>

አሁንም የዘር ቆጠራ አባዜ (ከይኄይስ እውነቱ)

አሁንም የዘር ቆጠራ አባዜ

ከይኄይስ እውነቱ

ለዛሬው አስተያየት መነሻ የሆነኝ ጉዳይ ‹‹ጭብጨባውና እስክታውን ቀነስ አድርገን ነገሮችን በአንክሮና በተዘክሮ መመርመር ይገባል!!›› በሚል ርእስ አቶ ታደለ ጥበቡ የተባሉ ግለሰብ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ የጽሑፉ ጭብጥ የዶ/ር ዐቢይ ‹አስተዳደር› በርካታ ተሿሚዎች ኦሮሞዎች ናቸው፤ ይህም የወያኔ ትግሬ አገዛዝ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ባለሥልጣናትን በኹሉም መንግሥታዊ መዋቅሮች እንዲሰለጥኑ ያደረገበትን አካሄድ መድገም ስለሚሆን ከቸበር ቻቻው ሰከን ብለን እየተደረገ ያለውን በጥንቃቄ እናስተውል፤ አገሪቱ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በመሆኑ በሹመት ክፍፍሉ የጎሣ ስብጥሩ ይመጣጠን፤ አለበለዚያ ‹መደመር› የለም የሚል ነው፡፡ ጸሐፊው ለዚህ አስተያየት መነሻ ቢሆኑም ዓላማው ጸሐፊውን በተናጥል ለመንቀፍ ያለመ ሳይሆን አጠቃላይ መልእክት ለማስተላለፍ መሆኑን አንባቢ እንዲረዳልኝ በትህትና እጠይቃለኹ፡፡

በቅድሚያ የጠ/ሚ ዐቢይ ‹አስተዳደር› የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ በምርጫ የሰየመው አለመሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ ሁለተኛ፤ ራሱን ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ቢሆንም በ‹መንግሥትነት› ያለው አካል ሕወሓትን ጨምሮ እሱ የፈጠራቸውና ‹ኢሕአዴግ› የሚል የሽፋን ስም የሰጡት 3 የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ሦስተኛ፤ እንኳን ፌዴራላዊ (የአብሮነት) ሥርዓት በይስሙላ ሕገ መንግሥታቸው ጽፈናል ያሉት ጎሣን መሠረት ያደረገው ፌዴራላዊ ሥርዓት አልነበርም፤ አሁንም የለም፡፡

ኢትዮጵያ አሁን በምትገኝበት ጅምር የለውጥ ሂደት ቀዳሚው ጥያቄ በዶ/ር ዐቢይ ‹አመራር› የተጀመረው በጎ ለውጥ ዘላቂነት ያለውና ሕዝብ ወደሚፈልገው መዳረሻ – ከወያኔያዊ አገዛዝ ተላቅቀን ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣በዜግነት ላይ የተመሠረተ መንግሥተ ሕዝብ የሚቆምባት አዲሲቱን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ሆና ማየትን – የሚያደርሰን መሆኑን ማረጋገጥ ይመስለኛል፡፡

ይህ መዳረሻ የሚያስማማን ከሆነ፣ መዳረሻው አስቀድሞ ግምት ውስጥ የሚያስገባው  አዲስ በሚቆም ሕገ መንግሥት አማካይነት የመብትና ነፃነት ተጠቃሚ ለመሆን፣ ባንፃሩም ግዴታና ኃላፊነትን ለመቀበል መሠረት የሚያደርገው ከፍ ሲል ሰውነት ዝቅ ሲል ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ብቻ ነው፡፡ በሕዝብ ፈቃድ የሚመሠረተው አገራዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት ከዘር/ነገድ/ጎሣ (ብሔር የሚለው ቃል ቦታን እንጂ የሰዎችን ስብስብ/ቡድን አያመለክትም) ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማይኖረው ታሳቢ የሚያደርግ ነው፡፡

ባንፃሩም ከቀዳሚው ጥያቄ ጎን ለጎን የሚታየውና ፋታ የማይሰጠው ሌላው ጥያቄ በወያኔ ትግሬ የሚመሩ ፀረ-ለውጥ ኃይሎችን አደብ አስገዝቶ አገርን የማረጋጋት ሥራ ነው፡፡

የጠ/ሚ ዐቢይ ‹አስተዳደር› በካቢኔው እና በልዩ ልዩ የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች የሰየማቸው ባለሥልጣናት ከሚመራው የፖለቲካ ግንባር አባላት መካከል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በዚህም ሹመት ብዙ ተገቢ ወቀሳዎች ተሠንዝረዋል፡፡ የወቀሳው መሠረት ግን የዘር ጉዳይ ሳይሆን ብቃትና እየተካሄደ ላለው በጎ የለውጥ ጅማሮች እንቅፋት ይሆናሉ ከሚል ሥጋት ይመስለኛል፡፡

ቢሮክራሲውን ያበደነው ይህ የዘር ቆጠራ መሆኑን ለምን እንዘነጋለን፡፡ ሕዝብ ምርጫ አድርጎ ከሚሞላቸው ተቋማት ውጭ የሚደረግ ሹመትም ሆነ ምደባ መሠረቱ ብቃት (merit) እንጂ የፖለቲካ ታማኝነትና ቀረቤታ መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጣቱን ‹መሪ› ማገዝ የሚገባው ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት እውን ለማድረግ ነው፡፡ ጎሣ ማመጣጠን/የጎሣ ተዋጽኦ የሚለው የተወላገደ አስተሳሰብ ወያኔ ትግሬ አገር ለማፍረስና የሕዝብን አብሮነት ለማጥፋት በተከተለው የዘር ፖለቲካ የረጨው መርዝ ነው፡፡

በእኔ ትሁት እምነት ባለንበት 21ኛው መቶ ክ/ዘመን ፖለቲካን ከዘር/ነገድ/ጎሣ ጋር አቆራኝቶ ማሰብ ቢያንስ የተሟላ የሰውነት ደረጃ ላይ አለመድረስ ሲሆን፣ ሲከፋ ደግሞ ሥር የሰደደ ደዌ ነው፡፡ የማጅራት መቺዎቹ የወያኔ ሥርዓት ላለፉት 27 ዓመታት ለዚህ ዕኩይ ዓላማ ተግቶ በመሥራቱ የ‹ተዋሕሱ› ተሸካሚዎች/በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች ቊጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም ተግዳሮቱ በተለያየ መልኩ ሊገለጥና ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን እንደሚዘልቅ ይገመታል፡፡ ይህን የአስተሳሰብ መርዝ ለማብረስ ኢትዮጵያ በኹሉም የሞያ መስክ ተግተው የሚሠሩ ቅን አዋቂዎችን/‹ባለመድኃኒቶችን› ትሻለች፡፡

በመጨረሻም እኔ ‹መደመር›ን በጥቅሉ የምረዳው በብሔራዊ/ኢትዮጵያዊ ማንነት ሥር ልዩነትን አውቆና አክብሮ በአብሮነት የመኖር መርህ አድርጌ ነው፡፡ መንደርተኝነትን ከሚያመለክት የዘር አስተሳሰብ መላቀቅ ነው፡፡ ከዘር ቆጠራ አባዜ ወጥተን ጥያቄአችን ብቃትን (merit) ፣ ቅንነትንና የሞራል ልዕልናን (integrity) ወይም መርህን መሠረት ሲያደርግ ኹላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡

 

Filed in: Amharic