የብሽሽቅ ፖለቲካን እናቁም አልተባለም እንዴ !
ዩሱፍ ያሲን / ኦስሎ
ጠቅላይ ሚንስትሩ የኤርትራን ልዑካን በተቀበሉበት ጊዜ ‘’የብሽሽቅ ፖለቲካ’’ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እርግፍ አድርገን እንተወው ያሉ መሰለኝ ፡፡ ትክክለኛውን አባባላቸውን ባላስታውሰውም ቅሉ፣ መንፈሱ ይህ ነው ፡፡ ድንቅ ሃሳብ ነው ፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ግን አሁንም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው የሆኑትን ህወሀቶችንም ሆነ የእናት አባት ዘመዶቻቸው የሆኑትን “ዓጋሜዎች” ከማብሸቅ አልተቆጠቡም ፡፡ The game is over ! Woyane እያሉ እየተሳለቁባቸው ነው ፡፡ ይህ ብሽሽቅ ፖለቲካ ካልተባለ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል ?
የኤርትራው (አባትና መስራች) የተሰኙት ፕሬዚዴንት ሃገራቸውን ከነስሟ ሃገረ ኤርትራ /State of Ertrea/ ተብላ አንድትሰየም የፈለጉበት ምክንያት “ሃገራዊነቷ” እንዲደላደልና እውቅና ተጎናጽፎ አንዲቀጥል ነው፡፡ ፕሬዚዴንቱ ግን ስለበይነ መንግስታት ግንኙነት ሳይሆን በአወቅሁሽ ናቅሁሽ ወያኔ ጋር አተካራ ለመግጠም የመረጡ ይመስላል፡፡
በሰመራ ከተማ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የተሰበሰቡት የአፋር ሽማግሌዎች በኤርትራ አፋሮችና በአሰብ ወደብ ጉዳይ እኛም እንካተት የሚል ማሳሰቢያ ነበር እንጂ የመሬት ጥያቄ አላነሱም ፣ እንዲያውም የመሬት ጥያቄ የላቸውም ፡፡ ለምን ቢባል መልሱ ድንበር ዘለል የሆኑቱ አፋሮች ከኤርትራ ውስጥ ከተካለሉት ዘመዶቻቸው ያለው ግንኙነትና ትሥሥር ፥ ዝምድና አንድ ነን ባይነት ፣ ‘’ከትግርኛ ተናጋሪዎች’’ ጋር እርስ በርስ ካላቸው ዝምድና ከስር መሠረቱ ይለያል ፡፡ ትግርኛ ተናጋሪዎች ያልኳቸው በአንድነት እንደ አፋሮቹ ፥ ኩናማዎቹ ፥ ሳሆዎቹ ፥(ኢሮብ) የወል መጠሪያ ወይም መታወቂያ ስያሜ የለንም ባዮች ስለሆኑ ነው ፡፡ አንዱ የችግሩ ምንጭ እዚህ ላይ ነው ፡፡ ወደ ታሪካዊው ዳራው የኋሊት መፍሰስ ያስፈለገውም ስለዚህ ነው ፡፡ በአጪሩ የሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች (ተዛረብቲ ትግርኛ) ውዝግብ መንስዔው ገሚሱ ታሪካዊ ተበደልኩ ባይነት ሲሆን ገሚሱ ደግሞ አንዲያው የስነ ልቡና ቁጥርጥር (Complex) ውጤት ነው፡፡ ለዚህም ነው አሁንም ጥንቃቀቄ ያስፈልጋል የምንለው፡፡ መቼም ከ1983-1990 ወደነበረው ህንፍሽፍሽ ( ምስቅልቅል) እንደማንመለስ ተስፋችን የጸና ነው፡፡
ፈረንጆች የሁለቱ ጦርነት sensless war (ትርጉም አልባ) ትሥሥሩ ደግሞ የወንድማማቾች አምባጓሮ/ brothers at war እያሉ ለመረዳት ሞክራ ለመረዳት ያስቸገራቸውና ምስቅልቅሉን ለማስረዳት የባጁት ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድንበር አካላዩ ኮሚሽን ድንበሩን ሲያካልል ወደ አፋር ክልል (ኢትዮጵያ) ያካተተው ሰፊ መሬት አለ ፡፡ ለምሳሌ የቢሩ ሱልጣኔት የተሰጠው መሬትና አዩማን የተባሉት አካባቢ ሁለት ወረዳዎች ሊወጣቸው የሚችል ሰፊ የኢትዮጵያ የአፋር መሬት ነው ፡፡ ስለዚህ መሬት ወያኔ አልተቸገረም አውርቶም አያውቅም ፡፡ አፋሮችም አልተወዛገቡም ፡፡ መሬቱ የአፋር ጎሳዎች መሬት እስከሆነ ድረስ ለነሱ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለባለቤትነት መወዛገባቸው ከቁባቸው አልገባም ፡፡ ድንበሩም ለነርሱ ‘’ትርጉም’’ የለውም ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ የጎሳ መሪው ወይም ሡልጣኑ ወዲህና ወደዚያ ያሉትን አሁንም እንደ ዜጎቻቸው ያስተዳድራሉና ፡፡ ልክ ጠቅላይ ሚንስትሩ በኬንያ ድንበር ያሉት ኦሮሞዎች በአንድ አባ ገዳ ይተዳደራሉ እንዳሉት መሆኑ ነው ፡፡
በተቃራኒው ‘’የትግርኛ ተናጋሪ’’ ትግሬ ብሄረሰብና ኤርትራውያን ትግርኛ ተናጋሪ ወይም ራሳቸው እንደሚጠሩት ተጋሩ መሃል የምንመለከተው ትሥሥር ለየት ያለ ነው ፡፡ አስቸጋሪ ነው ! አወዛጋቢም ነው ፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉ ውዝግቦች ምንጭ የሆነ ችግር ሲሆን ሳዳም ሁሴን የችግሮቹ ሁሉ እናት /Mother of all problems ያለው አይነት መሆኑ ነው ፡፡ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገው ችግር ነው ፡፡ በአንድ የፌስቡክ ጦማር የሚካተት ሊሆን ግን አይችልም መቸም ፡፡ ነገር ግን አንድ ልብ ልንለው የሚገባ እውነታ አለ የዛሬ ስምንት ዓመት ማርች 2010 በሳንሆዜ ከተማ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ወዳጅነት ኮንፈረንስ ላይ “የትግርኛ ተናጋሪዎች ቋሚና ተለዋዋጭ የማንነት መገለጫዎችና፣ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ረገድ የሚኖረው ሚና” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ባንድ አገር ልጅነትም ሆነ ፣ በሁለት አገር ልጅነት ጎን ለጎን መኖር የጂኦግራፊና የታሪክ ግዴታቸው ነው የሁለቱን አገር ህዝቦች አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች (ተዘርብቲ ትግሪኛ ) ህዝብ ሳይነጋገርና ሳይቀራረብ ፣ ይቀራረባሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው” ብየ ነበር ፡፡
‘’ የትግሪኛ ተናጋሪዎች ‘’ ቋሚና ተለዋዋጭ የማንነት መገለጫዎች ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ረግድ የሚኖራቸው ሚና አሁንም አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ባለመሆኑና ተግባራዊነቱም ወሳኝ ስለሆነ ይህንኑ ማሳስቢያ በድጋሚ የማላስተላልፍበትና የምልደግምበት ምክንያቱ አይታየኝም ፡፡ ድንበሩ ተካልሎ ፥ ችካሉ ተቸክሎ ቤተክርስቲያኑ ተገምሶ ፥ ማሳው በሁለት ተክፍሎ ለሚፈጠረው ምስቅልቅል መፈትሔ ይፈለጋል ይገኛልም ዋናው ቁም ነገር ግን ኖርማል (ልሙዱና ጤናማው) የሁለቱ በይነ መንግስታት ግንኙነት ወደ መደበኛው መመለሱ ነው ፡፡ አሁንም የምንመለከተው ግን ከኖርማሉ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ወይም አተያይ ነው ፡፡ ያውም ቁጥርጥር /complex የተባለው ውጤት ነው ፡፡
የሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለሰ ዜናዊ ወላጅ እናት ወ/ሮ አለማሽ ገብረ ልዑል የዓዲኳላ መንደፈራ ሰው ነበሩ ፡፡ ይህ ምስጢር አልነበረም ፡፡ ወይም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ አያፍሩም ነበር ፡፡ በተቃራኒው የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወላጅ እናት ወ/ሮ አድሃነችም ሆኑ አያታቸው ወ/ሮ መድህን መሰለ የኪዳኔ መሰለ እህትና የታጋዩ የማነ ኪዳኔ aka ጃማይካ ወላጅ አባት ጭምር የትግራይ ተወላጆች ናቸው ፡፡ አያቱም ከተንቤን የፈለሱ ናቸው ይባላል ፡፡ ይህ ግን የአስመራ ሕዝብ በሹክሹክታ የሚያወራው መንግስታዊ ወይም ሀገራዊ ምስጢር/state secret ነው እንጂ የታሪኩ ባለቤት የሚቀበሉት አልሆነም ፡፡ያልተለመደ ቁጥርጥር/ complex ውጤት ነው ፡፡ ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ የወላጆቾቻቸው “ዓጋሜነት” በይፋ መታወቁ በደቂ አስመራ ዘንድ መበሻሸቂያ እንዳይሆን ነው ፍራቻው ፡፡ የሺመቤት ዓሊ የጃንሆይ እናት አይነገሬ ምስጢር አይነት መሆኑ ነው ፡፡
የየሺመቤት አባት ስማቸው ዓሊ እንደነበረ ሀገራዊ/state secreat እንደነበር ዓይነቱ ግራ አጋቢ እንቆቅልሽ፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ወይዘሮ የሺመቤት ትክክለኛ ስማቸው የሺመቤት ዓሊ ሓሰን ገንጮ ፈረዶ እንደነበረ ማወቅ ችለናል ፡፡ ምስጢሩ የናታቸው ስም ሙስሊም መሆናቸውን ያሳብቃል ፥ያጋልጣል ተብሎ ይሆን ? የሁለቱ ትግሬዎች ችግሩ ታሪካዊ ዳራም አለው ተብሏል፡፡ እነሱ ችግሩ ፉክክሩም ፥ ቅናትም ፥ ቁርሾም ጭምር የቋጠሩት ከሸዋ አማራዎች ጋር ብቻ ሳይሆን አስመራ ካሉት “ሓማሴኖች” ጋርም ጭምር ነው ፡፡ ምክንያቱም በሃገሪቱ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ምልክት ሆነው ይታዩ የነበሩት ሁለቱ ማዕከላት አዲስ አበባና አስመራ ነበሩና ነው ፡፡
እድገታቸው “በትግራይ ሂሳብ” እንደተከናወነ ያምኑ ነበር፡፡ በአንደኛ ወያኔም ሆነ በሁለተኛ ወያኔ ወይም የደደቢት ፋኖዎች ለአመፅ ያነሳሳውና ለቅስቀሳ የተጠቀሙበት ይህንኑ የመበደል ስሜት ነው በአመዛኙ ፡፡ ግደይ ዘርዓፅዮን በቅርቡ ባሳተሙት “ ከትግል ትዝታዬ የደደቢት አብዮት በሴረኞች መቀጨት ሰኔ 2010 “ መጽሐፍ በአንዱ ምዕራፍ ይህንን ታሪካዊ የበደል ስሜት በሰፊው ያብራራሉ ፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ በነበሩበት 13 ዓመታት ፣ (ከ1953–1966) ከኤርትራ አስተዳዳሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲያላትማቸውና ሲያወዛግባቸው የነበረው ይኽው ያልተመጣጠነ እድገት ነው ቢባል አሁንም ምንም ማጋነን የለበትም ፡፡ ልዑሉ ከአዲስ አበባ አስመራ የሚጓጓዙ ማመለሻዎች በሙሉ መቀሌ ጎራ ሳይሉ አይለፉ ብለው አስተላለፉት የሚባለው መመርያ ብጤ ከምሳሌዎቹ አንዲቷ ናት ፡፡ ሌላ መወዛገቢያ ምሳሌ ልጨምር ! በዳሎል በዚያን ጊዜ የሁለቱ ጠቅላይ ግዛቶች ድንበር ዛሬ ዛሬ የሁለቱ አገራት ወሰን ላይ M. parsons company የሚባለው የፖታሽ ቆፋሪ አሜሪካዊ ካምፓኒ ታክስ ለማን ይክፈል ? ሠራተኛ ከየት ይመልምል ?… ሠራተኞች ለዕረፍት በሔሊኮፕተርወደ አስመራ ይሂዱ ወይስ ወደ መቀሌ ይሂዱ የሚለው አነጋጋሪና ያለመግባባት ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ልዑሉ ለተጋሩ እና ለጠቅላይ ግዛቱ የነበራቸውን ቶሎ የማደግ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ እና ከአስመራ ጋር የነበራቸውን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ያመለክታል ፡፡ ዛሬም በኤርትራ በኩል በኩሉሊ ፣ በኢትዮጵያ በኩል በዳሎል የተለያዩ የውጭ ማእድን ቆፋሪ ካምፓኒዎች በዚያ ድንበር ፖታሽ እያወጡ ናቸው ፡፡ መረሳት የሌለበት ከላይ የተጠቀሰው አሜሪካዊው ካምፓኒ ለምርቱ ባህር መውጫ አድርጎ የተለመው 92 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘውን ራስ አንዳዳይን ነበር ፡፡ ራስ አንዳዳይ ደግሞ ከመርሳ ፋጡማ በስተ ደቡብ ብዙ የማትርቅ የተፈጥሮ ጥልቅ ባሕር ወደብ ናት፡፡ ዛሬ ግን የኢትዮጵያ የዳሎል ፖታሽ ፣ ከ 700 ኪሎሜትር በላይ ተጓጉዞ በጅቡቲዋ ታጁራ ወደብ እንዲጫን ነው የተፈለገው ፡፡ የወያኔና የሻዕብያ አወቅሁሽ ናቅሁሽ በፈጠረው የእሳት አንጫጫር ቀውስ ፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ከታሪክ የማይማሩ ፥ ታሪክን ለመድገም ይገደዳሉ ፡፡Those who never learn from history are doomed to repeat it ! ሁሉንም በመጠኑ እናድርገው፡፡ ስንጣላ የምንታረቅበት ወቅት እንደሚኖር ፣ ስንታረቅ ድግሞ ልንጣላ የምንችልበት ሁኔታ ሊመጣ አንደሚችል እሳቤ በመውሰድ ፡፡ ዶ/ር አቢይ አህመድ በአካባቢው እሱን ከከበቡት የእሱን ዕድሜ በመነበረ ስልጣን የተዘፈዘፉት አዛውንት መሪዎች ከኢሳይያስ…እስከ ሙሴቪኒ ፥ ከአልበሽር ፥ እስከ እስማኤል ዑመር ገሌ ፥ ለሱ የሚያስተምሩት የመሪነት ብልሃት እምብዛም ቢሆንም በሌላም በኩል የአቢይ አብነትና ተምሳሌት ለዕድሜ ጠገብ አስተዳደራቸው አስጊ መሆኑን መቼም ሳይገነዘቡት አይቀሩምና አቢይን ወያኔዎችን ብቻ ሳይሆን ከአባትህ እኩያዎች ተጠንቀቅ፡፡ ፕሬዚዴንት ኢሳይያስ ደግሞ የአረብ ኢሜሬት መሪዎች እንኳን እርስዎን የትራምፕን አስተዳደር ለመሰለል ዩሱፍ ኡቴባ በተባለው በኢሜሬቱ የአሜሪካ አምባሳደር በኩል የተከፈለው ገንዘብ በአሜሪካ ጋዜጦች ይፋ እየወጣ ነውና ለእርስዎም አይተኙልዎትም፡፡ ይህንን አያውቁትም ለማለት ሳይሆን “ፈዘክር ! ፈኢና ዚክራ ተንፋዑ አልሙሚኒን” ይላል ቁርአኑ፡፡(አስታውስ ! ማስታወስ ለአማኞች ጠቃሚ ነውና) የሚሉትን ልመርቅልዎ ነው፡፡