>

ሽፈራው ሽጉጤ የጨምበላላ ቀን፤ "ዓመት ዓመቱ አያድርስህ" - የሲዳማ ሽማግሌዎች፤

ሽፈራው ሽጉጤ የጨምበላላ ቀን፤

“ዓመት ዓመቱ አያድርስህ”የሲዳማ ሽማግሌዎች፤

ውብሸት ሞላ
ሲዳማ ከነበሩት የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳደሮች መካከል ሲዳማዎች ወደዋቸው መንግሥት የጠላቸው አቶ አባተ ኪሾ ናቸው።
በመንግሥት ተወድዶ በሲዳማዎች የተጠሉት ደግሞ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው።
መቼም የሲዳማ ሕዝብ በጀግንነቱም በብልሃተኛነቱም የሚገርም ሕዝብ ነው። በአጼ ምኒልክ ዘመን “ራስ ተሰማ ናደው በደሉን” ብሎ ሽማግሌ ተመርጦ አዲስ አበባ ለአቤቱታ መጡ አሉ።
ከዚያም ሽማግሌዎቹ አጼ ምኒሊክ ጋር ሲቀርቡ ጭንቅላታቸው ላይ በሸክላ እሳት እያነደዱ ቀረቡ። እምዬም “ውይ ውይ አውርዱሉኝ እሳቱን፤ ምን ሆናችሁ? ምን ሆናችሁ? አሉ” አሉ።
ሽማግሌዎቹም “ራስ ተሰማ አቃጠሉን አሉ” አሉ። በደሉን ለማለት ነው እንጂ በእሳት አቃጥለው አይደለም።
አጼ ምኒልክም ወዲያውኑ ራስ ተሰማ እንዲታሰሩ አዘዙ አሉ።
የሲዳማ ሕዝብ የክልል ምስረታ ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ማንሳቱ ይውወቃል። መብቶቹን ለማስከበር ሲጠይቅ በኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ እንኳን በርካታ የሲዳማ ወጣቶች በሐዋሳ ከተማ ላይ በጠራራ ፀሐይ መገደላቸውን እናውቃለን።
አቶ ሽፈራው የክልሉ ርእሰ መስተዳድር እያሉ የአማራ ተወላጆች ከጉራፋርዳ እንዲባረሩ፣ በዝምታ በማለፍ ብቻ ሳይሆን ከርእሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ አማካይነት፣ አድርገዋል። የክልሉን ነባር ብሔሮችንም ጭምር በድለዋል።
የአቶ ሽፈራው ክፋት ለሌላ ብሔር ብቻ ሳይሆን ለሲዳም ጭምር ነው። ሲዳማዎችም የሽፈራው በደል ሲበዛባቸው ሽማግሌዎች ልጆቻችንን በወታደር አንስጨርስም የፍቼ ጨምበላላ እንገናኝ እና እኛ መላ መላ እንላለን አሉ። እንዳሉትም የሲዳማ ሽማግሌችዎ ሐዋሳ ተገናኙ።
የፍቼ ጨምበላላ ቀን ሽፈራውን እንዲርመቅ ያደርጉታል። ሽፈራውም ወደ መድረክ በመውጣት በሲዳምኛ “ዓመት ዓመቱ ያደርሰን” ሲሉ ሽማግሌዎቹ ዓመት ዓመቱ አያድርስህ አሉ።
አቶ ሽፈራው ሁለተኛ ይህንኑ ሲደግሙ ሽማግሌዎቹም እንደዚያው “ዓመት ዓመቱ አያድርስህ”  አሉ።
የሽፈራው ምርቃት ቆመ። ሽማግሌዎቹም መፍትሔ ሳናገኝ አንመለስም በማለታቸው ከፌደራልም ከክልልም ባለሥልጣናት ስብሰባ ጀመሩ። መጨረሻም ሽማግሌዎቹ ስትፈልጉ ወደ ፌደራል ውሰዱት ስላሉ ደሴ ዳልኬን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በማድረግ ከፌደራል ወደ ክልል፤ሽፈራውን ወደ ፌደራል ተቀያየሩ።
አቶ ሽፈራው በሲዳማ ዘንድ እንኳን የማይወደዱ መሆናቸው እየታወቀ እነ በረከት ስምኦን አባዱላን ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረግ ሲሳናቸው ሁለተኛ ምርጫ አደረጓቸው። ሲዳማ ጠልቶዎት  ሳለ ስለምን ወደ ፌደራል መጡ? ያስብላል። ማንን ወክለው?
መልካም የፍቼ ጨምበላላ በዓል!
ማስታወሻ፥
ታሪኩን ያጫወቱኝ ከሽማግሌዎቹ አንዱ ናቸው። ስማቸውን መግለጽ ተገቢ ባለመሆኑ ትቼዋለሁ።
Filed in: Amharic