>

የማንነት ብያኔ አፈና… (በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

ከእኛ አገር የማያልቁ ችግሮች መካከል አንዱ የማንነት አረዳድ እና አበያየን ጉዳይ ነው። ማንነት እና ምንነት የፖለቲካ ጫወታችን አስኳል ሆኖ ሳለ፣ የማንነት አበያየናችን ግን ግለሰቦች የራሳቸውን ማንነት የሚበይኑበት ነጻ ዕድል የማይሰጥ ነው።
የኦነጉ በያን አሶባ ባንድ ወቅት ከኢሳት ቴሌቪዥን “ኦሮሞ ማነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “ኦሮሞ ነኝ ያለ” የሚል ምርጥ መልስ ሰጥተዋል። ነገር ግን ብዙዎች ማንነትን በዘር የሚወረስ እንጂ በማኅበራዊ-ሥሪት (social construction) የሚመጣ ነገር አድርገው አይመለከቱትም። እውነት መሆኑን ከራሷ ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጂ ድምፃዊ ሴና ሰለሞን ከአማራ ተወላጆች የተወለደች ኦሮሞ ነች፤ “ኦሮሞ ነኝ” ስላለች። ራሷን የምትገልጸው እንደ ኦሮሞ ሲሆን፣ በዘፈኖቿ የታገለችውም ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ነው። የወላጆቿ የማንነት ታሪክ የሐሰት ወሬ ቢሆን እንኳ ነባራዊ ምሳሌ እናጣለን እንጂ፣ ምሳሌው ማንነትን የመምረጥ ግለሰባዊ ነጻነቱን የተሳሳተ አያደርገውም።
‘ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ፣ የለም? ጎጃሜ ማንነት አለ፣ የለም? አዲሳበቤ ማንነት አለ፣ የለም?’ የሚሉት ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ምንጫቸው የግለሰቦች ማንነት እኛ ራሳችንን እንዲሁም ሌሎችን ከምንረዳበት መንገድ ውጪ መወሰን የለበትም ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። በቀላል ቋንቋ ለመግለጽ አባባሉ “እኔ ናችሁ ከምላችሁ ውጪ መሆን አትችሉም” ነው።
በበኩሌ ሰዎች የራሳቸውን ማንነት ብለው የሚጠሩት ወይ ‘የሚኮሩበትን’ አሊያም ‘የተበደለባቸውን’ [ወይም የተበደለባቸው የሚመስላቸውን] ማንነታቸውን ነው ብዬ ነው የማምነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰዎች ማኅበራዊ ሥሪታቸው ከብዙ ድርብ፣ ድርብርብ ማንነቶች የተገነባ ነው። ጥቁር ሕዝብ መሐል ላደጉ ኢትዮጵያውያን ጥቁርነት የማንነታቸው መገለጫ መሆኑ ትዝ ብሏቸው አያውቅም። ነገር ግን ከኢትዮጵያዊ ወላጆች ተወልደው ነጮች አገር ያደጉ ኢትዮጵያውያን “ምንድን ነህ/ምንድን ነሽ?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸው፣ ጥቁርነታቸው ቀድሞ የሚመጣባቸው መልስ ሊሆን ይችላል? “ምንድን ነህ/ነሽ?” የሚለው ጥያቄ የማንነት ወይም የምንነት ጥያቄ መሆኑ አያጠራጥርም። መልሱ ግን ወጥ አይደለም። እንደ ሁኔታው እና ቦታው ይለያያል። አንዱ “አካውንታንት ነኝ” ብሎ ሙያውን እንደማንነቱ መገለጫ ሊጠቅስ ይችላል፣ ሌላዋ “ሙስሊም ነኝ” ልትል ትችላለች። በሁኔታው፣ በወቅቱ እና በቦታው ሰዎች ስለማንነታቸው የሚሰማቸው ስሜት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ይህም የማንነትን ወጥ አለመሆንና ድርብርብነት ያረጋግጣል።
እኔ በማንነቴ ቀረፃ ውስጥ “የድሀ ልጅ” መሆኔን ያክል ተፅዕኖ የፈጠረብኝ ነገር አለ ብዬ አላምንም። የድሀ ልጅ ሆኖ ማደግ ያለንን ነገር ‘ላጣው እችላለሁ’ በሚል ፍርሐት እና የሌለንን ነገር ‘ላገኘው አልችልም’ በሚል ስጋት ውስጥ መኖር ማለት ነው። ይህ ማንነት ነው። በድህነት ውስጥ ላደገ ሰው፣ ዓለም ማለት የመግዛት አቅም ባላቸው እና በሌላቸው ሰዎች የተሞላች ናት። የአዲስ አበባ ድሀ፣ ከብራዚል ድሀ ጋር በሥነ ልቦና የሚያግባባ ማንነት አለው። ነገር ግን “የድሀ ልጅ” የሚባል ማንነት በኛ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት የለም። ስለዚህ ከዚህ ውጪ ብዙ ማንነቶች አሉኝ። ለምሳሌ ጦማሪነት። ከዚህ በፊት ስታሰር ስፈታ የነበርኩት ተቺ ጦማሪ ስለሆንኩ ነው። ስለዚህ ምንድን ነህ ስባል ‘ብሎገር ነኝ’ የምልባቸው ግዜያት ብዙ ናቸው። ለምሳሌ እስር ቤት በማንነቴ ነው የታሰርኩት የሚሉ ነበሩ። እነሱ “ኦሮሞ በመሆኔ”፣ “አማራ በመሆኔ” ሲሉ እኔ ደግሞ “ብሎገር በመሆኔ” እል ነበር። ይህም ማንነት ነው። ይህንን ብነፈግ እንኳ በትምህርት ያፈራሁት፣ በተወለድኩበት አካባቢ ያፈራሁት፣ በእምነቴ ወይም ባለማመኔ ያፈራሁት ብዙ ማንነቶች አለኝ።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብያኔ መሠረት እነዚህ ሁሉ ማንነቶቼ ዋጋ የላቸውም። “ምንድን ነህ?” ስባል የወላጆቼን የዘውግ ማንነት እንድናገር ይጠበቅብኛል። ወላጆቼ ቅይጥ ቢሆኑ እንኳን የአባቴን [ይህ ካልሆነ ደግሞ የእናቴን] የዘውግ ቡድን ማንነቴ ብዬ እንድናገር ይጠበቅብኛል። እኔ እኔን ይገልጸኛል የምለው ማንነት እንዲኖረኝ ነጻነቱ የለኝም። በዚህ አካሔድ “ኦሮሞ ነኝ” ማለት፣ ወይም “አማራ ነኝ” ማለት፣ ወይም “አዲሳበቤ ነኝ” ማለት ምንም ዋጋ/ጥቅም የለውም። ምክንያቱም በኔ ማንነት ላይ እኔ የመወሰን ነጻነቱ የለኝም።
Filed in: Amharic