቾቭ ከስርአቱ ሆድ እቃ ለውጥ ፈላጊው ብቻ ሳይሆን ነጻ አውጪው ነብይ ተመዞ የወጣ እንደ ሆነ ሁሉ ያስተምራሉ ፡፡ አንድ የሃይማኖት አባት በፈርዖን ቤተ መንግሥት *? ማደግ የእስራኤል ህዝብ መሪነቱና ሀራ ማውጣት ተልእኮውን አልጋረደበትም ይሉናል ፡፡ ሌሎቹ የጎርባቾቭ ስም ከሶብየት ህብረት ኮሚንስት ፓርቲ ውስጥ አድጎና ተመንደጎ በግላስኖትስና ፣ በፐርስቶሪይካ አማካኝነት ታላቋን የሶቭየት ህብረት ከስር መሰረቱ ውልቅልቋን አውጥቶ የለውጥ ኃይል ይሆናል ብሎ የገመተ የለም ይሉናል ፡፡ የዚህ ሁሉ ምሳሌ ዳራ ፣ ለዶክተር ዓብይ ዕድል እንስጥው ነው መልዕክታቸው ፡፡
እርግጥ ለውጡ በሃገር ቤት እየፈጠነ ነው ፡፡ እንደ ደርጉ ባቡር እያራገፈ ብቻ ሳይሆን እያፈናጠጠ ነው ፡፡ ገሚሱ ዶክተር አቢይና ቲም ለማን እንርዳ በማለት ሲቀላቀሉዋቸው ፣ ገሚሱ ደግሞ በተለመደው አፈ ጮሌነት ማዕበሉን መፈናጠጥ ተያይዘውታል ፡፡ ዓረቦቹ – አርከብ አል ሞጃ – የሚሉት አይነት እሩጫ ነው ፡፡ ያም ሆነ ይህ የትግሉ ማዕከል ወደ ሃገር ቤት እየተመለሰ ነው ፡፡ ዲያስፖራው ሚናውና ድርሻውን ብቻ ሳይሆን የትግል ስልቱንም እየፈተሽ ነው ፡፡ ሌላም ቸር ወሬ አለ ! ሁሉም ሰከን ማለት ጀምሯል ፡፡ ለስልጣን አለመታገላቸውንም እየማሉና እየተገዘቱ ባለድርሻናተቸውን ተቀብለው ከሌሎች ጋር ለመሥራት ዝግጁነታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው ፡፡ በዶክተር አብይ ቋንቋ ለመደመር እየተዘጋጁ ናቸው ፡፡ ይበል ! የሚያሰኝ ነው ፡፡ ዕድል የማስመለጡም አባዜም ሆነ እርግማን እንዳይለጠፍበት ሁሉም ጥንቃቄ እየወሰደ ነው፡፡ በዲያስፖራው ካለው ኢትዮጵያዊ አብዛኛው ዘውዱን በኪሱ ይዞ ይዞራል እንዳልተባለ ሁሉ፣ አሁን አሁን የተወሰነ ትህትና እየተመለከትን ነን፡፡ ልካቸውን ፣ ሚናቸውን ፣ የትግል ድርሻቸውንም እየተረዱ እንዳሉ ሁሉ ፀሃይቱ ጎህ ቀዳ በጧት ብቅ የምትለው ጩኽቴን/ ትዕዛዜን / ሰምታ ነው ብሎ ይኩራራል እንደሚባልለት አውራ ዶሮ ፣ ቄሮም ፋኖም ፣ ዘርማም ፣ ሁሉንም ከኋላ የማዞረው እኔ ነኝ ባይ ግብዝ ታጋይም ዛሬም አልጠፋም ፡፡
በሰከን ማለቱ ግንባር ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች ቢኖሩ ከእስር ቤት የፈቱ መሪዎች ናቸው ፡፡ትህትናቸው አስተማሪ ነው፣ የትግል ወኔያቸውም እንዲሁ ፡፡ የትግላችን መዳረሻ ያው ዲሞክሪያሳዊት ኢትዮጵያን መመስረት ጠፍቶህ ነው ወይ ? የትግላችን መዳረሻው የት ነው ብለህ ጉንጭ አልፋ ጥያቄ የምትሰነዝረው ለምትሉኝ አንባቢያን መዳረሻ መንገዱ ነው አስቸጋሪውና ውስብስቡ እላለሁ ፡፡ ከሁሉ የተሻለ ሲናርዮ ብትጠይቁኝ በሽግግር መንግሥት አማካኝነት የሚካሄድ የሽግግር ሂደት ነው ፡፡ በዚህ ሂደት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ እስከ ምርጫው የሚዘልቅ የሽግግር ሂደት ነው እላለሁ ፡ ይህ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ መሳካት መቻሉን እጠራጠራለሁ፣ ስለዚህ አብዛኛዎቹን ባለ ድርሻ አካላቶች ያሳተፈ ማንንም ያላገለለ የሽግግር ሰነድ የሚነድፍ አካል መስርቶ አንድ ሽግግር ሳይሆን በርካታ ሽግግሮች እንደሚያስፈልገን አምኖ መቀበል ነው ፡፡ አዲስ ህገ መንግስትን የመንደፉን ተግባር ለሁለተኛው ሽግግር በመተው ያሁኑ ሽግግር በብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ማውረዱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ስምምነት መድረስ ነው ፡፡ ምክንያቱ እምብዛም አያመራምርም ፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተፋጠው እንዲደራጁ የተደረጉ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ዙርያ ማቀራረቡ ለነገ የማይባል ነው ፡፡ ጥርጣሬው ሞልቶ ፈሷል ፡፡ የዶክተር አብይን ጥረቶች እንደ ኦሮሞ አንግስ ጥረቶች አድርገው የሚመለከቱ አሉ ፡፡ አይፈረድባቸውም ፡፡ ተራው የኦሮሞ እንደሆነ የሚያስመስሉ ወገኖችም አሉ ፡፡ የኦሮሞው ብሄረትኝነት ተግዳሮቶች ተደቅነውበታል ፣ የአማራም ፣ የትግሬም እንዲሁ ፡፡ በሁሉም ተሳትፎ ተረቆ በሁሉም ይሁንታ መታጀብ ባለበት የሽግግር ሰነድ የፌዴራል ስርአቱ አወቃቀር ሊያወዛግብ ይችላል ፡፡ የአማራ ብሄረተኞች ስርአቱን ከጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ውርሶች አንዱ የሆነው ፀረ ነፍጠኛ አማራ ? ግንባር አድርገው እስከተመለከቱት ድረስ የሁሉ ስምምነት * ምልእተ ስምምነት Consensus በፌዴራል ክፍፍሉ ላይ መገኘት ሊያስቸግር ይችላል ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ብሄረተኞች ያልተማከለው የስልጣን ድልድል decentralization በፌዴራል ቅርጹ በመሰረቱ እስከተቀበሉ ድረስ የራሳችን የሚሉት እይታ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ የህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን ወደ ሁለተኛው ሽግግር ለመሸጋገር የፈለግሁበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ፡፡
በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ብሄራዊ መግባባት ውይይቱ ተጀምሯል እስከተባለ ድረስ የውይይቱ መጠናቀቂያ ላይ የሚወጣው ሰነድ አቅጣጫ አመልካች ነው የሚሆነው ፡፡ አስማሚም ነው መሆን ያለበት ፡፡ ለድርድሩ መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰነዶችም ያሉ ይመስሉናል ፡፡ የባለሙያዎቹ conflict managment resolution expertsየጥናት ድርሻም በግምት መውሰድ ሊያስፈልግ ነው ፡፡ ከአምባገነን ስርአት ወደ ዲሞክራሲ የሚደረጉ ጉዞዎች ተሞክሮዎች አሉ ፡ እኛ ከተጨናገፉትም ሆነ ከተሳኩት ዲሞክሪያሳዊ ሽግግሮች ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል ፡፡ መካድ የማንችለው አንድ እውነታ ፍንትው ብሎ ይታያል ፡፡ ኢትዮጵያ በለውጥ ዋዜማ ላይ መገኘቷ ለክፉም ለደግ የምትለውን ሃረግ ልጨምር መሰለኝ !! ፡፡