>

"እንዳንነቃ ፀሎት ጀምሬያለሁ!!!" (መጋቤ ኃዲስ እሸቱ አለማየሁ)

በያሬድ ሹመቴ

“እንዳንነቃ ፀሎት ጀምሬያለሁ!!!”

~መጋቤ ኃዲስ እሸቱ አለማየሁ
ከሁለት አመት በፊት የተነገረ የትንቢት ቃል
፦ ተስፋችሁ ሙትት ብሎባችኋል? እኔ ግን ተስፋ አለኝ…
*ብሔራችን ሳይጠየቅ
* ኃይማኖታችን ሳይፈተሽ
* መጀምሪያ ሰው መሆናችን
* ክቡር ኢትዮጵያዊያን መሆናችን ብቻ ታይቶ እንደልባችን በደስታ የምንኖርበት ዘመን ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ዛሬ ጠዋት መጋቤ ኃዲስ እሸቱ አለማየሁ በስልክ እንዲህ አሉኝ።
“ሰሞኑን እየተነገረ እየተሰማ ያለው ነገር በሙሉ በህልማችን ከሆነ ‘እባክህ ጌታ ሆይ ህልማችንን ዘላለማዊ አድርግልን’ እያልኩ ነው። እኔማ ከእንቅልፋችን እንዳንነቃ ፀሎት ጀምሬያለሁ። በእውነት እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው።  ይልቅ የአሸናፊ እና የተሸናፊነት ስሜት እንዳይኖር መጠንቀቅ አለበት። የኛ ጥያቄ ዳቦውን ተካፍለን እንብላ እንጂ ዳቦውን ጠቅልለን እንብላ መሆን የለበት። የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ገብተን የሞኝ ስራ እንዳንሰራ መጠንቀቅ አለብን።
በኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉም አሸናፊ የሆነበት አጋጣሚ የሚመስለኝ ይሔ ነው። ገሎ መክበር፤ ጥሎ ማለፍ በእኛ ቤት ታሪክ የተለመደ ነው። በቀደም ዶክተር ዐብይ ሲሉ ነበር፤ ‘ማሰር ያደግንበት ነው’ እውነታቸውን ነው። አሁን ደግሞ እስኪ ያላደግንበትን እንሞክረው በግልባጩ። ተሸናፊዎች የአሸናፊዎች ውበት ናቸው። ኃይሌ ገበረሥላሴ አንደኛ የወጣው ሁለተኛ እና ሶስተኛ የሚወጣለት ስላለ ነው። እነዛ ሰዎች ቢያምፁ እኮ እሱ አንደኛ መሆን አይችልም። ለምነህም ሸልመህም ቢሆን የሚፎካከርህ ያስፈልግሀል።
ነገር ግን እንዲህ አይነት ደስታ ሲፈጠር ያላሰብንባቸውን ነገር ተናግረን፤ ሰዎችን አስከፍተን፤ ወንድሞቻችንን አስቀይመን ሌላ መከራ ውስጥ እንዳንገባ ጥንቃቄ እንዲደረግ እወዳለሁ”
ይህንን ካሉኝ በኋላ የዛሬ አመት ከመንፈቅ በአሜሪካ ውስጥ ያደረጉትን ንግግር አስታወስኳቸው። እናም ዛሬ የደረስንበትን ግዜ እሳቸው የዛኔ እንዴት ተስፋ ያደርጉ እንደነበር ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ።
“በነብዩ ኢሳያስ ትንቢት…በሬ እና አንበሳ ተቃራኒ ነበሩ። የነዚህ ልጆች ደግሞ አባትና እናታቸውን እያዩ አብረው ሲጫወቱ ይውላሉ።እንዴት ይገርማል መሰላችሁ። ነብርና ፍየል ተቃራኒ ነበሩ። አይደለም? ህጻን ልጅም በመርዛማው እባብ ጉድጓድ ላይ ሲጫወት ይውላል። እባቡን በእጁ ይዞ እየተጫወተ መርዙ አይነካውም።
በሬንና አንበሳን ፍየልንና ነብርን በግን እና ተኩላን ትንሽ እረኛ ሲጠብቃቸው ይውላል። ምክንያቱም አንበሳውም ቅስም ሰባሪነቱን፤ ነብርም ቧጫሪነቱን፤ ተኩላውም ዘራፊነቱን፤ ስለለወጠ እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች አንድ ህጻን ልጅ ይጠብቃቸዋል።
ነገር ግን ይላል ነብዩ ኢሳያስ ‘ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? ባህር በውሃ እንደሚሞላው ሁሉ ምድሪቱ እግዚአብሔርን በማወቅ በምትሞላ ግዜ ፍየሉ ከነብር አንበሳው ከበሬ በግም ከተኩላ አብረው ይውላሉ። እረኛቸውም ነፍስ ያላወቀ ህጻን ልጅ ይሆናል’ ይላል።
ወገኖቼ! እንደው ተስፋችሁ ሙትት ብሎባችኋል… እኔ ግን ተስፋ አለኝ። ከአዲስ አበባ አስመራ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሞቃዲሾ፤ ከጎንደር እስከ ሱዳን ጫፍ ድረስ ባቡር ተዘርግቶ እንደልባችን፤ ከየት መጣህ ሳንባል መልካችን ሳይታይ ብሔራችን ሳይጠየቅ፤ ኃይማኖታችን ሳይፈተሽ፤ መጀምሪያ ሰው መሆናችን፤ ሁለተኛ ክቡር ኢትዮጵያዊያን መሆናችን ብቻ ታይቶ እንደልባችን በደስታ የምንኖርበት ዘመን ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ይሄ እንዲመጣ ግን ከጥላቻ ነጻ መውጣት አለብን። ደግሜ ደጋግሜ እናገራለሁ። ከጥላቻ ነጻ መውጣት አለብን። ማንንም ጠልተም የመስደብ መብት የለንም። ፀጉሩ ሲቆሽሽበት ራሴን ካልተቆረጥኩ አይባልም። መታጠብ ነው እንጂ። እንደ አንፖል ከጣራ በታች የሚያስብ ሳይሆን እንደ ፀሐይ ከሰማይ በታች የሚያስብ ሰው ነው ጀግና ማለት።”
Filed in: Amharic