*ሀገሪቱ እንዲህ የከበዱ ውሳኔዎችን ከማስተላለፍ በፊት፣ አድብቶ ዝም ያለ የመሰለውንና የታመቀውን የፖለቲካ ችግር፣ ለመፈንዳት የመጨረሻዎቹን ቲክ-ቲክ ድምፆችን የሚያሰማውን የጥፋት ፈንጂ ለምን መርሳት ተፈለገ?
*ሀገሪቱን አላላውስ ያላት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ለዚህ ውሳኔ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሩ በዋነኛነት የተከሰተው በፖለቲካዊው ውጥንቅጥ ምክንያትነት እንጂ በራሱ የተከሰተ የኢኮኖሚ ችግር አይደለም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካው መፍታታት ብቻ ነው ያንን ችግር በራሱ መልከ የሚያሲዘው፡፡ አለበለዚያ ከነፖለቲካዊ ችግሮች የትኛውንም አይነት የኢኮኖሚ እርምጃ ቢወሰድ፣ ውጥንቅጡን ጭራሹን ከማደበላለቅ ባለፈ የሚፈይደው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡
*በዘረፋ፣ ተሰምቶ በማይታወቅ ከባባድ ሙስና አማካይነት፣ ሀብት ያካበቱ የኢኮኖሚ ወንበዴዎች ጉዳይ መች መልክ ያዘ? የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጠፍንገው መድረሻ መላወሻ ያሳጡት እነ ኤፈርት እና ግብረአበሮቻቸው መቼ በሕግ መልክ እንዲይዙ ተደረገ? ሀገራችንን ዛሬ ላይ ለምትገኝበት ውጥንቅጥ የእነዚሁ ድርጅቶች ውንብድና ዋነኛው መሆኑ እየታወቀ ለምን ባላየ ለማለፍ ተፈለገ?!
*እርቅ፣ ሠላምና ይቅርታ ማለት እኮ በደፈናው የዘረፈውም የተዘረፈውም፤ የገደለውም፣ የተገደለውም ካቆማችሁበት ቀጥሉ ማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ በዳይም ተበዳይም በሕግ ዳኝነት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንግሥትም ይቅርታ ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ አላግባብ የተያዙ የኢኮኖሚ መሠረቶች በሕግና በመንግሥት በኩል ወደ ሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ መመለስ ይገባቸዋል፡፡
*ያ ሳይደረግ ቀርቶ፣ በዘረፋ የተያዙ ምናልባትም የሀገሪቱን ሲሶ የኢኮኖሚ አቅም ይዘው እንደሚገኙ የሚነገርላቸው፣ ሀገሪቱን አላላውስ ያሉ ግለሶብችንና ድርጅቶችን ባላችሁበት ቀጥሉ ማለት ምን ማለት ነው? የኢኮኖሚው አቅም በሙሉ አላግባብ በእነሱ እጅ ተይዞ ሳለ፣ ትላላቅ ሀብቶችን ወደ ግል ይዞታ ይዘዋወሩ ማለት ገዢዎቹ ከእነሱ ውጭ እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ ስለሆነም እነዚሁኑ ወንጀሎኞች ይበልጥ ማጎልበትና ያደለቡትን ሕገ-ወጥ ሀብት ሕጋዊ መልክ እንዲይዝ አድርጎ የመፍቀድ (money laundring) ተግባር ነው፡፡
*የኢትዮጵያ አየር መንገድስ ጉዳይ ከዚህ በፊት በዕዳ መያዣነት በቻይና መንግሥት ተይዞ ይገኛል ከሚለው መረጃ ጋር ተያይዞ የመጣ ገፊ ምክንያት ሊኖር የሚችልበት ዕድልም ሊኖር ይችላል፡፡ የጉድ ሀገር! አየር መንገዱ ብሔራዊ አርማነቱን ሆን ተብሎ ሲገፈፍ ተኖሯል፣ የእኔነት ስሜቱን ለማሳጣት ብዙ አሳፋሪ ርቀት ተኼዷል፡፡ ተስፋ ለመቁረጥም ተስፋ ያስፈልጋል፤ ቢያንስ ተስፋ መቁረጫችንን እንኳ ተዉልን እንጂ¡