>

የአብይን አመራር የመቃወም ፈተና (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

የአብይን አመራር መቃወም እንደወትሮው ቀላል አይሆንም ወዳጄ! ሰውዬው ቀደም ሲል ለተቃውሞው ጎራ የህልውና መሠረት የሆኑ አጀንዳዎችን ጠራርጎ እየወሰደ ነው። አሁን ጌታዬ; “ጠባብ ብሔርተኛ”; “ዘረኛ ቡድን”; “የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ ያነገበ”; “ገንጣይ – ተገንጣይ – አስገንጣይ”;  “ሀገር አፍራሽ” … ወዘተ ብትል ማንም አይሰማህም። እንዳውም “ተቸካይ”; “የመሸበት ተቃዋሚ”; “ሁሉን ነገር የመቃወም አባዜ ያለበት”; “ጭር ሲል የማይወድ” ብለው ሊሳለቁብህ ይችላሉ።
እንደወትሮው “ዘራፊ ወንበዴ”; “አፋኝ አገዛዝ”; “ቅንነት የጎደለው”; “የጥላቻ ፖለቲካ” … ወዘተ የሚሉና የመሳሰሉ የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት መገለጫዎችን በቦታው ላታገኛቸው ትችላለህ። አሊያም ህዝቡን ያልበላውን ለማከክ ትሞክርና ወዲያ ገፍትሮ ሊጥልህም ይችላል። አያያዙን ስናዬው; ከዚህ በኋላ ሥርዓቱን እያወገዙና “እውነተኛ ተቃዋሚ” እየተባሉ መኖር የሚቻልበት ዕድል የሚኖር አይመስልም።
እንደወትሮው “የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል” ብሎ በማለቃቀስ የህዝብን ልብ ለመብላት መሞከር “ፋሽኑ ያለፈበት” ወይም አራዶቹ እንደሚሉት “የተበላበት” ዜማ ሊሆን ይችላል። ወዳጄ; አሁን አገሪቷ ስሟን የሚያንቆለጳጵስና ስለአንድነቷ የሚሰብክ መሪ አግኝታለች። ምናልባት አንተ የነአብይ ኢትዮጵያዊነት “fake” ነው በሚል አጉል ጥርጣሬ ለመፍጠር ትሞክር ይሆናል። ግን እንዳትሸወድ ወዳጄ; “origionaሌው” ኢትዮጵያዊነት የትኛው ነው?” ብሎ ሊሞግትህ/ሊያፋጥጥህ የሚችል እሳት የላሰ ትውልድ መፈጠሩን ልብ በል!
አጀንዳ ከመንጠቅ ጋር በተያያዘማ; ሰውዬው “ስግብግብ” ብጤ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ በፊት በተቃዋሚው ጎራ ሲቀነቀንና የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ እንደጦር ሲፈራው የነበረውን “የብሔራዊ እርቅና መግባባት” ጥያቄ “ላፍ” አድርጎ ሲወስደው ካልባነንክ አጀንዳው ብቻ ሳይሆን አንተም ተበልተሃል ማለት ይቻላል። ከዚህ በፊት ተቃዋሚው “ከቂምና – በቀል የፀዳ ፖለቲካ” በሚል የሚገልፀውንና ህዝቡ በቀቢፀ-ተስፋ  የሚጠብቀውን የፖለቲካ ባህል እነዶ/ር  አብይ ድንገት መጥተው “መገለጫቸው” እያደረጉት መሆኑን እንዴት አድርጌ ላርዳህ!? አሁንኮ “የታሠሩት ይፈቱ” የሚል የመታገያ አጀንዳ የተቃውሞ ፖለቲካው እስትንፋስ ሆኖ የመቀጠሉ ጉዳይ አጠያያቂ ነው።
ሰውዬው ኢኮኖሚውን “liberalize” ለማድረግ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ካየህ ደግሞ; ወደፊት “የልማታዊ መንግሥትን” ፍልስፍና እና ባህሪ መተንተን ትርጉም እንደማይኖረው ትገነዘባለህ። “የፍላጎትና አቅርቦት ሚዛን” በሚል የነአዳም ስሚዝን አስተምህሮ የጠቀሰልህ ይህ “ብልጣብልጥነትም” የማያጣው ሰው ከዚህ በፊት “ስለነፃ ገበያ” የኢኮኖሚ ፖሊሲ የነበረህን ጥራዝ ነጠቅ ግንዛቤ አፍህ ላይ ሊያሟሟውና የምትናገረው ሊያሳጣህ እንደሚችል ብታስብ; አስተዋይ እንጅ ፈሪ ልትባል አትችልም።
ምናልባት አንዱ ዕድልህ “በብሔር/በዘር” ላይ በተመሠረተ አደረጃጀቱ ጥጉን እንዲይዝ (corner) ማድረግ ሊሆን ይችላል። ግን ሰውዬው “ኢህአዴግ” የተሰኘውን የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ይዞ የሚንገታገት “ሞኛሞኝ” አይመስልም። ይህን የአራት ድርጅቶች ጥምረት ጨፍልቆና ሌሎችንም ጨምሮ አንድ ጠንካራ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመፍጠር እየሠራ እንደሆነስ ምን ታውቃለህ? እኔ ባዶ ግምቴን አይደለም – የምነግርህ። ይልቁንም ኃይለማርያም ሥልጣኑን ተገፍቶ/ሸሽቶ ከመልቀቁ በፊት በአደባባይ “ኢህአዴግን አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፓርቲ ለማድረግ እየተሠራ ነው” ብሎ የተናገረውን ላስታውስህ እወዳለሁ።
አሁንም አንድ ሌላ ዕድል አለህ። በዘርና በቋንቋ ላይ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓት “የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው” በሚል (በተለይ አንቀፅ 39ን በመጥቀስ) በሰላ ትችት ልትሸነቁጠው ትችላለህ። እሱንም ዝንጉ ሆኖ ቀዳዳውን ካልደፈነብህ ነው። መቼም የሕገ-መንግሥቱ አንዳንድ አንቀፆች እንደሚሻሻሉ ሲናገር አልሰማሁም አትለኝም። እናማ “የፌዴራል አወቃቀሩ ችግር አለበት” የሚለውንም አጀንዳ ወስዶ ባዶ ሊያስቀርህ እንደሚችል አለመጠርጠር ለወቅቱ ፖለቲካ የሚመጥን ቁመና ላይ አለመሆንህን ያሳብቃል።
እህሳ? ምን ተሻለህ – ወዳጄ? እርግጥ ነው; ምንም እንኳ የተጨበጠ ለውጥ ባታመጣም የተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ቆይተሃል። እናማ እንደዋዛ ከፖለቲካው ተገፍተህ “ከባህር የወጣ ዓሣ” መሆን የምትፈልግ አይመስለኝም። ስለሆነም ከወትሮው ለዬት ባለ መንገድ ጠንከር ብለህ መታገል ይኖርብሃል። እንደወትሮው ገዥውን ፓርቲ በማውገዝ ብቻ ግን “ጨዋታውን” መቀጠል አትችልም። “ተጋጣሚው ተጨዋች” ብቻ ሳይሆን “የጨዋታው ህግም” እንደሚቀየር መገመት ትችላለህ።
ስለሆነም የትግሉ ባህሪ አዲስ ሊሆንብህ ይችላል። ቀደም ሲል የትግልህ መሠረት የነበረው ሁኔታ ሲቀያየርብህ የምትይዝ የምትጨብጠውን ልታጣና የማይገቡ ነገሮችን (frustrate) ልታደርግ ትችላለህ።
እኔ እያሟረትኩብህ አይደለም -ወዳጄ! ይልቁንም; ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበና ወደፊት ሊያራምድህ የሚችል የመታገያ/የማታገያ (progressive) አጀንዳ እንድትቀርፅና ለወቅቱ የሚመጥን የትግል ስልትና ስትራቴጂ እንድትቀይስ ላሳስብህ ነው። እኔ ከማሳሰብ ባለፈ አጀንዳዎቹን ልቀርፅልህም ሆነ ስትራቴጂያዊ ግቦችህን ላስቀምጥልህና የማስፈፀሚያ ስልቶችህን ላመላክትህ አልችልም። እሱ ያንተ ሥራ ነው።
የለም; አያሳስበኝም; “በነበርኩበት ረግጣለሁ” ካልክም አንተ ታውቃለህ። ያልበላህን አክኬ አናድጄህ ከሆነም ከባድ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለዚህ “ጥፋቴ” ቅጣቱ ስድብ ሆኖ እንዳሻህ ብታዘንብብኝም እችለዋለሁ። ስድብና ዝናብ የሚያበሰብስ አይመስለኝም።
ማሳሰቢያዬን በቅንነት ካየኸው ግን; ይበልጥ ተጠቃሚው አንተ ብትሆንም – እነሆ ቀድሜ አመሠግናለሁ።
አላህ ልቦና ይስጠን!!!
*          *           *
“እኔ በህግ የተሰጠኝን አስፈፃሚውን አካል የማደራጀት ሥልጣን የሌለኝ የሚመስለው አካል አለ” 
ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ
ይኸ እንግዲህ አክርረው የመቱት የመልስ ምት መሆኑ ነው። ሰውዬው የዋዛ አይደሉም። ጨዋታው ብቻ ሳይሆን የጨዋታው ህግም በደንብ ገብቷቸዋል ልበል?
Filed in: Amharic