በፋሲል የኔዓለም
አቶ ደመቀ መኮንን ምንም በማያውቁት ሲወነጀሉ መኖራቸው በእጅጉ ያሳዝናል። አቶ አባይ ጸሃዬ መሬቱን ለሱዳን አሳልፈው እንዲሰጡ ካዘዙዋቸው ሰዎች መካከል በወቅቱ የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ሙሉአለም ገሌ በዝርዝር አጫውተውኛል። የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ አባይ፣ ከአቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ ሙሉ ታሪቀኝ፣ ሙሉጌታ ወርቁና ኮሎኔል ከበደ ጋር በመሆን ግንቦት 1995 ዓም ገላባት ላይ ሄሊኮፕተራቸውን አሳርፈው፣ ደለሎ ቁጥር 3፣ 4 እና 5 ለሱዳኖች መሰጠት አለበት ብለው ትእዛዝ ሲሰጡ አቶ ሙሉአለም “ ህዝቡን ሳላናግር ይህን አልቀበልም፣ አስፈጽምም” በማለት ተቃውመዋል። አቶ አባይም መልሰው “ ሻዕቢያ በዛ
ተቃዋሚ እየላከችብን፣ ሱዳኖችም በዚህ ሁኔታ እየጠየቁ መሬቱን እያረሱ ይቆዩ ብለን ነው፣ ጠላት
እያፈራን መሄድ የለብንም” ብለው ለአቶ ሙለዓለም ሲናገሩ፣ አቶ ሙሉዓለም “ ይህን የመተማ ህዝብ ሳይናገርበት እኔ እጄን አላስገባም” በማለት ሲከራከሩ፣ “ጦረኛ” ብለው ከዘለፉዋቸው በሁዋላ ” ቁጥር 4 እና 5
በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳይሰጥ ቢቀር እርምጃ እወስዳለሁ” ብለው መናገራቸውንና በዚህም ሱዳኖች መደሰታቸውን ነግረውኛል።
ሰኔ ላይ ሱዳኖች መሬቱ ተሰጥቶናል በማለት ለማረስ ሲመጡ የአካባቢው ህዝብ፣ “ይህን የምታደርጉት በእኛ አጥንት ተረማምዳችሁ ነው” በማለት ባለው ሃይል ሁሉ ተከላክሏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሱዳኖች በየጊዜው እየገቡ ችግር በመፍጠር ላይ ናቸው። አርበኛው አቶ ሙሉአለም በዚህ ሰበብ ታስረው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። አቶ ሙለዓለም ሰሞኑን የኢሳት እንግዳ ሆነው ሲቀርቡ ሁሉንም በዝርዝር ይነግሩናል። አቶ አባይ ጸሃዬ በዚች አገር ላይ የሰሩት ወንጀል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይመስለኝም። ሰውዬው በአገር ክዳት ወንጀል የሚጠየቁበትን
ጊዜ ማየት እጅግ ናፍቆኛል።