>
5:18 pm - Saturday June 16, 2266

"ቁስሌን ሕዝብን እሰብክበታለሁ" ዮናስ ጋሻው

“ቁስሌን ሕዝብን እሰብክበታለሁ” ዮናስ ጋሻው
~”አንድ ቀን ከአስከሬን ጋር አሳድረውኛል” ዮናስ ጋሻው”
~”ህግ ባይኖር እኔ ነበርኩ የምገድልህ” የቂሊንጦው ገብረእዝጊ ዮናስ ሲፈታ የተናገረው
በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው
ብርቱን ዮናስ ጋሻውን አግኝቼ ሳዋራው ብርታቱ ደነቀኝ። የደረሰበት ጉዳት ሰቅጣጭ ነው። ማታ 2 ሰዓት ሰቅለውት ሌሊት 6 ሰዓት ላይ እንደሚያወርዱት አጫወተን። በምርመራ ወቅት ከሚደረገው ደብደባ በላይ በማንነቱ የሚፈፀም ዘለፋ አስከፊ ነው።
 ብልቱ ላይ ሁለት ሊትር ውሃ፣ እንዲሁም ፍሬው ላይ ሁለት ሊትር አንጠልጥለውበታል። በአንዴ አራት ሊትር ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ፍሬዎቹ እንደፈሰሱ ይናገራል።
ዘቅዝቀው እንደሰቀሉትም ይናገራል። ከተሰቀለበት መሬት ላይ ሲጥሉት ወገቡን ተመትቷል። በዚህ ምክንያት ነርቭ ጉዳት ደርሶበታል። የቀኝ  እግሩ መንቀጥቀጡንም አቁሞ መታጠፍ ተስኖታል። ደህና የነበረው የግራ እግሩ መንቀጥቀጥ እንደጀመረ ይናገራል።
ዮናስ ጋሻው የተያዘው አዲስ አበባ ነው። እንደተያዘ ወደ ኮተቤው የደህንነት ቢሮ ይወስዱታል። ጨካኙ (የማዕከላዊ ገራፊዎች ኃላፊ) ተክላይ መብርሃቱ እየበረረ በለሊቲ ይደርሳል። 9 ሰዓት። ሊገድለው ሲል የያዙት ደህንነቶች “ኧረ እህቱ አይታናለች” በማለታቸው ያደገው ፀጉሩ ላይ ይተኩስበታል። እህቱ ባታየው ገድለውት ነበር። ከኮተቤ ማሰቃያ ወደ ጦር ሀይሎቹ ሌላኛው ድብቅ እስር ቤት ይወስዱታል። ከዛም ወደማዕከላዊ!
ዮናስ ሲያዝ ደህንነቶቹ የትዳር ቀለበቱንም ቀምተውታል። ሲቀሙት “ምን ያደርግልሃል? አትወልድ!” ነበር ያሉት። ምን እንደሚደርጉት ያውቃሉና።
ወደማዕከላዊ ከተዛወረ በኋላ እቴነሽ ወልደሩፋኤል “አማራ አይወልድም” ብላዋለች። ባሉት መሰረት አኮላሽተውታል።  “አንድ ቀን ከአስከሬን ጋር አሳድረውኛል” ይላል ዮናስ! ያላደረጉት ነገር የለም። መርማሪዎች ብቻ ሳይሆን የቂሊንጦ ኃላፊዎችም ቢገድሉት በወደዱ ነበር። ከእስር ሲፈታ ገብረእግዚ የተባለ ሀላፊ “ህግ ባይኖር እኔ ነበርኩ የምገድልህ” ብሎኛል ይላል ዮናስ። ገብረእግዚ ማን አለበት? “ፈታነህ ማለት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነህ ማለት አይደለም” ይላል።
የዮናስ ስቃይ የከሳሾችን ስሜት እንኳ ይፈታተናል። ለምሳሌ የ19 ኛ ችሎት ዳኞችን አንገት አስደፍቷል። “መናገር አትችልም” ሲሉት ሱሪውን አውልቆ ጉዳቱን ሲያሳይ ፀጥ ብለው ንግግሩን አስጨርሰውታል። በከሳሽነቱ ለታወቀው አቃቤ ሕጉ ምክትል ብርሃኑ ወልደሰማያት ሱሪውን አውልቆ ሲያሳየው ያ ጨካኝ ብርሃኑ አልቅሷል። ዮናስ እንዳጫወተን!
እንደዛም ሆኖም ግን ዮናስ ብርቱ ነው! የእሱ ስቃይ ሌሎች ወንድሞቹ ላይ ለደረሰው ማሳያ ነው ብሎ ያምናል። ሕዝብ ላይ ለደረሰው በደል ማሳያ የሆነውን የእሱን ቁስል “ሕዝብን እሰብክበታለሁ!” ይላል ዮናስ!
ዮናስ ሕክምና ካላገኘ ሁለቱም እግሮቹ ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ነው። ውጭ ሀገር ወጥቶ መታከም እንዳለበት ተነግሮታል! ለዚህ ብርቱ እርዳታ ያስፈልገዋል!
Filed in: Amharic