>
5:18 pm - Saturday June 15, 3839

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ፍቃዱ ተመልሶለት ቢሮው ገብቷል !!! (ዳዊት ሰለሞን)

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ፍቃዱ ተመልሶለት ቢሮው ገብቷል !!!
ዳዊት ሰለሞን
የፀረ ሽብር አዋጁ ከአገሪቱ ህገመንግስትና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ህግጋት ጋር እንደሚጋጭ በመግለፅ በአደባባይ በመቃወም ከህግ ባለሞያዎች መካከል ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የመጀመሪያው ይመስለኛል።
ተማም በአገሪቱ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን ፣የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያዘጋጇቸውን መድረኮች በመጠቀም የአዋጁን አፋኝነትና የፖለቲካ መገልገያነት እየነቀሱ በማውጣት አስረድተዋል።
ጠበቃው በዚህ ብቻ ሳይወሰን  በሽብር ወንጀል ለተከሰሱ የህሊና እስረኞች፣ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ያለክፍያ ጭምር ጥብቅና በመቆም በካንጋሮው ፍርድ ቤት የወከላቸውን ሰዎች ንፅህና አውጇል።
ተማም በዋናነት የፀረ ሽብር አዋጁ ከመነሻው አፋኝ መሆኑን ስለተረዳ በአዋጁ የተከሰሱ ሰዎችን የሚመለከተው እንደራሱ ነበር ለዚህም ነው “እኔም አቡበከር ነኝ”ያለው።
አቡበከር ሽብርተኛ ተብሎ እየተወነጀለ ተማም ግን ኢትዮጵያዊ ሆኖ አሸባሪ የሚሆን የለም። እነአቡበከር የአዋጁ ኢላማዎች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም በማለት በይፋ “እኔም አቡበከር ነኝ”ብሏል።
በአደባባይና በይስሙላው የፖለቲካ ፍርድ ቤት ተማምን በሐሳብ መርታት የተሳናቸው የስርዓቱ ሎሌዎች የጠበቃውን የጥብቅና ፈቃድ በማገድ ለተወሰኑ ጊዜያት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል ።
አሁን ጠበቃው ተማም በአዲስ ጉልበት፣የስራ መነሳሳትና የፍትህ ናፍቆት ወደቢሮው ተመልሷል።
ተማም ለፍትህ፣ለአላማውና ለሐይማኖቱ ዘብ የሚቆም የማይሰበር ስነልቦና ያለው በመሆኑ አሳዳጆቹ ያደረሱበት የኢኮኖሚ ችግር በአቋሙ ላይ ቅንጣት ተፅእኖ እንደማያሳርፍ ማወቅ ልብን በሐሴት ይሞላል ።
ይህ የፍትህ ወኪል ወደስራው በመመለሱም “እንኳን ደስ አለህ”ልንለውና የፍርድ ቤት ጉዳዮች ያሉብንም አገልግሎቱን ለማግኘት የመጀመሪያ ምርጫችን እናድርገው። ተማም የህዝብ ልጅ!!!!
Filed in: Amharic