>

‹መስከረም ሲወጣ ሲፈነዳ አደይ፣ አስመራ እንቁጣጣሽ አትይንም ወይ› ….(እንዳለ ጌታ ከበደ)

መስከረም ሲወጣ ሲፈነዳ አደይ
አስመራ እንቁጣጣሽ አትይንም ወይ›
….እንዳለ ጌታ ከበደ
<ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሶስቱን ቀለማት
እባካችሁ ሰዎች እንዳለ ተዉት
ሰሀጢ-ጉድጉዲ-መተማ-አድዋ – ማይጨው ያለቁቱ ለዚች ባንዲራ ነው መልኳን አታጥፏት፡፡>
ይህን ያሉት ተሰማ እሸቴ ናቸው፡፡ ተሰማ እሸቴ – ነጋድራስ፣የቅኔና የዜማ ሰው፡፡ ከላይ የተነበበውን ስንኝ የቋጠሩት ለኤርትራ ነው፡፡ ግጥሙን ከተናገሩትም 65 ዓመት ሞልቶታል፡፡ መስከረም 1 ቀን 1945 ኣ.ም፣ ኤርትራ በፌዴሬሽን ስትዋሃድና ለሃምሳ አመታት ተለያይተው የነበሩትን ሁለቱን አገሮች ሲቀላቀሉ በማየታቸው  ደስታቸውን ለመግለጽ ነው እንዲያ ማለታቸው፡፡
እንቁጣጣሽ አውደ ዓመት ነው፡፡ አደይ የሚያብበት፣እሸት የሚያብበበት፣ወንዝ የሚጎድልበት፣ሰዉም አዕዋፉም መስኩም የሚዋብበት ነው፡፡ ‹መስከረም ሲወጣ ሲፈነዳ አደይ….›
እንቁጣጣሽ፣ ፍንክንክ፣ፍልቅልቅ፣አጀብ በሚበዛበት ወር ውስጥ ተሞሽሮ የሚገኝ በዓል ነው፡፡ጣጣ የሚበዛበት እንቁ ነው፡፡ ወርሃ መስከረም፡ መስክ ዓረም፡፡ ብዙ የሚባልለት፣ሰዉ ለአዲስ ተልዕኮ ራሱን የሚያጭበት፣እድፍ ጉድፉን ነቅሶ ለማስወገድ ለራሱ ቃል የሚገባበት፣የተነፋፋቀ የሚገናኝበት ወር!
‹….አስመራ እንቁጣጣሽ አትይንም ወይ›
እንቁጣጣሽ የሁልጊዜ ክዋኔ አይደለም፡፡ ወቅት አለው፡፡ የሁሉም ዝማሬም አይደለም፡፡ ጾታ ይመርጣል፡፡ ዕድሜ ይለያል፡፡ ለብቻ የሚጫወቱት ዜማም አይደለም፡፡ የጋራ ዝማሬ፣የእኩዮሽ ጨወታ ነው፡፡ አበባ የመሰሉ ልጃገረዶች ‹አበባ አየሽ ወይ› የሚባባሉበት ቅኝት ነው፡፡ በልጃገረዶች ድምጽ ሲሰማ የሰነበተ፣ ሀገር በቀል ጨወታ ሲሆን፣ጨወታው በመቀበልና በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምንም ፍቅር፣ባህልና ወቅት የወለደው ጨወታ ቢሆን፣ወይዛዝርቱ አምረው ተውበው በየደጁ እየቆሙ፣የእንቁጣጣሽን ዜማ ሲያንቆረቁሩ፣ባለቤቶቹ በምን ግድ የለሽነት ጆሮአቸውን አይከረችሙም፡፡ የሚሰጡት አላቸው፡፡ትናንት የተቀበለችዋ ዛሬ ሰጭ ትሆናለች፡፡የሂደቱ ተሳታፊ!ባህሉን አስተላላፊ!!
‹እንቁጣጣሽ አትይንም ወይ› የምትባል ሴት የምትናፈቅ፣የምትወደድ ስትሆን ነው፡፡ አምሮብሽ ተውበሽ ላይሽ እፈልጋለሁ ነው፡፡ ስትመጪ የምሰጥሽ አለኝ፤አንቺ ብቻ በፍቅር ቋንቋ አናግሪኝ፣ድምጽሽን መስማት ያነቃኛል፤ያተጋኛል፤ዘመኑን ያበስርልኛል የሚል መልዕክት አለው፡፡
 ‹መስከረም ሲወጣ ሲፈነዳ አደይ
 አስመራ እንቁጣጣሽ አትይንም ወይ›
….
.ተሰማ እሸቴ ድንቅ የቅኔ ሰው ናቸው፡፡ ቅኔዎቻቸው ይሄው ከ60ና 70 ዓመታት በሁዋላ ሲነበቡም የትናንት ይመስላሉ፡፡
<አርበኛ ለኢትዮጵያ ሰርቷል መንገዷን
እንግዲህ መጓዝ ነው ተሸዋ ሀማሴን..>
Filed in: Amharic