የኢህአዴግ ፖለቲካ ከሚገለፅባቸው ባህሪዎቹ ውስጥ ድብቅነት፣ ሴረኛነት፣ አደርባይነት፣ ስግብግብነት፣ ግለኝነት፣ ትዕቢተኛነትና ማን አህሎኝነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በእነዚህ ባህሪዎቹ የተነሳ የኢህአዴግ ፖለቲካ ሰብዓዊነት የማይሰማውና ለዜጎቹም ግዴለሽ የሆነ መንግስት ፈጥሯል። ይሄም ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ ድብርትን፣ ተስፋ ቢስነትን፣ ባይተዋርነትንና ስደትን አስከትሏል። ዶ/ር አብይ የተረከቧት ኢትዮጵያ እንደዚህ የስሜት፣ የስነልቦናና የሞራል ስብራት የደረሰባትን ሀገርና ዜጎች ነው። በመሆኑም፣ የዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ተግባር በየክልሉ እየሄዱ ዜጎች ከዚህ የተስፋ ቢስነትና የድብታ ስሜት እንዲላቀቁ መርዳት ነው። ይሄንንም ላለፉት ሁለት ወራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ዋናውና ትልቁ ፈተና ያለው ግን ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የተቋማት ህክምና ነው። ይሄንን ህክምና በሁለት ዘርፎች ከፍሎ ማየት ይሻላል – ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ድርድርና የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ላይ የሚሰራ ማሻሻያ።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ድርድር ወሳኝ የሚሆነው የመወዳደሪያ ሜዳውንና ህጉን ስለሚነካ ነው። በመሆኑም ድርድሩ የምርጫ ቦርድን፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ቁመናና አወቃቀር የሚነካ ነው። በዚህ ረገድ እስከ ዛሬ ኢህአዴግ በሽፈራው ሽጉጤ በኩል “የለበጣ” ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል።
አሁን ግን የጠ/ሚ/ር አብይ መንግስት የኢህአዴግን የትዕቢትና የማን አህሎኝነት ባህሪ በመስበር ከዋነኛ ተቃዋሚዎች (መድረክና ሰማያዊ) ጋር “በሦስተኛና ገለልተኛ ወገን” ለመደራደር ራሱ ኢህአዴግ ጥያቄ አቅርቧል። ትዕቢተኛውን አደራዳሪ ሽፈራው ሽጉጤንም አንስቷል። ይሄ ቀላል እርምጃ አይደለም።
ሌላው የተቋማት ህክምና ሊደረግለት የታሰበው መከላከያውና ደህንነቱ ነው። ዶ/ር አብይ ትናንት (ግንቦት 24፣ 2010 ዓም) ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ለታሰበው ለውጥ እንዲዘጋጁ ነግረዋቸዋል።
ሁሉን አቀፍ የእርቅ እና የመግባባት ጉባዔ ጠርቶ ውይይት ማካሄድ ለነገ ሊባል አይገባም የዶክተር አብይ የለውጥ ፈላጊነት የመጨረሻ መለኪያው ይህ እንጂ ጥገናዊ ለውጥ ወይም ፖለቲካዊ ማሽኮርመም አይደለም።
ይቺ የኔ የማትናወጥ አቋም ናት
የህወሓት ምላሽ ምን ይሆናል?
ዶ/ር አብይ ላለፉት ሁለት ወራት ባደረጉት የስሜትና የስነልቦና ህክምና ላይ ህወሓት ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጥ ነገሩን በአንክሮ እየተከታተለው ቆይቷል። ህወሓት ፖለቲካው ውስጥ ቁልፍ የሆኑ የስልጣን ቦታዎችን ቢያጣም፣ በደህንነቱና በመከላከያው ውስጥ ግን አሁንም ወሳኝ ቦታዎችን እንደያዘ ነው። ዶ/ር መረራ ብዙ ጊዜ እንደሚሉት “ምርጫ ቦርድ፣ መከላከያና ደህንነቱ” ዋነኛ የህወሓት/ኢህአዴግ የህልውና ቦታዎች ናቸው። ዶ/ር አብይ አሁን ፊቱን ያዞረውም በእነዚህ ተቋማት ተሃድሶ ላይ ነው። ህወሓት ለዚህ ምን ምላሽ ይኖረዋል? የስሜት ህክምናው ላይ እንዳደረገው ህወሓት የእነዚህ የህልውናው ተቋማት ላይ የሚደረገውን ህክምና በዝምታ ይከታተለዋል ወይስ “አሁንስ በዛ!!” ብሎ ቀይ መስመር ያሰምራል? መልሱን በመጭዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የምናየው ይሆናል!!!
በብሩህ ዓለም