>
5:13 pm - Tuesday April 20, 8483

ማንም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ ሊሆን አይገባውም (ከይኄይስ እውነቱ)

ማንም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ ሊሆን አይገባውም

(Nemo Judex In Causa Suaኔሞ ዑዴክስ ኢን ካውዛ ሷ)

ከይኄይስ እውነቱ

በርእስነት የመረጥኩትና በላቲን ቋንቋ የታወቀው ሐረግ በሕጉ ዓለም ሁለንተናዊ ዕውቅና ያለው ሲሆን፣ የተፈጥሮ ፍትሕ መርህ ነው፡፡ ማንም ሰው ባንድ ወይም በሌላ መልኩ እሱ የጥቅም ተካፋይ በሆነበት ወይም እሱን በሚመለከተው ወይም ውሳኔው የሚያስከትለው ውጤት መብቱን ወይም ጥቅሙን በአዎንታዊ ወይም  አሉታዊ መልኩ በሚነካበት ጉዳይ ዳኝነት ተሰይሞ ጉዳዩን ማየት እንደማይገባው የሚያሳስብ ወይም ማሰጠንቀቂያ የሚሰጥ መርህ ነው፡፡ ይህ መርህ አድልዎን የሚቃወም ደንብ በመባልም ይታወቃል፡፡ ‹‹በራሱ ጉዳይ›› የሚለው አገላለጽ የግድ የሙግት ተከፋይነትን ብቻ እንደማያመለክት፣ ለምሳሌ÷ አንድ ግለሰብ የአክሲዮን ባለድርሻ የሆነበት ኩባንያ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ተካፋይ ቢሆንና በዳኝነት ጉዳዩን ለማየት በወንበርነት ቢሰየም ይህንን ዓለምአቀፋዊ የሕግ መርህ የሚጥስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሚዛናዊነትን፣ እኩልነትንና ርትዕን መሠረት ያደረገ መርህ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ ዳኝነት ሊያዩ የሚችሉ ዳኝነት-አከል አካላት (quasi-judicial bodies) እና የአስተዳደር አካላትም ውሳኔ ሲሰጡ ሊከተሉት የሚገባ መሠረታዊ የፍትሕ መርህ ነው፡፡

የወያኔ ትግሬ አገዛዝ (ቋሚ መንግሥት እንኳን ሳይሆን) የኢትዮጵያን ሕዝብና የአገራችንን ሉዐላዊነት በማንአለብኝነት ጥሶ ኤርትራን በማስገንጠልና ታላቋን ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በማድረግ የፈጸመውን ይቅርታ የሌለው ታሪካዊ ጥፋት ኹላችን የምናስታውሰውና የወያኔን የጥፋት ተልእኮ ገና ከማለዳው ያወቅንበት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ ውሎ አድሮም ወያኔና ሻእቢያ በለኮሱት መሠረት-አልባ ጦርነት አእላፋት ኢትዮጵያውያን የማይተካ ሕይወታቸውን ለአገር ብለው ከገበሩ በኋላ ያገኙትን ወታደራዊ የበላይነት ተጠቅሞ በየትኛውም የዓለም አቀፍ ሕግ መመዘኛ ኢትዮጵያ ባለመብት የሆነችበትን የአሰብ ወደብ የማስመለስ ዕድል ሆን ተብሎና በድንቁርና እንድናጣ መደረጉ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ የኢትዮጵያ ግዛቶችን  መለስና ኢሳይያስ በመረጧቸው ቅጥረኞች ‹‹የግልግል ዳኞች›› ለኤርትራ ተላልፈው እንዲሰጡ መወሰኑም ይታወሳል፡፡ የሚያሳዝነኝ ይህንን ቅጥረኛ ወንበዴ ነው አንዳንዶች ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት›› እያሉ ሲጠሩ የማያፍሩት፡፡ ከዛ በኋላ ላለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የማጥፋትና የማዋረድ ሂደቶች የጥልያን ፋሽስትን ማረኝ እንደሚያስብል ምሁራን ገልጸውታል፡፡

ሰሞኑን የወያኔ ፓርቲ (ለእኔ ኢሕአዴግ የሚባል አልነበረም፤ የለምም) በአልጀርሱ ውሳኔ መሠረት ባድመን፣ ፆረናን እና ዛላአንበሳን ለኤርትራ ለመስጠት እንደተስማማ፡፡ ከዚህ ጋር ባልተያያዘ ሌላ ዜና ደግሞ ቊልፍ መንግሥታዊ ድርጅቶችን አነስተኛ ድርሻ ወደግሉ ዘርፍ (ላገር ውስጥና ለውጭ ‹ባለሀብቶች›) ለማዛወር መወሰኑን ሰምተናል፡፡ እንደ ቅድመ ዶ/ር ዓቢይ የወያኔ ዘመን አሁንም ሕዝብ ባገሩ ጉዳይ ባይተዋር ሆኖ ዘርፈ-ብዙ አንደምታ ባለው አገራዊ ጉዳይ ተወሰኖልሃል ስማ መባሉ ባያስገርመኝም እውን ለውጥ የማድረግ ፍላጎት ካለ ከየት ነው የሚጀምረው ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡

ሁላችን እንደምናውቀው የዶ/ር ዓቢይ ‹አመራር› በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድና ምርጫ የተሰየመ አይደለም፡፡ ሌላው እውነት ደግሞ እንደ ድርጅት አሁንም ያለው የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡ በአስተሳሰብ ከወያኔ በማፈንገጥ አንዳንድ አዎንታዊ የጥገና ለውጦች/ርምጃዎች እየወሰደ ያለው የዶ/ር ዓቢይ ቡድን አቋም ገና ለይቶለት አልታወቀም፡፡

በዚህ ወቅት ወያኔ ባልተለመደ መልኩ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ እነዚህን 2 አገራዊ ውሳኔዎች የወሰነው ባለቤቱ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በተለይም ለአገር ተቆርቋሪ ምሁራንን አማክሮ አይደለም፡፡ (ባህሉ ባለመሆኑና በሕዝብ አናት ላይ በጉልበት የተቀመጠ ድርጅት በመሆኑ ይህንን አንጠብቅም፡፡ በአስተሳሰብ ከተለዩትና የለውጥ አቀንቃኝ ነኝ ከሚሉት ከዶ/ር ዓቢይና ቡድናቸው ግን እንጠብቅ ነበር፡፡)

በእኔ እምነት በእነዚህ 2 ዐበይት ውሳኔዎች ላይ ሊነሳ የሚገባው አንገብጋቢና ተቀዳሚ ጥያቄ ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን ብቻ አይደለም፡፡ ለምን አሁን? ካሉን አንገብጋቢ አገራዊ አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚዎቹ እነዚህ ናቸው ወይ? በወያኔ ዘመን ባለን ተሞክሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ‹‹ግል›› የተዛወሩበትን ሂደት ለምናውቅ፣ ወያኔ ትግሬ አሁንም በዝርፊያ የፈረጠመ የኢኮኖሚ ይዞታ ኖሮት ከቀድሞው አፈጻጸም የተለየ እንደሚሆን ምን ዋስትና አለ? የውጭ የሚባለው አብዛኛው ‹ባለሀብት› በእስከዛሬው ተሞክሮ ከወያኔ ትግሬ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሠራ ያለ ነው፡፡ ይህ አስተያየት አቅራቢ በስሚ ስሚ ሳይሆን የመጀመሪያ ደረጃ ምስክርነት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡ እስቲ ‹ትላልቅ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን› ፈትሹ፡፡ በባለአክሲዮንነት ወይም በቦርድ አባልነት ወይም በአማካሪነት ወይም በጉዳይ አስፈጻሚነት ወዘተ. የወያኔ ትግሬ ባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው በቡድን ወይም በግለሰብ ደረጃ የሌሉበት፡፡ በቀጣይስ የተለየ እንደሚሆን ምን ማስተማመኛ አለ? ሕግና ሥርዓት በሌለበት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ንግድ ባንኮች አገራዊ አቋም ባልያዙበት፤ በእውቂያና በንቅዘት በሚሠራበት አገር ‹‹እውነተኛ›› የሚባል ባለሀብት ማግኘት ይቻላል ወይ? በኢትዮጵያ ምድር መሬት ሸጦ የጠፋ፣ እንደ ወያኔ ትግሬ የባንክ ብድር ተበድሮ ‹ድርጅቱን› ዘግቶ የጠፋ አስመሳይ የውጭ ባለሀብት የተመዘገበበት ‹ባለቤት አልባ› አገር ውስጥ እንዳለን መዘንጋት የለብንም፡፡ አብዛኞቹ የውጭ ‹ባለሀብት› ተብዬዎች በወያኔ ከለላ ከወያኔ ጋር አብሮ በዝርፊያ የተሠማሩ፣ ለአገራዊው ኢኮኖሚ ዕድገት÷ ለዜጎቻችን ሥራ ፈጠራ÷ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር÷ በጥሪት (ካፒታል) ምንጭነት÷ በውጭ ምንዛሬ ግኝት÷ ድርጅታዊ ማኅበራዊ ኃላፊነትን (corporate social responsibility) በመወጣት÷ አገራዊ አቅምን በመገንባት ወዘተ. ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ ኢምንት ነው፡፡ አንዳንዶቹም ነጥቀው በራሪዎች (flight by night scammers) መሆናቸውንም ታዝበናል፡፡ መቅደም ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊና ንግድ ባንክን ብሔራዊ ተቋማትነት ከማረጋገጡ ጋር በነዚህ ተቋማት የተዘረፉ የአገር ሀብትና ንብረቶችን ማስመለስ፣ በሕገ ወጥ ውሳኔዎች በየደረጃው የተሳተፉ ወያኔ ትግሬዎችንና ሌሎች ሆዳም ግብረ አበሮቻቸውን በሕግ ፊት ተጠያቂ ማድረግ፤ መቅደም ያለበት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንጡራ የተፈጥሮ ሀብትና ንግድ በዝርፊያ የተቆጣጠረው ኤፈርትና ሜቴክ ሀብትና ዕዳ በገለልተኛ የአገር ውስጥና የውጭ አካላት ተጣርቶ (የተዘረፈው ሀብት፣ ያልተከፈለው ግብር፣ አላግባብ የተሠረዘው ብድር ጭምር) አጥፊዎቹ በሕግ ሳይጠየቁና ድርጅቶቹም ወደ ሕዝብ ሀብትነት ማዛወር፤ መቅደም ያለበት በየክፍለሃገሩ ነዋሪ ዜጎችን አፈናቅለው በግል ቅጠረኛ ወታደርና ደኅንነታቸው እየታገዙ ‹በኢንቨስትመንት ስም› መሬት ነጥቀው ወረራ የፈጸሙ የወያኔ ትግሬና ግብረአበሮቹ መሬቱን ለሕዝብ ሳይመልሱና ፍትሕ ሳይደላደል ሌላ ተጨማሪ ምስቅልቅል መፍጠር ለምን አስፈለገ? ወዘተ. ወይስ እንደተለመደው ይህም ውሳኔ ነጮችን በማስደሰት ብድርና ርጥባን ለማግኘት የታለመ ርምጃ ነው?  

በሌላ ወገን የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይወክል ቅጥረኛ አገዛዝ ኢትዮጵያውያንን በጦርነት ከማገደ በኋላ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነ ባዕድ ዳኛ ሰይሞና ከብሔራዊ ጥቅሟ ተቃራኒ ውሳኔ አሰጥቶ የግዛታችንን አካላት ያለ ክርክር አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ እስካሁንም ሳይፈጸም  የቆየው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ተጨንቆ ሳይሆን የግል ጥቅሙን ሲያሰላና በሕገ ወጥነት ነው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ዕብዶች በጫሩት አላስፈላጊ ጦርነት ያለቁ ኢትዮጵያውያን ለጋ ወጣቶች እና ቤተሰባቸው ተገቢውን ካሣና ክብር አግኝተዋል ወይ? በዚያ በኩልም ያለው አገዛዝ ወፈፌነቱ ከወያኔ ትግሬ የማይተናነስ ነው፡፡ ከለማበት የተጋባበት ሆኖ ወያኔ በተንኮሉ ሻእቢያን አስከነዳው እንጂ፡፡

ዶ/ር ዓቢይ እንደሚሉት የሁለቱ አገር ሕዝቦች በደም የተሳሰሩ በመሆናቸው (ያበዱ አገዛዞቻቸውን ወያኔ ትግሬና ሻእቢያን ትተን) ሕዝብ ለሕዝብ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረት ግንኙነት ቢጀመር፣ ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት የየብስ መንገዱም ቢከፈት በጎ ጅማሬ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የዶ/ር ዓቢይ ‹አመራር› ፓርቲ ወስኖለት በተለመደው መልኩ መፈጸም ከሆነ በጥቂት ያሳየንን የለውጥ ጅማሬ መቀልበስ ይሆናል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ጉዳይና የተከተለው ጥፋት የወያኔ ትግሬ ቡድን ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ልቡ በጥላቻ እንደተመረዘ ወደ ጥልቁ የወረደው የመሠሪው መለስ ደባ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት ግን በአሁን ደረጃ ዶ/ር ዓቢይ ምንም ማድረግ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ የሁለቱን አገሮችና ሕዝቦች ከአገዛዞቻቸው አልፎ በማየት የተሟላ አጀንዳ በመያዝ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ንግግሮች መጀመር ያስፈልጋል፡፡ መጥፎ ስም ያለውን የአልጀርሱን ስምምነት ለመፈጸም ዝግጁ ነን ማለት ብቻውን ከአጭር ጊዜ ጥቅም የዘለለና እንደ መጀመሪያው ውሳኔ ‹የዓለም ማኅበረሰብ› የተባሉትን ምዕራባውያን ለማስደሰት ፍጆታ ብቻ የሚውል ከመሆን አያልፍም፡፡ በተለይም የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ስለ አሰብ ወደብ ባለቤትነት (የመጠቀም መብት አይደለም) በተለያየ ጊዜ ያቀረቧቸውን ጽሑፎችና በቅርቡም ለዶ/ር ዓቢይ የጻፉትን ደብዳቤ በጥሞና ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በመግቢያዬ ላይ ማንም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ መሆን የለበትም የሚለውን ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ያለው የሕግ መርህ ለዶ/ር ዓቢይ ‹አመራር› ያለውን ተፈጻሚነት ነው በማጠቃለያዬ ላይ ነው ማንሳት የምፈልገው፡፡ የዶ/ሩን የእስካሁን አካሄድ እንደተከታተልኩት በ‹ዕርቅ› ስም ወያኔ ትግሬ እና ግብረአበሮቹ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሟቸውን፣ ፋሽስት ጥልያንን የሚያስንቁ ግፍና በደሎች፣ ዝርፊያ ጭምር ያለ ተጠያቂነት ብናልፋቸው የሚል አንደምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ ይህንን ዕድል ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) ካጣው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የእውነተኛ ዕርቅ ወይም ይቅርታ መሠረቱ እውነትን ፍለጋ ነው፡፡ የበደለውን ክሶ የጠፋውን መልሶ እንዲሉ ሊቃውንት፡፡ በቅድሚያ ላለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙትንና ተመዝግበው የሚገኙትን እንደ ተራራ የገዘፈ፣ እንደ ባሕር የሰፋና የጠለቀ ግፍ ማመን፣ መጸጸት፣ ይቅርታ መጠየቅ፣ በሕግ የበላይነት በሚቋቋም ዳኝነት መጠየቅ፣ መካስና መመለስ የእውነተኛ ዕርቅ መሠረቶች ናቸው፡፡ በማድበስበስ ማለፍ ግን ዘላቂ ሰላምን ሳይሆን ውሎ አድሮ መዘዙ ከምንገምተው በላይ የከፋ ይሆናል፡፡

ስለሆነም የወያኔ አገዛዝ በሚባለው ‹የውንብድና ኩባንያ› ውስጥ ዶ/ር ዓቢይና ቡድናቸው ‹ባለአክሲዮን› ሆነው ቆይተዋል፡፡ አሁንም ናቸው፡፡ እንዲያውም የዕለት ተዕለት ሥራውን የሚመሩ ባለአክሲዮን (“managing partner”) ሆነዋል፡፡ አሁን በ2ቱም ዐበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ በግልም ሆነ በቡድን ደረጃ ዳኛ ሆነው ውሳኔ መስጠት የሚያስችላቸው አቋም ያለ አይመስልም፡፡ ድርጅታቸውና አባላቱ በሚጠየቁበት አገራዊ ጉዳይ ዳኝነት መቀመጣቸውና 2ቱም ውሳኔዎች ተጠያቂነትን የመሸፈን ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ስለሚገመት ዳኝነታቸው በየትኛውም መመዘኛ ለትግል ጓዶቻቸው አድልዎ/ወገንተኛ እንደማይሆን ምንም ዋስትና የለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የፓርቲው ውሳኔዎች (በዋናነት የሕወሓት የእጅ መጠምዘዝ ሥራ ስላለበት) ብሔራዊ ጥቅምን ያስጠብቃሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡

በእኔ እምነት እነዚህ ውሳኔዎች እጅግ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው እንጂ እንደ አንዳንዶች አመለካከት የሚያስፈነጥዙና ለወያኔ ትግሬ የማይመቹ ተደርጎ የማየት አዝማሚያ ትክክል አይመስለኝም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ዶ/ር ዓቢይ በቅርቡ ከወሰዷቸው ርምጃዎች (መሾም የማይገባቸውን በመሾም፣ ከእስር መፈታት የሌለባቸውን እንደነ ገብረዋሕድ ያሉ ቀንደኛ የንቅዘት ምሳሌዎችን መፍታት) እና የለውጥ ጓዳቸው አቶ ለማ በሚመሩት ክ/ሃገር ጭምር ያልተቋረጠ የዜጎቻችን መፈናቀልና እንግልት ጋር ባንድነት ሳየው ስለ ዶ/ር ዓቢይ ያለኝ አመለካከት በጉም የተሸፈነ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ጽሑፌን የምቋጨው ዶ/ር ዓቢይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ ሰሞን መጋቢት 25/2010 ከጻፍኩት አስተያየት በተወሰደ አሳብ ይሆናል፡፡ በዛ አስተያየት ዶ/ር ዓቢይን ከመልካም ንግግራቸው፣ እግዚአብሔርን ከመፍራታቸው፣ ከበጎ አስተሳሰባቸው፣ ከቅን ፍላጎታቸውና ምኞታቸው በመነሳት ለመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ/አቅኝ) ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ ሆኖም መልካም ውጥናቸውና ዕቅዳቸው የሚሳካው ወይም እኛ እንደ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ፈላጊ ሕዝብ ልናግዛቸው የምንችለው በወያኔ ትግሬ አገዛዝ ላይ ስናካሂድ የቆየነውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት/ሰላማዊ ተቃውሞ አጠናክረን ስንቀጠል ብቻ መሆኑን አመልክቼአለሁ፡፡ አሁንም መፍትሄው ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ ሁለት ወገንን ለማስታመም የሚመስል አካሄድ መጨረሻው ዶ/ር ዓቢይና ቡድኖት÷ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደማይፈልገውና በእርስዎ ሲመት ዋዜማ በአገራችን ላይ አንዣቦ ወደነበረው አደጋ መመለስ እንዳይሆን ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡

Filed in: Amharic