>

በባንዲራ ቀለም ከመነታረክ ሀገርን ከብተና ማትረፍ ይቀድማል!!!  (ታዬ ደንደአ)

በባንዲራ ቀለም ከመነታረክ ሀገርን ከብተና ማትረፍ ይቀድማል!!! 
ታዬ ደንደአ
ራሳችንን ማታለል የለብንም። የኢትዮጵያ ችግር ዉስብስብ ነዉ። የተለያዩ ፍላጎቶች አሉ። ልዩነቶችን ለማስታረቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ከስሜት በላይ ሆኖ መደማመጥን ይጠይቃል። የራስን ስሜት ብቻ ማቀንቀን ለአደጋ ይዳርገናል።
አሁን ባንድራን አስመልክቶ ከፍተኛ ንትርክ ይታያል። በአንድ በኩል በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ላይ የኮከብ ምልክት መደረጉ እንደወንጀል ይቆጠራል። ምልክት ያለዉ ይቀደዳል። በሌላ በኩል ምልክት ያለዉ ይፈለጋል። በተጨማሪ ደግሞ ምልክቱ ኦዳ እንዲሆን የሚፈልጉ ተከስቷል። ክርክሩ እየከረረ ነዉ። ግን እጅግ ያሳዝናል። በዝህ ወሳኝ ወቅት በዝህ ጉዳይ መነታረክ አለመንቃታችንን ያሳያል። እሳት ይዞ ለመጣብን ጠላት ነዳጅ ማቀበል ይሆናል። በእርግጥ ባንድራ የሀገር መለያ መሆኑ ይታወቃል። ትልቅ ክብር ይገበዋል። ግን አሁን ሀገር ከባድ አደጋ ላይ ነዉ። የቀን ጅቦች ሊያባሉን አሰፍስፏል። ሀገርን አጥፍቶ ሊጠፉ ወስኗል። ታዲያ ሀገር ከሌሌ ባንዲራ ለምን ይጠቅማል? ባንዲራ ይዞ ከመጨፈር ሀገርን ከብተና ማትረፍ ይቀድማል።
በኔ እምነት ሁሉም ጤና ያለዉ ዜጋ የሀገሩን አንድነት፣ ሠላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ እና ብልፅግና ይፈልጋል። ይህ ግን የሚወዱትን ባንዲራ ይዞ በመጨፈር ወይም የማይወዱትን ባንዲራ በማቃጠል አይመጣም። ከፍተኛ ዋጋ መክፈል ይጠይቃል። ዋጋዉ መሞት ወይም መግደል አይደለም። ይህ ቀላል ነዉ። ላለፉት ሀምሳ አመታት ስናደርገዉ ቆይተናል። ግን ዉጤት አላመጣንም። ከባዱ ነገር ከጊዜያዊ ስሜት በላይ ሆኖ የሌላዉን ፍላጎት በትክክል መረዳት ነዉ። የሀገሪቱ ወጣቶች እና ምሁራን ከ1960-ዎቹ ጀምሮ ሀገሪቱን ለመለወጥ ሲጥሩ ቆይቷል። መስዋዕትነት ከፍለዉ አምባገነኖችን ጥሏል። ግን የራሳቸዉን ስሜት ማሸነፍ አቃታቸዉ። መደማመጥ ባለመቻላቸዉ ተጠላልፎ በመዉደቅ ሀገርን ለአሳፋሪ ዉድቀት ደርጓል። መኢሶንን እና ኢህአፓን ማስታወስ በዝህ ወቅት እጅግ ይጠቅማል። ነገሮችን በራሳችን መነፅር ብቻ ማየት በከፍተኛ ዋጋ ያገኘነዉን ድል ከእጃችን ያስመልጣል። ወደ ፊት ለመሄድ ቢያንስ ሌሎች መነፅሮች መኖራቸዉን ማወቅ ያስፈልጋል።
ሀገራችን አሁን በወሳኝ ወቅት ላይ ነች። ትልቅ ለወጥ ተጀምሯል። ክቡር ጠሚ አብይ እና ጓዶቻቸዉ በአጭር ጊዜ ገራሚ ለዉጥ አሳይቷል። ግን ደግሞ ትልቅ ፈተና አለብን። ለዉጡን የማይፈልጉ የቀን ጅቦች ሊያደናቅፉን ለአጥፍቶ መጥፋት ተዘገጅቷል። አሸንፈን ለማለፍ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይጠበቅብናል። ከሁሉም በላይ ከስሜታዊነት መዉጣት ያስፈልጋል። በስሌት እና በህብረት ከልያዝነዉ ሀገር ይወድቃል። ከሁሉም ሀገር ይቀድማል። የባንዲራ ጉዳይ ብቆይልን ይሻላል። አሁን የለዉጥ ህደቱ እንዳይዛነፍ ሁላችንም በያለንበት ዘብ መቆም ይኖርብናል።
ሠላም ዋሉ!
Filed in: Amharic